Saturday, February 22, 2014

እውን እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይወዳል?

እውን እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይወዳል?

"ነቢያት እንዳ'ሸን፣ በፈሉበት ዘመን፣
ምነው ይሄ ትንቢት፣ ምነው ይሄ ንግርት፣ ለኔ ኣልሰምር ኣለ!?" ብያ'ላማርርም።  
በልቤ መቅደስ ውስጥ፣ ነግሳ እምትኖር፣ ኣንዲት እውነት ኣለች፤ ሌላ ኣያሻኝም።
ኣዕላፍ ነቢያት፣ ኣዕላፍ ድርሳናት፣ እልፍ ትንቢት ቢያኖሩም፣
ኣዕላፍ ጠንቋያት፣ ኣዕላፍ መናፍስት፣ ንግርት ቢደርቱም፤
በየቅፅበታቴ የምርጫዎች ኩርባ፣
በማኖረው ግብር፣ በማኖረው ምስል፣
መዳኔን መጥፋቴን፣ በጄ ካላመጣሁ፣
የትኛውም ትንቢት፣ የትኛውም ንግርት፣ ከቶ'ይፈፀምም!  

    
ይህችን የሰነበተች (በታህሳስ ኣጋማሽ 1996 ተጥፋ በኔሽን ጋዜጣ ላይም ወጥታ የነበር) መጣጥፌን ሳነብ ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች በድጋሚ ወደ ኣንባቢዎች እንዳደርሳት ገፋፉኝ፡

የተመረጥን ነን፤ ማለት ቀላል ነው። በተለይ እንደ እግዚኣብሄር የቅርብ ሩቅ በሆነ፣ እውን መርጠሀናልን? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ በዋዛ በማይደመጥ መራጭ፣ የተመረጥን ነን፤ ማለት። የመራጩ ማንነት ለምን እንደተመረጥን ማወቅንም ፈተና ያደርገዋል። እውን በእርሱ ለምክንያት እንደተመርጠን እምናምን ከሆነ ደግሞ፣ ለዚያ ምክንያት ብቁ ሆኖ መኖር ትልቁ፣ እጅግ ትልቁ፣ ፈተና ሆኖ ከፊታችን ይደቀናል። ወይም የጉዞኣችንን ኣቅጣጫ ኣመላካች ሆኖ እርምጃችንን ይመራል። እምንፈረደው በተሰጠን ፀጋ መጠን ከሆነና ለፀጋው ብቁ ሆነን ካልተገኘን፣ መመረጣችን እርግማን ሊሆንብንም ይችላል። እንዲህ ታለ የምርቃት እርግማን ነፃ ለመሆን የመመረጣችንን ምክንያትና ግብ ኣውቀን ማድረግ ያለብንን ማድረግ ግዴታ ይሆንብናል። በተመረጠች ኣገር ለመፈጠር የኔ ድርሻ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ጊዜን የሁዋሊት ማሽከርከር መስሎ ከተሰማን፣ ቢያንስ፣ በመመረጣችን ዕዳ ውስጥ የኔ ቀንበር የቱ ነው? ማለቱ ተገቢ ሳይሆን ኣይቀርም። ዕዳን ለመሸከም ከመዘጋጀት ኣስቀድሞ ደግሞ እውን የመመረጥ ዕዳ እንዳለብን ማጣራቱ እሚገባ ነው። ይህ ከምክንያቶቼ ቀዳሚው ነው - ፍለጋዬ ያሳየኝን ማሳየት።  

ታሪክ ባለቤት ኣለው፤ ግልፅ ነው። ታሪክ፣ የየትኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን የስሜት ድርሻ፣ የስልጣን ድርሻ ኣይደለም፣ ይህም ግልፅ ነው። ግን፣ ብዙዎች ኣይኖሩትም። ታሪክ፣ ታሪክን የመንገርም የመጠበቅም ባለመብት እኔ ነኝ፤ የሚሉ ተራኪያንም ተዋንያንም ያሉበት ተረክና ተውኔትም ነውና። በተለይ ኣመዛኝ ታሪኳ በተረት በተሸመነ በ’ንደኛዋ ዓይነት ኣገር፣ የ’ንዲህ ዓይነቱ የስሜት ባለቤትነት መገለጫዎች በየታሪክ ምዕራፉ ነግሰው ይታያሉ። ይህ ክፋት ላይኖረው ይችላል። እኛ እንጂ እናንተ ስለታሪካችን ኣታውቁም። እኛ እንጂ እናንተ ለቅርሶቻችን ኣትቆረቆሩም፤ እያስባለ፣ ሌላ ታሪክ ነጋሪን፣ ሌሎች ተዋኒያንን፣ የመናገርም የመተወንም ድርሻ ካልነፈገ። መከፋፈልን ካላመጣ። የዕይታን መነፅር ካላጠበበ። ወይም መነፅራችንን ባንድ ዓይነት ቀለም ብቻ ካልቀባው። ብዙውን ጊዜ ይህ ይሆናልና ይህ የስሜት ባለድርሻነት ውጤቱ ኣሉታዊ ይሆናል፡- ታሪክን ሰፋ ካለ ኣንፃር ኣይቶ፣ በታሪካዊ ሂደቶች ውስጥ ያለውን ህብር (ፓተርን) ለማየት እንዳይቻል ያደርጋል። የታሪኩንም የማንነቱንም ምክንያትና ውጤት የማይረዳንና የማያብራራን፣ በኣማራጭ ትርክቶች ስሜቱ በቀላሉ የሚነካን፣ በዛሬውም በወደፊቱም ህልውናው እርግጠኛነት የማይታይበትን፣ ሲከፋም በትዕቢትና በንቀት፣ በማን-ኣህሎኝነት ስሜት የተሞለን፣ ትውልድ ያፈራል።

እውን እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይወዳታልን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስም፣ ጉዳዩን ቀድሞ ከሚነገርበት የዕይታ ኣንፃር ሰፋ ኣድርጎ ማየት በታሪካችን (በኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በኣፍሪካም ሆነ በመላው የሰው ዘር ታሪክ) ውስጥ ያለን፣ ብዙ ግዜ የማይስተዋልን፣ ህብር ሊያሳይ ይችላል። በዚያ ህብር ውስጥ፣ እንደ ትውልድ ኣባል የያንዳንዳችንን፣ እንደ ኣገርና እንደ ኣህጉርም፣ የኢትዮጵያንና የኣፍሪካን ድርሻ በጭላንጭሉም ቢሆን ሊያሳይ። ይህ ሁለተኛው ምክንያት ነው - በጋሪዮሻዊ ታሪካችን ውስጥ ህብርን የማየት ጥረት።

እኛ በተራ ዜግነታችን ይህንን እንጠይቃለን። ይህንን እናስባለን። ይህንንም እንላለን። እንዲህች ኣይነቷ፣ከዕውቀት ይልቅ ፍቅር ያመዘነባት፣ ሙከራችን ታላላቅ ምሁራኖቻችንን በጉዳዩ ላይ ይበልጥ እንዲሰሩበት ካሳሰበች፣ እውነቱን ከነማረጋገጫው ለማሳየት እንዲተጉም ካነሳሳች፣ ውይይታችን ተጨማሪ ፍሬ ኣፈራች ማለት ነው። እነሆ፡-


ኢትዮጵያዊነት - የመለኮት ባላደራነት?

"ምነው፣ መከራችን በዛሳ?" ብሎ ለሚጠይቅ ኢትዮጵያዊ ምዕመን ኣንድ የተለመደ መልስ ኣለ፡- "ኣባት እሚወደውን ልጁን ነው እሚቀጣ!" የሚል። "ምነው ምስኪን ኢትዮጵያ፣ እናት ኢትዮጵያ፣ ስቃይዋ መረረ፣ ፀሃይዋ ገረረ፣ ምድሯ ኣረረ፣ ሸክሟ ከረረ?" ለሚል፡- "ኣባት እሚወደውን ልጁን ነው እሚቀጣ!"

የማያቋርጥ ቁንጥጫን በፍቅር መገለጫነት ተቀብሎ፣ በሰቆቃ ሽልማትነት ተደልሎ፣ ከመጠየቅ የቦዘነ ግን ያለ ኣይመስልም። "ኣልበዛም? ለምን?" እናም፣ ይህ መልስ፣ መልስ የማይሆነው ብዙ ኣለ። ምላሹ ተጨማሪ ጥያቄዎችን እሚቀፈቅፍበትም፣ ብዙ!

ስለቅጣቱ ዕማኝ ማስቆጠሩ ኣያሻን ይሆናል። ነገር ግን፣ "ኣባት እግዚኣብሄር፣ ልጅ ኢትዮጵያን ስለመውደዱ ምን ማስረጃ ኣለ?" ብንል፣ ያወያያል። ይህ ቀላል ጥያቄ ኣይመስልም። በእርግጥ እግዚኣብሄር ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር ኣለውን?

ፍቅር ኣይታይምና መገለጫ ምልክቶቹን ማመዛዘን ምላሹን ይጠቁመን ይሆናል። (የቅጣትን የፍቅር ምልክትነት ለጊዜው እንተውና) ቢያንስ ሁለት ኣስተማማኝ መገለጫዎቹን እንመልከት፡-

ኣንድ፡- ኣፍቃሪ የተወዳጁን ስም ከኣፉ ኣይጥልም።
ሁለት፡- ኣፍቃሪ ተወዳጁ ከጎኑ እንዲለይ ኣይፈልግም።

(በነዚህ መመዘኛዎች፣ በነዚህ የፍቅር መገለጫዎች፣ ብዙዎቻችን እንደምንስማማ በማመን) እንጠይቅ፡- ኢትዮጵያን በተመለከተ እነኚህ ምልክቶች በሰው ልጅ መንፈሳዊ ታሪክ ውስጥ በማያጠራጥር መልኩ የተገለፁበት ጊዜና ሁኔታ ኣለ? ለዚህ ጥያቄ እንደ ምላሽ የሚሰነዘር ሌላ የተለመደ መልስ፡-

"ኢትዮጵያ በመፅሃፍቅዱስ ውስጥ ከ40 ጊዜ በላይ ተጠቅሳለች።"

ነገር ግን፣ ይህ ምላሽ ብዙ ሰዎች ያለጥርጣሬ የሚቀበሉት የታሪክ እማኝ ኣይደለም። ምክንያት፡-

ኣንድ፡- "ኢትዮጵያ" የሚለው ስያሜ፣ የኣጠቃላዩ ጥቁር ህዝብ መጠሪያ ነበር፣ የሚሉ ስላሉ በመፅሃፍቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰችው ኢትዮጵያ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዊያን የተባሉትም በዚህች ምድር ሰፍረው የነበሩ ህዝቦች፣ ስለመሆናቸው ያለጥርጣሬ ለማረጋገጥ ማስረጃው በቂ ኣይደለም።

ሁለት፡- ኣንዳንድ የመፅሃፍ ቅዱስ ህትመቶች፣ "ኢትዮጵያ" የሚለውን ቃል፣ "ኩሽ" ወይም "ሱዳን" በሚል ቃል ተክተው ያቀርባሉ። እንዲህ ዓይነቱ ልዩነትና መለዋወጥ ደግሞ ኢትዮጵያ ጨርሶ መፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ መጠቀሷንም ከጥያቄ ውስጥ ያስገባል። (ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ የተተረጎመው "ኩሽ" ከሚለው የግሪኩ ቃል ነው።)

ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች ክፍል በመሆኗ ቃሉ፣ "ኩሽ" ወይም፣ "ሱዳን" ይሁን፣ "ኢትዮጵያ፣" ልዩነት ኣያመጣ ይሆናል። ነገር ግን፣ የዛሬዋን ኢትዮጵያ እንደተወዳጅ የእግዚኣብሄር ልጅ በማየት ለሚኩራራ ህዝብ፣ ኩራቱ መሠረት አንዲኖረው ተጨማሪ ማስረጃ መጠየቁና ማቅረብ መቻሉ ግድ ነው።

ቢያንስ ከሙሴ ዘመን ጀምረን በሰው ልጅ መንፈሳዊ የታሪክ ሃዲድ ላይ እስከዛሬ ብንጓዝ የማይስተባበሉ እማኞች ግልፅ የሚያደርጉት እውነት ኣለ። ዘመኑ ረጅም ነው። ማስረጃውም ብዙ! ስለዚህም በዝህች ኣጭር ፅሁፍ መጥቀስ የምንችለው ኣንኳር ኣንኳሩን ብቻ ነው። በእምነት ታሪክ ውስጥ ወደር-ኣልባው ኣንኳር ያለው ደግሞ በእግዚኣብሄር መልዕክተኞች ታሪክ ውስጥ ነው። "እግኣብሄር ኢትዮጵያን ከኣፉ ኣይጥልም፤ ከጎኑም ኣይለይም።" እምንል ከሆነ ይህ ፍቅር በተለይና በላቀ ሁኔታ ሊገለፅ የሚችለው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ከእግዚኣብሄር መልዕክተኞች ጋር ባላቸው ቀጥተኛ ግንኙነት ነው። [የእግዚኣብሄር መልዕክተኞች ስል፣ እንደ ኢሳያስ፣ ኤርሚያስ፣ እና ዮሃንስ፣ … ያሉ፣ በኣንድ በተመሰረተ ሃይማኖት ውስጥ የሚነሱ፣ ተራ ነቢያትን ሳይሆን፣ ኣዲስ የእግዝኣብሄር ህግና ሥርዓትን ለምድር የሚገልፁ፣ ኣዲስ ሃይማኖትን የሚመሰርቱ፣ ኣዲስ ዘመንን የሚያስጀምሩ፣ የቀድሞ ህግጋትንና ስርዓቶችን የመሻርም የማጥበቅም የማብራራትም ሙሉ ስልጣን ይዘው የሚመጡ፣ የእግዚኣብሄር ነቢያትን፣ ማለቴ ነው።)  ከሙሴ እንጀምር፡

ሙሴና ኢትዮጵያ

"ሙሴም ኢትዮጵያዊቱን ኣግብቶኣልና ባገባት በኢትዮጵያዊቱ ምክንያት ማርያምና ኣሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ።" (ዘህልቁ 12፡1)

እግዚኣብሄር የማርያምና የኣሮን ተቃውሞ ኣሳዝኖት ገሰጣቸው፡-

"ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፣ እኔ እግዚኣብሄር በራዕይ እገለጥለታለሁ፤ ወይም በህልም ኣናግረዋለሁ። ሙሴ ግን እንዲህ ኣይደለም፤ እርሱ በቤቴ ተሁሉ የታመነ ነው። እኔ ኣፍ ለኣፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፣ በምሳሌ ኣይደለም፤ የእግዚኣብሄርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለምን ኣልፈራችሁም?" (ዘሁልቁ 12፡6-8)

ማርያም በለምፅ ኣሮን ደግሞ በፀፀት ተቀጣ፡- "ኣሮንም ሙሴን፡- ጌታዬ ሆይ፣ ስንፍና ኣድርገናልና፣ በድለንማልና እባክህ፣ ሃጢኣት ኣታድርግብን። …" ኣለ። (ዘሁልቁ 12፡11)

እንግዲህ ከነቢያት ሁሉ ልዬ ነቢይ የሆነው፣ የእግዚኣብሄርንም መልክ ያየው፣ ከእግዚኣብሄርም ጋር ኣፍ ለኣፍ የተናገረው፣ የመልዕክተኛው የሙሴ ባለቤት ኢትዮጵያዊት ነበረች፤ ወይም፣ እህት ሱዳናዊት ነበረች፣ ወይም ጥቁር የኩሽ ዘር ነበረች!

ክርስትናና ኢትዮጵያ

ከክርስቶስ ምድራዊ ቆይታ ጋር በቀጥታ የተገናኘ የኢትዮጵያ ወይም የኢትዮጵያዊያን ታሪክ ስለመኖሩ ኣላውቅምና ነው ይህንን ርዕስ፣ "ክርስቶስና ኢትዮጵያ፣" ከማለት ይልቅ፣ "ክርስትናና ኢትዮጵያ፣" ያልኩት። ነገር ግን፣ በሃዋሪያት ስራ ውስጥ የእግዚኣብሄር መልኣክ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ያስተምረውና ያጠምቀው ዘንድ ሃዋሪያውን ፍሊጶስን እንደላከው እናነብባለን። የኢትዮጵያዊው ወይም የኣፍሪካዊው ጃንደረባና የፍሊጶስ መገናኘት የኣጋጣሚ ጉዳይ ሳይሆን ኢትዮጵያን ወይም ኣፍሪካን ከክርስትና ግልፀት ጋር ለማቆራኘት የተላከ ሰማያዊ የታሪክ ቀለበት እንደሆነ እንረዳለን። 

ነቢዩ ሙሃመድና ኢትዮጵያ

ነቢዩ ሙሃመድ በእምነት ባድማ ውስጥ መለኮታዊ መለከታቸውን ሲነፉ የኣመፃ ሰራዊት የጭካኔ ፍላፃውን ሰበቀባቸው። ሰቆቃ ዶፍ ሆነ። ነቢዩ ተከታዮቻቸውን ከዚህ መዓት የታደጉት ፍፁም ጥበቃ ወዳለባቸው ቦታዎች እንዲሸሹ በማድረግ ነበር። ኣንዱ ሰላማዊ መጠለያ የነበረው ኢትዮጵያዊው ፅኑ ክርስቲያን ንጉስ ነጃሺ ነበር። (ኣንዳንድ ፀሃፍት፣ ኣድጃሚህ ኣብጁር፣ ይሉታል።) በ615 እ.ኤ.ኣ. ግድም ኢትዮጵያዊው ንጉስ የእግዚኣብሄርን ኣደራ (ከ83 እስከ 109 የሚገመቱ የነቢዩ ሙሃመድ ተከታዮችን) በፍቅርና በኣክብሮት ተቀበለ። ይህ የመለኮት ኣደራ ጠባቂነት ሁዋላ በወርቅ ተፈትኖ እንከን ኣልባነቱ ተረጋገጠ። ፅኑው ክርስቲያን ንጉስ የነቢዩ ሙሃመድን ቃልና ተልዕኮ እውነተኛነት መስክሮ ለእግዚኣብሄር ጥሪ ያለውን ታማኝነት በድጋሚ እውን ኣደረገ። ዓለም በክህደትና በኣመፃ ድንጉላ ላይ በሚጋልብበት ዘመን ነጃሺ በእምነት ከፍተኛ ዙፋን ላይ በመቀመጥ ኢትዮጵያ የዚህ ወደር ኣልባ በረከት ተቋዳሽ እንድትሆን ኣደረጉኣት። እንዲህ ተፅፏል፡-

"ንጉሱ (ስደተኞቹን) ጠየቃቸው፣ እንዲናገሩም ኣላቸው። እነርሱም መለሱ፡- 'ንጉስ ሆይ! ጣዖት እናመልክ ነበር፣ በርክሰትም ውስጥ እንኖር ነበር፤ ሙታንንም እንበላ፣ ሃጢኣትንም እንናገር ነበር። ... እግዚኣብሄር በመካከላችን ኣንድ ሰው ኣስነሳ፤ ... እርሱም ወደ እግዚኣብሄር ኣሃድነት ጠራን። ርክሰትንም እንድንሸሽ፣ ከሃጢኣትም እንድንርቅ ኣስተማረን።' ንጉሱም ከነቢዩ ቃላት ጥቂት እንዲያሰሙ ጠየቀ። ጃፋር የተባለው የሙሃመድ የቅርብ ዘመድ ስደተኞችን በመወከል ሱረቱ መርያም የተባለውን፣ ስለዘካሪያስ፣ ስለዮሃንስ መጥምቁና ስለ ማርያም የሚተርከውንና ክርስቶስ እንደተወለደ፡- 'ኣላህም በኔ ላይ ነው፤ በተወለድሁ ቀን፣ በምሞትበትም ቀን፣ ህያው ሆኜ በምነሳበትም ቀን፤' (ቁጥር 33) ስለማለቱ የተፃፈበትን ምዕራፍ ኣነበበ። ንጉሱም በበትሩ መሬት ላይ መስመር ኣሰመረና ኣለ፡- 'በእውነቱ በእናንተና በእኛ እምነት መሃል ከዚህ ትንሽ ጭረት የሚበልጥ ልዩነት የለም።'" (Mirzieh Gail: Dawn Over Mount Hira, P.4, H.M. Balyuzi, Muhammad and the Course of Islam, p. 33) (ትርጉም የራሴ)

የነጃሺ ዜና ዕረፍት በተሰማ ጊዜ ነቢዩ ኣሉ፡- "ዛሬ ኢትዮጵያዊው ፅኑ ኣማኝ ኣርፏል። የሙታን ፀሎት ለማድረግ ተሰባሰቡ።" (Hadith, Bukhari.Vol. 2) ታላቁ ነቢይ ለኢትዮጵያዊው ንጉስ የተደረገውን ፀሎተ-ሙታን መሩ። ይህ ሊታሰብ የሚከብድ ክብር ነው።

የነቢዩ ሙሃመድና የኢትዮጵያ ግንኙነት ታሪክ፣ ያች በየመፅሃፍቱ እምትጠቀሰው ኢትዮጵያ፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ስለመሆኗ ሊኖር የሚችለውን ጥርጣሬ ለመግፈፍ የሚያግዝ ይመስላል። ከላይ ባየነው ታሪክ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ የተሰኘችው ምድር፣ በትግራይ፣ ውቅሮ ኣቅራቢያ፣ ያለችውን የነጃሺ መንደር የሚመለከት ነው። ወደዚህች መንደር ጎራ ያለ፣ የነቢዩ ተከታዮችን መካነ-መቃብር ኣይቶ ይህንን ማረጋገጥ ይችላል።

ሌላው ኢትዮጵያ በመለኮታዊ የግብር ዕልፍኝ ውስጥ በክብር የታደመችው በእስልምና ታሪክ ውስጥ ከታላላቅ የእምነትና የፅናት ታሪኮች ኣንዱ በሆነው በቢላል ኢቢን ርቫን ልብ ኣሟቂ ታሪክ ውስጥ ነው። ኢትዮጵያዊው ቢላል በእምነቱ የማይነገር ስቃይን ተቀበለ። ኣበሻው ቢላል በእምነቱ ከሰዋዊ የባርነት ሰንሰለት ነፃ ወጥቶ የእግዚኣብሄር ባርነትን ኣክሊል ደፋ። ኣፍሪካዊው ቢላል በእምነቱ በነቢዩ ሙሃመድ የተሾመ የመጀመሪያው ሙኣዚን የመሆንን ክብር ኣገኘ። እንዲህም ኣሉ ነቢዩ፡-

"ቢላል ሆይ! ተነስና ይህንን ኣውጅ፡ ኣማኝ ካልሆነ በስተቀር ወደ ገነት የሚገባ ማንም የለም፤ …" (Hadith, Bukhari Vol. 8)

እረኛው ቢላል፣ ቴምር ሻጩ ቢላል፣ ኣፍቃረ-መለኮቱ ቢላል፣ በእምነቱ እስከ ዕለተ-ዕረፍታቸው ድረስ የነቢዩ ሙሃመድ የቅርብ ኣገልጋይ የመሆንን ወደር ኣልባ ክብር ኣገኘ። ነቢዩም ስለቢላል ታላቅነት እንዲህ በማለት ተናገሩ፡

"[ቢላል ሆይ!] የጫማዎችህን ዱካ በገነት ውስጥ ከፊት-ፊቴ ሰምቻቸዋለሁ።"
(Hadith, Bukhari Vol. 5)

ኡመርም እንዲህ ይል እንደነበር ተፅፏል፡ "ኣቡበከር ጌታችን ነው፤ ጌታችንንም (ቢላልን) ከባርነት ነፃ ኣወጣው።" (Hadith, Bukhari Vol. 5)

ሃፊዝንና ሩሚን የመሳሰሉ ታላላቅ ባለቅኔዎችም ከቢላል የፅናት ታሪክ የጥበብ ጥልቀትን ጨለፉ። እጅግ የተማሩና ያወቁ፣ በእምነትና በቅርበትም የበቁ የሚባሉ ሰዎች፣ ለኣዲስ ግልፀት ሲታወሩ፣ ቢላልን የመሰሉ ምስኪኖች የእምነት ጣሪያ ላይ መውጣታቸው ባለቅኔውን ሃፊዝን ኣስደንቆት እንዲህ ኣለ፡-

From Basrah comes Hasan,
from Habash comes Bilal,
From Sham comes Suhayb;
but from the soil of Mecca arises
Abu-Jahl; how strange!

"ከባስራ ሃሰን፣ ቢላል ከኢትዮጵያ ይመጣል፤
ከሻምም ሱሃይብ፣ ኣለሁ! ይላል።
ከመካ ምድር ኣቡ-ጃህል፣
የኣመፃን ጦር ይሰብቃል፤
በል፣ ይህ እንግዳም ኣይደል!"

(መካዊው ኣቡ-ጃህል ከነቢዩ ሙሃመድ ቀንደኛ ተቃዋሚዎች ኣንዱ ነበር።)

እንዲህ ሆነና፣ ነጃሺና ቢላል ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን በማያጠራጥር ሁኔታ ከመለኮታዊ ግልፀት ጋር ያቆራኙ ሰማያዊ ቀለበቶች ሆኑ።

ባብና ኢትዮጵያ

የብዙ ሃይማኖታዊ መፅሃፍት፣ የብዙ ምዕተ-ዓመታት ትንቢት፣ ሊፈፀም ነው። ሰማይና ምድር በምጥ ላይ ናቸው። በ1760 እ.ኤ.ኣ በሼክ ኣህመድ የተጀመረው ፍለጋ በሰማዕታት መስዋዕትነት፣ በፅኑዓን ትጋት፣ ፈለጉን ኣድምቆ በ1844 ላይ ደርሷል። የጠራ መንፈሳዊ ዓይን ያላቸው ደማቋ መለኮታዊ ኮከብ ከሽራዝ ኣድማስ ላይ ክንብንቧን ስትገልፅ ተመልክተዋል። ጊዜው ኣስፈሪ ነው። የተናፈቀው ምፅዓት ይዞት የሚመጣው መከራና ፀጋ ኣስፈሪ ነው። የሚፈለገው፣ በፍርድና በምህረት ሴይፉ፣ የትንቢትን ዘመን ደምድሞ የፍፃሜን ዘመን የሚያስጀምረው የእግዚኣብሄር መልዕክተኛ ነው። የሚፈለገው፣ በልሳን ሽፋን ስር ተከልሎ የቆየው ሰማያዊ ሙሽራ ነው። የሚፈለገው፣ ለዘመናት የፃድቃን ራዕይና የሰማዕታት ደም የጎረፈለት ቃይም ነው። የሚፈለገው ባብ ነው። የእግዚኣብሄር በር ሲከፈት፣ ገፁ በነጎድጓዳዊ ሃይል ሲገለፅ፣ ለማየት እርግጠኛ መሆን ያስፈራል። ሰማይና ምድር ድንገት ሲገጥሙ ምስክር ለመሆን መዘጋጀት ያስፈራል።

ጎህ ሲቀድ እንደሚደመጥ የቤተክርስቲያን ደወል በምድር ዙሪያ ከሚደመጡ የፍፃሜ ደወሎች በስተቀር ዓለም ሁሉ ተኝቷል። የነቁ ጥቂቶቹ፣ ከነቁ ጥቂቶቹም የተመረጡት እፍኝ የማይሞሉቱ፣ ግን በመንፈሳዊ ፍኖተ-ብርሃን እየተመሩ ሽራዝ ደርሰዋል። ኣዲስ ዘመን ሲወለድ በዓይናቸው ከሚያዩ ጥቂት ብፁኣን የመጀመሪያው መሆን ያስፈራል! ሙላ-ሁሴንን መሆን ያስፈራል!  

ከፅኑ ፈላጊዎች ዋነኛው የሆነውን፣ ሁዋላ በባብ በራሱ ባቡል-ባብ ተብሎ የተሰየመሙን ("ባብ" በኣረብኛ በር ማለት ነው። "ባቡል-ባብ" ደግሞ የበሩ በር ማለት።) ሙላ ሁሴንን በሽራዝ መግቢያ ላይ የተቀበለው ባብ እራሱ ነው። ሙላ ሁሴን ግን ኣላወቀም። እንዴት ሊያውቅ ይችላል? በውቅያኖሱ ይሆንታ ካልሆነ በስተር ጠብታ በውቂያኖስ ፊት መቆሟን እንዴት ልታውቅ ይቻላታል? ድንገት በሚበርቅ ፀሃይ ፊት ዓይን እንዴት ሊገለጥ ይችላል?

በባብ ዝምታ ውስጥ ሩህሩህነት ነበር። በሩህሩህነቱ ውስጥ ግብዣ ነበር። ጉዞ ያደከመውን ሙላ-ሁሴንን፣ ከከተማው ውጭ ባለ መስጊድ ውስጥ ወደሚጠብቁት ባልንጀሮቹ ለመመለስ ልቡ የተሰቀለውን ሙላ-ሁሴንን፣ ወደ ባብ ቤት የሚጣራ ንጉሳዊ ግብዣ። በግብዣው ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነበር! ኣዎን፣ በባብ ግብዣ ውስጥ ኢትዮጵያዊው የባብ ኣገልጋይ ሃጂ ሙባረክ ነበር! ቅዱሱ ሙባረክ! …

ባብን ተከትሎ ወደ ቤቱ ያመራው ሙላ-ሁሴን ሁዋላ እንደተረከው፡-

"ብዙም ሳይቆይ ኣንድ ልከኛ ቤት በር ላይ ደረስን። እርሱ (ባብ) በሩን ኣንኳኳ። በሩም በኢትዮጵያዊው ኣገልጋይ ተከፈተ። ባብ ጉበኑን ሲሻገር፣ 'ፀጥተኞች ሁናችሁ በሰላም ግቧት፤' (ቁርዓን 15፡6) በማለት እንድከተለው ኣመለከተኝ።"

ኢትዮጵያዊው ሃጂ ሙባረክ ከመቼ ጀምሮ ባብን ሲያገለግል እንደቆየና ከዚያች ቀን በፊት የባብን መልዕክተኛነት ያውቅ መሆን ኣለመሆኑን የወደፊት የታሪክ ተመራማሪዎች ምላሽ ይሰጡበት ይሆናል። ነገር ግን፣ የሙባረክ ክፍል ከባብ ክፍል ለጥቆ ያለ ስለነበርና ሙባረክ ለጌታው ጥሪ ቅፅበታዊ ምላሽ ለመስጠት በንቃት ይጠባበቅ ስለነበር፣ በዚያች የተቀደሰች ምሽት፣ ባብ ራሱ፣ "ይህች ምሽት፣ ይህች ሰዓት፣ በሚመጡት ኣዝማናት፣ ከታላላቆችና እጅግ ከፍተኛ ክብር ካላቸው ክብረ-በዓላት ኣንዷ ትሆናለች።" ባላት የግንቦት 22፣ 1844 (እ.ኤ.ኣ) ምሽት፣ ባብ ታላቁን ተልዕኮውን ለሙላ ሁሴንና ለፍጡራን ሁሉ ሲያውጅ፣ የትኛውም ዓይን ኣይቶት፣ የትኛውም ጆሮ ሰምቶት፣ የትኛውም ልብ ኣልሞት የማያውቀውን፣ እያንዳንዱ የተፈጠረ ነገር ነፍሱን ለእግዚኣብሄር እንዲሰጥ ያደረገውን መለከቱን ሲነፋ፣ ሙባረክ ምስክር ነበር። የዘለዓለማዊነት ሞገድ የጊዜን ግድብ ሲደረምስ ሙባረክ ምስክር ነበር። ዘመነፈጁ የመቅደስ መጋረጃ ተተርትሮ የእግዚኣብሄር ገፅ ሲገለፅ፣ ሙባረክ ምስክር ነበር። ኣሮጌው ሰማይ ተጠቅልሎ በምትኩ ኣዲስ ሰማይ ሲዘረጋ፣ ሙባረክ ምስክር ነበር። የባብ የመጀመሪያ ቅዱስ መፅሃፍ፣ ነፍስና ስጋን በሚያርድ ራዕያዊ ነጎድጓድ ሲንዶቀዶቅ፣ ሙባረክ ምስክር ነበር። ኣዎ፣ የእግዚኣብሄር ቀን ስትወለድ፣ ኢትዮጵያዊው ሙባረክ፣ ኣፍሪካዊው ሙባረክ፣ የኩሽ ዘሩ ሙባረክ፣ የተመረጠ የታሪክ ዕማኝ፣ የተመረጠ የታሪክ ተሳታፊ ነበር!

ባብ መልዕክቱን ባወጀ በሶስተኛው ቀን ሙላ ሁሴንና የባብን ማንነት በራዕይ ኣይቶ የተቀበለው ሙላ ኣሊ ወደ ባብ ቤት በደስታና በፍቅር ሰክረው ሲመጡ የተቀበላቸው ሙባረክ ነበር። ኣላቸውም፡-

"ጎህ ሲቀድ፣ ወደ ጌታዬ ተጠራሁ። እርሱም የቤቱን በር ከፍቼ በጥበቃ እቆም ዘንድ ኣዘዘኝ። ኣለኝም፡- 'ሁለት እንግዶች ዛሬ በጠዋቱ እዚህ ይደርሳሉ። በእኔ ስም የሞቀ ሰላምታ ኣቅርብላቸው። ስለእኔም ሁነህ እንዲህ በላቸው፡- 'እነሆ፣ በእግዚኣብሄር ስም ግቧት።'"

ታሪክ ራሷን የደገመች መሰለ። ቢላል፣ በነቢዩ ሙሃመድ፣ "ተነስና ይህንን ኣውጅ፡- ኣማኝ ካልሆነ በስተቀር ወደ ገነት የሚገባ ማንም የለም፤ …"  እንዲል እንደተነገረው፣ ሙባረክም በገነት መግቢያ ላይ ቆሞ፡- "እነሆ፣ በእግዚኣብሄር ስም ግቧት።" እንዲል ታዘዘ።

ትረካው በዚህ ብቻ ኣላበቃም። ባብ ለሃይማኖታዊ ጉዞ ወደ መካ ለመሄድ በሚዘጋጅበት ወቅት ኣብረውት ይጓዙ ዘንድ የመረጠው ሁለት ሰዎችን ብቻ ነበር። ኣንዱ "የህያዉ ፊደላት፣"  ተብለው ከሚጠሩት ከ18ቱ ደቀመዛሙርት ከፍተኛውን የቅድስና ደረጃ የያዘው፣ ቅዱስ የተባለው፣ የ22 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ ሁለተኛው ግን ሙባረክ ነበር። ባብ በሃይማኖታዊ ጉዞው ወቅት በኣንድ የተቀደሰ መካነ-መቃብር ውስጥ እንደ ተለምዶኣዊው ስርዓት 19 ጠቦቶችን መስዋዕት ሲያደርግ፣ ዘጠኙን የሰዋው በራሱ ስም ሲሆን፣ ሰባቱን በቅዱስ ስም፣ ሶስቱን ደግሞ በሙባረክ ስም ነበር።

ከስድስት የእስራትና የግዞት ዓመታት በሁዋላ፣ በሃምሌ 9፣ 1850 እ.ኤ.ኣ ባብ መስዋዕት ሲደረግ ዜና ዕርገቱ ለቅዱሱ ቤተሰብና ለኣገልጋዮቹ ኣልተነገረም ነበር። ወዲያውም የባብ እናት ሙባረክን ኣስከትለው ከኢራን ወደ ኢራቅ ኣመሩ። ሙባረክ የባብን መመለስ እጅግ ኣድርጎ ይመኝና ይናፍቅ ስለነበር ኣረንጓዴ መያዣ ያለው መጥረጊያ ኣበጅቶ በየዕለቱ ጎህ ሲቀድ ከኣረቢያ ውጭ እጅግ ቅዱስ ከሆኑት ቦታዎች ዋናው በሆነው በኢማም ሁሴን መካነ-መቃብር ዙሪያ ያለውን ደጀሰላም መጥረግ ጀመረ። (ኣረንጓዴ ከነቢዩ ሙሃመድ ቀጥተኛ ዝርያዎች ጋር የተያያዘ ቀለም ሲሆን፣ ባብም የሙሃመድ ዘር በመሆኑ፣ የመጥረጊያው መያዣ ቀለም የዚያ ምሳሌ ነው።) ባብ እስኪመለስ ድረስም ይህንን ግብረ-እምነት ሊፈፅም መሃላ ኣደረገ። ኢትዮጵያዊው ሙባረክ፣ የባብ ታማኝ ኣገልጋይ የነበረው ሙባረክ፣ በኣርባ ዓመቱ ሲያርፍ የባብን ምልሰት በፍፁም እምነት በመጠባበቅ ላይ ነበር። ታላቅ የቅድስና ኣገልግሎቱን ፈፅሞ፣ ኢትዮጵያንም በማይደበዝዝው ሰማያዊ መዝገብ ላይ እንደገና እንድትሰፍር ኣድርጎ፣ በወዲያኛው መንግስት በእምነታቸው የተሰዉ ዕልፍ ኣዕላፍ ሰማዕታትን ሲቀላቀል፣ ባብን በመጠባበቅ ላይ ነበር። ሙባረክ የባብን ምልሰት በመጠበቅ በየዕለቱ ይጠርገው በነበረው ቅዱስ መካነ-መቃብር ኣቅራቢ ያርፍ ዘንድ የኣምላክ ፈቃድ ሆነ።

ባሃኦላህና ኢትዮጵያ 

ከባሃኦላህ ኣገልጋዮች ውስጥ ኢትዮጵያዊያን እንደነበሩ ኣንዳንድ ፅሁፎች ይጠቁማሉ። ይህንና የነዚህን ሰዎች ማንነትና ደረጃ በዝርዝር ለማወቅ ሰፊ ጥናት ይጠይቃል። ባሃኦላህ ለኢትዮጵያ የሰጣት ክብር ግን የተለየ መልክ ኣለው። ከቢላልና ከኣልነጃሺ ጋር በተያያዘ በቅዱስ ብዕሩ ኢትዮጵያን ኣነሳ። የዓለም ነገስታት የኢትዮጵያን ንጉስ ምሳሌ ይከተሉ ዘንድ ለነገስታት በፃፈው ፅላቱ ላይ እንዲህ ኣለ፡-

"የባታው ፀሃይ [ሙሃመድ] ከጌታህ፣ ከተከበረው፣ ከፍፁም ታላቁ፣ ፈቃድ ኣድማስ በላይ ያበራባቸውን ቀናት ኣስታውስ። የዚያን ዘመን የሃይማኖት መሪዎችም እንዴት ፊታቸውን ከእሱ እንደመለሱ፣ ሊቃውንትም ከእሱ ጋር እንደምን እንደተሟገቱ፣ ኣስብ። … ከየኣቅጣጫው ይደርስበት የነበረው መከራ እጅግ የከፋ ስለነበር፣ ኣጋሮቹ እንዲበታተኑ ኣዘዛቸው። ከመለኮታዊ ክብር ገነት፣ ትዕዛዙ እንዲህ ተገለፀ። ስለዚህም ልብ በል፤ ከነዚህ ተከታዮች ኣንዱ የሆነው፣ በኢትዮጵያዊው ንጉስ ፊት ቀርቦ፣ ከቁርኣን ኣንድ ምዕራፍ ሲያዜም፣ ንጉሱ ለባለሟሎቹ እንዲህ በማለት ተናገረ፡- 'ይህ በእውነቱ ሁሉን ኣዋቂው፣ ፍፁም ጠቢብ በሆነው፣ የተገለፀ ነው። የኢየሱስን እውነተኛነት የሚቀበልና ትምህርቶቹን የሚያምን ኣሁን የተዜመውን ከቶም ሊክድ ኣይችልም። በእውነቱ በራሱ ተብቃቂ፣ በኣደጋ ጊዜ ረዳት፣ በሆነው (ለተገለፀው) እኛ ዘንድ ላለው ለእግዚኣብሄር መፅሃፍ እንደምንመሰክር ሁሉ ስለዚህ (ቃል) እውነትነት እንመሰክራለን።' "  (Baha'u'llah, The Summons of the Lord of Hosts, p. 101) (ትርጉም የራሴ)

እመግቢያችን ላይ እንዳልነው፣ ታሪክ ነጋሪ መንገር እሚፈልገውን ተረክ ይመርጣልና፣ ዛሬ የንጉስ ነጃሺን ታሪክ በኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳናት ውስጥ ማግኘት ከባድ ነው። ይህንን የማንነታችንን ኣኩሪ ገፅታ ለመግለጥ ባህር መሻገር፣ ኣድማስ ማሳበር፣ ይኖርብናል። ቢሆንም፣ ድካማችን ለከንቱ ኣይሆንም። ሰብዓዊው ንጉስ ነጃሺ፣ ኢትዮጵያዊው ንጉስ ነጃሺ፣ ኣፍሪካዊው ንጉስ ነጃሺ፣ በመለኮታዊ የግልፀት ፅላቶች ውስጥ ከስሜት በላይ፣ ከዘመን በላይ፣ ከሃብትም ከግዛትም በላይ በሆነ ኢመዋቲ ክብር ተመዝግቦ እናገኘዋለንና። ንጉሳችን፣ ሰው በሚያበጀው፣ ሰው በሚያፈርሰው፣ ታሪክ ውስጥ ያላቸውን ክብር ቢንቁ ምን ይጎድልባቸዋል ታዲያ? ይህንን ነው ባሃኦላህም ለዓለም ነገስታት ልብ እንዲሉ ያሳሰበው። ከላይ የጠቀስኩትን የንጉስ ነጃሺን ፅድቅ መስክሮ ሲያበቃ የኢራኑን ንጉስ ናስሩዲን ሻህን እንዲህ ይለዋል፡-

"በእግዚኣብሄር ስም እምልልሃለሁ፣ ንጉስ ሆይ! በጌታ፣ በፍፁም መሃሪው፣ ትዕዛዝ ከሚስጢራዊው ቅርንጫፍ ላይ፣ በኣዕላፍ ቅላፄዎች ለሚያዜመው ለዚያ ዘማሪ ወፍ ጆሮህን ብትሰጥ ኖሮ፣ ሉዓላዊነትህን ኣሽቀንጥረህ ጥለህ፣ ከኣድማሱ በላይ የንጋቱ መፅሃፍ ወደሚያበራበት ወደዚያ ልዕለ-ፍጥረታዊ ክብር ፊትህን ባዞርክ ነበር። የእግዚኣብሄርን ነገሮች ለማግኘት ባለህም ጉጉት፣ ያካበትከውን ሃብትም በሙሉ ትተው ነበር። ያኔ፣ ራስህን ወደ ከፍተኛነት ጉልላት፣ ወደ ክቡርነት ቁንጮ እና ወደ ነፃነት መጥቀህ ታገኝ ነበር። … ዛሬ ያንተ የሆኑት፣ ነገ ግን ሌሎች የሚወርሷቸው ነገሮች፣ ምን ፋይዳ ይኖራቸዋል? …" (Baha'u'llah, The Summons of the Lord of Hosts, p. 101) (ትርጉም የራሴ)

ኣዎ፣ ዛሬ የኛ በሆኑ፣ ነገ ግን ሌሎች በሚወርሷቸው ነገሮች መመካት ምን ዋጋ ይኖረዋል? እነኛን ፍሬ ከርስኪ ነገሮች ነበር ንጉስ ነጃሺ ኣሽቀንጥረው ጥለው ዘለዓለማዊውን ክብር የመረጡት። ብዙ የኣገር መሪዎች፣ የሃይማኖትም መሪዎች፣ ከዘለዓለማዊው ክብር ኣላፊውን ይመርጣሉ። ያን ማጣት በእግዚኣብሄር መንገድ እሚያመጣባቸውን ህማም ይሸሻሉ። ተከታዮቻቸም በየዘመናቸው የሚመጣላቸውን ብርሃን ትተው እነሱኑ ይከተላሉ። ይህንን የሰው ልጅ ድክመት ቢያውቅም ባሃኦላህ ዓለማዊም ሆኑ ሃይማኖታዊ መሪዎች የኢትዮጵያዊውን ንጉስ ምሳሌ እንዲከተሉ ኣሳሰባቸው። መሪዎች ብቻም ሳይሆኑ የእኔ ብጤ ተራ ሰዎችም ንጉስ ነጃሺን ምሳሌያቸው እንዲያደርጉ።   

መፅሃፍ ቅዱስንና የትውፊት ድርሳናትን መሰረት በማድረግ በክርስቲያኖች፣ በተለይም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቃውንት ዘንድ፣ የሚታመን ኣንድ ትንቢት ኣለ፡- "ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን እንደምሳሌ ይጠቅሳል።" የሚል። ምናልባት ባሃኦላህ ስለንጉሳችን የመሰከረው ቃል የዚህ ትንቢት ፍፃሜ ይሆናል። ምናልባትም ግጥምጥሞሽ። ነገር ግን፣ ባሃኦላህ በቅዱስ ብዕሩ ለኢትዮጵያ የሰጠው ክብር መለኮታዊው ኣንደበት ይህችን ምድር ካንደበቱም ከመለኮታዊ ቅርበቱም እንዳልጣለ ሌላው እማኝ ይሆናል። ይህና፣ ከላይ ያየናቸው የየሃይማኖቱ የታሪክ መረጃዎች፣ "እርግጥ እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይወዳታልን?" የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የኣፍቃሪንና የተፈቃሪን ግንኙነት ለማሳየት ካነሳናቸው መስፈርቶች ኣኳያ፣ የማያጠራጥር ድምዳሜ ላይ እሚያደርሰን ተጨማሪ ማስረጃ ይሆነናል።

ምናልባት ኢትዮጵያዊነት ወይም ኣፍሪካዊነት የቦታና የመወለድ ጉዳይ ይሆናል። ከላይ ያየነው ግን የመንፈሳዊ ጥሪ ጉዳይ ነው። ቦታና መወለድም ቢሆኑ በየግልፀት ምዕራፉ ደምቀው መነሳታቸው ለከንቱ ሊሆን ኣይችልም። ውሉን በማይስተው መለኮታዊና ዘለዓለማዊ ኣቅድ ውስጥ፣ ከንቱነትና ኣጋጣሚ ቦታ የላቸውምና። ምክንያቱን ልናብራራ ባንችልም፣ የዘመናት ኬላ ያላገደው ሰማያዊ ጥሪ በኢትዮጵያዊነታችንም ይሁን በኣፍሪቃዊነታችን ሲስተጋባልን ኣድምጠናል። የተላለፈልን መንፈሳዊ ቅርስ የደረሰን በደምና በዕንባ ጎርፍ ውስጥ ነው። ስለዚህም እንጠይቅ፡- ኢትዮጵያዊነት ማለት በዚህ ፍፁም ክቡር ቅርስ መኩራት ማለት ብቻ ነው ወይስ ተጠያቂነትም ያለበት የመለኮት ባለኣደራነት?

በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ኣንድ ብስራታዊ ትንቢት ኣለ፡- "ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚኣብሄር ትዘረጋለች።" (መዝ. 68፡31) የሚል። ኣንዳንዴ ሳስበው፣ ዕውን ይህ ትንቢት ገና ወደፊት ሊፈፀም ያለ ነው ወይስ ገና ድሮ ተፈፅሞ ኣብቅቶለታል? እላለሁ። ተፈፅሞ፣ በእኛ ምክንያት የመሆን ዕድሉ መክኖ፣ ይሆን ወይ? እላለሁ። ስለዚህ ትንቢት ሳስብ፣ ተመሳሳይ ትንቢት ይጠብቁ ስለነበሩ ህዝቦችና ዘመኖች ኣስባለሁ።

ኢስራኤላዊያን የሚያድናቸውን መሲህ፣ ነፃ የሚደርጋቸውን ንጉስ፣ ክብራቸውን የሚመልስላቸውን ቅዱስ መንፈስ ይጠብቁ ነበር። ይህ ትንቢት በኢየሱስ በኩል ተሟላ። እነሱ ግን ይጠብቁ የነበሩት በልቦናቸው ውስጥ ቀርፀው ያቆዩትን መሲህ፣ በምናባቸው የሳሉትን ንጉስ፣ በህልማቸው ያበጁትን መንፈስ ነበር። መቼም፣ እነሱን ሊያድን፣ እነሱን ሊለውጥና ነፃ ሊያወጣ የሚመጣ ኣዳኝ የነሱ ምናብ እንዳነፀው የሃሳብ ጣዖት ኣይሆንም። መቼም፣ መሳታቸውን ሊያቀና የሚመጣ መምህር የሃናንና የቀያፋን ካባ ለብሶ ኣይመጣም። ከነሱ ፍፁም ልዩ፣ ከሃሳባቸው ጥፍጥፍም ፍፁም የላቀ፣ ከካህኖቻቸውና ከኣለቆቻቸውም ፍፁም የበለጠና የተከበረ መሆን ኣለበት። ክርስቶስ እንዲያ ሆኖ መጣ። ኢስራኤላዊያን ግን ኣልተቀበሉትም። ሊያድናቸው የመጣው ፀጋ፣ የተተነበየለት የዓርነት ዕድልም፣ እንዲያመልጣቸው ኣደረጉ። ያንንም እነሱ ኣላወቁም። ስላላወቁም፣ ወይም ኣውቀው እምቢ ስላሉም፣ ደስ ኣላቸው። በመመረጣቸው እየተመፃደቁ፣ መሲሃቸውን መናፈቅን፣ ኣዳኛቸውን መጠበቅን፣ ንግዳቸውና ስራቸው እንዳደረጉ ቀጠሉ። ያኔ፣ ኢትዮጵያ በጃንደረባዋ በኩል እጆቿን ወደ እግዚኣብሄር ኣነሳች። ከፀጋውም ለመቋደስ በቃች።

እግዚኣብሄር እግዚኣብሄር ነውና፣ በኣንድ ዕድል ህዝቡን ኣይፈርድም። በኣንድ ዕድል ልጆቹን ኣያዋርድም። ሌላ ዕድል ይሰጣል። ሌላ ዘምን ያመጣል። ለኢስራኤላዊያን በነቢዩ ሙሃመድ በኩል እንደገና መዳናቸው መጣላቸው። ኣሁንም እነሱ ኣልተቀበሉትም። በዚህ የግልፀት ዘመንም፣ ኢትዮጵያ፣ ቢያንስ በንጉስ ነጃሺና በቢላል በኩል፣ እጆቿን ወደ እግዚኣብሄር ኣነሳች። ሌላ ዘመን ተወለደ። የሌላ ሰማያዊ ፀሃይ ጎህ ቀደደ። በዚህ በምንኖርበት ዘመን ለኢስራኤላዊያን በባብና በባሃኦላህ በኩል መዳናቸው መጣለቸው። ከማንም በላይ በሚያውቁት መፃፋቸው እንደተፃፈው፣ ወደ ተስፋ ምድራቸው ያሰባሰባቸውን የዚህን ዘመን የትንቢት ፍፃሜ ቢኖሩበትም፣ ኣሁንም መሲሃቸውን፣ ኣሁንም መዳናቸውን፣ ከማይመጣላቸው ወደፊት ውስጥ እየተጠባበቁ ኣሉ። ኢትዮጵያ ግን፣ ኢትዮጵያ፣ በሙባረኳ በኩል ለዘመኑ የመዳን ዕድል እንደገና እጆቿን ወደ እግዚኣብሄር ኣነሳች። … (በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ፣ እግዚኣብሄር፣ ኢትዮጵያዊያንንና ኢስራኤላዊያንን ማነፃፀሩ ለዚህ ይሆን? ብለን እንጠይቅ?)

ይህን፣ ይህን ኣስብና፣ ታዲያ የኢትዮጵያ መዳን የታለ? ኣርነቷስ፣ ልዕልናዋስ፣ ብልፅግናዋስ፣ ቅድስናዋስ፣ የታለ? ብዬ ራሴኑ እሞግታለሁ። ምላሹ ታዲያ ሌላ ጥያቄ ሆኖ ይመጣል፡ ሙሉ መቀበል ሳይኖር ሙሉ መዳን ይኖራልን? ኢትዮጵያ በየዘመኑና በየግልፀቱ ሙሉ መቀበል ነበራትን? እግዚኣብሄር ያለማቋረጥ የሚያወርድላትን ፀጋ በምስጋና ተቀብላ ልቧን በቡራኬ፣ ምድሯን በብልፅግና፣ ትሞላ ዘንድ ሙሉ ዝግጅት፣ ሙሉ እሽታ፣ ነበራትን? እኛም እንደ ኢስራኤላዊያን የተተነበየልንን የመዳን ዕድል ደግመን ደጋግመን እንዲያመልጠን ኣድርገን ይሆን?    

በትንቢት ውስጥ ስንኖር ፍፃሜውን እናያለንና እንጠብቅ፤ ማለት ቸልተኛነት ይሆንብናል። ለኔ፣ የትንቢት ፍፃሜ ያለው በወደፊቱ ዓለም ብቻ ኣይደለም። እያንዳንዱ ትውልድ፣ እያንዳንዱ ዘመን፣ በየዕለቱ በሚያደርገው ግብር፣ በየዘመን ኩርባው በሚወስደው ምርጫ፣ ለትንቢቱ መሟላት የየራሱን ድርሻ ይወጣል። ያለዚያ፣ ትንቢት የየትኛውም ነፍስ ኣስተዋፅዖ የሌለበት፣ የማይታጠፍ የሰማያዊ ኣቅድ (ፕሮግራም) ፍፃሜ ይሆናል። በንዲህ ዓይነት ፍፃሜ ውስጥ ምን እሚሉት መዳን ሊኖር ይችላል? ምን እሚሉት ኣርነት?

የኢትዮጵያ የመዳን ዕድል በየዘመኑ የሚመጣ፣ በየዕለቱ የሚፈፀም፣ እንደሆነ እምናስብም ሆነ ትንቢቱ የማናችንንም ኣስተዋፅ ሳይሻ ሊፈፀም ርቆ እንደተቀመጠ እምናምንም፣ ራሳችንን እንጠይቅ። ምላሽ ከየልባችን ሲወጣ፣ ድርጊት በስኬት ይዋባልና፣ ነፍሳችንንም ህሊናችንንም ኣንፅተን ራሳችንን ኣበክረን እንጠይቅ፡- የኣጠቃላዩ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ቅርስ በሚፈጥረው ህብር ውስጥ እኛን የሚወክለው ክር እንዳይበጠስ ምን እናድርግ?  በመቀጣታችን ተፈቃሪነታችንን ከመናገር ይልቅ በእምነታችን የኣፍሪካ ፍኖተ-ብርሃን እንሆን ዘንድ ምን እናድርግ? እኛስ በተራችን በኢትዮጵያዊነታችንና በኣፍሪካዊነታችን ለቀጣዩ ዘመንና ትውልድ እማይደመሰስ ቅርስ ጥለን ለማለፍ ምን እናድርግ?


የሙባረክን ሃውልት ምረቃ (11/5/96 ዓ.ም.) በማስመልከት ከተፃፈ ፅሁፍ። (ለዚህ ብሎግ ጥቂት ጭማሪዎች ተደርገውበታል።) 

Wednesday, February 5, 2014