Saturday, November 7, 2015

የመግደላዊት ማሪያም ወንጌል - ገፅ 7

ከ30 የማያንሱ ወንጌሎች ነበሩ ኣሉ (ታሪክንም እንደተረት “ኣሉ“ ብለው ቢያወሩት ሳያምርበት ይቀራል?) በ4ኛው ምዕተ-ዓመት በኒቂያ የተሰባሰቡ ካህናት ዛሬ “ኣዲስ ኪዳን“ በሚል እምናውቃቸውን ኣራቱን ወንጌላትና መልዕክቶች መርጠው፣ “የኢየሱስን ትምህርት የሚወክሉቱ እኚህ ናቸው!“ ብለው ወሰኑ። ያኔ ክርስትና ዛሬ በምናውቀው መልክ ተበጀ። ያ ጉባዔ ባይኖር ኖሮስ? ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ኣንዱ ይህ ነው፦ ኣሁን ወደኣማርኛ መልሼ ላጋራችሁ የጀመርኩት ወንጌል ከቅዱሳን ኣናቅፅት እንደኣንዱ ተቆጥሮ ይሰበክ፣ ይመለክ ነበር። በተጨማሪም፦ የዓለም ታሪክ፣ የዕውቀት ታሪክ ልዩ ይሆን ነበር። ሴትነትም፣ ፆታዊ ፍቅርም ይበልጥ ይከበር ነበር። በእርግጥ የሆነው ግን ይህ ነው፦ ከኒቂያ ጉባዔ በሁዋለ የተመረጡት ወንጌላት በኣንድ መድበል ተጠረዙ። የቀሩት ተወገዙ፣ ተገነዙ። እናም፣ ያልተመረጡቱ ወንጌላት በኣብዛኛው ሲጠፉ ጥቂቶቹ በሌሎች መዛግብት ውስጥ በእግረ-መንገድ መልክ ተጠቅሰው በስም ብቻ ከመቃብር በላይ ቆዩ። ከ2000 ዓመታት የመቃብር ህይወት በሁዋላ፣ በባለፈው ምዕተ ዓመት ተዘንግተው ከነበሩ ወንጌላት ውስጥ የጥቂቶቹ ቅጂዎች በየኣጋጣሚው ተገኝተው ዳግመ-ትንሳዔን ተቀዳጁ። ከነዚህ ውስጥ እ.ኤ.ኣ በ1947ዓ.ም የተገኙት “የቀይ ባህር ጥቅልሎች“ እና “የናግ ሃማዲ ላይብራሪ“ በመባል የሚታወቁቱ ጥንታዊ መዛግብት የክርስትና ታሪክ በዓዲስ ዓይን ይታይ ዘንድ ትልቁን ኣስተዋፅዖ ኣድርገዋል።  እርግጥ ነው፣ ይህ ክርስትናን ኣልቀየረውም፤ ኣይቀይረውምም። ምክንያቱም ክርስትና መፅሃፍ ቅዱስ ብቻ ኣይደለም። ታሪክም ጭምር ነው። ባህልም ጭምር ነው። ተቋምም ጭምር ነው። ስልጣንም፣ ሃብትም ጭምር ነው። ይበልጥ ብልጣብልጥ ለሆኑቱ፣ እማይነጥፍ የጥገት ላም። እንደቆ ቀለም፣ መለያም መኩሪያም ጭምር ነው ክርስትና። እስከነጥቅሱ፣ “ነብር ዥጉርጉርነቱን ኣይቀይርም!“ ነው መልሱ። ቅዱሳን ቃላቱ የዚህ ውስብስብ ሥርዓት ኣንድ ገፅታ ብቻ ናቸው። ቃላት ከምድር ቀርቶ ከሰማይ ቢወርዱም ክርስትናን ኣይቀም። 


ይህ የመግደላዊት ማሪያም ወንጌል በ1896ዓ.ም. ኣከባቢ በግብፅ ውስጥ በኮፕቲክ ቋንቋ ተፅፎ ከተገኘ ፓፒረስ የተወሰደ ነው። ወንጌሉ ተሟልቶ ባይገኝም ስለክርስትና የጠዋት ታሪክና ስለመግደላዊት ማሪያም ኣዳዲስ ነገሮችን እናውቅ ዘንደ በቂ መልዕክቶችን ይዟል። ለመሆኑ፣ መግደላዊት ማሪያም ማን ናት? መግቢያዬን ላለማርዘም ይህንን ጥያቄ በሚቀጥሉት ጦማሮቼ ብመልሰውስ? ባጭሩ ግን ይህንን ልበል፦ ይህችን እንስት ኣዲስ ኪዳን በሽርፍርፉ ጠቅሷታል። ክርስትና ታሪክ ኣዛብቶ ስሏታል። በዚህ ወንጌሏ ውስጥ እርሷ እኛ ከሰጠናት ስም ይበልጥ ቅድስት፣ ከፃፍንላት ታሪኳም በላይ ንፅህት ነች። 

በከፊል የተገኘው የመግደላዊት ማሪያም ወንጌል የተለያዩ የእንግልዝኛ ትርጉሞች ኣሉት። ከነዚህ ውስጥ እኔ ያነፃፀርኩት ሶስቱን ብቻ ነው። ይህ የኔ ትርጉም በኣመዛኙ የተመሠረተው በJean-Yves Leloup (1997) የእንግልዝኛ ትርጉም ላይ ቢሆንም ኣንዳንድ ዓረፍተነገሮችን ለራሴም ለኣንባቢዎቼም ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ ሌሎችን ትርጉሞች ተጠቅሜኣለሁ። ከዛሬ ጀምሮ የወንጌሉን የኣማርኛ ትርጉም የማሰላሰያ ቀናትን እየዘለልኩ ገፅ በገፅ ኣቀርብላችሁዋለሁ። እንደኣስፈላጊነቱ ስለተጠቀምኩባቸው ቃላትና ሃረጎች ማብራሪያ እሰጣለሁ። ይህ የመጀመሪያው ገፅ (ገፅ 7) ነው። መድረኩ ለጥያቄም ለኣስተያየትም ክፍት ነው።

No comments:

Post a Comment