Sunday, December 6, 2015

ኢየሱስ እንስተ-መለኮት (Sacred Feminine) ያስፈልገው ነበር?

እውን መግደላዊት ማርያም የኢየሱስ ሚሽት ነበረች?

ኢየሱስ ኣግብቶም ወልዶም ነበር የሚለው ሙጉት ታሪካዊም ሎዢካዊም መሠረት የለውም። ዳን ብራውንን የመሳሰሉ የብዙሃኑ ባህል (Mass Culture) ከዋክብት ጉዳዩን የዓለም መነጋገሪያ ካደረጉት ወዲህ ጥቂት ፀሃፍት ይህ እምነት ታሪካዊ መሠረቱ የፀና እንዳይደለ ለማሳየት ሞክረዋል። በበኩሌ፣ ሎዢካዊ እንከኑን ኣንጥሮ በማውጣት ጠንከር ያለ የምላሽ ሙጉት (counter argument) ያደረገ ፀሃፊ ኣልገጠመኝም። በተለይ፣ ”መግደላዊት ማርያም የኢየሱስ እንስተ-መለኮት (Sacred Feminine) መገለጫ፣ የመሲህነቱም ተጋሪ፣ ናት፤” ለሚለው ሃሳብ ኣጥጋቢ ምላሽ የሰጠ። በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ኣለመባሉ እኔ ኣጭር ምላሽ ልሰጥበት እንድሞክር ኣነሳሳኝ። እውን፣ ኢየሱስ እንስተ-መለኮት ያስፈልገው ነበር? እውን ባልና ሚስት የኑሮን ቀንበር በጋራ መሸከም እንዳለባቸው ኢየሱስ የመሲህነቱን ቀንበር እምትጋራው እንስት ታስፈልገው ነበር? እግረመንገዴንም ሞቷል ስለተባለው እግዚኣብሔር ጥቂት ነገሮችን እላለሁ።  

ጉዳዩን በቅጡ ለማወቅ ዕድሉ ላልገጠማቸው እንደመንደርደሪያ የሙጉቱን ዋና ዋና ሃሳቦች በማንሳት ወደራሴ ሃሳብ ኣዘግማለሁ፡  

ዳን ብራውን መግደላዊት ማርያም የኢየሱስ ሚስት እንደነበረች ለመሟገት የመጀመሪያው ሰው ባይሆንም እርሱ፣ ”ዘ ዳቬንቺ ኮድ” (2003) በሚባለው መፅሃፉ ጉዳዩ ግልፅ የታሪክ መረጃ እንዳለው፣ ቤተክርስትያናት (በተለይም ካቶሊኮች) መረጃዎቹን ለማጥፋት ባደረጉት የዘመናት ጥረት ጉዳዩ ተዳፍኖ መቆየቱን፣ በቅርቡ የተገኙ መረጃዎች ሚስጢሩን ገሃድ እንዳወጡትና የዚያ መለኮታዊ ቤተሰብ ዝሪያዎች ዛሬም በመካከላችን ስለመኖራቸው ልብ ሰቃይ በሆነ ትረካ ማቅረቡ፣ በዓለም ዙሪያ የእርሱን ስራ ያነበቡ እና በዚያም ላይ የተመሰረተውን ፊልም ያዩ ብዙ ሰዎች (በኣንድ ሰርቬይ 19 በመቶ) እንዲያምኑት ኣደረገ። ግን፣ ይህ እውነት ነበር? እውን ዳን ብራውን እንደሚለው የኢየሱስንና የመግደላዊት ማርያምን ፆታዊ ፍቅርና የጋራ ልጅ ማፍራት የሚያሳዩ የታሪክ መረጃዎች ኣሉ? በነገራችን ላይ ያንን መፅሃፍ ያነበብኩ ሰሞን “እናት ኢትዮጵያ ይህንን ብትሰማ በድንጋጤ ዕጢዋ ዱብ ይላል!” ብዬ ኣስቤ ነበር። ሁዋላ መፅሃፉ ተተርጉሞ በጋዜጣና በመፅሃፍ መነበቡ የኛ ጦቢያም ብዙ ነፃ ኣንባቢያን እንዳሏት ኣሳይቶኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳዩ መነጋገሪያ ኣለመደረጉና ምሁራንም ሆኑ የኔ ብጤ ተራ ኣንባቢያን (እንደብዙ ጊዜው በስሜት ሳይሆን በእውቀት) የራሳቸውን ኣቋም ሊገልፁ ሲሞክሩ ኣለማየቴ፣ “ምነው፣ የኛ ነገር፣ የዚህች የሥነ-መለኮት ዓምባ እምንላት ምድር ነገር፣ ሌሎችን ማንበብና ማስተጋባት ብቻ ነው እንዴ?“ ኣስብሎኛል። የሆነ ሆኖ፣ እስቲ ዳን ብራውን መረጃ ብሎ ላቀረባቸው ነጥቦች ኣንዳንድ ፀሃፍት የሰጧቸውን ምላሾች ባጭር ባጭሩ እንይና ወደኔ ሙጉት እንሸጋገር፡
 
I.                    የዳን ብራውን መፅሃፍቅዱሳዊ ማስረጃዎች፡
ዳን ብራውን በገፀባህሪይው ላንዶን ኣማካኝነት እንዲህ ይላል፡ በወቅቱ የነበረው ማህበራዊ ስርዓት የኣይሁድ ወንድ እንዲያገባ ያስገድድ ነበር። በኣሁዶች ልማድ፣ ኣለማግባት ውግዝ ነበር…“ (ገፅ 245)

ይህ ሙሉ በሙሉ እውነት ኣይደለም። ኢየሱስ በኣካለ-ስጋ በነበረ ጊዜ ኣለማግባት በሰፊው የሚተገበር ነገር ባይሆንም ጨርሶ እማይደረግ ነገር ግን ኣልነበረም። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያላገቡ የእግዚኣብሔር ኣገልጋዮች ተጠቅሰዋል። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ “ኤሴን/Essene“ የተባሉ፣ ከመጥምቁ ዮሃንስና ከኢየሱስ ጋርም ግንኙነት የነበራቸው፣ ቡድኖች ጋብቻን በመናቅ ገዳማዊ ዓይነት ህይወት ይኖሩ፣ ያም ኣኗኗራቸው በኦርቶዶክስ ኣይሁዳዊያን ዘንድም ጭምር በክብር ዓይን ይታይ እንደነበር፣ የወቅቱ የታሪክ ፀሃፍት ፊሎ እና ጆሴፌስ ዘግበዋል። በወንጌል ውስጥም ኣንድ ሰው ሳያገባ እግዚኣብሔርን ለማገልገል ቢመርጥ ክፋት እንደሌለው ተጠቅሷል። ስለዚህ የኢየሱስ ኣለማግባት ፈፅሞ ሊታሰብ እንደማይችል ነገር ተቆጥሮ ስለማግባቱ ማስረጃ ሊሆን ኣይችልም።


 
II.                 የዳን ብራውን ታሪካዊ ማስረጃዎች
ዳን ብራውን ለሙጉቱ ኣብዝቶ የተመረኮዘው ጠፍተው በቅርቡ በተገኙቱ የግኖስቲክ ወንጌሎች ላይ ነው። እኚህ ወንጌሎች መግደላዊት ማርያም ለኢየሱስ ከወንዶች ደቀመዛሙርት ይልቅ የነበራትን ቅርበትና ለመንፈሳዊ እውነታዎች የነበራትን ከሌሎች የላቀ መረዳት የሚያሳዩ ቢሆኑም ከኢየሱስ ጋር ስለመጋባቷ ወይም ከእርሱ ጋር ስለነበራት ፆታዊ የፍቅር ግንኙነት በግልፅ ኣይናገሩም። ዳን ብራውን ከነዚህ ወንጌላት በተለይ የፍሊጶስን ወንጌል እንደጥሩ መረጃ ያቀርባል። በዚያ ውስጥ ለእርሱ ለሙጉቱ ማስረጃ የሚመስሉ ሁለት ጥቅሶች ኣሉ። እነዚህም፡

ሀ. “ጌታን ሰርክ የሚከተሉ ሶስት ነበሩ፡ የእርሱ እናት የሆነችው ማርያም፣ እህቱ፣ እና ባልንጀራው ይሏት የነበረችው መግደላዊት።/ There were three who always walked with the Lord: Mary his mother and her sister and Magdalene, the one who was called his companion.“ (የፊሊጶስ ወንጌል ክፍል 59)

ብራውን ከላይኛው ጥቅስ ውስጥ በተለይ “ባልንጀራ/companion“ ለሚለው ቃል ልዩ ትኩረት ይሰጣል። በግሪኩ ኦርጂናሌ ውስጥ ይህ ቃል “koinonos/ኮይኖስስ ሲሆን ይህም ጋብቻን የሚያመለክት ቃል ነው፤“ ይለናል ብራውን። ይህ ግን እውነት ኣይደለም። ለምሳሌ የግርኩ ኣዲስ ኪዳን ይህንን ቃል ኣስር ጊዜ ያህል ይጠቀምበታል። (ማቴ. 23፡30፤ ሉቃ. 5፡10፤ 1ኛ ቆሮ. 10፡18፣ 20፡2፤ 2ኛ ቆሮ. 1፡7፣ 8፡23፤ ፊሊ. 17፤ እብ. 10፡33፤ 1ኛ ጴጥ 5. 1፣ 2፤ 2ኛ ጴጥ 1፡4) ነገር ግን፣ በሁሉም ቦታዎች የንግድን፣ የድርጊትን፣ እና የሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶችን ኣጋርነት ወይም ሸሪክነት፣ ወይም ባልንጀራነት ወይም ወዳጅነት፣ ወይም ግብረ-ኣበርነት ለማመልከት እንጂ ጋብቻን ለማመልከት ኣይደለም። ብራውን የተመካበት ይህ ጥቅስ ስለጋብቻ ለማሳየት ብርታት የሌለው ማስረጃ ነው ማለት ነው።

ለ. “የኣዳኙ ባልንጀራ መግደላዊት ማርያም ነች። ክርስቶስ ግን ከሌሎች ደቀመዛሙርት ሁሉ ኣብልጦ እርሷን ይወዳት፣ ብዙውን ጊዜም ኣፏ ላይ ይስማት ነበር። ሌሎች ደቀመዛሙርት ይህ ኣስቆጥቶኣቸው ኣጉረመረሙ። ለእርሱም እንዲህ ኣሉት፣ ‘ከእኛ ኣብልጠህ እምትወዳት ስለምንድነው?‘ ኣዳኙ መልሶ እንዲህ ኣላቸው፡ ‘እናንተን የእሷን ያህል የማልወዳችሁ ስለምንድነው? ዓይነ-ስውር ሰውና ዓይናማ ሰው በኣንድ ላይ በጨለማ ውስጥ ቢሆኑ በሁለቱ መካከል ምንም ልዩነት ኣይኖርም። ብርሃኑ ሲመጣ ግን ያ ዓይናማው ብርሃኑን ያየዋል፤ ዓይነ-ስውሩ ግን ጨለማ ውስጥ እንደሆነ ይቀራል።‘” (ክፍል 63-63).   

ይህ ጥቅስ ወሲባዊ ግንኙነትን የሚያመለክት ሊመስል ቢችልም በቅርበት ስንመረምረው ግን ”‘ኢየሱስ ማርያምን ይስማት ነበር፤‘ መባሉ በእርግጥ ፍቅረኛነትን ወይም ጋብቻን የሚያመለክት ነውን?” ያስብለናል። እስቲ ዳን ብራውንም ሆነ ሌሎች ሰዎች እንደጥሩ የጋብቻ ማስረጃ በሚያቀርቡት በዚህ ጥቅስ ላይ ኣንዳንድ ጥያቄዎችን እናንሳ፡
1.       እንደሚታሰበው መግደላዊት ማርያምና ኢየሱስ ፍቅረኛሞች ወይም ባልና ሚስቶች ቢሆኑ ሌሎች ደቀመዛሙርት መሳሳማቸውን ለምን ይቃወሙታል?
2.       ወንዶች ደቀመዛሙርት የተቃወሙት ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም ፆታዊ ፍቅር ማሳየቱን ሳይሆን እርሷን ከእነሱ ይበልጥ ማፍቀሩን መሆኑ ለምንድነው? ”ለምን ከእኛ ኣስበለጥካት?” እንጂ፣ ”ሴትነቷን ለምን ኣፈቀርከው?” ኣለማለታቸው ኢየሱስ ለማርያም ያሳያት የነበረው ፍቅር ለእነርሱም ያሳያቸው የነበረውን ዓይነት ፍቅር መሆኑን ኣያመለክትም? 
3.       ኢየሱስ በምላሹ፣ ”ምስቴን በሳምኩ እናንተ ምን ቁርጥ ኣደረጋችሁ!? ኧረ ንሽቴ!” ኣለማለቱ ለምንድነው? ይልቅ ያላቸው፣ እርሱ እርሷን የማስበለጡ ምክንያት እርሷ ከእነርሱ ይልቅ የመንፈስ ዓይኗ የበራ በመሆኑ እንጂ በሴትነቷ ምክንያት እንዳይደለ ነው። እና ታዲያ እርሱ ለእርሷ የነበረው ፍቅር፣ ፍቅሩን ሊገልፅላት ይጠቀምበት የነበረውም መንገድ መንፈሳዊ ኣይሆን ይሆን? ከዚያ ግዜ ልማድ‘ኮ እጅግ ርቀን ነው ያለነው። በዛሬ ሚዛናችን ከሁለት ሺ ዓመታት ኣስቀድሞ የነበረውን ኣድራጎት መስፈራችን ስህተት የለውም ማለት እንችላለን?   

እንግዲህ ይህም ጥቅስ የኢየሱስንና የማርያምን ፆታዊ ፍቅር ወይም ጋብቻ ለማመልከት ኣቅም የለውም ማለት ነው።

ከላይ በኣጭሩ ያየናቸው መረጃዎች የዳን ብራውን ሙጉት ታሪካዊ መሠረቱ በራሱ የማይቆም ሰንበሌጥ እንደሆነ ያስረዳሉ። ቀጥሎ የማርያምን እንስተ-መለኮትነትን ጉዳይ እንመልከት፡

III.               የዳን ብራውን ሎዢካዊ ማስረጃዎች

ዳን ብራውንና ሌሎች የኢየሱስ-ወ-ማርያም ጋብቻ ሃሳብ ኣራማጆች ከሚያቀርቧቸው ሎዢካዊ ማስረጃዎች ዋናው፣ ኢየሱስ እና ማርያም (እንደ ቻይናዊያኑ ኢን እና ያንግ) የመለኮት ሴት እና ወንድ (ወይም ጥቁርና ነጭ) መገለጫዎች ናቸው የሚል ነው። ወንዴ- ወይም ተባዕተ-መለኮት በኢየሱስ ተገለጠ። ሴቴ- ወይም እንስተ-መለኮት ደግሞ በማርያም። ስለዚህ ማርያም የኢየሱስ ሚስት ብቻ ሳትሆን የመሲህነቱም ተጋሪ ናት። በእርሷ በኩል ባይሆን ኖሮ መለኮት በምልዓት ለዓለም ባልተገለጠም ነበር። ከዚህ ፀጋ ዓለም ኣይነፈግ ዘንድ መለኮት እንስታዊ ባህሪይውን በመግደላዊት ማርያም በኩል ሊገልፅ ወደደ። ቀድሞም የሰው ልጅ እንስታዊ ባህሪይ እና ተባዕታዊ ባህሪይ መነጣጠሉ ነው ለውድቀቱ (ከገነት ለመውጣቱ) ምክንያት የነበር። ኣንዳንድ ሰዎች እነዚህን ባህሪያቱን ይበልጥ ለማዋሃድ መትጋታቸው የመዳናቸው መንገድ በዚያ እንደሁ በማወቃቸው ነው። ይህ ነው እስከዛሬ በተለያዩ እምነቶች ውስጥ በቅድስት እናት፣ በእናት ኣማልክት፣ በፅገሬዳ፣ በቅዱስ ፅዋ፣ ወዘተ… እየተመሰለ፣ ኣይሲስ፣ ቬኑስ፣ ኣፎርዳይት፣ ኣርቴሚስ፣ ዴሚትር፣ ዲያና፣ ኣቴና፣ ወዘተ… በሚሉ ስሞችም እየተጠራ ሲመለክ እምናየዉ። ኢየሱስ ከማርያም ጋር በፈፀመው ጋብቻ ኣማካኝነት ይህንን የድህነት ሚስጥር ገለፀ። በዚህም ወሲብ ሰብዓዊ ማንነት ወደምልዓቱ የሚመለስበት የመለኮት መንገድ ተደረገ።

ይህ በተለይ በሴታዊነት (feminism) ኣራማጆች ዘንድ የሚዘወተር ሳቢ ሙጉት ቢሆንም በሎዢክ ሚዛን ላይ ሲቀመጥ ግን ውሃ ኣያነሳም (የሎዢክ ሚዛን እንደባለሎዢኩ ሊለያይ መቻሉ እንዳለ ሆኖ)።

እንደኔ እምነት ችግሩ ያለው የእግዚኣብሔርን እና የኢየሱስን መለኮታዊ ባህሪይ ከመረዳት ላይ ነው። ፈላስፋዎችን ለዘመናት ያፋጩ ውስብስብ ሥነ-መለኮታዊ ጉዳዮችን ወደጎን ትተን እንደውይይት መነሻ ስለእግዚኣብሔርና ስለኢየሱስ ባህሪያት ብዙዎቻችንን ሊያስማሙ የሚችሉ ኣንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ፡

እግዚኣብሔር ፍፁም ነው። እግዚኣብሔር የስሞችና የባህሪያት ሁሉ ጌታ ነው። እግዚኣብሔር የሃይላትና የስልጣናት ሁሉ ባለቤት ነው። በብዙ ባህሎች በወንዴ ፆታ መጠራቱ የቋንቋና የተለምዶ ጉዳይ ሆኖ እንጂ እግዚኣብሔር ከፆታዊ እሳቤዎች የላቀና የረቀቀ መለኮታዊ ህላዌ ነው። ወንበር ኣናፂውን መረዳት እንደማይችል ሁሉ የሰው ልጅ ኣዕምሮም ፈጣሪውን በምልዓት ሊረዳው ኣይችልም። እኛ ስለእግዚኣብሔር የሚኖረን ሃሳብ ብዙውን ጊዜ ባለን ዕውቀትና የመንፈስ ብቃት የተወሰነ እንጂ የእርሱን እውነተኛ ህልውና የሚወክል ኣይደለም። ለብዙዎቻችን እግዚኣብሔር በግዙፍ ዙፋን ላይ ተቀምጦ በትልቅ-በትንሹ ላይ የሚፈርድ ፂማም ሽማግሌ ነው። ይህንን የመሳሰሉ የምናብ ስዕሎቻችንን እንደብቸኛና ትክክለኛ የእግዚኣብሔር ምስል ማሰብ ስንጀምር ያንን ምስል ጣዖት ማድረግ እንጀምራለን። ከእንጨትና ከዲንጋይ የሚሰሩ ጣዖቶች ነባራዊ ህልውና ያላቸው ነገሮች ናቸው። በዓዕምሮኣችን የምንስለው የእግዚዓብሔር ምስል ግን ምንም ዓይነት ህልውና የሌለው ጣዖት ነው። ስለዚህ ከእንጨትና ከድንጋይ ጣዖቶች ይልቅ ይህ እጅግ ኣደገኛና ኣጥፊ ነው። በዓለም ላይ የታላላቅ ውዝግቦችና ክፍፍሎች፣ የኣሰቃቂ ጦርነቶችና ዕልቂቶች ምንጭ የሆነውም ይህ ምናባዊ ጣዖት ነው። ኣንዳንድ ነፃ ኣሳቢዎች፣ ”እግዚኣብሔር የለም፤” ሲሉ፣ ”እግዚኣብሔር ሞቷል፤” ሲሉ፣ እንዲያ የሚሉት ይህንን ጣዖታዊ ምስል እያሰቡ ነው። እንዲህ ያለው እግዚኣብሔር ቀድሞም ህይወት ኣልነበረውምና እውነት ነው ሙት ነው። ውስንነት ኢውስንነትን ኣያካትትምና እግዚኣብሔር የሰው ዓዕምሮ የቱንም ዓይነት ብቃት ቢኖረው ሊፀንሰውና ሊገልፀው ከሚችለው በላይ የሆነ ህያው እሳቤ።


ኢየሱስ እግዚኣብሔር የምንለው ሕልውና ፍፁማዊ መገለጥ ነው። ሰው እግዚኣብሔርን በቀጥታ ሊያገኘውና ሊያውቀው ኣይችልምና እርሱ ሰውን ሆኖ ኖሮ የእርሱን ፈቃድና መንገድ ያሳየን ዘንድ ከሰማይ የወረደ የፈጣሪ ክስተት ነው። ለዚያ ነው እሱን ያየ ኣምላክን ያየ የሚሆነው። ለዚያ ነው እርሱ ህይወትም መንገድም የሚሆነው። እርሱ የእግዚኣብሔር ፍፁማዊ መገለጫ በመሆኑም የእግዚኣብሔር ስሞችና ባሕርይት፣ የሃይላቱና የስልጣናቱ ሁሉ ባለቤት ነው። እርሱ ጋ የሌሉ ነገሮች እግዚኣብሔር ጋ የሌሉ ነበሮች ብቻ ናቸው። ያኚም፣ በራሳቸው ህልውና የሌላቸው ጥላቻንና እኩይነትን የመሳሰሉ ነገሮች እንጂ ሌላ ሊሆኑ ኣይችሉም። እግዚኣብሔር ከፆታ እሳቦቶች በላይ በመሆኑም በኢየሱስ ኣማካኝነት የተገለፀልን መንፈስቅዱስም ከፆታ እሳቦቶች በላይ ነው። ሰው ሴታዊ ወይም ወንዳዊ ባህሪያትን (በስነልቦናና በፍልስፍና ”ኢሮስ” እና ”ሎጎስ” የሚባሉ ዓይነት ዝንባሌዎችን) በትንሹ ወይም በትልቁ ሊያሳይ ይችላል። የፍፁምነት ክስተት የሆነው ኢየሱስ ግን እነዚህን ባህርያት በምልዓትና በእኩልነት የያየዘ ነው። ስለዚህ፣ ኢየሱስ ወንድ በመሆኑ በተለይ የመለኮትን ተባዕታዊ ባህሪይ ኣብዝቶ ይገልፃል ልንል ኣንችልም። በዚህም ላይ ተመስርተን፣ እግዚኣብሔር እንስታዊ ባህሪይው ለፍጡራኑ ይደርሰን ዘንድ የወንድ መልዕክተኞቹን ሴት ኣጋሮች ማስነሳት ነበረበት የሚል ሙጉት ልናቀርብ ኣንችልም። መግደላዊት ማርያም በቅድስናዋ ምንም ያህል ከፍ ያለች ብትሆን የኢየሱስን መሲህነት ልትጋራ የምትችልበት መንገድ ኣይኖርም። እርሷ የኢየሱስ ሚስት ስለሆኗ የማያጠራጥሩ መረጃዎች ቢገኙም እንኳ ያ የመሲህነቱ ተጋሪ ኣያደርጋትም። ኢየሱስ መለኮትን በምልዓት ሊሸከም ኣጋዥ ኣያሻውም። ያ ከሆነ የእርሱ ፍፅምና ኣንፃራዊ ፍፅምና ይሆናል። ሰብዓዊ እንጂ መለኮታዊ ፍፅምና ብሎ ኣንፃራዊነት ደግሞ የለም። የመግደላዊት ማርያም ቅድስና ምንጩ ለኢየሱስ ያላት መንፈሳዊ ቅርበት እንጂ ስጋዊ ቅርበቷ ኣይደለም። ይህ ለእርሷ ሊሰጣት የሚገባውን ክብር በምንም ኣይነት ኣያኮስስም፣ ኣያጎድፍም። የክብሮች ሁሉ ክብር የመለኮታዊ ቅርበት ክብር ነውና። ያንን የክብር መንበር ደግሞ መግደላዊት ማርያም ከማንኛውም ተራ ሟች ይልቅ ተቀዳጅታዋለች።