Sunday, December 6, 2015

ኢየሱስ እንስተ-መለኮት (Sacred Feminine) ያስፈልገው ነበር?

እውን መግደላዊት ማርያም የኢየሱስ ሚሽት ነበረች?

ኢየሱስ ኣግብቶም ወልዶም ነበር የሚለው ሙጉት ታሪካዊም ሎዢካዊም መሠረት የለውም። ዳን ብራውንን የመሳሰሉ የብዙሃኑ ባህል (Mass Culture) ከዋክብት ጉዳዩን የዓለም መነጋገሪያ ካደረጉት ወዲህ ጥቂት ፀሃፍት ይህ እምነት ታሪካዊ መሠረቱ የፀና እንዳይደለ ለማሳየት ሞክረዋል። በበኩሌ፣ ሎዢካዊ እንከኑን ኣንጥሮ በማውጣት ጠንከር ያለ የምላሽ ሙጉት (counter argument) ያደረገ ፀሃፊ ኣልገጠመኝም። በተለይ፣ ”መግደላዊት ማርያም የኢየሱስ እንስተ-መለኮት (Sacred Feminine) መገለጫ፣ የመሲህነቱም ተጋሪ፣ ናት፤” ለሚለው ሃሳብ ኣጥጋቢ ምላሽ የሰጠ። በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ኣለመባሉ እኔ ኣጭር ምላሽ ልሰጥበት እንድሞክር ኣነሳሳኝ። እውን፣ ኢየሱስ እንስተ-መለኮት ያስፈልገው ነበር? እውን ባልና ሚስት የኑሮን ቀንበር በጋራ መሸከም እንዳለባቸው ኢየሱስ የመሲህነቱን ቀንበር እምትጋራው እንስት ታስፈልገው ነበር? እግረመንገዴንም ሞቷል ስለተባለው እግዚኣብሔር ጥቂት ነገሮችን እላለሁ።  

ጉዳዩን በቅጡ ለማወቅ ዕድሉ ላልገጠማቸው እንደመንደርደሪያ የሙጉቱን ዋና ዋና ሃሳቦች በማንሳት ወደራሴ ሃሳብ ኣዘግማለሁ፡  

ዳን ብራውን መግደላዊት ማርያም የኢየሱስ ሚስት እንደነበረች ለመሟገት የመጀመሪያው ሰው ባይሆንም እርሱ፣ ”ዘ ዳቬንቺ ኮድ” (2003) በሚባለው መፅሃፉ ጉዳዩ ግልፅ የታሪክ መረጃ እንዳለው፣ ቤተክርስትያናት (በተለይም ካቶሊኮች) መረጃዎቹን ለማጥፋት ባደረጉት የዘመናት ጥረት ጉዳዩ ተዳፍኖ መቆየቱን፣ በቅርቡ የተገኙ መረጃዎች ሚስጢሩን ገሃድ እንዳወጡትና የዚያ መለኮታዊ ቤተሰብ ዝሪያዎች ዛሬም በመካከላችን ስለመኖራቸው ልብ ሰቃይ በሆነ ትረካ ማቅረቡ፣ በዓለም ዙሪያ የእርሱን ስራ ያነበቡ እና በዚያም ላይ የተመሰረተውን ፊልም ያዩ ብዙ ሰዎች (በኣንድ ሰርቬይ 19 በመቶ) እንዲያምኑት ኣደረገ። ግን፣ ይህ እውነት ነበር? እውን ዳን ብራውን እንደሚለው የኢየሱስንና የመግደላዊት ማርያምን ፆታዊ ፍቅርና የጋራ ልጅ ማፍራት የሚያሳዩ የታሪክ መረጃዎች ኣሉ? በነገራችን ላይ ያንን መፅሃፍ ያነበብኩ ሰሞን “እናት ኢትዮጵያ ይህንን ብትሰማ በድንጋጤ ዕጢዋ ዱብ ይላል!” ብዬ ኣስቤ ነበር። ሁዋላ መፅሃፉ ተተርጉሞ በጋዜጣና በመፅሃፍ መነበቡ የኛ ጦቢያም ብዙ ነፃ ኣንባቢያን እንዳሏት ኣሳይቶኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳዩ መነጋገሪያ ኣለመደረጉና ምሁራንም ሆኑ የኔ ብጤ ተራ ኣንባቢያን (እንደብዙ ጊዜው በስሜት ሳይሆን በእውቀት) የራሳቸውን ኣቋም ሊገልፁ ሲሞክሩ ኣለማየቴ፣ “ምነው፣ የኛ ነገር፣ የዚህች የሥነ-መለኮት ዓምባ እምንላት ምድር ነገር፣ ሌሎችን ማንበብና ማስተጋባት ብቻ ነው እንዴ?“ ኣስብሎኛል። የሆነ ሆኖ፣ እስቲ ዳን ብራውን መረጃ ብሎ ላቀረባቸው ነጥቦች ኣንዳንድ ፀሃፍት የሰጧቸውን ምላሾች ባጭር ባጭሩ እንይና ወደኔ ሙጉት እንሸጋገር፡
 
I.                    የዳን ብራውን መፅሃፍቅዱሳዊ ማስረጃዎች፡
ዳን ብራውን በገፀባህሪይው ላንዶን ኣማካኝነት እንዲህ ይላል፡ በወቅቱ የነበረው ማህበራዊ ስርዓት የኣይሁድ ወንድ እንዲያገባ ያስገድድ ነበር። በኣሁዶች ልማድ፣ ኣለማግባት ውግዝ ነበር…“ (ገፅ 245)

ይህ ሙሉ በሙሉ እውነት ኣይደለም። ኢየሱስ በኣካለ-ስጋ በነበረ ጊዜ ኣለማግባት በሰፊው የሚተገበር ነገር ባይሆንም ጨርሶ እማይደረግ ነገር ግን ኣልነበረም። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያላገቡ የእግዚኣብሔር ኣገልጋዮች ተጠቅሰዋል። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ “ኤሴን/Essene“ የተባሉ፣ ከመጥምቁ ዮሃንስና ከኢየሱስ ጋርም ግንኙነት የነበራቸው፣ ቡድኖች ጋብቻን በመናቅ ገዳማዊ ዓይነት ህይወት ይኖሩ፣ ያም ኣኗኗራቸው በኦርቶዶክስ ኣይሁዳዊያን ዘንድም ጭምር በክብር ዓይን ይታይ እንደነበር፣ የወቅቱ የታሪክ ፀሃፍት ፊሎ እና ጆሴፌስ ዘግበዋል። በወንጌል ውስጥም ኣንድ ሰው ሳያገባ እግዚኣብሔርን ለማገልገል ቢመርጥ ክፋት እንደሌለው ተጠቅሷል። ስለዚህ የኢየሱስ ኣለማግባት ፈፅሞ ሊታሰብ እንደማይችል ነገር ተቆጥሮ ስለማግባቱ ማስረጃ ሊሆን ኣይችልም።


 
II.                 የዳን ብራውን ታሪካዊ ማስረጃዎች
ዳን ብራውን ለሙጉቱ ኣብዝቶ የተመረኮዘው ጠፍተው በቅርቡ በተገኙቱ የግኖስቲክ ወንጌሎች ላይ ነው። እኚህ ወንጌሎች መግደላዊት ማርያም ለኢየሱስ ከወንዶች ደቀመዛሙርት ይልቅ የነበራትን ቅርበትና ለመንፈሳዊ እውነታዎች የነበራትን ከሌሎች የላቀ መረዳት የሚያሳዩ ቢሆኑም ከኢየሱስ ጋር ስለመጋባቷ ወይም ከእርሱ ጋር ስለነበራት ፆታዊ የፍቅር ግንኙነት በግልፅ ኣይናገሩም። ዳን ብራውን ከነዚህ ወንጌላት በተለይ የፍሊጶስን ወንጌል እንደጥሩ መረጃ ያቀርባል። በዚያ ውስጥ ለእርሱ ለሙጉቱ ማስረጃ የሚመስሉ ሁለት ጥቅሶች ኣሉ። እነዚህም፡

ሀ. “ጌታን ሰርክ የሚከተሉ ሶስት ነበሩ፡ የእርሱ እናት የሆነችው ማርያም፣ እህቱ፣ እና ባልንጀራው ይሏት የነበረችው መግደላዊት።/ There were three who always walked with the Lord: Mary his mother and her sister and Magdalene, the one who was called his companion.“ (የፊሊጶስ ወንጌል ክፍል 59)

ብራውን ከላይኛው ጥቅስ ውስጥ በተለይ “ባልንጀራ/companion“ ለሚለው ቃል ልዩ ትኩረት ይሰጣል። በግሪኩ ኦርጂናሌ ውስጥ ይህ ቃል “koinonos/ኮይኖስስ ሲሆን ይህም ጋብቻን የሚያመለክት ቃል ነው፤“ ይለናል ብራውን። ይህ ግን እውነት ኣይደለም። ለምሳሌ የግርኩ ኣዲስ ኪዳን ይህንን ቃል ኣስር ጊዜ ያህል ይጠቀምበታል። (ማቴ. 23፡30፤ ሉቃ. 5፡10፤ 1ኛ ቆሮ. 10፡18፣ 20፡2፤ 2ኛ ቆሮ. 1፡7፣ 8፡23፤ ፊሊ. 17፤ እብ. 10፡33፤ 1ኛ ጴጥ 5. 1፣ 2፤ 2ኛ ጴጥ 1፡4) ነገር ግን፣ በሁሉም ቦታዎች የንግድን፣ የድርጊትን፣ እና የሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶችን ኣጋርነት ወይም ሸሪክነት፣ ወይም ባልንጀራነት ወይም ወዳጅነት፣ ወይም ግብረ-ኣበርነት ለማመልከት እንጂ ጋብቻን ለማመልከት ኣይደለም። ብራውን የተመካበት ይህ ጥቅስ ስለጋብቻ ለማሳየት ብርታት የሌለው ማስረጃ ነው ማለት ነው።

ለ. “የኣዳኙ ባልንጀራ መግደላዊት ማርያም ነች። ክርስቶስ ግን ከሌሎች ደቀመዛሙርት ሁሉ ኣብልጦ እርሷን ይወዳት፣ ብዙውን ጊዜም ኣፏ ላይ ይስማት ነበር። ሌሎች ደቀመዛሙርት ይህ ኣስቆጥቶኣቸው ኣጉረመረሙ። ለእርሱም እንዲህ ኣሉት፣ ‘ከእኛ ኣብልጠህ እምትወዳት ስለምንድነው?‘ ኣዳኙ መልሶ እንዲህ ኣላቸው፡ ‘እናንተን የእሷን ያህል የማልወዳችሁ ስለምንድነው? ዓይነ-ስውር ሰውና ዓይናማ ሰው በኣንድ ላይ በጨለማ ውስጥ ቢሆኑ በሁለቱ መካከል ምንም ልዩነት ኣይኖርም። ብርሃኑ ሲመጣ ግን ያ ዓይናማው ብርሃኑን ያየዋል፤ ዓይነ-ስውሩ ግን ጨለማ ውስጥ እንደሆነ ይቀራል።‘” (ክፍል 63-63).   

ይህ ጥቅስ ወሲባዊ ግንኙነትን የሚያመለክት ሊመስል ቢችልም በቅርበት ስንመረምረው ግን ”‘ኢየሱስ ማርያምን ይስማት ነበር፤‘ መባሉ በእርግጥ ፍቅረኛነትን ወይም ጋብቻን የሚያመለክት ነውን?” ያስብለናል። እስቲ ዳን ብራውንም ሆነ ሌሎች ሰዎች እንደጥሩ የጋብቻ ማስረጃ በሚያቀርቡት በዚህ ጥቅስ ላይ ኣንዳንድ ጥያቄዎችን እናንሳ፡
1.       እንደሚታሰበው መግደላዊት ማርያምና ኢየሱስ ፍቅረኛሞች ወይም ባልና ሚስቶች ቢሆኑ ሌሎች ደቀመዛሙርት መሳሳማቸውን ለምን ይቃወሙታል?
2.       ወንዶች ደቀመዛሙርት የተቃወሙት ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም ፆታዊ ፍቅር ማሳየቱን ሳይሆን እርሷን ከእነሱ ይበልጥ ማፍቀሩን መሆኑ ለምንድነው? ”ለምን ከእኛ ኣስበለጥካት?” እንጂ፣ ”ሴትነቷን ለምን ኣፈቀርከው?” ኣለማለታቸው ኢየሱስ ለማርያም ያሳያት የነበረው ፍቅር ለእነርሱም ያሳያቸው የነበረውን ዓይነት ፍቅር መሆኑን ኣያመለክትም? 
3.       ኢየሱስ በምላሹ፣ ”ምስቴን በሳምኩ እናንተ ምን ቁርጥ ኣደረጋችሁ!? ኧረ ንሽቴ!” ኣለማለቱ ለምንድነው? ይልቅ ያላቸው፣ እርሱ እርሷን የማስበለጡ ምክንያት እርሷ ከእነርሱ ይልቅ የመንፈስ ዓይኗ የበራ በመሆኑ እንጂ በሴትነቷ ምክንያት እንዳይደለ ነው። እና ታዲያ እርሱ ለእርሷ የነበረው ፍቅር፣ ፍቅሩን ሊገልፅላት ይጠቀምበት የነበረውም መንገድ መንፈሳዊ ኣይሆን ይሆን? ከዚያ ግዜ ልማድ‘ኮ እጅግ ርቀን ነው ያለነው። በዛሬ ሚዛናችን ከሁለት ሺ ዓመታት ኣስቀድሞ የነበረውን ኣድራጎት መስፈራችን ስህተት የለውም ማለት እንችላለን?   

እንግዲህ ይህም ጥቅስ የኢየሱስንና የማርያምን ፆታዊ ፍቅር ወይም ጋብቻ ለማመልከት ኣቅም የለውም ማለት ነው።

ከላይ በኣጭሩ ያየናቸው መረጃዎች የዳን ብራውን ሙጉት ታሪካዊ መሠረቱ በራሱ የማይቆም ሰንበሌጥ እንደሆነ ያስረዳሉ። ቀጥሎ የማርያምን እንስተ-መለኮትነትን ጉዳይ እንመልከት፡

III.               የዳን ብራውን ሎዢካዊ ማስረጃዎች

ዳን ብራውንና ሌሎች የኢየሱስ-ወ-ማርያም ጋብቻ ሃሳብ ኣራማጆች ከሚያቀርቧቸው ሎዢካዊ ማስረጃዎች ዋናው፣ ኢየሱስ እና ማርያም (እንደ ቻይናዊያኑ ኢን እና ያንግ) የመለኮት ሴት እና ወንድ (ወይም ጥቁርና ነጭ) መገለጫዎች ናቸው የሚል ነው። ወንዴ- ወይም ተባዕተ-መለኮት በኢየሱስ ተገለጠ። ሴቴ- ወይም እንስተ-መለኮት ደግሞ በማርያም። ስለዚህ ማርያም የኢየሱስ ሚስት ብቻ ሳትሆን የመሲህነቱም ተጋሪ ናት። በእርሷ በኩል ባይሆን ኖሮ መለኮት በምልዓት ለዓለም ባልተገለጠም ነበር። ከዚህ ፀጋ ዓለም ኣይነፈግ ዘንድ መለኮት እንስታዊ ባህሪይውን በመግደላዊት ማርያም በኩል ሊገልፅ ወደደ። ቀድሞም የሰው ልጅ እንስታዊ ባህሪይ እና ተባዕታዊ ባህሪይ መነጣጠሉ ነው ለውድቀቱ (ከገነት ለመውጣቱ) ምክንያት የነበር። ኣንዳንድ ሰዎች እነዚህን ባህሪያቱን ይበልጥ ለማዋሃድ መትጋታቸው የመዳናቸው መንገድ በዚያ እንደሁ በማወቃቸው ነው። ይህ ነው እስከዛሬ በተለያዩ እምነቶች ውስጥ በቅድስት እናት፣ በእናት ኣማልክት፣ በፅገሬዳ፣ በቅዱስ ፅዋ፣ ወዘተ… እየተመሰለ፣ ኣይሲስ፣ ቬኑስ፣ ኣፎርዳይት፣ ኣርቴሚስ፣ ዴሚትር፣ ዲያና፣ ኣቴና፣ ወዘተ… በሚሉ ስሞችም እየተጠራ ሲመለክ እምናየዉ። ኢየሱስ ከማርያም ጋር በፈፀመው ጋብቻ ኣማካኝነት ይህንን የድህነት ሚስጥር ገለፀ። በዚህም ወሲብ ሰብዓዊ ማንነት ወደምልዓቱ የሚመለስበት የመለኮት መንገድ ተደረገ።

ይህ በተለይ በሴታዊነት (feminism) ኣራማጆች ዘንድ የሚዘወተር ሳቢ ሙጉት ቢሆንም በሎዢክ ሚዛን ላይ ሲቀመጥ ግን ውሃ ኣያነሳም (የሎዢክ ሚዛን እንደባለሎዢኩ ሊለያይ መቻሉ እንዳለ ሆኖ)።

እንደኔ እምነት ችግሩ ያለው የእግዚኣብሔርን እና የኢየሱስን መለኮታዊ ባህሪይ ከመረዳት ላይ ነው። ፈላስፋዎችን ለዘመናት ያፋጩ ውስብስብ ሥነ-መለኮታዊ ጉዳዮችን ወደጎን ትተን እንደውይይት መነሻ ስለእግዚኣብሔርና ስለኢየሱስ ባህሪያት ብዙዎቻችንን ሊያስማሙ የሚችሉ ኣንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ፡

እግዚኣብሔር ፍፁም ነው። እግዚኣብሔር የስሞችና የባህሪያት ሁሉ ጌታ ነው። እግዚኣብሔር የሃይላትና የስልጣናት ሁሉ ባለቤት ነው። በብዙ ባህሎች በወንዴ ፆታ መጠራቱ የቋንቋና የተለምዶ ጉዳይ ሆኖ እንጂ እግዚኣብሔር ከፆታዊ እሳቤዎች የላቀና የረቀቀ መለኮታዊ ህላዌ ነው። ወንበር ኣናፂውን መረዳት እንደማይችል ሁሉ የሰው ልጅ ኣዕምሮም ፈጣሪውን በምልዓት ሊረዳው ኣይችልም። እኛ ስለእግዚኣብሔር የሚኖረን ሃሳብ ብዙውን ጊዜ ባለን ዕውቀትና የመንፈስ ብቃት የተወሰነ እንጂ የእርሱን እውነተኛ ህልውና የሚወክል ኣይደለም። ለብዙዎቻችን እግዚኣብሔር በግዙፍ ዙፋን ላይ ተቀምጦ በትልቅ-በትንሹ ላይ የሚፈርድ ፂማም ሽማግሌ ነው። ይህንን የመሳሰሉ የምናብ ስዕሎቻችንን እንደብቸኛና ትክክለኛ የእግዚኣብሔር ምስል ማሰብ ስንጀምር ያንን ምስል ጣዖት ማድረግ እንጀምራለን። ከእንጨትና ከዲንጋይ የሚሰሩ ጣዖቶች ነባራዊ ህልውና ያላቸው ነገሮች ናቸው። በዓዕምሮኣችን የምንስለው የእግዚዓብሔር ምስል ግን ምንም ዓይነት ህልውና የሌለው ጣዖት ነው። ስለዚህ ከእንጨትና ከድንጋይ ጣዖቶች ይልቅ ይህ እጅግ ኣደገኛና ኣጥፊ ነው። በዓለም ላይ የታላላቅ ውዝግቦችና ክፍፍሎች፣ የኣሰቃቂ ጦርነቶችና ዕልቂቶች ምንጭ የሆነውም ይህ ምናባዊ ጣዖት ነው። ኣንዳንድ ነፃ ኣሳቢዎች፣ ”እግዚኣብሔር የለም፤” ሲሉ፣ ”እግዚኣብሔር ሞቷል፤” ሲሉ፣ እንዲያ የሚሉት ይህንን ጣዖታዊ ምስል እያሰቡ ነው። እንዲህ ያለው እግዚኣብሔር ቀድሞም ህይወት ኣልነበረውምና እውነት ነው ሙት ነው። ውስንነት ኢውስንነትን ኣያካትትምና እግዚኣብሔር የሰው ዓዕምሮ የቱንም ዓይነት ብቃት ቢኖረው ሊፀንሰውና ሊገልፀው ከሚችለው በላይ የሆነ ህያው እሳቤ።


ኢየሱስ እግዚኣብሔር የምንለው ሕልውና ፍፁማዊ መገለጥ ነው። ሰው እግዚኣብሔርን በቀጥታ ሊያገኘውና ሊያውቀው ኣይችልምና እርሱ ሰውን ሆኖ ኖሮ የእርሱን ፈቃድና መንገድ ያሳየን ዘንድ ከሰማይ የወረደ የፈጣሪ ክስተት ነው። ለዚያ ነው እሱን ያየ ኣምላክን ያየ የሚሆነው። ለዚያ ነው እርሱ ህይወትም መንገድም የሚሆነው። እርሱ የእግዚኣብሔር ፍፁማዊ መገለጫ በመሆኑም የእግዚኣብሔር ስሞችና ባሕርይት፣ የሃይላቱና የስልጣናቱ ሁሉ ባለቤት ነው። እርሱ ጋ የሌሉ ነገሮች እግዚኣብሔር ጋ የሌሉ ነበሮች ብቻ ናቸው። ያኚም፣ በራሳቸው ህልውና የሌላቸው ጥላቻንና እኩይነትን የመሳሰሉ ነገሮች እንጂ ሌላ ሊሆኑ ኣይችሉም። እግዚኣብሔር ከፆታ እሳቦቶች በላይ በመሆኑም በኢየሱስ ኣማካኝነት የተገለፀልን መንፈስቅዱስም ከፆታ እሳቦቶች በላይ ነው። ሰው ሴታዊ ወይም ወንዳዊ ባህሪያትን (በስነልቦናና በፍልስፍና ”ኢሮስ” እና ”ሎጎስ” የሚባሉ ዓይነት ዝንባሌዎችን) በትንሹ ወይም በትልቁ ሊያሳይ ይችላል። የፍፁምነት ክስተት የሆነው ኢየሱስ ግን እነዚህን ባህርያት በምልዓትና በእኩልነት የያየዘ ነው። ስለዚህ፣ ኢየሱስ ወንድ በመሆኑ በተለይ የመለኮትን ተባዕታዊ ባህሪይ ኣብዝቶ ይገልፃል ልንል ኣንችልም። በዚህም ላይ ተመስርተን፣ እግዚኣብሔር እንስታዊ ባህሪይው ለፍጡራኑ ይደርሰን ዘንድ የወንድ መልዕክተኞቹን ሴት ኣጋሮች ማስነሳት ነበረበት የሚል ሙጉት ልናቀርብ ኣንችልም። መግደላዊት ማርያም በቅድስናዋ ምንም ያህል ከፍ ያለች ብትሆን የኢየሱስን መሲህነት ልትጋራ የምትችልበት መንገድ ኣይኖርም። እርሷ የኢየሱስ ሚስት ስለሆኗ የማያጠራጥሩ መረጃዎች ቢገኙም እንኳ ያ የመሲህነቱ ተጋሪ ኣያደርጋትም። ኢየሱስ መለኮትን በምልዓት ሊሸከም ኣጋዥ ኣያሻውም። ያ ከሆነ የእርሱ ፍፅምና ኣንፃራዊ ፍፅምና ይሆናል። ሰብዓዊ እንጂ መለኮታዊ ፍፅምና ብሎ ኣንፃራዊነት ደግሞ የለም። የመግደላዊት ማርያም ቅድስና ምንጩ ለኢየሱስ ያላት መንፈሳዊ ቅርበት እንጂ ስጋዊ ቅርበቷ ኣይደለም። ይህ ለእርሷ ሊሰጣት የሚገባውን ክብር በምንም ኣይነት ኣያኮስስም፣ ኣያጎድፍም። የክብሮች ሁሉ ክብር የመለኮታዊ ቅርበት ክብር ነውና። ያንን የክብር መንበር ደግሞ መግደላዊት ማርያም ከማንኛውም ተራ ሟች ይልቅ ተቀዳጅታዋለች። 

Friday, November 20, 2015

የዮሐንስ ወንጌል የማርያም ወንጌል ስለመሆኑ የቀረቡ ማረጋገጫዎች

ክርስትና በመሰረቱ የሴቶች እምነት ነበር። ወንዶች ኣያያዙን ሳያውቁት ነጠቋቸውና እንዳይሆን፣ እንዳይሆን ኣደረገጉት አንጂ። እስቲ ኣስቡት፡ ከወንጌል ታሪክ ውስጥ መሳጩ ታሪክ የሴቶች ታሪክ ነው። ከፅኑ የኢየሱስ ተከታዮች ውስጥ ዋናዎቹ ሴቶች ነበሩ። ኢየሱስንና ተከታዮቹን በገንዘባቸውም ጭምር ይደጉሙ የነበሩት ሴቶች ነበሩ። በኢየሱስ የእንግልትና የስቅላት ጊዜ ወንዶች ደቀመዛሙርት በሙሉ ፈርተው ሲሸሹ በፅናት ኣብረውት እስከመጨረሻው የቆሙት ሴቶች ነበሩ። እርሱ ከተቀበረም በሁዋላ መቃብሩን ለመጎብኘት የሄዱ፣ በሽቱም ሊያጥኑት ያሰቡ፣ ሴቶች ነበሩ። ኢየሱስ ከሙት በተነሳ ሰዓትም በመጀመሪያ ያናገራቸው፣ ለወንዶች ደቀመዛሙርት የትንሳዔውን ብስራት እንዲያውጁ ተልዕኮ የተሰጠው፣ ለሴቶች ነው። ወንዶች ደቀመዛሙርት ትንሳዔውን ለመቀበል ተጠራጥረው ሲያንገራግሩ በእምነታቸው ፀንተው የቆሙት ሴቶች ናቸው። ሴቶች ኣዲስ የተገለፀውን እምነት እንዲያ በነፍስና በልባቸው የመቀበላቸው ምስጥር ዛሬ የምሁራን መነጋገሪያ ነው። ክርስቶስ ሴቶችን እጅግ ስላከበረ ይሆን? የወቅቱ የኣይሁድ ካህናትና ምዕመናን፣ የእርሱ ደቀመዛሙርትም ጭምር፣ በኣድራጎቱ ሲያንጎራጉሩ፣ እርሱ ሴቶችን፣ በተለይም ከተናቀው እና ከተበደለው ወገን የሆኑትን፣ በእኩልነት መንፈስ ያነጋግር፣ ይፈውስ፣ ኣብሮኣቸውም ይመገብ፣ ያንን ፍቅሩን ለመመለስ የሚያደርጉትን መስዋዕትነትም በፍቅራዊ ደግነት ይቀበል ነበር። በእውነቱ፣ እርሱ ለሴቶች እጅግ ርህሩህና በምህረት የተሞላ ነበር። ይህንን ሁሉ ስናይ፣ ኢየሱስ እውነቱን በተለይ ለሴቶች በኣደራ እንደሰጠው እናስበለን። እና ታዲያ፣ ክርስትና እንደምን ከሴቶች እጅ ወጣ? ኣንዳንዴ ሳስበው፣ ‘ሴቶች ክርስትናን ባይነጠቁት ኖሮ፣ የመስቀል ጦርነትን፣ “The Inquisition”ን፣ “Ku Klux Klan”ን፣ “The Witch Hunts”ን፣  “Lord’s Resistance Army”ን የመሳሰሉ ክርስቲያናዊ መርገምት ምድርን ይጎበኙኣት ነበር ወይ?’ እላለሁ።
በባለፈው ጦማሬ በከፊል ያስነበብኳችሁ የጥናት ውጤት፣ “ወንጌልም እኮ ይነጠቃል፤ ይሰረቃል!” ይለናል። “የመግደላዊት ማርያም ወንጌል ተነጥቆና ተቀይሮ ለዮሐንስ ተሰጠ!“ ይለናል። “’በዚያ ወንጌል ውስጥ፣ ‘ኢየሱስ ይወደው የነበረው፣’ ‘በእራት ጊዜ በኢየሱስ ደረት ላይ ተደግፎ የነበረው፣’ ‘እናቱን በኣደራ ሰጠው’“ የተባለለት፣ ምን ፆታው ተቀይሮ በወንድ ቢገለጥም ያ ደቀመዝሙር በእርግጥ መግደላዊት ማርያም ነበረች!“ ይለናል። “የዚያ ወንጌል ኦርጂናሌው በጠዋቱ የሃዋርያት ቤተክርቲያን ተፅዕኖ በመቀየሩ እንጂ፣ መፃፉ ራሱ የሚመሰክረው እውነት ይህ ነው፤ ወንጌሉ ስለመቀየሩም ግልፅ የሆኑ ማረጋገጫዎች ኣሉ!“ ይለናል። በዚህ ፅሁፍ የመጀመርያ ክፍል፣ በቀጣይነት የዚህን ሙጉት ማረጋገጫዎች እንደማቀርብ ቃል ገብቼ ነበር። ማረጋገጫዎችን ከማየታችን በፊት ኣንድ ጥያቄ ለመመለስ ልሞክር፡ ጥንታዊያኑ የሐዋርያት ቤተክርስቲያናት መሪዎች ወንጌሉን በእርግጥ ለውጠውት ከሆነ፣ በዚህ ቅዱስ መፅሃፍ ላይ ይህንን ዓይነት ጥፋት ያመጡ ዘንድ ሊያነሳሱኣቸው የቻሉ ነገሮች ምንድር ናቸው?
የጥንት ቤተክርስቲያናት ወንጌሉን ለመለወጥ ኣስገድደዋቸዋል የሚባሉ ነገሮች
ከክርስቶስ እርገት በሁዋላም ሴቶች ኣዲሱን የክርስትና እምነት በማስፋፋት ሁነኛ ሚና እንደነበራቸው የታሪክ መረጃዎች ያመለክታሉ። “የጳዉሎስና የቴክላ ሥራ/Acts of Paul and Thecla“ የተሰኘው ፅሁፍ እንደሚያመለክተው ሴቶች እንደ ወንድ ደቀመዛሙርት ሁሉ በየቦታው እየተዘዋወሩ ወንጌሉን ያስፋፉና እምነቱን ለመቀበል የፈቀዱትን ሰዎችም ያጠምቁ ነበር። ወቅቱ ግን በሴቶች ላይ ታላቅ ገደብ ይደረግ የነበረበት ወቅት ነበር። በተለይ ያላገቡ ሴቶች እንደልቅና ጋጠዎጥ ይታዩ ነበር። መግደላዊት ማርያም መለያዋ ቦታ እንጂ ቤተሰብ (ኣባት፣ ባል፣ ወንድም፣ ወዘተ) ኣለመሆኑ ላጤ እንደነበረች ያመለክታል። ይህ፣ በሐዋርያቱ እና ገና በመደራጀት ላይ ባለው የክርስቲያን ቤተሰብ ዘንድ ኣሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ እንደነበር መገመት ኣያዳግትም። በሁዋላ በመግደላዊት ማሪያም ላይ ለተፈጠረው የተዛባ ኣመለካከትም ላጤነቷ ኣስተዋፅዖ ያደረገ ይመስላል።
በኣይሁድም ሆነ በወቅቱ ይገዙኣቸው በነበሩቱ ሮማዊያን ማህበራዊ መዋቅር ውስጥ ያልታቀፉቱ የኢየሱስ ተከታዮች፣ ምንዝርና ባለስልጣን የሌለበት፣ ሁሉም እኩል የሚታይበት፣ ትንሽ ማህበረሰብ ነበር። ክርስቶስ ካረገ በሁዋላ ግን የኣመራርና የስልጣን መዋቅር ጉዳይ ጥያቄ ሆኖ ተነሳ። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ያ ትንሽ የክርስቲያን ማህበረሰብ ወደተለያዩ ቡድኖች ተከፋፈለ። ከነዚህ ውስጥ ዋናዎቹ ጴጥሮስን እንደመሪ የወሰደው የሐዋርያቱ ቡድን እና የተለያዩ ትንንሽ ቡድኖች የነበሩት በኣጠቃላይ ግን “ግኖስቲክስ“ በመባል የሚታወቀው፣ በኣመዛኙ መግደላዊት ማርያምን እንደመሪ የወሰደው፣ ቡድን ነበር። (ግኖስቲኮች፣ ባጭሩ፣ “እግዚኣብሔር እውስጣችን ኣለ፤” በሚለው እምነት መሠረትነት መዳን ራስን፣ ውስጥን፣ ከማወቅ ይመጣል ባዮች ናቸው። ኢየሱስም ያስተማረው ያንን እንደሁ ያምናሉ። ጠፍተው የተገኙቱ ወንጌላት በኣብዛኛው የግኖስቲኮች ወንጌላት ሲሆኑ ይዘታቸው ከምናውቃቸው ወንጌላት ለየት የሚለው ለዚያ ነው።) ዓመታት ሲያልፉ ከተወዳዳሪ የክርስትና ቡድኖች መሃል የሐዋርያቱ ቤተክርስትያን ኣሸናፊነት እየተረጋገጠ መጣ። የቤተክርስትያኒቱ መሪዎች፣ የተከፋፈለውን የክርስቶስ ቤተሰብ ለማዋሃድ ወጥ የሆነ ቅዱስ መፅሃፍ እንደሚያስፈልግ ኣምነው፣ በሚቀጥሉት ሦስት ምዕተዓመታት በብዙ ጉባዔዎች፣ ውይይቶች፣ ውዝግቦችና ግጭቶች ውስጥ ሃያሰባቱን የኣዲስ ኪዳን መፅሃፍት መረጡ። በዚህ ሂደት ቤተክርስቲያኒቱ ከተቀበለቻቸው መርሆዎች ጋር የማይጣጣሙ የሚመስሉ ነገሮችን የያዙ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው የግኖስቲኮች ወንጌላት፣ ደብዳቤዎችና ታሪኮች በመናፍቅ መፅሃፍትነት ተፈርጀው ተወገዙ፤ እንዲወድሙም ተደረገ። ከነዚህ መፅሃፍት መጥፋት ጋር፣ በግኖስቲኮች ዘንድ ከኢየሱስ ቀጥሎ እንደመሪ ትታይ የነበረችው የመግደላዊት ማርያም ስምም እየደበዘዘ መጣ።
በሐዋርያት ቤተክርስቲያን፣ በተለይም በካቶሊክ፣ ጴጥሮስ ስልጣኑን ከኢየሱስ የተቀበለ የሐዋርያት ቤተክርስትያን መሪ እነደሆነ ተቆጠረ። በእርሱ ወንበር ላይ የሚቀመጡ የሮማን ካቶሊክ ጳጳሳትም ያው የክርስቶስ ስልጣን ተቀባይ እንደሆኑ ታመነ። በዚህ ውስጥ የመግደላዊት ማርያም የሐዋርያነት እና የበላይነት ጉዳይ የጴጥሮስን እና የወራሾቹን ጳጳሳት ስልጣን መለኮታዊነት ከጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆነ። ስለዚህም የመግደላዊት ማርያምን ክብርና ሞገስ የሚያጎድፍ ዘመቻ ማካሃድ ወንጌላትን ከማጥፋት ጎን ለጎን የሐዋርያት ቤተክርስቲያን ኣንደኛው የትግል መስመር ሆኖ ወጣ። ማርያም የኢየሱስን ትንሳዔ እማኝ፣ ይህንንም ለሐዋርያቱ ታበስር ዘንድ ተልዕኮ የተሰጣት፣ በመሆኗ “Hyppolytus“ የተሰኙ በሁለተኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻ ኣከባቢ የነበሩ ጳጳስ፣ “የሐዋርያት ሁሉ ሐዋርያ” የሚል የክብር ስም ቢሰጧትም ከእርሳቸው ቀጥሎ የመጡት ጳጳስ ይህንን ስላጣጣሉት የጳጳስ ሂፖሊተስ ምስክርነት በመግደላዊት ማርያም ላይ የተያዘውን ዘመቻ በመግታት በኩል ኣስተዋፅዖው እምብዛም ነበር። ዘመቻው በእርሷ ላይ ብቻ ኣልነበረም። በሴቶች የኣመራርና የኣገልግሎት ሚና ላይም ጭምር እንጂ። ለምሳሌ፣ በኣንደኛው ምዕተዓመት መጨረሻ ላይ የሮሙ ካህን ክሌሜንት እና በሁለተኛው ምዕተዓመት የኣፍሪካ ቤተክርስቲያናት ጳጳስ ተርቱሊያን፣ ሴቶች በቤተክርስቲያናት ውስጥ ምንም ዓይነት ኣገልግሎት እንዳይሰጡና በመሪነትም ቦታ ላይ እንዳይቀመጡ ኣዘዙ። በኣራተኛው ክፍለዘመን፣ “Apostilic Constitution“ የተሰኘው ደንብ፡ “ከመፀለይና ስብከትን ከማድመጥ በስተቀር፣ ሴቶቻችን በቤተክርስቲያን ውስጥ እንዲያስተምሩ ኣንፈቅድም፤“ የሚል ክልከላ ይዞ ወጣ።
የመግደላዊት ማርያምን ሞገስ ለማጣጣል በቀጥታ በእርሷ ላይ የተደረጉ ስብከቶች እና የተፃፉ ፅሁፎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሁሉንም እዚህ መጥቀሱ ይህንን ፅሁፍ ኣለቅጥ ያረዝመዋል። (ዝርዝር የሚፈልጉ ከዚህ ፅሁፍ መጨረሻ ላይ የተጠቀሱትን ዋቢዎች ይመልከቱ።) በኣጠቃላይ ግን፣ እርሷን ከሌሎች የወንጌል ሴቶች የማትለይ (ተራ) ሴት እንደሆነች ለማሳየት፣ ማንነቷንም ከሌሎች ሴቶች ጋር ኣምታቶ ለማቅረብ፣ ክርስቶስ ከሰባት ኣጋንንት ፈወሳት በሚለው ታሪክ ላይ በማትኮር ሃጥዓተኛነቷን ለማጉላት፣ የመሳሳት ምክንያት ተደርጋ ከምትታየው ከሄዋን ጋርም ኣንድ እንደሆነች ለማሳመን፣ የኢየሱስንም ትንሳዔ ለመመስከር የማትበቃ ሴት እንደሆነች ለማሳየት፣ ከትንሳዔው በሁዋላ ኢየሱስ፣ “ኣትንኪኝ፣ ገና ወደኣባቴ ኣልሄድኩም፤” ያላት በሃጥዓቷ ምክንያት እንደሆነ ለማሳመን፣ ወዘተ የሚጥሩ ነበሩ። የቤተክርስቲያን ኣባቶች የማርያም መግደላዊትን ምንነት በተመለከተ ውስብስብ ስነ-መለኮታዊ ትንታኔ ውስጥ ገቡ። ይህንን ኣምስት ምዕተ-ዓመት የዘለቀ ዘመቻ ማሳረጊያ ያበጁለት ጳጳስ ግሪጎሪ ናቸው፡ በኦፊሴል፣ “መግደላዊት ማርያም፣ ሉቃስ የጠቀሳት ሴተኛ ኣዳሪዋ ሴት እንደሆነች እናምናለን!” በማለት።  
እንግዲህ የግኖስቲኮችን ፅሁፎች ለማጥፋት፣ ሴቶች በኣጠቃላይ፣ በተለይም መግደላዊት ማርያም፣ በክርስትና ውስጥ ያላቸውን ክብርና ቦታ ለመንጠቅ፣ ከተደረገው የከረረ እና የተራዘመ ዘመቻ ኣንፃር መነሻችን የሆነውን የ“ዮሐንስ“ን ወንጌል ጉዳይ እናስብ። ኣጥኚዎቹ እንደሚነግሩን፣ ይህ ወንጌል በጠዋቱ የክርስትና ታሪክ ውስጥ በመጀመሪያ በግኖስቲኮች ዘንድ ይበልጥ የታወቀና የእነርሱም እንደሆነ የሚቆጠር ነበር። (በወንጌሉ ላይ የተገኘው እጅግ ጥንታዊው ኣንደምታ የግኖስቲኮች ኣንደምታ ነው።) እንደተባለው፣ “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር፣“ በሚለው ስም-የለሽ ደቀመዝሙር ምትክ የመግደላዊት ማርያምን ስም ተክተን ብናነብ ያ በወንዶች ደቀመዛሙርት እና በጴጥሮስ መለኮታዊ መሪነት በሚያምኑት ሐዋርያዊያኑ ቤተክርስቲያናት ዘንድ የሚፈጥረውን ሥነ-መለኮታዊ ፈተና እናስብ። ይህ ከሆነ፣ እነዚያ ቤተክርስቲያናት ወንጌሉን የራሳቸው ካደረጉት በሁዋላ፣ ይዘቱን ለማስተካከል መገደዳቸው እንደማይቀር ግልፅ ይሆናል።
ወንጌሉን የለወጡ ሰዎች ለምን የመግደላዊት ማርያምን ስም ሙሉ በሙሉ ኣላወጡትም?
የሆነ ሰው ወንጌሉን ለውጦታል፣ የመግደላዊት ማርያምን ስም “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር፣“ በሚል ተክቶታል፣ ፆታውንም ወደወንድ ቀይሮታል፤ የሚለውን ምጉት ብንቀበል፣ ያ የለወጠው ሰው ለውጡን ለምን በከፊል ብቻ ኣደረገው? ለምን የመግደላዊት ማርያምን ስም ከሁሉም ቦታ ኣላወጣውም? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል።
መልሱ ቀላል ነው፤ ይላሉ የጥናቱ ኣቅራቢዎች። የዮሐንስ ወንጌል በሐዋርያኑ ቤተክርስቲያናት ተቀባይነት ከማግኘቱ በፊት የሉቃስ፣ የማርቆስና የማቴዎስ ወንጌላት በሰፊው ይታወቁ ነበር። በነዚያ ውስጥ ደግሞ በኢየሱስ የስቅላት፣ የቀብርና የትንሳዔ ሰዓት መግደላዊት ማርያምን ጨምሮ ሌሎች ሴቶች በቦታው እንደነበሩ በግልፅ ይናገራል። ኦርጂናሉን ወንጌል የቀየረው ሰው ከሌሎች ቦታዎች ላይ የማርያምን ስም ሊያወጣና በወንድ ሊለውጣት ቢቀልለውም ስለኢየሱስ ስቅላትና ትንሳዔ ከሚያወሩ ጥቅሶች ውስጥ ማውጣት ኣይችልም ማለት ነው። ይህንን ማድረግ ስላልቻለ፣ ለዋጩ ሌላ ዘዴ ተጠቅሞ እነዚያን ጥቅሶች ቀይሮኣቸዋል። ምን በማድረግ? “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር፣“ ከመግደላዊት ማርያም የተለየ ሰው መሆኑን ለማሳየት በነዚያ ተረኮች ውስጥ ያንን ስም-ኣልባ ደቀመዝሙር በጣልቃነት በማስገባት እርሱና ማርያም በኣንድ ቦታና ጊዜ በኣንድ ላይ የተገኙ ሁለት ሰዎች እንደሆኑ ለማሳየት መሞከር! ማርያምና ያ ደቀመዝሙር በኣንድ ላይ የተገኙት በነዚህ የስቅላት እና የትንሳዔ ቦታዎች ብቻ መሆኑ ይህ ምጉት ምክንያታዊ እንደሁ ያመለክታል። ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ፣ ለዋጩ የሌለ ሰው ጣልቃ ማስገባቱን የሚያመለክቱ ከሌላ ወንጌል ጋር የመጣረስ፣ የትረካ፣ እና የመዋቅር ስህተቶች በነዚህ ሁለት ቦታዎች ብቻ መኖራቸው ነው። ይህም፣ ቢያንስ እነዚያ ጥቅሶች ስለመቀየራቸው ግልፅ ማስረጃ ይሆናል።
1.      ወንጌሉ የማርያም ስለመሆኑ ወንጌላዊ ማረጋገጫዎች
ጥቅሶች በመለወጣቸው የተፈጠሩ ስህተቶች
ሀ. በኢየሱስ ስቅላት ሰዓት ወንድ ደቀመዝሙር በቦታው ኣልነበሩም፡
የሉቃስ፣ የማርቆስና የማቴዎስ ወንጌላት በኢየሱስ ስቅላት እና ቀብር ወቅት ኣብረውት የነበሩት ተከታዮች ከገሊላ የመጡ ሴቶች ብቻ እንደሆኑ ነው የሚገልፁት። (ሉቃ. 23፡49፤ 23፡55፤ ማር. 15፡40-41፤ 45፤ ማቴ. 27፡55) እኚህ ወንጌላት ወንዶች ደቀመዛሙርት በቦታው እንደነበሩ ኣይጠቅሱም። ይህም ወንዶቹ ደቀመዛሙርት በሙሉ ጥለውት እንደሸሹ (ማቴ. 26፡56) ከሚናገረው ጥቅስ ጋር ስምም ነው። ነገር ግን፣ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር በስቅላቱ ወቅት ከመስቀሉ ሥር እንደነበር ይናገራል። ይህ ደቀመዝሙር እንደተባለው ወንድ ከሆነ ቃሉ ከሌሎች ወንጌላት ጋር ኣይጣጣምም።  
ለ. በዮሐ. 19፡25-27 ያለው የተፋለሰ ትረካ ስህተት እንዳለ ያሳያል፡
በሚቀጥሉት ሁለት ዓረፍተነገሮች ውስጥ ያለውን መፋለስ እንመልከት፡ "በኢየሱስ መስቀል ኣጠገብ እናቱ፣ የእናቱም እህት፣ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፣ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር። ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በኣጠገቡ ቆመው ባየ ጊዜ እናቱን፡- ኣንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ፤ ኣላት።"
ፀሃፊው በሁለተኛው ኣረፍተነገር በመስቀሉ ስር ከነበሩ ሴቶች ስለኣንዱ ነው የሚያወራው? ከሆነ፣ያ ደቀመዝሙር ሴት ነው ማለት ነው። ካልሆነ ግን፣ በመጀመሪያው ዓረፍተነገር ውስጥ ያልነበረን ደቀመዝሙር ኢየሱስ በሁለተኛው ዓረፍተነገር ውስጥ ያየዋል ማለት ነው። ይህ ሰው ከዬት መጣ? እንዲህ ያለስ ኣተራረክ ልክ ይመስላል?
ሐ. ጴጥሮስ ብቻውን ነበር ወይስ ከሌላ ሰው ጋር?
ሉቃስ ኢየሱስ በተቀበረ ማግስት ጴጥሮስ መቃብሩ መፈንቀሉን ሰምቶ ወደመቃብሩ የሮጠው ብቻውን እንደሆነ ይተርካል። (24፡12) ማቴዎስና ማርቆስ ይህንን ኣይጠቅሱም። የዮሐንስ ወንጌል ግን (ዮሐ. 20፡ 1-11) ወደመቃብሩ የሮጡት “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር፣“ እና ጴጥሮስ መሆናቸውን ይናገራል። ሉቃስ ያልጠቀሰው ያ ደቀመዝሙር እዚህ ከዬት መጣ? ይህ ደቀመዝሙር በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ጣልቃ መግባቱ ከታች እንደምናየው የትረካ ስህተትም ኣምጥቷል።  
መ. መግደላዊት ማርያም ወደመቃብሩ ተመልሳ ነበር?
በዮሐ. 20፡ 1-11 ወደመቃብሩ በተደረገው የሩጫ ተረክ ውስጥ መግደላዊት ማርያም ለጴጥሮስና ለስም-ዓልባው ደቀመዝሙር የመቃብሩን መፈንቀል ከነገረች በሁዋላ ጴጥሮስና ያ ደቀመዝሙር ወደመቃብሩ ሮጡ ቢልም ስለመግደላዊት ማርያም ወደመቃብሩ መመለስ ኣይናገርም። ጴጥሮስና ስም ኣልባው ደቀመዝሙር ወደመቃብሩ ውስጥ እንደገቡ በሚናገር ሰዓትም መግደላዊት ማርያም የት እንደነበረች ኣይናገርም። መጨረሻ ላይ፤ ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ነበር፤ (20፡11) ይላል። ማርያም ወደመቃብሩ እንዴትና መቼ ተመለሰች? ተራኪው ይህንን እንዴት ዘለለው? ከጥቅስ 2 እስከ 10 ውስጥ የተጠቀሰው ተወዳጅ ደቀመዝሙር እርሷ እንደሆነች ካሰብን ግን ይህ የትረካ መፋለስ ኣይኖርም።
ሠ. ኣመኑ ወይስ ኣላመኑም? ያመነው ማነው? ያላመነውስ? 
ከላይ በተጠቀሰው ተረክ ውስጥ ሌላው የተምታታ ነገር፣ “በዚያን ጊዜ ኣስቀድሞ ወደ መቃብሩ የመጣውም ሌላ ደቀመዝሙር ደግሞ ገባ፣ ኣየም፣ አመነም፤ ከሙታን ይነሳ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና ኣላወቁም ነበርና።“ (20፡ 8-9) የሚለው ጥቅስ ነው። ይህ ጥቅስ ምንድነው የሚለው? ‘ኣመነ’ ነው ወይስ ‘ኣላመነም’? ከላይ ስም-ኣልባውን ደቀመዝሙር ‘ኣመነ’ ካለ፤ ከታች ‘ኣላወቁም/ኣላመኑም’ የሚለው ጴጥሮስንና ማርያምን ነው? ማርያም ግን ኣይታ ኣምናለች። ይህ፣ ወንዶች ደቀመዛሙርት የክርስቶስ ትንሳዔ ሲነገራቸው እንዳላመኑ ከሚናገሩት ከሌሎች ወንጌላት ተረክ (ማቴ. 28፡17፣ ማር. 16፡9፣ ሉቃ. 24፡11) ጋር ለማመሳሰል የተደረገ ያልተሳካ ጥረት ይመስላል። ማርያም ኣየች ኣመነችም፤ ጴጥሮስ ግን ስላላወቀ ኣላመነም ቢል የሰመረ፣ ከሌሎች ወንጌላትም ጋር የሚስማማ ትረካ ይሆን ነበር።
2.      ታሪካዊ ማረጋገጫዎች
‘የዮሐንስ ወንጌል የተፃፈው በመግደላዊት ማርያም ነው’ ለሚለው ምጉታቸው ኣጥኚዎቹ ያቀረቧቸው የታሪክ መረጃዎች ባጭሩ የሚከተሉት ናቸው፡
ሀ. ኣራተኛው (የዮሐንስ) ወንጌል ከሰባ ዓ.ምህረት በፊት ስለነበሩት የኣይሁድ ባህሎችና ቦታዎች ከሌሎች በተሻለ ትክክለኛ መረጃ ይሰጣል። ይህም፣ በወቅቱ በነበረ የዓይን ምስክር እንደተፃፈ ያመለክታል።
ለ. ኣራተኛው ወንጌል በቅርቡ ከዋሻ ውስጥ በተገኙት የግኖስቲኮች ወንጌላት ጋር በይዘት፣ በተለይ በመግደላዊት ማርያም እና በጴጥሮስ መካከል የነበረውን የፍኩኩር ግንኙነት በሚመለከት፣ የሚመሳሰል ነው። (ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር በብዙ መንገድ ከጴጥሮስ በልጦ መገኘቱ ጴጥሮስን ቅናት ውስጥ እንደከተተው ከዚህ ቀደም ኣይተናል።)
ሐ. ኣራተኛው ወንጌል ለሴቶች የሚሰጠው ክብር የግኖስቲክ ወንጌላት ለሴቶች ከሚሰጠው ክብር ጋር ይመሳሰላል። በተለይ ስም-ኣልባውን ደቀመዝሙር በመግደላዊት ማርያም ተክተን ካነበብን ይህ ይበልጥ ግልፅ ይሆናል።
ማሳረግያ፡
የዮሐንስ ወንጌል፣ በዜብዲዮሱ ልጅ በዮሐንስ ተፃፈ የሚለውን እምነት ዛሬ የመፅሃፍቅዱስ ምሁራንም ሆኑ ኣንዳንድ ቤተክርስቲያናት ኣይቀበሉትም። ‘እና ማን ፃፈው?’ ለሚለው ጥያቄ ደግሞ፣ ወንጌሉ ራሱ ‘ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር ፃፈው፣’ ብሎ ይመልሳል። ይህ ሚስጥራዊ ደቀ መዝሙር ማነው? ይህ ደቀመዝሙር መግደላዊት ማርይም ልትሆን እንደምትችል ወንጌላዊም ሆነ ታሪካዊ መረጃዎችን ጠቅሰን ኣይተናል። እንዲያ ከሆነ፣ የ’ዮሐንስ’ በሚል ስም እምናውቀው ወንጌል በእርግጥ የመግደላዊት ማርያም ነው ማለት ነው። ለካስ፣ ወንጌልም ይሰረቃል! ይህ ባይሆን ኖሮ፣ ኢየሱስና ወንጌላት ለሴቶች ይሰጡት የነበረውን ክብር የቤተክርስቲያናት ታሪክ ባያጎድፈው ኖሮ፣ ዓለም ሰቆቃዋ ምን ያህል በቀለለ ነበር!

1. R.K. Jusino, 1998፡ Mary Magdalene: Author of the Fourth Gospel?

2. Janice Meighan “Mary Magdalene, Partner or Prostitute: An in-depth study of the transformation of Mary Magdalene in church history” York University Research Paper, (2005) 

Sunday, November 15, 2015

የመግደላዊት ማርያም ወንጌል ገጽ 9

የዮሐንስ ወንጌልም የመግደላዊት ማርያም ወንጌል ነው?  
ይህ እጅግ ኣስደንቆኛል። እናንተንም እንደሚያስደንቃችሁ እርግጠኛ ነኝ። ባለፈው፣ መግደላዊት ማርያም የኢየሱስ ፍቅረኛ በመሆን ኣለመሆኗ ጥያቄ ላይ እንደምፅፍ ቃል ገብቼ ነበር። ይህ ኣሁን ያገኘሁት ምስጥር ከዚያም ይልቅ ኣስገራሚ ሆኖ ስላገኘሁት ነው ያንን ለግዜው ያቆየሁት። እኔ እምብዛም የመጽሐፍቅዱስ ደጋሚ ኣይደለሁም። ይህንን ያህል ያፈጠጠ ጉዳይ ዓይኔ ሥር ተደብቆ ሲያልፈኝ መክረሙ ግን “ኣጀብ!” ኣስብሎኛል። ቢያንስ ሲጠይቁ ኣለመስማቴ!
ሰሞኑን ባጋጣሚ የገባሁበት የመግደላዊት ማርያም ጉዳይ ኣስገራሚ የኣድቬንቼር ዓለም ሆኖ ኣገኘሁት። የትኛውንም የዕውቀት ዘርፍ እጣታችን ጫፍ ላይ ላመጣው ዘመን ምስጋን ይግባው! ባለሞያ ኣይደለንም ብለን ከፍለጋ ሳንገታ በመረጥነው የዕውቀት ዘርፍ የቻልነውን ያህል እንጓዝ ዘንድ ጎዳናውን ክፍት ኣድርጎልናል ዘመኑ። እሸት የደረሰለት ያገሬ ገበሬ፣ “እነሆ ቅመሱልኝ!“ እንደሚል፣ እኔም ኣጭር ጉዞዬ ያስጠረጠረችኝን እሸት “እነሆ“ ለማለት ወግ ሆኖ ኣገኘሁት። መቼም ፍለጋ የየራስ ነው። ይህ የዘመኑ ዕድል ግን የሁላችንም ነው። “ቄሱም ዝም፤ መፅሃፉም ዝም!“ እምንልበት ዘመን ካበቃ ሰነበተ። ቄሱ ከተለጎሙ መጽሐፉን እምናናግርባቸው እልፍ ቁልፎች በየጣሪያችን፣ በየጣታችን ሥር ናቸው። ኣማኞች እንደሚሉት ፍርድ የእግዚኣብሔር ነው። እግዚኣብሔር ደግሞ ሚዛኑን በየልባችን ኣኑሯል። የቱም ነፍስ በሌላው ነፍስ ተጠያቂ ኣይሆን ዘንድ የየግል ፍለጋ የዘመኑ ግዴታ ሆኗል። ለኔ፣ ይህ የፍለጋዬ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ ኣይደለም። በመግደላዊት ማርያም ዙርያ ያለው ታሪክ እጅግ ኣጓጊና መሳጭ ነው። ሃሰሳዬ ይቀጥላል። በየራሳችሁ መንገድ በፍለጋው መጀመሪያም መሃልም ሆነ መጨረሻ ላይ ያላችሁ፣ ምናልባት በዚህ መንገድ ኣላለፋችሁ እንደሁ፣ እነሆ የተደነቅሁበት የሰሞኑ ግኝት፡
“የዮሐንስ ወንጌል ደራሲ መግደላዊት ማርያም ናት፤“ ይላል ከድረገፅ ያገኘሁት ኣንድ የጥናት ወረቀት። “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?“ ኣልኩኝ ይህንን ርዕስ እንዳየሁ። ፀሃፊው ማስረጃውን በኣመዛኙ ከዚያው ከዮሐንስ ወንጌል መምዘዙ የመደነቄ መጀመሪያ ሆነ።
የዮሐንስ ወንጌል ከሌሎች ወንጌላት በብዙ መልኩ የተለየ ነው። ከሌሎች ወንጌላዊያን ይልቅ ለኢየሱስ ቅርብ የሆነና በመንፈሳዊ ዕይታውም ከፍተኛ ደረጃን የተቀዳጀ ሰው እንደፃፈው ይታወቃል። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደሚስማሙበት የዚህ ወንጌል ደራሲ ኣይታወቅም። ቀድሞ፣ ደራሲው ሐዋሪያው ዮሐንስ (የዘብዲዮስ ልጅ) እንደሆነ ይታሰብ ነበር። ለዚያ እምነት የተገኘው ማስረጃ፣ Irenaeus የተባሉ የሁለተኛው ክፍለዘምን ጳጳስ የልጅነት ትዝታ ብቻ ሆኖ ተገኘ፡ “በልጅነቴ ጳጳስ Polycarp ነግረውኝ ነው፤“ ያሉት። ይህ እምነት እውነት እንዳይደለ ብዙ ኣጥኚዎች ይስማማሉ። ከነዚህ ውስጥ የወንጌሉ ትክክለኛ ደራሲ በዚያው ወንጌል ውስጥ በተደጋጋሚ የተጠቀሰው ክርስቶስ እጅግ ይወደው የነበር ደቀመዝሙር ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ወንጌሉ ራሱ ያንን ይመሰክራል። ያ ደግሞ ሐዋሪያው ዮሐንስ ኣይደለም።  
ካስደነቁኝ ነገሮች ኣንዱ እንግዲህ ይህ ነው። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ለክርስቶስ ከሌሎች ደቀመዛሙርት ሁሉ ይልቅ የቀረበ፤ ከኢየሱስ ጥምቀት ጀምሮ ይከተለው የጀመረ፣ ነገር ግን ስሙ ሆን ተብሎ በሚመስል መልኩ ያልተጠቀሰ፣ ኣንድ ምስጥራዊ ደቀመዝሙር መኖሩ ነው። ይህ ደቀመዝሙር ክርስቶስን ያን ያህልከ ይቀርበው ከነበር፣ ስሙ ኣለመጠቀሱ ለምን ይሆን? ትሉ ይሆናል። ያ የኔም ጥያቄ ነበር። መልሱ ከምር፣ “ወይ ግሩም!” ኣስብሎኛል። ስለ መግደላዊት ማርያም ከማውራታችን በፊት፣ ይህ ደቀመዝሙር ከክርስቶስ ጋር ምን ያህል ይቀራረብ እንደነበር ለማሳየት እርሱ የተጠቀሰባቸውን ኣናቅፅት ማየት ግድ ይለናል (ረዘም ያሉ ጥቅሶችን በትዕምርተ-ጥቅስ ቀንፌ ስለማሳጥራቸው ለተሟላ መረጃ መፅሃፍቅዱሳችሁን መግለፅ ይኖርባችሁ ይሆናል)፡
1.       ዮሐ 1፡ 35-40 - "…[መጥምቁ] ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ቆመው ነበር፣ ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ - እነሆ የእግዚኣብሔር በግ ኣለ። ሁለቱ ደቀመዛሙርት ሰምተውት ኢየሱስን ተከተሉት። …" ምናልባትም እኚህ ኢየሱስን ኣውቀው የተከተሉ የመጀመሪያ ደቀመዛሙርት ናቸው። ቀድመው መሲሁ እንደሚመጣ ኣውቀው ሲፈልጉት የነበር ይመስላል። በኢየሱስ ግብዣ ወደ እርሱ ቤት ሄደው ኣብረውት ዋሉ። ከነዚህ ሁለት ደቀመዛሙርት ኣንዱ እንድርያስ እንደሆነ ዝቅ ብሎ ተጠቅሷል። የሌላው ማንነት ኣልተጠቀሰም። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ይህ ስሙ ያልተጠቀሰው ሰው ገና የኢየሱስ ደቀመዝሙር መሆኑ ነበርና፣ "ኢየሱስ የሚወደው ደቀመዝሙር" ኣልተባለም። ቢሆንም፣ በሌሎች ቦታዎች ላይ "ኢየሱስ የሚወደው" የተባለው ይኸው ሰው እንደሆነ ኣንዳንድ የመፅሃፍቅዱስ ኣጥኚዎች ያምናሉ።
2.       ሐ. 13፡ 23-26፡ "ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀመዛሙርቱ ኣንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ/… there was leaning on Jesus’ bosom one of his disciples, whom Jesus loved…(King James Bible)" እነሆ ተወዳጁ እዚህ በግልፅ ተጠቀሰ። ስሙ ግን ኣሁንም ተዘልሏል። ያን ተወዳጅ ጴጥሮስ በዓይኑ ጠቅሶት የሚከዳው ማን እንደሁ ኢየሱስን እንዲጠይቅ ይጠይቀዋል።
3.       ዮሐ. 18፡15-16፡ ኢየሱስ ለእስር/ለጥያቄ ከተያዘ በሁዋላ፣ "ስሞዖን ጴጥሮስም፣ ሌላውም ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። …" ያ ደቀመዝሙር በሊቀካህናቱ ዘንድ የታወቀ ስለነበር፣ በእስር ቤቱ በር ላይ ጴጥሮስ ተከልክሎ ሲቀር እርሱ ገብቶ ይመለስና በረኛዋን ኣስፈቅዶ ጴጥሮስን ያስገባዋል። እዚህ ላይ፣ ይህ ደቀመዝሙር "ተወዳጁ" ተብሎ ባይጠራም፣ ስሙን ለመጥቀስ ያልተፈለገ በሚመስል መልኩ፣ "ሌላውም ደቀመዝሙር" ተብሎ ታልፏል። ይህም ሰው ያ ኢየሱስ የሚወደው ደቀመዝሙር እንደሆነ የጥናቱ ኣቅራቢዎች ያስባሉ።  
4.       ዮሐ. 19፡25-27፡ "… ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በኣጠገቡ ቆመው ባየ ጊዜ …" እናቱን ለዚያ ይወደው ለነበረው ደቀ መዝሙር ኣደራ ሰጠ፤ ደቀመዝሙሩም ይዟት ወደቤቱ ሄደ። እዚህ ቦታ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ መግደላዊት ማርያም እና ያ ተወዳጅ ደቀመዝሙር በኣንድ ጊዜ ኣንድ ላይ የነበሩ ሁለት የተለያዩ ሰዎች እንደሆኑ ተጠቅሰዋል። ግን፣ ይህንን ጥቅስ በትኩረት ያየ የሆነ ስህተት እንዳለበት ይረዳል። በዚህ ላይ ወደሁዋላ እንመለስበታለን።
5.       ዮሐ. 20፡ 1-11፡ "… መግደላዊት ማርያም … ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሉ ኣየች። እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ …" ኢየሱስ መነሳቱን ትነግራቸዋለች። ጴጥሮስና ተወዳጁ ደቀመዝሙር ሮጠው ወደመቃብሩ ይሄዳሉ፤ ኢየሱስንም ያጡታል። በእነዚህም ጥቅሶች ውስጥ ተወዳጁን ደቀመዝሙር በስም ላለመጥቀስ ጥንቃቄ የተደረገ ይመስላል። ተወዳጁ ደቀመዝሙርና መግደላዊት ማርያም በኣንድ ላይ እንደነበሩ ለሁለተኛ ጊዜ ተጠቅሷል። ይህ ሁኔታ የተገለፀባቸውን ጥቅሶ በትኩረት ብናይ ልክ እንደላይኛው (ተ.ቁ. 4) ሁሉ እዚህም የሆነ የተፋለሰ ነገር እንዳለ ይታያል። በዚህ ላይም ቆየት ብዬ እንመለስበታለሁ።
6.        ዮሐ. 21፡7 - ጴጥሮስና ሌሎች ደቀመዛሙርት ዓሳ በማጥመድ ላይ ሳሉ ኢየሱስ ይገለጥላቸዋል። ሌሎች ደቀመዛሙርት ማንነቱን ኣላወቁም። "…ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር ጴጥሮስን ጌታ እኮ ነው ኣለው።" በእዚህ ቦታ የተገለጠላቸውን ኢየሱስ ያ ተወዳጅ ከጴጥሮስም ቀድሞ ኣወቀው። ጴጥሮስ ራቁቱን ስለነበር (በሃፍረት ይሁን በድንጋጤ ኣይታወቅም፤) ተሸፋፍኖ ራሱን ወደሃይቁ ወረወረ።
7.       ዮሐ. 21፡20-23 - "ጴጥሮስ ዞር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀመዝሙር ሲከተለው ኣየ፡ እርሱም ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ - ጌታ ሆይ ኣሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው ያለው ነበር።" ጴጥሮስ የዚህን ደቀመዝሙር መከተል ያልወደደው ኣይነት፣ "ጌታ ሆይ፣ ይህስ እንዴት ይሆናል?" ብሎ ኢየሱስን ይጠይቀዋል። ኢየሱስም፣ ኣንተ ስለሱ ምን ኣገባህ? ዝም ብለህ እኔን ተከተለኝ፤ በሚል ድምፀት ይመልስለታል፡ "እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን ኣግዶህ? ኣንተ ተከተለኝ…" ይህ የኢየሱስ ሚስጥራዊ ኣገላለፅ ያ ተወዳጅ ደቀመዝሙር በስጋም ሕያው ሆኖ እንደሚኖር ሌሎች ደቀመዛሙርት እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል።
8.       ዮሐ. 21፡ 25 - ይህ ከላይ የተጠቀሰውን በዚያ ተወዳጅ ደቀመዝሙር ላይ የተደረገውን ውይይት የሚከተል ጥቅስ የወንጌሉ ፀሃፊ ያ ተወዳጅ እንደሆነ ይናገራል፡ "ስለ እነዚህም የመሰከረ፣ ይህንንም ጽፎ ያለ ይህ ደቀመዝሙር ነው፤ ምስክሩም እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።"
ይህ ተወዳጅ የዘብዲዮሱ ዮሐንስም፣ ይሁዳም፣ እንዳይደለ ግልፅ ማሳያዎች ኣሉ። እርሱ፣ ከኢየሱስ ጥምቀት እስከእርገቱ፣ ከዚያም በመንፈስ ተገልፆ ሌሎቹን ደቀመዛሙርት ባፅናናበት ጊዜ ሁሉ ከኢየሱስ ጋር ነበር። ይህ ሰው በስም ከተጠቀሱት ከኣስራሁለቱ ደቀመዛሙርት ከየትኛውም ጋር ኣንድ ተደርጎ የተጠቀሰበት ቦታ የለም። ሁሉም ቦታ፣ "ሌላው ደቀመዝሙር፣" ወይም "ክርስቶስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር፣" በሚል ብቻ ነው የተጠቀሰው። በቅድስናውና ለኢየሱስ ባለው ቅርበት ከጴጥሮስም ሆነ ከሌሎች ደቀመዛሙርት ሁሉ የላቀ እንደሆነ በግልፅ ይታያል። ማህበራዊ ግንኙነቱና ተፅዕኖውም ከፍተኛ መሆኑ በእስርቤቱ በር ላይ የሆነው ታሪክ ያሳረዳል። ታዲያ እንዲህ ያለ "የወንጌል ኮከብ" ሊባል የሚችል ደቀመዝሙር ስሙ መደበቁ ለምን ነው? ኢየሱስ ስም ኣልባ ኣስራሶስተኛ ደቀመዝሙር ነበረው? ከ12ቱ ደቀመዛሙርት እንደኣንዱ እንኳ ኣልተቆጠረም። ከሌሎች መብለጥ ያሳንሳል? ወይስ የሆነ ድብቅ ሚስጥር ወይም ሴራ ኣለ? ምናልባት ያ ተወዳጅ ሴት ስለሆነ ይሆን? ለኢየሱስ በኣካልም ጭምር የነበረው ቅርበት ልክ እንደልዩ ምልክት ከኣንዴም ሁለቴ መጠቀሱን (በእራት ላይ የኢየሱስን ደረት ተደግፎ/ተጠግቶ መቀመጡን) በዛሬ ዓይን ስናይ፣ ያ ሰው ሴት እንደሆነ ያስጠረጥረናል። ከሌሎች ደቀመዛሙርት እንደኣንዱ ያልተቆጠረውና ስሙ ያልተጠቀሰው በዚያ ምክንያት ይሆን? እና ሴት ከነበር ለምን በታሪኩ ውስጥ እንደወንድ ተገለፀ? እውን የሆነ ስህተት ኣልያም ሴራ ኣለ?   
የጥናቱ ባለቤቶች፣ ሆን ተብሎ የተሰራ ሴራ ኣለ፤ ነው እሚሉት። ወንጌላትንና ሌሎች የታሪክ መዛግብትን መሠረት ኣድርገው፣ በወንድ ፆታ የተገለፀው ይህ ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር በእርግጥ መግደላዊት ማርያም እንደሆነች ያስረዳሉ። እንዲያ ከሆነ ደግሞ፣ የዮሐንስ ወንጌል ደራሲ እርሷ ነች ማለት ነው። (ድሮ፣ በእጁ የፃፈ ብቻ ሳይሆን ትምህርቱን በቃል ያስተላለፈም እንደደራሲ ይቆጠር የነበር ቢሆንም፣ በወንጌሉ መጨረሻ ላይ ያለው መደምደሚያ ወንጌሉን ያ ተወዳጅ ጻፈው ነው እሚል። ያ የመደምደሚያ ዓረፍተነገር የሌላ ሰው ሊሆን ይችላል።) እንዲያ ከሆነ፣ ኣሁን የምናነበው የዮሐንስ ወንጌል ኦሪጅናሌው ኣይደለም ማለት ነው። ምክንያቱም መግደላዊት ማርይም ሴትም ወንድም መሆን ኣትችልም። የሆነ ሰው ወንጌሉን ኤዲት ኣድርጎታል (ኣርትዖት ሰርቶበታል) ማለት ነው። ግን ግን፣ ይህንን ሙጉት እንቀበለው ቢባል እንኳ ያንን ለውጥ ያደረገው ሰው ኣንዳንድ ቦታ የማርያምን ስም ሲያወጣና ፆታዋን ሲቀይር፣ በሌላ ቦታ ለምን እንዳለ ተወው? በተጨማሪም፣ መግደላዊት ማርያም እና ያ ተወዳጅ በኣንድ ቦታ በኣንድ ላይ ተገኝተው የነበር ሁለት ሰዎች እንዴት ሊሆኑ ቻሉ? ለነዚህ ጥያቄዎችም መልስ ኣላቸው የዚህ ጥናት ባለቤቶች። በተለይ መግደላዊት ማርያምና ያ የኢየሱስ ተወዳጅ እንደሁለት ሰው የቀረቡባቸው ቦታዎችን ወንጌሉ ተቀይሯል ለሚለው ሙጉታቸው እንደ ግልፅ ማስረጃ ነው እሚያቀርቡት። ምክንያቱም ቢያንስ በነዚህ ሁለት ቦታዎች ያልተገቡ ለውጦች እንደተደረጉ የሚያሳዩ የማያከራክሩ የኣተራረክና የመዋቅር ስህተቶች ኣሉ። እኚህ ሰዎች የሚሉት እውነት ከሆነ፣ የወንጌል ምሁራንም ሆነ ቤተክርስቲያናት ሊመልሱት የሚገባቸው ታላቅ ጥያቄ ይደነቀርባቸዋል ማለት ነው። 

በእኔ ሚዛን የነዚህ ሰዎች ማስረጃ ኣሳማኝ ነው። ያንን ያመነ ሰው ደግሞ፣ መግደላዊት ማርያም የትኛውም ደቀመዝሙር ሊስተካከለው ከሚችለው በላይ የከበረ ደረጃ እንደነበራት ያምናል። እነዚህ ማስረጃዎች እናንተንም ያሳምኑ እንደሁ ኣይታችሁ ትፈርዱ ዘንድ፣ ወይም የመልስ መከራከሪያ (counter argument) ታቀርቡ ዘንድ፣ ማረጋገጫዎቹን በቀጣዩ ጦማሬ ኣስነብባችሁዋለሁ። የለም ማስረጃውን ባይናችን ማየትና የራሳችንን ጥናት ማድረግ ኣለብን ካላችሁ፡ ይህ ፅሁፍ የተመሠረተበት የጥናት ወረቀት እነሆ፡ R.K. Jusino, 1998 Mary Magdalene: Author of the Fourth Gospel?

Wednesday, November 11, 2015

የመግደላዊት ማርያም ወንጌል ገፅ 8

መግደላዊት ማርያም ሴተኛ ኣዳሪ ኣልነበረችም!
የስህተቱ መጀመሪያ ጳጳስ ግሪጎሪ (Pope Gregory) ናቸው ኣሉ። እኝህን ካህን ያምታታቸው ደግሞ ሰባት የሚሆኑ ማርያሞች በወንጌል ውስጥ መጠቀሳቸው ነው። በእርሳቸው የ591ዓ.ም ስብከት ምክንያት ቅድስት መግደላዊት ማርያም የተሳሳተ ማንነት ሰለባ ተደረገች። በክርስትና የጠዋት ታሪክ ውስጥ የሴቶችን የመሪነት ሚና ለማኮሰስ ይደረግ ከነበረው ጥረት ጋር ተዳምሮ ይህ ስብከት እንደእውነት (በካቶሊኩም፣ በኦርቶዶክሱም፣ በፕሮቴስታንቱም) ቤተክርስቲያናት ተስተጋባ። ክብር ጎደፈ፤ ታሪክም ተፋለሰ። እንጂማ፣ በወንጌል ውስጥ ኣንድም ቦታ መግደላዊት ማርያም ሴተኛ ኣዳሪ ነበረች የሚል ቃል የለም። ስህተቱንም እውነቱንም ጥቂት ጥቅሶችን እየጠቀስን እንይ፡
በወንጌል ውስጥ መግደላዊት ማርያምን ቀድሞ የሚያስተዋውቀን ሉቃስ ነው (ሉቃ. 8፡ 1-3)። ይህ ምዕራፍ ሉቃስ ኢየሱስን በሽቱ ስለቀባች ኣንዲት ሃጢኣተኛ ሴት ከተረከ በሁዋላ የሚከተል ነው። የጠቀስናቸው ካህን መግደላዊት ማርያምን ያምታቱት ከዚህች ባለሽቱ ሴት ጋር ነው። እንዲህ ብለው፡
”ሉቃስ ሃጢኣተኛ የሚላት ያች ሴት፣ ዮሐንስ ደግሞ ማርያም የሚላት፣ እሷ ሰባት ኣጋንንት የወጡባት ሴት እንደሆነች እናምናለን። እኚህ ሰባቱ ኣጋንንት የሚወክሉት ርክሰት እምንላቸውን ነገሮች ሁሉ ካልሆነ ሌላ ምንን ሊሆን ይችላል? … ወንድሞች ሆይ፣ ያች ሴት ከዚያ ቀድም ያንን ሽቱ በሃጢኣት ስራዋ ጊዜ ኣካሏን ለመቀባት ትጠቀምበት ነበር።”
ይህንን ከዬት ኣመጡት ኣባው? ወንጌሉን በትኩረት ስናይ ሉቃስ ቀድሞ የጠቀሳት ሃጢኣተኛ ሴት መግደላዊት ማርያም እንዳይደለች ግልፅ ይሆናል። ሉቃስ በምዕራፍ 7 መጨረሻ ግድም ስለዚች ሴት ከተረከ በሁዋላ በምዕራፍ 8 መጀመሪያ ላይ መግደላዊት ማርያምን እንደኣዲስ ያስተዋውቃታል፡ ”… ከደዌ ተፈውሰው የነበሩ ኣንዳንድ ሴቶች፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም፣ …” (ሉቃ. 8፡2) ወንጌላዊው መግደላዊት ማርያምን ከጥቂት ዓረፍተነገሮች ቀድሞ ካነሳት ስሟ ካልተጠቀሰው ሴት ጋር ኣለማያያዙና መግደላዊት ማርያምን እንደኣዲስ ማስተዋወቁ እርሷ ከዚያች ሴት ጋር ኣንድ እንዳይደለች ኣያሳይም? ጳጳሱን ካምታቱኣቸው ነገሮች ኣንዱ ኢየሱስን በሽቱ ስለቀቡ ሴቶች የተነገረው ተረክ መብዛቱ ይሆን ይሆናል፡
1.       ከላይ ያየነው (ሉቃስ 7፡ 36-50)፡ ቦታው ኣልተጠቀሰም (በገሊላ)፣ ቤቱ የለምፃሙ የሲሞን፣ ባለሽቱዋ ሴት - ስሟ ያልተጠቀሰ፤
2.       ማቴ. 26፡ 6-12፡ ቦታው በቢታኒያ፣ ቤቱ የለምፃሙ የሲሞን፣ ባለሽቱዋ ሴት - ስሟ ያልተጠቀሰ፤
3.       ማር. 14፡ 3-9፡ ቦታው በቢታኒያ፣ ቤቱ የለምፃሙ የሲሞን፣ ባለሽቱዋ ሴት - ስሟ ያልተጠቀሰ፤
4.       ዮሐ. 12፡ 1-8፡ ቦታው በቢታኒያ፣ ቤቱ የኢየሱስ ወዳጆች የነበሩት የኣልዓዛር፣ የማርያም፣ እና የማርታ። የባለሽቱዋ ሴት ስም፣ ማርያም (ይህችኛዋ የቢታኒያ ማርያምም መግደላዊት ማርያም ኣይደለችም - ዮሐ፡ 11፡ 1-4)።
5.       በሁሉም ወንጌላት ውስጥ የኢየሱስን መቃብር የወረደ ኣካል በሽቱ ለማበስ ከሄዱ ሴቶች ውስጥ መግደላዊት ማርያም በቀዳሚነት ተጠቅሳለች።
እንግዲህ መግደላዊት ማርያም ኢየሱስን በሽቱ ከመቀባት ጋር ተያይዞ በግልፅ የተጠቀሰችሁ ኢየሱስ ከተሰቀለ በሁዋላ ብቻ ነው። ያኔ ደግሞ በኣካል ኣላገኘችውም፣ ኣልቀባችውምም። ያ እርሷን እግሩን በሽቶ ከቀባችዪቱ ሴት ጋር ኣንድ ኣድርጎ ለማንበብ ምን መሠረት ይሰጣል?
በኣንፃሩ፣ ወንጌላት ሁሉ መግደላዊት ማሪያምን እጅግ በከበረ ኣገላለፅ ያነሱኣታል፡
1.       መግደላዊት ማርያምና ሌሎች ሴቶች ክርስቶስን በየሄደበት ሁሉ ይከተሉትና በገንዘባቸውም ያገለግሉት ነበር። (ሉቃ 8፡2)
2.       ወንዶች ደቀመዛሙርት ሁሉ ሲሸሹ (ማቴ. 26፡56) መግደላዊት ማርያም ከሌሎች ሴቶች ጋር በኢየሱስ የስቃይና የስቅላት ሰዓት ኣብራው ነበረች። (ማቴ. 27፡56፣ ማር. 15፡40፣ ሉቃ. 23፡ 55፣ ዮሐ. 19፡25)
3.       በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ብቻዋን (በሌሎች ወንጌላት ከሌሎች ሴቶች ጋር፣) የኢየሱስን ባዶ መቃብር ለማግኘት ቀዳሚዋ ነች። (ማቴ. 28፡10፣ ሉቃ. 24፡10፣ ዮሐ. 20፡2)
4.       በዮሐንስና በማርቆስ ወንጌላት ውስጥ ብቻዋን (በሌሎች ውስጥ ከሌሎች ሴቶች ጋር) የኢየሱስን የተነሳ ኣካል ለማየት ቀዳሚዋ ናት። (ማቴ. 28፡29፣ ማር. 16፡9፣ ዮሐ. 20፡11)
5.       የክርስቶስን ትንሳዔ ለሌሎች ታበስር ዘንድ ተልዕኮ የተሰጣት ብቸኛዋ ሴት ናት። (ዮሐ. 20፡15)
6.       በወንጌል ውስጥ የሴቶች ስም በተነሳ ቁጥር በኣብሳኛው ቀድሞ የሚጠቀሰው የእርሷ ስም ነው። ይህ ከሌሎች ሴቶች ሁሉ ይልቅ ያላትን የከበረ ደረጃ ኣያመለክትም?
እንግዲህ መግደላዊት ማርያም ወንጌል ይህንን ያህል ክብር የሚሰጣት ክርስትና ግን የሚገባትን ክብር የነፈጋት ቅድስት ሴት ነች። እርሷ ሴተኛ ኣዳሪ እንደነበረች የሚያመለክት ምንም ማስረጃ በወንጌል ውስጥ የለም። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እንዲያ ትታይ ዘንድ ምክንያት ለሆኑት ለጳጳስ ግሪጎሪ፣ ”ማነው ምንትስ?” የሚለውን የፀጋዬ ገ/መድህንን ግጥም ጋብዘን ለዛሬ በዚህ እናብቃ። በሚቀጥለው ጦማሬ፣ ”እውን መግደላዊት ማሪያም የኢየሱስ ሚስት ነችን?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እሞክራለሁ።

እነሆ የመግደላዊት ማርያም ወንጌል ገፅ 8


Saturday, November 7, 2015

የመግደላዊት ማሪያም ወንጌል - ገፅ 7

ከ30 የማያንሱ ወንጌሎች ነበሩ ኣሉ (ታሪክንም እንደተረት “ኣሉ“ ብለው ቢያወሩት ሳያምርበት ይቀራል?) በ4ኛው ምዕተ-ዓመት በኒቂያ የተሰባሰቡ ካህናት ዛሬ “ኣዲስ ኪዳን“ በሚል እምናውቃቸውን ኣራቱን ወንጌላትና መልዕክቶች መርጠው፣ “የኢየሱስን ትምህርት የሚወክሉቱ እኚህ ናቸው!“ ብለው ወሰኑ። ያኔ ክርስትና ዛሬ በምናውቀው መልክ ተበጀ። ያ ጉባዔ ባይኖር ኖሮስ? ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ኣንዱ ይህ ነው፦ ኣሁን ወደኣማርኛ መልሼ ላጋራችሁ የጀመርኩት ወንጌል ከቅዱሳን ኣናቅፅት እንደኣንዱ ተቆጥሮ ይሰበክ፣ ይመለክ ነበር። በተጨማሪም፦ የዓለም ታሪክ፣ የዕውቀት ታሪክ ልዩ ይሆን ነበር። ሴትነትም፣ ፆታዊ ፍቅርም ይበልጥ ይከበር ነበር። በእርግጥ የሆነው ግን ይህ ነው፦ ከኒቂያ ጉባዔ በሁዋለ የተመረጡት ወንጌላት በኣንድ መድበል ተጠረዙ። የቀሩት ተወገዙ፣ ተገነዙ። እናም፣ ያልተመረጡቱ ወንጌላት በኣብዛኛው ሲጠፉ ጥቂቶቹ በሌሎች መዛግብት ውስጥ በእግረ-መንገድ መልክ ተጠቅሰው በስም ብቻ ከመቃብር በላይ ቆዩ። ከ2000 ዓመታት የመቃብር ህይወት በሁዋላ፣ በባለፈው ምዕተ ዓመት ተዘንግተው ከነበሩ ወንጌላት ውስጥ የጥቂቶቹ ቅጂዎች በየኣጋጣሚው ተገኝተው ዳግመ-ትንሳዔን ተቀዳጁ። ከነዚህ ውስጥ እ.ኤ.ኣ በ1947ዓ.ም የተገኙት “የቀይ ባህር ጥቅልሎች“ እና “የናግ ሃማዲ ላይብራሪ“ በመባል የሚታወቁቱ ጥንታዊ መዛግብት የክርስትና ታሪክ በዓዲስ ዓይን ይታይ ዘንድ ትልቁን ኣስተዋፅዖ ኣድርገዋል።  እርግጥ ነው፣ ይህ ክርስትናን ኣልቀየረውም፤ ኣይቀይረውምም። ምክንያቱም ክርስትና መፅሃፍ ቅዱስ ብቻ ኣይደለም። ታሪክም ጭምር ነው። ባህልም ጭምር ነው። ተቋምም ጭምር ነው። ስልጣንም፣ ሃብትም ጭምር ነው። ይበልጥ ብልጣብልጥ ለሆኑቱ፣ እማይነጥፍ የጥገት ላም። እንደቆ ቀለም፣ መለያም መኩሪያም ጭምር ነው ክርስትና። እስከነጥቅሱ፣ “ነብር ዥጉርጉርነቱን ኣይቀይርም!“ ነው መልሱ። ቅዱሳን ቃላቱ የዚህ ውስብስብ ሥርዓት ኣንድ ገፅታ ብቻ ናቸው። ቃላት ከምድር ቀርቶ ከሰማይ ቢወርዱም ክርስትናን ኣይቀም። 


ይህ የመግደላዊት ማሪያም ወንጌል በ1896ዓ.ም. ኣከባቢ በግብፅ ውስጥ በኮፕቲክ ቋንቋ ተፅፎ ከተገኘ ፓፒረስ የተወሰደ ነው። ወንጌሉ ተሟልቶ ባይገኝም ስለክርስትና የጠዋት ታሪክና ስለመግደላዊት ማሪያም ኣዳዲስ ነገሮችን እናውቅ ዘንደ በቂ መልዕክቶችን ይዟል። ለመሆኑ፣ መግደላዊት ማሪያም ማን ናት? መግቢያዬን ላለማርዘም ይህንን ጥያቄ በሚቀጥሉት ጦማሮቼ ብመልሰውስ? ባጭሩ ግን ይህንን ልበል፦ ይህችን እንስት ኣዲስ ኪዳን በሽርፍርፉ ጠቅሷታል። ክርስትና ታሪክ ኣዛብቶ ስሏታል። በዚህ ወንጌሏ ውስጥ እርሷ እኛ ከሰጠናት ስም ይበልጥ ቅድስት፣ ከፃፍንላት ታሪኳም በላይ ንፅህት ነች። 

በከፊል የተገኘው የመግደላዊት ማሪያም ወንጌል የተለያዩ የእንግልዝኛ ትርጉሞች ኣሉት። ከነዚህ ውስጥ እኔ ያነፃፀርኩት ሶስቱን ብቻ ነው። ይህ የኔ ትርጉም በኣመዛኙ የተመሠረተው በJean-Yves Leloup (1997) የእንግልዝኛ ትርጉም ላይ ቢሆንም ኣንዳንድ ዓረፍተነገሮችን ለራሴም ለኣንባቢዎቼም ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ ሌሎችን ትርጉሞች ተጠቅሜኣለሁ። ከዛሬ ጀምሮ የወንጌሉን የኣማርኛ ትርጉም የማሰላሰያ ቀናትን እየዘለልኩ ገፅ በገፅ ኣቀርብላችሁዋለሁ። እንደኣስፈላጊነቱ ስለተጠቀምኩባቸው ቃላትና ሃረጎች ማብራሪያ እሰጣለሁ። ይህ የመጀመሪያው ገፅ (ገፅ 7) ነው። መድረኩ ለጥያቄም ለኣስተያየትም ክፍት ነው።

Thursday, November 5, 2015

The Holiest Sinner

A Quote from Catch Your Thunder: Rendezvous With the End

ፍፁም ቅዱሷ ሃጥዓተኛ

ከሜሮን ጋር ሻይ ቡና እያልን ስለመንፈሳዊነት (mysticism) ስናወጋ መግደላዊት ማሪያም ተነሳች። “ካች ዩር ተንደር” በህትመት ሂደት ላይ ነበር ያኔ። ከረቂቁ ላይ ይህችን ቅድስት የሚያነሳን ኣንድ ምዕራፍ ኣነበብኩላት። (ከታች በስዕሉ ላይ የጠቀስኩትን።) በሌላ ጊዜ ስንገናኝ ሜሮን “የመግደላዊት ማሪያም ወንጌል“ (በእንግሊዝኛ) የሚለውን የJean-Yves Leloup መፅሃፍ ኣዋሰችኝ። እንዲህ በቀላሉ ኣገኘዋለሁ ብዬ ያላሰብኩት መፅሃፍ ነበር። “ተባረኪ ኣቦ!” ብዬ ተቀበልኳት። መፅሃፉን ሳነብበው ስለመግደላዊት ማሪያምም ሆነ ስለክርስትና ኣላውቃቸው የነበሩ ብዙ ነገሮችን ኣገኘሁበት። ይህ ክርስትና ብዙዎቻችን ከምናስበው ውጪ ብዙ ድብቅ ታሪኮች እንዳሉት እና ኢየሱስ ያስተማረው ክርስትና እኛ ጋ ሙሉ በሙሉ እንዳልደረሰ ከሚያሳዩ መፅሃፍት ኣንዱ መሆኑ ነው። “ፍፁም ቅዱሷ ሃጥዓተኛ“ የሚለው ሃሳብ ይህንን መፅሃፍ ከማንበቤ በፊት የነበረኝ ዕይታ ነበር። ኣሁን ግን ሃጥዓተኛነትን ከመግደላዊት ማሪያም ጋር ኣገናኝቶ ማሰብም ራሱ “ይቅር በለኝ!“ የሚያስብል እንደሁ ተረድቻለሁ። (እዚህ በተለይ በክርስትና ተረክ ተፅዕኖ የተበጀውን የቀድሞ ዕይታዬን ለማሳየት ብቻ ተጠቀምኩበት።) በሚቀጥሉት ጦማሮቼ ከጠቀስኩላችሁ መፅሃፍ ያገኘሁዋቸውን ኣንዳንድ ነገሮች ወደኣማርኛ መልሼ ላጋራችሁ ተዘጋጅቻለሁና ተጋበዙ፣ ተገባበዙልኝ። እተረጉመው ዘንድ የስህን (ዶ/ር) ቀና ግፊት ጉልበት ሆኖኛልና ለሜሮንና ለእርሷ ምስጋና!

Sunday, November 1, 2015

ድህነት ታሪክ የለውም

ድህነት ሕይወት የለውም። ድህነት ታሪክ የለውም። ቅርስም ውርስም ኣይደለም ድህነት። ጥላህ እንጂ ማተብህ ኣይደለም ድህነት። ስላጣህ ደሃ ነኝ፣ ትንሽ ነኝ ኣትበል። በሙሉ ልብ በብርሃኑ ላይ ከቆምክ ድህነት ኣብሮህ ኣይኖርምና። ለድህነት ሕይወትም ልብም እምትሰጠው ኣንተ ነህ። ለእርሱ የገበርከውን ሕይወት ያህል ኣንተ ሕይወት ታጣለህ። ራስህ ሞተህ ድህነት እንዲኖር እምትፈቅድ ኣንተ ማነህ? በፈጠረህ፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ ኣትበለኝ!

Wednesday, October 28, 2015

AN ANGEL KILLER/መልዓክ ገዳይ!

Do you sometimes feel like you want to cry or weep or feel totally uncomfortable for apparently no reason? Frowning, someone somewhere might have killed an angel. This then is opposite to the contagiousness of joy. A little smile, please.

አንዳንዴ ከሜዳ ተነስቶ ብስጭት ብስጭት፣ ጭንቅ ጭንቅ፣ ይልሻል? ወይም ጩሂ ጩሂ፣ ኣልቅሺ ኣልቅሺ ይልሻል? ወይም እንዲሁ እረፍትና ምቾት ሳይሰማሽ ይውላል? እንግዲያው፣ የሆነ ቦታ የሆነ ሰው ፊቱን ኣጉል ኣጨፍግጎ ያንድ መልዓክ ሞት ምክንያት ሆኖ ይሆናል (አርባ ጠብታዎችሕብረ-ነፍስለምታውቋት፣ ይህ የዚያ ተቃራኒ መሆኑ ነው፡፡) ያለምክንያት የሚሆን ነገር የት ኣለ! ትንሽ ፈገግታ፣ እባክህ!