Sunday, January 19, 2014

ከውጥንቅጡ ባሻገር

ህይወት ምስቅልቅሏ፣ ህልምና እውኗ የተሳከረባት፣ ብዬ’ንኳ ኣላማም።
መልከ-ጥፉነቷ፣ ዕብደቷ ሚስጢሯ ባይኖርማ ኖሮ ውበቷን ኣላይም።
ብዬ ልፅናና ስል፣ የራሴው ልቦና ራሴኑ ሞገተው፡
በልብህ ያኖርከው፣ ህልሜ እምትለው፣ ይሄ ህልም የማ’ነው?
ዓለሜ ናት ያልካት፣ የማ’ነች ይች ዓለም?
ይወቴ ነው ያልከው፣ የማ’ነው ይህ ህይወት?
ይህንን ሳትመልስ እንዴት ታየህ ውበት?

የሲሳዬ ልጆች/ኬክሮስና ኬንትሮስ
ልቦለድ ታሪክ ከኦ’ታም ፑልቶ
መግቢያ ወይም መውጫ

ኣንዳንዴ የምትጽፋቸው ነገሮች ከእውነታው ዓለም ውጪ ይሆናሉ፤ ይሉኛል ሰዎች። ለኔ ግን እውን ሆኖ እሚታየኝ እነሱ ከእውነታው ወጣብን እሚሉት ነው፤ ብሎ ነበር ዶስቶዬቪስኪ። ካርል ዩንግ ደግሞ፣ ህይወትን ሙሉ እሚያደርጋት በሚስጢራት፣ በማይለኩና በማይተነበዩ ነገሮች መሞላቷ ነው፤ ይላል። (ሁለቱም ከቆየ የንባብ ትውስታዬ በኔ ኣባባል የተቀመጡ)። ይህ የህይወት ሚስጢራዊነት ዶስቶዮቪስኪን ለምናባዊ ፈጠራ፣ ካርል ዩንግን ለሳይንሳዊ ፈጠራ ኣነሳሳቸው። ግን፣ ምናባዊው ፈጠራ የቱ፣ ሳይንሱስ የቱ ነው? ዶስቶዮቪስኪና ኣንባቢዎቹ እውኑን ከፍንጠዛው (Fantasy) መለየት እንደተቸገሩት እኛም ኣንዳንዴ ሳይንሱን ከምናባዊ ፈጠራው ለመለየት እንቸገራለን። እንዲያውም እኚህ “ሳይንስ፣” “ፈጠራ፣” እሚባሉቱ ስያሜዎች እንዲሁ ልክ እንደሸቀጥ ማሻሻጫ ከላይ የተለጠፉ ነገሮች ብቻ እንደሆኑም እስከማሰብ እንደርሳለን። የሆነ ሆኖ፣ እነሆ የህይወት ውስብስብነትና ከስጋና ከደም በላይ የመሆን ኣዝማሚያዋ ጸሐፊውን ወደ ቅኔ፣ ሳይንቲስቱን ወደሳይንስ፣ ሙዚቀኛውን ወደሙዘቃ፣ ሃይማኖተኛውን ወደምናኔ እየመራ ኣለ። የሚስቶና የበያይነቱ ወዳጆች ደግሞ፣ ህይወት በየተቀመመችበት መልኩ ቀምሰው ለማጣጣም፣ በየተከፈተላቸው በር ሁሉ እየገቡም ኣገላብጠዋት ለማየት፣ ያዩትንም ለማሳየት፣ ይፍጨረጨራሉ። እንግዲህ፣ የሲሳዬ ልጆች/ኬክሮስና ኬንትሮስ፣ እንዲ ካሉ የበያይነቱ ወዳጆች ባንዱ የተጣፈ፣ በሳይንስም ሆነ በፈጠራ፣ በእውነታም ሆነ በፍንጠዛ፣ በህልምም ሆነ በእውን፣ በፍልስፍናም ሆነ በእምነት መሃል ድንበር እማይስል የህይወት ዳሰሳ ነው። ስለዚህም፣ …

የሲሳዬ ልጆች/ኬክሮስና ኬንትሮስ የፍለጋ ታሪክ ነው። በውስጡ ሦስት ንዑስ ታሪኮችን ይዟል፡ ሀ) ኣስሬ ለ) ኣንድ ቢራቢሮና ሁለት ቢራቢሮዎች፣ እና ሐ) ጫማ ሰፊው። እነዚህ ታሪኮች በየራሳቸው ለብቻ የሚቆሙ ቢሆንም በመፃፉ ውስጥ በቀረቡበት መልኩ (ኣንዱ ታሪክ ካለቀ በሁዋላ ወደ ሁለተኛው ታሪክ የሚሸጋግር ሳይሆን የያንዳንዱ ታሪክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ይተረካል፤ ከዚያም የእያንዳንዱ ታሪክ ሁለተኛ ምዕራፍ ይቀጥላል፤ ወዘተ…) ኣንድ ላይ መነበባቸው፣ የሚጨምረው ብዙ ነገር፣ የሚያስተላልፈውም የራሱ የሆነ ፍልስፍና ኣለ። በሦስቱም ታሪኮች ውስጥ ያሉ ገፀባህሪያት በእውኑ ዓለም እምብዛም በንቃት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ኣያደርጉም። ኣንባቢያን ግን በያንዳንዱ ገፀ-ባህሪያትና በታሪኮች መካከል ያለውን ስውር ግንኙነት ይረዳሉ። የመጽሐፉን ርዕሶች (መጽሐፉ ለምን ሁለት ርዕሶች እንደተሰጡት መግቢያው ላይ ተገልፆኣል።) ማብራራት ይህ ኣተራረክ የሚያስተላልፈውን መልዕክት ግልፅ ሊያደርግ ይችላል:-

ርዕስ ኣንድ:- የሲሳዬ ልጆች - ሲሳዬ፣ አምስት፣ ስድስት ሰባት በተሰኘው የስብሀት ገ/እግዚአብሔር ኣጭር ልቦለድ ውስጥ ያለ በሬ ነው። ይህ በሬ በቤተሰቡ ውስጥ ልክ እንደቤተሰቡ ኣባል በፍቅር ያደገ በሬ ነበር። በኣከባቢው በገባ ረሃብ የተመታው ቤተሰብ (በኣባወራው በርሱፈቃድ ኣማካኝነት) ኣባላቱን ከእልቂት ሊታደግ በሬውን ይሰዋዋል። ይህ ስለፍቅር የተደረገ የሚያፈቅሩትን የመሰዋት ታሪክ፣ ኣቶ በርሱፈቃድን ለዕብደትና ለሞት ይዳርጋል። ሌላ መስዋዕትነት። ይህ የጋሽ ስብሃት ታሪክ፣ በኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች ውስጥ ያለውን ጥልቅ የፍቅርና የመስዋዕትነት ሕይወት እጅግ ውብ፣ እጅግ ልብ-ነኪ ኣድርጎ የሚገልፅ፣ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሥነጽሑፍ ነው። ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን የዚህ ዓይነት የፍቅር ታሪክ ውልዶች ነን ማለት ይቻላል። በየቤታችን፣ እንዲህ ኣይነት ግንኙነት፣ እንዲህ ኣይነት ትሥሥር ኣለ። የሲሳዬ ልጆች ከሚያሳየው እውነታ ኣንዱ ይህ ነው - በኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች ውስጥ ያለውን ጥልቅ የፍቅርና የመስዋዕትነት ሕይወት (ይህ በተለይ ኣስሬ በተሰኘው ታሪክ ውስጥ በኣስሬና በእናቱ፣ ቀጥሎም በኣስሬና በሚስቱ፣ በልጆቻቸውም መካከል፣ ባለው ጥብቅ ግንኙነት ይገለፃል)። ይህ የእያንዳንዳችን የሚታይ ግንኙነት፣ የሚታይ ታሪክ ምሳሌ ነው። ነገር ግን፣ በሕይወታችን ውስጥ የሚታይ ግንኙነት ብቻ ነው ያለው? ሁለተኛው ርዕስ፣ ይህንን ጥያቄ ይመልሳል። 

ርዕስ ሁለት፡- ኬክሮስና ኬንትሮስ - ኬክሮስና ኬንትሮስ (Latitude and Longitude)፣ በምድር ላይ ከምስራቅ ምዕራብ፣ ከሰሜን ደቡብ የተሠመረ የሃሳብ (imaginary) መስመር ነው። በመጽሐፉ ውስጥ ያለ ኣንድ ገፀባህሪይ፣ እኝህ መስመሮች የኣንድን ሰው ሃሳብ ከሌላ ሰው ሃሳብ፣ የኣንድን ሰው ህልም ከሌላ ሰው ህልም፣ የሚያገናኙ ሕቡዕ መስመሮች እንደሆኑ ኣድርጎ ይረዳል። ይህ፣ ሰዎች ምን በቦታ ቢለያዩ፣ በሰዎች መካከል ያለን ጥብቅና ስውር የእርስ በርስ ግንኙነት ያሳያል። ይህ ግንኙነት ምናልባት በመንፈስ (በፀሎት ወዘተ…) ወይም ደግሞ በኣዕምሮና በስሜት (ልክ በመንታዎች መካከል ኣለ ተብሎ እንደሚታመነው ኣይነት የልብ ለልብ ግንኙነት) ሊሆን ይችላል። ይህ፣ መጽሐፉ የሚያስተላልፈውን፣ በሰዎች መካከል፣ ጥብቅ ግን ስውር ግንኙነት ኣለ፤ እርስ-በርሳችን ከምናስበው በላይ የተሳሰርን ነን፤ የሚለውን ዋነኛ መልዕክት በኣጭሩ የሚያስተላልፍ ርዕስ ነው።

እንግዲህ፣ የታሪኩ ኣካሄድ (የኣተራረክ ዘዴ) ይህንኑ ፍልስፍና፣ ማለትም በሰዎች መካከል ያለን ግልፅና ስውር ግንኙነትና ትስስር፣ የሚያመለክት ነው። እያንዳንዱን ታሪክ በዝርዝር ስንመለከት እንዲህ ያለው የእርስ-በርስ ግንኙነትና ተፅዕኖ ያለው በግለሰቦች መካከል ብቻም ሳይሆን በኣገሮችም መካከል እንደሆነ እንረዳለን። በተለይ፣ ኣንድ ቢራቢሮና ሁለት ብራቢሮዎች የሚለው ንዑስ ታሪክ፣ ከተለያዩ ኣገሮች ከተገኙ ልቦለዶች (ከራሽያ፣ ከሰሜን ኣሜሪካ፣ ከቻይና፣ ከደቡብ ኣሜሪካ፣ ወዘተ…) ገፀ-ባህሪያትን እንደገፀባህሪ በመጠቀም፣ በኣገሮችና በባህሎች መካከል ያለውን ተመሳሳይ ግልፅና ሕቡዕ ትስስር ያሳያል። እና፣ ይህንን ታሪክ የሚያነቡ ሁሉ፣ “የህልማችን ደራሲ ማነው? የታሪክ፣ የዕጣ-ፈንታችን ሸማኔ ማነው? ብቻችንን ነን?” የሚል ዓይነት ሁነኛ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ። ዛሬ ዓለም በግሎባላይዜሽን ተሳስራለች ከሚባለው ውጭም በሰዎችና በኣገሮች መካከል እጅግ ጥልቅ የሆነ የእርስ-በርስ ግንኙነት እንዳለ ተረድተውም ተግባራዊ ምላሽም ወደመስጠት ሊሄዱ ይችላሉ።

ከላይ እንደተባለው፣ የሲሳዬ ልጆች/ኬክሮስና ኬንትሮስ፣ የፍለጋ ታሪክ ነው። ምን ፍለጋ? የሚለውን እያንዳንዱን ንዑስ ታሪክ ባጭሩ በመዳሰስ እንመለከት:-

ኣስሬ:- ኣስሬ፣ በኣስተዳደጉ ዘገምተኛነት ምክንያት (እሱ ኦቲዝም እንዳለበት ነው የሚያስበው) ጓደኞቹም ሆኑ ሌሎች የማህበረሰቡ ኣባላት ጅል ሲሉት፣ ሲያንጓጥጡት፣ ሲያገልሉትና ሲፈሩት የሚያድግ ልጅ ነው። ማኅበረሰብ በግለ-ሰቦች ህይወት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምሳሌ የሆነው ይህ ተፅዕኖ፣ ኣስሬ ፍፁም ወደራሱ ዓለም ውስጥ እንዲሰጥም ያደርገዋል፤ ለጥፋት በዳረገው ነበር፣ ግን፣ ኣስሬ በልቡ ውስጥ ታላቅ ህልም ያገኛል። ይህ ህልም ምን እንደሁ ግልፅ ባይሆንም (ተደራሲ በታሪኩ ውስጥ ከሚነሱ ጉዳዮች ህልሙ ከኢትዮጵያ ትንሳኤ/ህዳሴ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይረዳሉ።) እሱ ህልሙን እውን ለማድረግ ይቆርጣል፤ ዝግጅትም ይጀምራል። ፈተናው ግን ብዙ ነው። ይህ፣ ከሚያፈቅረው ቤተሰብም ከማህበረሰቡም የሚመጣ ከባድ ፈተና ነው። ታሪኩ የሚያጠነጥነው ኣስሬ ይህንን የፍቅር ተፅዕኖ ሰብሮ ታላቅ ህልሙን እውን ለማድረግ በሚያደርገው ትግል ላይ ነው። ያሸንፍ ይሆን? ጠላትን ማሸነፍ ቀላል ይሆን ይሆናል። ፍቅርን ማሸነፍ እንዲያ ቀላል ይሆን? ወይስ፣ ሌላ መንገድ ኣለ? ይህ፣ ተደራሲያን ታሪኩን ሲያነቡ ደረጃ በደረጃ የሚመልሱት ጥያቄ ነው። ይህ የኣስሬ ታሪክ በኢትዮጵያዊያን መካከል ያለው ጥልቅ የፍቅር ግንኙነት የዕድገት/የለውጥ መሰናክልም ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል። ግን ነው? በድጋሚ፣ ሌላ ኣማራጭ መንገድ ኣለ? ኣሁንም ምላሹን ተደራሲያን ከታሪኩ ያገኛሉ።

ጫማ ሰፊው:- በቤተሰቡ ውስጥ (ለኣባቱ ወንጀል ማህበረሰቡ በሰጠው ምላሽ ኣማካኝነት) ስነልቦናዊ ጉዳት የደረሰበት ኣንድ ልጅ፣ ተፅዕኖው ሊቋቋመው ከሚችለው በላይ ቢሆንበት፣ ኣከባቢውን ጥሎ ይጠፋል። የሚጠፋው ግን ከኣከባቢው ብቻ ሳይሆን ከራሱም ጭምር እንደሁ ኣንባቢያን ከታሪኩ ሂደት ይረዳሉ። ልጁ ራሱን፣ ማንነቱን፣ የቀድሞ ታሪኩን ሁሉ ጨርሶ ይረሳና በኣሶሳ ውስጥ በጫማ ሰፊነት ይኖራል። ራሱን ለማግኘት፣ ማንነቱን ለማወቅ፣ ታሪኩን ለመረዳት፣ እጅግ ጥልቅ ኣሰሳ ያደርጋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ኣንድ እንግዳ የብቸኛነት ሕይወቱንና የብቻ-ብቸናነት ጎጆውን በርግዶ ይገባል። ይህ ሰው ማነው? ይህ ኣንባቢያንም ጫማ ሰፊው ራሱም ያለማቋረጥ የሚጠይቁት ጥያቄ ይሆናል። ደባሉ የሆነው ይህ እንግዳ ጎብኚ ጫማሰፊውን በሆነ-ባልሆነው መተነኳኮሱ ወደ ማንነቱ ያቀርበዋል ወይስ ጨርሶ ያጠፋዋል? ይህም ታሪኩ የሚመልሰው ሁነኛ ጥያቄ ነው። ይህ፣ በዋናነት የግላዊ ማንነት ፍለጋ ታሪክ ቢሆንም፣ ከማህበረሰቡ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። እንደገናም፣ በኢትዮጵያዊ ቤተሰቦችና ማህበረሰቦች ኣባላት መካከል ያለው ጥብቅ ትስስር በግለሰቦች ህይወት ውስጥ ምን ያህል ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ያሳያል። (ይህ ታሪክ፣ ጥልቅ የጓደኝነት ሕይወትን የሚያሳይ፣ ከኣስቂኝ/ኮሜዲ ዘውግ ሊመደብ የሚችል ትረካ ነው።)    

ኣንድ ቢራቢሮና ሁለት ቢራብሮ:- በዋናነት ከብራዚል ምድር ተነስተው ለኣንድ ታላቅ ተልዕኮ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ስለመጡ ሁለት ቢራብሮዎች የሚተርከው ይህ ታሪክ፣ ከላይ እንደተባለው፣ ባህሎችና ኣገሮች፣ በመንፈሳዊው/በዓዕምሮኣዊው ዓለም ውስጥ ምን ያህል እንደተሳሰሩ፣ በምድር የትኛውም ጥግ የሚሆን ኣንድ ክስተት በሌላው ማህበረሰብ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ፣ በተምሳሌታዊ ኣካሄድ ይመረምራል። ይህ፣ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን፣ ኣፍሪካም (የዓለም ጥቁር ሕዝቦች በኣጠቃላይ)፣ ታላቅ ሃይል ባላቸው ዓለም-ኣቀፋዊ የለውጥ ሂደቶች ውስጥ ማንነታቸውን/ኣወንታዊ ባህላዊ እሴቶቻቸውን/ ሳይለቁ እንዴት ለታላቅ ትንሳኤና ዕድገት ሊነሳሱ እንደሚችሉ የሚያመለክት፣ በይዘቱና በሚያነሳቸው ጉዳዮች፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች (ስነ-ልቦና፣ ማህበራዊ ሳይንስ፣ ስነ-ሰብዕ፣ ፍልስፍና፣ ዘመናዊው የፊዝክስ ሳይንስ፣ ወዘተ…) ኣነጋጋሪ ጉዳዮችን የሚያነሳ ታሪክ ነው።

የሲሳዬ ልጆች/ኬክሮስና ኬንትሮስ፣ ሳይንሱንና ምናቡን፣ እውነቱንና ተረቱን ያጣመረው የቱ ጋ ነው? የሚል ጠያቂ ቢኖር እንደምላሽ ከኣፃፃፉም ከይዘቱም ኣንዳንድ ሃሳቦችን ማየት ይቻላል። በሦስቱ ንዑስ ልቦለዶች ውስጥ ያሉ ገፀ-ባህሪያት በእውኑ ዓለም ብዙም እንደማይገናኛኙ፣ የኣንዱ ሃሳብና ድርጊት ግን በሌላው ላይ ተፅዕኖ ሲያደርስ እንደሚታይ፣ ከላይ ኣይተናል። ይህ የኣንድ ነገር ወይም ክስተት ከቦታና ከጊዜ እሳቦት ውጭም በሌላው ነገርና ክስተት ላይ ተፅዕኖ ሊያደርግ የመቻሉ ጉዳይ ከዘመናዊው ሳይንስ ከኳንተም ሜካኒክስ (ለምሳሌ፣ non-locality)፣ ከባህሉ ደግሞ፣ ያች ስቅ ኣለኝ፣ ማን ኣንስቶኝ ይሆን? እምትለዋ ኣይነት ከቦታም ሆነ ከጊዜ ቀጥተኛ ግንኙነት ውጭም የመገናኘት የህብረ-ነፍስ ሃሳብ የተዳቀለ ነው። ሌላው፣ ከመፅሃፉ ዋነኛ ይዘቶች ኣንዱ የሆነው፣ ልክ እንደ ኣየር ሁኔታ ያሉ ውስብስብ ዲናሚካዊ ሂደቶች በቀዳሚ ምክንያቶች የማያቋርጥ ተፅዕኖ (the sensitive dependence of dynamic systems to initial conditions) ውስጥ የመሆናቸውና ይህም ሊታሰብና ሊተነበይ ከሚችል ውጭ ወደሆነ ውጤት ሊመራ የመቻሉ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ የቢራቢሮ ክንፍ ፉርፉርታ እንደሱናሚ ያለ ታላቅ ነውጥና ማዕበል የማስነሳቱ ጉዳይ። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ውጥንቅጥና ስርዓት-ዓልባ የሚመስሉ ክስተቶች፣ ከፍ ባሉ (ወይም በረቀቁ) የቦታና የጊዜ ማዕቀፎች ውስጥ ሲታዩ የራሳቸው ስርዓት ሊኖራቸው ይችላል የሚለው እውነት ነው። ይህ፣ በኣተራረኩም ዘዴ ተገልፆኣል። የትረካው ኣካሄድ ካንድ ታሪክ ወደሌላ ታሪክ በዘፈቀደ የሚዘልል ይመስላል። ግን፣ቀስ በቀስ ፍፁም ህብር ወዳለው ስርዓት ያመራል። ይህ፣ ከሳይንሱ ኬዎስ ቲዬሪ (Chaos theory)፣ ከባህሉ ደግሞ፣ የኣዳም መሳት፣ ወይም የኖህ ልጅ በኣባቱ ሃጥዓት መሳለቅ፣ በሰው ልጅ ታሪክ ላይ እማይታበስ ዕዳ ኣምጥቷል፤ የሚለው ሃሳብ ጋብቻ የወለደው ልጅ ሃሳብ ነው። ይህ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሰው ልጅ ታሪክ፣ የኣንድ ኣገርም ሆነ የኣንድ ሰው ህይወት፣ ይብዛም ይነስም ከኣየር ሁኔታዎች ጋር ከሚመሳሰሉ ውስብስብ ዲናሚካል ሲስተምስ ኣንፃር ሊታይ እንደሚችል ያመላክታል። ሌላው፣ ትልልቅ ትረካዎች፣ በትንንሽ ትረካዎች፤ ትልልቅ ህልሞች፣ በትንንሽ ህልሞች፣ ትልልቅ ክስተቶች በትንንሽ ክስተቶች ውስጥ ራሳቸውን የሚደግሙበት ሁኔታ ነው። ከዚህ ጋርም ተያይዞ፣ የሰው ልብም ሆነ መንፈስ ድንበር ዓልባ፣ ታሪኩም ልማዱም ድንበር ዓልባ፣ ማንነቱም ሳይቀር ኣንዱ በሌላው ውስጥ የተወሻሸቀ የመሆኑ፣ ኣንዱ ራሱን በሌላው ውስጥ የማግኘቱ፣ ኣንዱ የሌላውን ህልም የማለሙ፣ ጉዳይ ነው። ከሳይንሱ ይህ ከፍራክታል ጂኦሜትሪ (Fractal Geometry) ፅንሰ-ሃሳብ ተወስዶ ከምናቃት ከዶቃም፣ ከምናጣጥማት ኣነባበሮም፣ ከምንኖራት ስቅታም ምስል ገዝቶ የተገለፀ የሃሳብ ምህዋር ነው። እንግዲህ ይህ መግቢያና መውጫ እንጂ መፃፉን ራሱን ኣይደለም። ከዚህ በላይ እንድነግራችሁ ካሻችሁ ወደመፃፉ ልምራችሁ። ከቻላችሁ፣ እግራችሁን እንደ ቡዲሂዎች ኣጣጥፋችሁ ኩፍስ በሉና ተመሰጡበት! ታተርፋላችሁ። 

No comments:

Post a Comment