Sunday, January 19, 2014

ኣንድ እርምጃ ወደራስ፣ ወይ ለዕብደት፣ ወይ ለዓርነት …

ህይወት መላወሻ፣ ማመለጫ ስትነሳው፤
ከራሱ ልቦና ጠለቆ ይገባል ሰው፡፡
ዓርነት ሊወጣ፣ ወይም … ጭራሹኑ ሊያብደው፡፡

ኤላን ፍለጋ/የኣዞ ኮሌጅ
ልቦለድ ታሪክ ከኦ’ታም ፑልቶ
መግቢያ ወይም መውጫ

ይህ፣ የትግል ታሪክ ነው። ይህ፣ ልንረዳውም ልንቆጣጠረውም ከምንችለው በላይ በሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ ማንነትን የመፈለግ፣ ህልምን ለሟሟላት የመውደቅና የመነሳት፣ እማይታሰብ ህማምን የመቀበል ታሪክ ነው። ዓለም በአሜኬላ እንደታጠረች እስር ቤት ሆናበት መሄጃ መላወሻ ስትነፍገው፣ ሰው ወደራሱ ውስጥ ይሰጥማል። ወይ ኣብዶ ቀውሶ ሊጠፋ፣ ወይም ፍፁም ሃያል ማንነቱን ሊያገኝ። ይህ፣ ወደራሱ ውስጥ ፍፁም ጠልቆ የራሱን ብቻ ሳይሆን የሁላችንንም ሃይል ከነፍሱ ማህፀን ፈልቅቆ ለማውጣት የቻለ የኣንድ ሰው ታሪክ ነው። ግን፣ ይህ ሃይሉ፣ መጥፊያውና መጥፊያችን ይሆን ይሆን ወይስ መዳኛውና መዳኛችን? ሃይሏ ዕዳዋ እንደሆነባት ዓለም ሃይሉ ዕዳውና ዕዳችን ይሆን ይሆን?

ይህ፣ በኣገር-በቀል ባህሎችና በዘመናዊነት መካከል እየሆነ ስላለው የማያቋርፅ ፀብ የሚተርክ ታሪክ ነው። በተፈጥሮና በፈጠራ፣ በለውጥና በቋሚነት፣ በግለሰብና በማህበረሰብ፣ በነፃነትና በታዛዥነት፣ … መካከል ስላለው የማያቋርጥ ፍልሚያ የሚተርክ ታሪክ። ይህ የኩሴ ታሪክ ነው። ይህ፣ ኤላን፣ በኮንሶ ስነ-መለኮት ውስጥ ሃያል የውሃ (የምንጭ) ጠባቂ መንፈስ የሆነውን ኤላን፣ ፍለጋ ወጥቶ ሺህ መናፍስትን ከልቡም ከየኣዙሪቱም ውስጥ ያገኘው የኮንሶው የኩሴ ታሪክ ነው። ባህሉን መጠበቅ የተፈጠረለት ዓላማ፣ የመወለዱም፣ የመኖሩም ምክንያት፣ እንደሆነ ያስብ ነበር ኩሴ። ግን፣ ከዚያው፣ ሊጠብቀው ከተነሳው ባህል ጋር እርቅ-ኣልባ በሚመስል ግጭት ውስጥ ይገባል። ምክንያቱ ጥላቻ ኣይደለም፤ ፍቅር ነው። ኣፈቀረ። ኣፈቀረና፣ ድንበር ዘለለ። ተገደለ፣ ገደለ፣ ተወገዘ፣ ተጋዘ። ፍቅር ሁልግዜም እንዲህ ያደርጋል። ግን፣ ይህ የፍቅር ዘለዓለማዊ ህግ ነው? ኩሴን መሳይ ሰዎች ይህንን እውነት ሊቀይሩ ኣይቻላቸውም? ይህች ዓለም፣ ይህች ኑሮ ምንድናት? ሰውስ ምንድነው? ባህልስ ምን? ተፈጥሮስ፣ ጊዜስ፣ ቦታስ፣ ነፍስስ፣ መንፈስስ፣ ሃይልስ፣ ስልጣንስ፣ እምነትስ፣ ፅናትስ? ትዕግስት እራሷ ምንድነች? ትዕግስት? ለነዚህ ሁሉ ምላሽ ለመስጠት እሚሳነው እማይመስለው ኩሴ፣ እንዴት ላረጀ የፍቅር ህግ ይገብራል? እንዴት ላረጀ የፍቅር ጥሪ ምላሽ ይሰጣል? ወይስ እሱ በፍቅር ሰንሰለት ተተብትበው ወደ ጥፋታቸው እንዳዘገሙ ታሪክ እንደማይረሳቸው ሃያላን፣ ሃይሉ ድክመቱም የሆነበት፣ የተፈረደበት ምስኪን ነው?

ምነው፣ ፍቅር እንዲህ ጨከነች? ምነው፣ ህይወት እንዲህ ፀለመች? ምነው፣ ትግል እንዲህ በረታች? ምነው፣ ጥበብ እንዲህ ትርጉም ኣጣች?

ይህ፣ የሞተ፤ ተነሳ፣ ኣሳደደ፤ ያዘ፤ ታሪክ ኣይደለም። ይህ፣ የጡዘትና የልብ ሰቀላ ተረክ ኣይደለም። ይህ፣ የጠያቂዎችና የፈላጊዎች፣ የፈረሱና የፈረሰኛው፣ ልቅ ሜዳ ነው። መውደቅ መነሳት የሚሆንበት፣ ሽንፈት ጀግንነት የሚሆንበት፣ ውድቀት ብቃት የሚሆንበት፣ ዝግመት ፍጥነት የሚሆንበት፣ በልቦና የመኳተን፣ በልቦና የመስጠም፣ በልቦና የመክነፍ ታሪክ። በዚያ ውስጥ ታላቅ ሃሴት፣ ታላቅ ስኬት፣ ታላቅ መብቃት ኣለ። ይህ፣ የኮንሶው የኩሴ፣ የሰው ልጆቹ የኛ ታሪክ ነው። ይህ፣ ወደ ራስ ማንነት፣ ወደ ነፍስ ጥልቀት፣ ወደ ተፈጥሮ ጉልጥምጥሚት፣ … የመመለስ ታሪክ ነው። ኣዎ፣ በዚያ ውስጥ ድንበር ዓልባነት፣ ዘመን ዓልባነት፣ ገደብ ዓልባነት ኣለ። መፃፉ፣ ታሪኩ፣ በሩን ብቻ ነው እሚከፍት። ዘልቀው እሚገቡት፣ እዚያ እሚደርሱት ኣንባቢያን ራሳቸው ናቸው። በዚህ በኣንድ በር ውስጥ የየራሳቸውን በር ያገኛሉ፤ በዚህ ኩሴ በተራመደበት ኣንድ መንገዱ ውስጥ የየራሳቸውን መንገድ ይቀይሳሉ። ታሪኩ በሶስት መቶ ገፆች ይጠናቀቃል። የኣንባቢያን ብራና ግን ከሺ ቅጠል በላይ ይገለጣል። ይህንን ስለዚህ መፃፍ ስናገር ኣላፍርም። ላለማንበብ ምክንያት የሚፈልግ፣ ካሻው ይህን ከምክንያቶቹ እንደ ኣንዱ ይቁጠር። የሚያነብ ግን ሁሌም ያነብባል። እርሱ እሚፈልገውን ያውቃልና ለማድረግ ምክንያት ኣያሻውም፤ ምክንያት ኣይገድበውም። እንዲህ ላለው ኣንባቢ ይህንን መፃፍ በልበ ሙሉነት እጋብዘዋለሁ። እርሱ፣ ያልኩት ሃሰት ወይም ግነት እንደሁ ኣንብቦ ይፈርዳል። በዚያ ውስጥ ቅሬታ የለም። ደስታ ብቻ። ምስጋና ብቻ።

ታሪኩ እንዲህ ነው፡ (ግድ የለም፣ የንባብ ስሜት እሚያጠፋ ሚስጥር ኣላወጣም፤ ሲጀመርም እንዲያ ያለ ምስጥር ብዙም የለበትምና።) - የኮንሶው ሰው ኩሴ ከባህሉ ጋር ይጋጭና፣ ለእስራትና ለስደት ይዳረጋል። ከዚያም ለኣርባ ዓመታት ግድም በኮንትሮባንድ ዓሳ ኣጥማጅነት በኣባያና በጫሞ ሃይቆች ላይ ይኖራል። በዚያ ህልም በሚመስል ውበት ውስጥ፣ በዚያ፣ ሞት በከበበው የኣዞ ኮሌጅ ውስጥ፣ ለኣርባ ዓመታት ህልም በሚመስል ህይወት ውስጥ በህማምም በትፍስህትም ይመላለሳል። ከልጅነቱ የተለከፈበትን፣ እቀዬው ተነበረች ምንጭ ውስጥ ፈልጎ ያላገኘውን፣ ሊያናግረው ተመኝቶ ኣለመወለደ ገደብ የሆነበትን፣ ኤላን መፈለጉን ኣያቆምም። እርግጥ ብዙ ግዜ ይክደዋል፤ እንደገና ግን ይፈልገዋል። ይህ የዕድሜ-ልክ ዕጣ-ፈንታው የሆነ ይመስላል። የሌለን ነገር፣ እማይገኝን ነገር፣ መፈለገ። ጥቁርን ድመት በጨለማ ክፍል ውስጥ መፈለግ እጅግ ኣስቸጋሪ ነው። በተለይ ድመቷ በዚያ ክፍል ውስጥ ካልሆነች፤ ይላሉ ኣሉ ሩሲያዊያን። (ይህ ሰዓሊ በቀለ መኮንን በኣንድ ዝግጅት ላይ ግጥሙን ኣንብቦ የግጥሙን መነሻ ሃሳብ ሲናገር የሰማሁት ነው።) ኣባባሉ ደስ ይላል። ፍለጋው ግን ለፈላጊው ጣዕር ነው። በተለይ እንደኩሴ ላሉ፣ ማንነታቸው፣ ህልምና እውናቸው፣ ፍቅርና ጥበባቸው በዚያች ጥቁር ድመት ዙሪያ ለሚሽከረከር ሰዎች።

ፍለጋ ግን በራሱ ስኬት ነው። ፅኑ ፍለጋ በራሱ ብቃትና ፅድቅ ነው። ልባዊ ፍለጋ በራሱ ማግኘት ነው። በማታብል፣ ማስመሰል በሌለባት ፍለጋ ውስጥ ሁሌም ባከነ እሚባል ጊዜ ኣይኖርም። እያንዳንዱ ስህተት፣ እያንዳንዱ ውድቀትም ኣንድ እርምጃ ወደፊት ነው። ከነፍስ የሆነ ፍለጋ ፈላጊው ባላሰበውም መንገድም ካንድ ግብ ሊያደርሰው ይችላል። ያ ግብ እሱ ያለመው ላይሆን ቢችልም። ግን፣ እዚያ ደረጃ የደረሰ፣ ሳያውቀውና ሳያልመው ይፈልገው የነበር ያንን ግብ እንደነ ይረዳል።

ኩሴ፣ በእንዲህ ኣይነት ኑሮ ውስጥ ኣልፎ የሕይወቱ መጨረሻ ላይ ደርሷል። ለህልፈቱ ኣንድ ሳምንት እንደቀረው ያውቃል። እና፣ ታሪኩ የሚሆነው በዚያ የኩሴ የመጨረሻ ሳምንት ውስጥ ነው። በዚህ ኣንድ ሳምንት ወስጥ የሰባ ዓመታት ህይወት እውን በሚመስል ትዝታና ምልሰት ኣነባበሮ ሆኖ ይቀርባል። እውን፣ ቀናት እንደ ቢይ ተነጣጥለው እሚንከባለሉ ጠጠሮች ናቸው? ወይስ እርስ በርሳቸው እንደ ጨሌ የተሰፋፉ፣ እንደ ኣነባበሮም ኣንዳቸው በሌላቸው ውስጥ ላይነጣጠሉ የተጋቡ፣ ሰፍነግን እንደሰረፀ ውሃስ ኣንዱ ቀን በሌላው ውስጥ የሰረፀ? … ብዙ ጥያቄ ያነሳል፣ ብዙ ጥያቄ ያስነሳል ትርክቱ። ማስታወስና መሆን ኣንደ የሚሆኑበት ልምደት።

ኩሴ፣ ሰባ ዓመታትን በሰባት ቀናት ውስጥ ይኖራል። ስምንተኛው ቀን ማጥፊያውና መጥፊያው ሊሆን እንዳለው ወስኗል። ይህ፣ ራሱ ብቻ የሚያውቀው፣ እንደ ቅዱስ ተልዕኮም እሚያየው ዕቅዱ ነው። ከሱ ሌላ ማንም የሚያውቀው የለምና ሊያደርስ ያለውን ጥፋት ማንም ሊመክተው፣ ማንም ሊቀንሰው የተዘጋጀ ኣይመስልም። በነዚህ ሰባት ቀናት ውስጥም ማመንና መክዳት፣ ፈልጎ ማጣትና ማግኘት፣ ተስፋና ቀቢፀተስፋ፣ ብራሄና ፅልመት፣ … ይፈራረቃሉ። ግን ግን፣ ሰው፣ በሰባት ቀናት ውስጥ ሰባ ዓመታት መኖር እየቻለ፣ ሰባ ዓመታት መዋተቱ ለምን ነው? ከነዚያ ዓይነት ሰባት ቀናት በላይስ ወይም በሁዋላስ መኖር ምን ትርጉም፣ ምን ፍሬ ሊኖረው? በተለይ ስምንተኛውን ቀን በፈቃድ ኣለማየት ለዓለም ምንዱባን ኣዲስ ቀን እሚወልድ ከሆነ፣ ራስን በፍቅር መሰዋት እሚበዛ ፅድቅ ነው? ኩሴ፣ ያንን የራዕየ-ዮሃንስን ዘንዶ በሚያክል ብርታት ዓለምን ሊውጣት ከዘንዶ ጋር ጎዞ ጀምሯል። የጉዞው መጨረሻ ያው ሁላችን እምናውቀው፣ ኣብረንም ባይሆን እምንደርስበት፣ ወደድንም ጠላንም ሁላችንም እምንሄድበት መቅደስ ነው። ሞት። ግን፣ ምን ዓይነት ሞት? ግን መቼ? ግን ለምን? ግን እንዴት? …


No comments:

Post a Comment