የዮሐንስ ወንጌልም
የመግደላዊት ማርያም ወንጌል ነው?
ይህ እጅግ ኣስደንቆኛል።
እናንተንም እንደሚያስደንቃችሁ እርግጠኛ ነኝ። ባለፈው፣ መግደላዊት ማርያም የኢየሱስ ፍቅረኛ በመሆን ኣለመሆኗ ጥያቄ ላይ እንደምፅፍ
ቃል ገብቼ ነበር። ይህ ኣሁን ያገኘሁት ምስጥር ከዚያም ይልቅ ኣስገራሚ ሆኖ ስላገኘሁት ነው ያንን ለግዜው ያቆየሁት። እኔ እምብዛም
የመጽሐፍቅዱስ ደጋሚ ኣይደለሁም። ይህንን ያህል ያፈጠጠ ጉዳይ ዓይኔ ሥር ተደብቆ ሲያልፈኝ መክረሙ ግን “ኣጀብ!” ኣስብሎኛል።
ቢያንስ ሲጠይቁ ኣለመስማቴ!
ሰሞኑን ባጋጣሚ
የገባሁበት የመግደላዊት ማርያም ጉዳይ ኣስገራሚ የኣድቬንቼር ዓለም ሆኖ ኣገኘሁት። የትኛውንም የዕውቀት ዘርፍ እጣታችን ጫፍ ላይ
ላመጣው ዘመን ምስጋን ይግባው! ባለሞያ ኣይደለንም ብለን ከፍለጋ ሳንገታ በመረጥነው የዕውቀት ዘርፍ የቻልነውን ያህል እንጓዝ ዘንድ
ጎዳናውን ክፍት ኣድርጎልናል ዘመኑ። እሸት የደረሰለት ያገሬ ገበሬ፣ “እነሆ ቅመሱልኝ!“ እንደሚል፣ እኔም ኣጭር ጉዞዬ ያስጠረጠረችኝን
እሸት “እነሆ“ ለማለት ወግ ሆኖ ኣገኘሁት። መቼም ፍለጋ የየራስ ነው። ይህ የዘመኑ ዕድል ግን የሁላችንም ነው። “ቄሱም ዝም፤
መፅሃፉም ዝም!“ እምንልበት ዘመን ካበቃ ሰነበተ። ቄሱ ከተለጎሙ መጽሐፉን እምናናግርባቸው እልፍ ቁልፎች በየጣሪያችን፣ በየጣታችን
ሥር ናቸው። ኣማኞች እንደሚሉት ፍርድ የእግዚኣብሔር ነው። እግዚኣብሔር ደግሞ ሚዛኑን በየልባችን ኣኑሯል። የቱም ነፍስ በሌላው
ነፍስ ተጠያቂ ኣይሆን ዘንድ የየግል ፍለጋ የዘመኑ ግዴታ ሆኗል። ለኔ፣ ይህ የፍለጋዬ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ ኣይደለም። በመግደላዊት
ማርያም ዙርያ ያለው ታሪክ እጅግ ኣጓጊና መሳጭ ነው። ሃሰሳዬ ይቀጥላል። በየራሳችሁ መንገድ በፍለጋው መጀመሪያም መሃልም ሆነ መጨረሻ
ላይ ያላችሁ፣ ምናልባት በዚህ መንገድ ኣላለፋችሁ እንደሁ፣ እነሆ የተደነቅሁበት የሰሞኑ ግኝት፡
“የዮሐንስ ወንጌል
ደራሲ መግደላዊት ማርያም ናት፤“ ይላል ከድረገፅ ያገኘሁት ኣንድ የጥናት ወረቀት። “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?“ ኣልኩኝ ይህንን
ርዕስ እንዳየሁ። ፀሃፊው ማስረጃውን በኣመዛኙ ከዚያው ከዮሐንስ ወንጌል መምዘዙ የመደነቄ መጀመሪያ ሆነ።
የዮሐንስ ወንጌል
ከሌሎች ወንጌላት በብዙ መልኩ የተለየ ነው። ከሌሎች ወንጌላዊያን ይልቅ ለኢየሱስ ቅርብ የሆነና በመንፈሳዊ ዕይታውም ከፍተኛ ደረጃን
የተቀዳጀ ሰው እንደፃፈው ይታወቃል። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደሚስማሙበት የዚህ ወንጌል ደራሲ ኣይታወቅም። ቀድሞ፣ ደራሲው
ሐዋሪያው ዮሐንስ (የዘብዲዮስ ልጅ) እንደሆነ ይታሰብ ነበር። ለዚያ እምነት የተገኘው ማስረጃ፣ Irenaeus የተባሉ የሁለተኛው
ክፍለዘምን ጳጳስ የልጅነት ትዝታ ብቻ ሆኖ ተገኘ፡ “በልጅነቴ ጳጳስ Polycarp ነግረውኝ ነው፤“ ያሉት። ይህ እምነት እውነት
እንዳይደለ ብዙ ኣጥኚዎች ይስማማሉ። ከነዚህ ውስጥ የወንጌሉ ትክክለኛ ደራሲ በዚያው ወንጌል ውስጥ በተደጋጋሚ የተጠቀሰው ክርስቶስ
እጅግ ይወደው የነበር ደቀመዝሙር ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ወንጌሉ ራሱ ያንን ይመሰክራል። ያ ደግሞ ሐዋሪያው ዮሐንስ ኣይደለም።
ካስደነቁኝ ነገሮች
ኣንዱ እንግዲህ ይህ ነው። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ለክርስቶስ ከሌሎች ደቀመዛሙርት ሁሉ ይልቅ የቀረበ፤ ከኢየሱስ ጥምቀት ጀምሮ
ይከተለው የጀመረ፣ ነገር ግን ስሙ ሆን ተብሎ በሚመስል መልኩ ያልተጠቀሰ፣ ኣንድ ምስጥራዊ ደቀመዝሙር መኖሩ ነው። ይህ ደቀመዝሙር
ክርስቶስን ያን ያህልከ ይቀርበው ከነበር፣ ስሙ ኣለመጠቀሱ ለምን ይሆን? ትሉ ይሆናል። ያ የኔም ጥያቄ ነበር። መልሱ ከምር፣ “ወይ
ግሩም!” ኣስብሎኛል። ስለ መግደላዊት ማርያም ከማውራታችን በፊት፣ ይህ ደቀመዝሙር ከክርስቶስ ጋር ምን ያህል ይቀራረብ እንደነበር
ለማሳየት እርሱ የተጠቀሰባቸውን ኣናቅፅት ማየት ግድ ይለናል (ረዘም ያሉ ጥቅሶችን በትዕምርተ-ጥቅስ ቀንፌ ስለማሳጥራቸው ለተሟላ
መረጃ መፅሃፍቅዱሳችሁን መግለፅ ይኖርባችሁ ይሆናል)፡
1. ዮሐ 1፡ 35-40 - "…[መጥምቁ] ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ቆመው ነበር፣ ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ
- እነሆ የእግዚኣብሔር በግ ኣለ። ሁለቱ ደቀመዛሙርት ሰምተውት ኢየሱስን ተከተሉት። …" ምናልባትም እኚህ ኢየሱስን ኣውቀው
የተከተሉ የመጀመሪያ ደቀመዛሙርት ናቸው። ቀድመው መሲሁ እንደሚመጣ ኣውቀው ሲፈልጉት የነበር ይመስላል። በኢየሱስ ግብዣ ወደ እርሱ
ቤት ሄደው ኣብረውት ዋሉ። ከነዚህ ሁለት ደቀመዛሙርት ኣንዱ እንድርያስ እንደሆነ ዝቅ ብሎ ተጠቅሷል። የሌላው ማንነት ኣልተጠቀሰም።
በዚህ ጥቅስ ውስጥ ይህ ስሙ ያልተጠቀሰው ሰው ገና የኢየሱስ ደቀመዝሙር መሆኑ ነበርና፣ "ኢየሱስ የሚወደው ደቀመዝሙር"
ኣልተባለም። ቢሆንም፣ በሌሎች ቦታዎች ላይ "ኢየሱስ የሚወደው" የተባለው ይኸው ሰው እንደሆነ ኣንዳንድ የመፅሃፍቅዱስ
ኣጥኚዎች ያምናሉ።
2. ዮሐ. 13፡ 23-26፡ "ኢየሱስም
ይወደው የነበረ ከደቀመዛሙርቱ ኣንዱ በኢየሱስ
ደረት ላይ ተጠጋ/… there was leaning on Jesus’ bosom one of his disciples, whom
Jesus loved…(King James Bible)" እነሆ ተወዳጁ እዚህ በግልፅ ተጠቀሰ። ስሙ ግን ኣሁንም ተዘልሏል። ያን ተወዳጅ ጴጥሮስ በዓይኑ ጠቅሶት የሚከዳው
ማን እንደሁ ኢየሱስን እንዲጠይቅ ይጠይቀዋል።
3. ዮሐ. 18፡15-16፡ ኢየሱስ ለእስር/ለጥያቄ ከተያዘ በሁዋላ፣ "ስሞዖን ጴጥሮስም፣ ሌላውም ደቀ
መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። …" ያ ደቀመዝሙር በሊቀካህናቱ ዘንድ የታወቀ ስለነበር፣ በእስር ቤቱ በር ላይ ጴጥሮስ
ተከልክሎ ሲቀር እርሱ ገብቶ ይመለስና በረኛዋን ኣስፈቅዶ ጴጥሮስን ያስገባዋል። እዚህ ላይ፣ ይህ ደቀመዝሙር "ተወዳጁ"
ተብሎ ባይጠራም፣ ስሙን ለመጥቀስ ያልተፈለገ በሚመስል መልኩ፣ "ሌላውም ደቀመዝሙር" ተብሎ ታልፏል። ይህም ሰው
ያ ኢየሱስ የሚወደው ደቀመዝሙር እንደሆነ የጥናቱ ኣቅራቢዎች ያስባሉ።
4. ዮሐ. 19፡25-27፡ "…
ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በኣጠገቡ ቆመው ባየ ጊዜ …" እናቱን ለዚያ ይወደው ለነበረው
ደቀ መዝሙር ኣደራ ሰጠ፤ ደቀመዝሙሩም ይዟት ወደቤቱ ሄደ። እዚህ ቦታ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ መግደላዊት ማርያም እና ያ ተወዳጅ ደቀመዝሙር
በኣንድ ጊዜ ኣንድ ላይ የነበሩ ሁለት የተለያዩ ሰዎች እንደሆኑ ተጠቅሰዋል። ግን፣ ይህንን ጥቅስ በትኩረት ያየ የሆነ ስህተት እንዳለበት
ይረዳል። በዚህ ላይ ወደሁዋላ እንመለስበታለን።
5. ዮሐ. 20፡ 1-11፡ "… መግደላዊት ማርያም … ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሉ ኣየች። እየሮጠችም ወደ ስምዖን
ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ …" ኢየሱስ መነሳቱን ትነግራቸዋለች። ጴጥሮስና
ተወዳጁ ደቀመዝሙር ሮጠው ወደመቃብሩ ይሄዳሉ፤ ኢየሱስንም ያጡታል። በእነዚህም ጥቅሶች ውስጥ ተወዳጁን ደቀመዝሙር በስም ላለመጥቀስ
ጥንቃቄ የተደረገ ይመስላል። ተወዳጁ ደቀመዝሙርና መግደላዊት ማርያም በኣንድ ላይ እንደነበሩ ለሁለተኛ ጊዜ ተጠቅሷል። ይህ ሁኔታ
የተገለፀባቸውን ጥቅሶ በትኩረት ብናይ ልክ እንደላይኛው (ተ.ቁ. 4) ሁሉ እዚህም የሆነ የተፋለሰ ነገር እንዳለ ይታያል። በዚህ
ላይም ቆየት ብዬ እንመለስበታለሁ።
6. ዮሐ. 21፡7 - ጴጥሮስና ሌሎች ደቀመዛሙርት ዓሳ በማጥመድ
ላይ ሳሉ ኢየሱስ ይገለጥላቸዋል። ሌሎች ደቀመዛሙርት ማንነቱን ኣላወቁም። "…ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር
ጴጥሮስን ጌታ እኮ ነው ኣለው።" በእዚህ ቦታ የተገለጠላቸውን ኢየሱስ ያ ተወዳጅ ከጴጥሮስም ቀድሞ ኣወቀው። ጴጥሮስ ራቁቱን
ስለነበር (በሃፍረት ይሁን በድንጋጤ ኣይታወቅም፤) ተሸፋፍኖ ራሱን ወደሃይቁ ወረወረ።
7. ዮሐ. 21፡20-23 - "ጴጥሮስ ዞር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀመዝሙር ሲከተለው ኣየ፡
እርሱም ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ - ጌታ ሆይ ኣሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው ያለው ነበር።" ጴጥሮስ የዚህን
ደቀመዝሙር መከተል ያልወደደው ኣይነት፣ "ጌታ ሆይ፣ ይህስ እንዴት ይሆናል?" ብሎ ኢየሱስን ይጠይቀዋል። ኢየሱስም፣
ኣንተ ስለሱ ምን ኣገባህ? ዝም ብለህ እኔን ተከተለኝ፤ በሚል ድምፀት ይመልስለታል፡ "እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ
ምን ኣግዶህ? ኣንተ ተከተለኝ…" ይህ የኢየሱስ ሚስጥራዊ ኣገላለፅ ያ ተወዳጅ ደቀመዝሙር በስጋም ሕያው ሆኖ እንደሚኖር
ሌሎች ደቀመዛሙርት እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል።
8. ዮሐ. 21፡ 25 - ይህ ከላይ የተጠቀሰውን በዚያ ተወዳጅ ደቀመዝሙር ላይ የተደረገውን ውይይት የሚከተል ጥቅስ የወንጌሉ
ፀሃፊ ያ ተወዳጅ እንደሆነ ይናገራል፡ "ስለ እነዚህም የመሰከረ፣ ይህንንም ጽፎ ያለ ይህ ደቀመዝሙር ነው፤ ምስክሩም
እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።"
ይህ ተወዳጅ የዘብዲዮሱ ዮሐንስም፣
ይሁዳም፣ እንዳይደለ ግልፅ ማሳያዎች ኣሉ። እርሱ፣ ከኢየሱስ ጥምቀት እስከእርገቱ፣ ከዚያም በመንፈስ ተገልፆ ሌሎቹን ደቀመዛሙርት
ባፅናናበት ጊዜ ሁሉ ከኢየሱስ ጋር ነበር። ይህ ሰው በስም ከተጠቀሱት ከኣስራሁለቱ ደቀመዛሙርት ከየትኛውም ጋር ኣንድ ተደርጎ የተጠቀሰበት
ቦታ የለም። ሁሉም ቦታ፣ "ሌላው ደቀመዝሙር፣" ወይም "ክርስቶስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር፣"
በሚል ብቻ ነው የተጠቀሰው። በቅድስናውና ለኢየሱስ ባለው ቅርበት ከጴጥሮስም ሆነ ከሌሎች ደቀመዛሙርት ሁሉ የላቀ እንደሆነ በግልፅ
ይታያል። ማህበራዊ ግንኙነቱና ተፅዕኖውም ከፍተኛ መሆኑ በእስርቤቱ በር ላይ የሆነው ታሪክ ያሳረዳል። ታዲያ እንዲህ ያለ "የወንጌል
ኮከብ" ሊባል የሚችል ደቀመዝሙር ስሙ መደበቁ ለምን ነው? ኢየሱስ ስም ኣልባ ኣስራሶስተኛ ደቀመዝሙር ነበረው? ከ12ቱ
ደቀመዛሙርት እንደኣንዱ እንኳ ኣልተቆጠረም። ከሌሎች መብለጥ ያሳንሳል? ወይስ የሆነ ድብቅ ሚስጥር ወይም ሴራ ኣለ? ምናልባት ያ
ተወዳጅ ሴት ስለሆነ ይሆን? ለኢየሱስ በኣካልም ጭምር የነበረው ቅርበት ልክ እንደልዩ ምልክት ከኣንዴም ሁለቴ መጠቀሱን (በእራት
ላይ የኢየሱስን ደረት ተደግፎ/ተጠግቶ መቀመጡን) በዛሬ ዓይን ስናይ፣ ያ ሰው ሴት እንደሆነ ያስጠረጥረናል። ከሌሎች ደቀመዛሙርት
እንደኣንዱ ያልተቆጠረውና ስሙ ያልተጠቀሰው በዚያ ምክንያት ይሆን? እና ሴት ከነበር ለምን በታሪኩ ውስጥ እንደወንድ ተገለፀ? እውን
የሆነ ስህተት ኣልያም ሴራ ኣለ?
የጥናቱ ባለቤቶች፣ ሆን ተብሎ
የተሰራ ሴራ ኣለ፤ ነው እሚሉት። ወንጌላትንና ሌሎች የታሪክ መዛግብትን መሠረት ኣድርገው፣ በወንድ ፆታ የተገለፀው ይህ ኢየሱስ
ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር በእርግጥ መግደላዊት ማርያም እንደሆነች ያስረዳሉ። እንዲያ ከሆነ ደግሞ፣ የዮሐንስ ወንጌል ደራሲ እርሷ
ነች ማለት ነው። (ድሮ፣ በእጁ የፃፈ ብቻ ሳይሆን ትምህርቱን በቃል ያስተላለፈም እንደደራሲ ይቆጠር የነበር ቢሆንም፣ በወንጌሉ
መጨረሻ ላይ ያለው መደምደሚያ ወንጌሉን ያ ተወዳጅ ጻፈው ነው እሚል። ያ የመደምደሚያ ዓረፍተነገር የሌላ ሰው ሊሆን ይችላል።)
እንዲያ ከሆነ፣ ኣሁን የምናነበው የዮሐንስ ወንጌል ኦሪጅናሌው ኣይደለም ማለት ነው። ምክንያቱም መግደላዊት ማርይም ሴትም ወንድም
መሆን ኣትችልም። የሆነ ሰው ወንጌሉን ኤዲት ኣድርጎታል (ኣርትዖት ሰርቶበታል) ማለት ነው። ግን ግን፣ ይህንን ሙጉት እንቀበለው
ቢባል እንኳ ያንን ለውጥ ያደረገው ሰው ኣንዳንድ ቦታ የማርያምን ስም ሲያወጣና ፆታዋን ሲቀይር፣ በሌላ ቦታ ለምን እንዳለ ተወው?
በተጨማሪም፣ መግደላዊት ማርያም እና ያ ተወዳጅ በኣንድ ቦታ በኣንድ ላይ ተገኝተው የነበር ሁለት ሰዎች እንዴት ሊሆኑ ቻሉ? ለነዚህ
ጥያቄዎችም መልስ ኣላቸው የዚህ ጥናት ባለቤቶች። በተለይ መግደላዊት ማርያምና ያ የኢየሱስ ተወዳጅ እንደሁለት ሰው የቀረቡባቸው
ቦታዎችን ወንጌሉ ተቀይሯል ለሚለው ሙጉታቸው እንደ ግልፅ ማስረጃ ነው እሚያቀርቡት። ምክንያቱም ቢያንስ በነዚህ ሁለት ቦታዎች ያልተገቡ
ለውጦች እንደተደረጉ የሚያሳዩ የማያከራክሩ የኣተራረክና የመዋቅር ስህተቶች ኣሉ። እኚህ ሰዎች የሚሉት እውነት ከሆነ፣ የወንጌል
ምሁራንም ሆነ ቤተክርስቲያናት ሊመልሱት የሚገባቸው ታላቅ ጥያቄ ይደነቀርባቸዋል ማለት ነው።
በእኔ ሚዛን የነዚህ ሰዎች
ማስረጃ ኣሳማኝ ነው። ያንን ያመነ ሰው ደግሞ፣ መግደላዊት ማርያም የትኛውም ደቀመዝሙር ሊስተካከለው ከሚችለው በላይ የከበረ ደረጃ
እንደነበራት ያምናል። እነዚህ ማስረጃዎች እናንተንም ያሳምኑ እንደሁ ኣይታችሁ ትፈርዱ ዘንድ፣ ወይም የመልስ መከራከሪያ (counter
argument) ታቀርቡ ዘንድ፣ ማረጋገጫዎቹን በቀጣዩ ጦማሬ ኣስነብባችሁዋለሁ። የለም ማስረጃውን ባይናችን
ማየትና የራሳችንን ጥናት ማድረግ ኣለብን ካላችሁ፡ ይህ ፅሁፍ የተመሠረተበት የጥናት ወረቀት እነሆ፡ R.K. Jusino, 1998፡ Mary Magdalene: Author of the Fourth Gospel?
No comments:
Post a Comment