Friday, November 20, 2015

የዮሐንስ ወንጌል የማርያም ወንጌል ስለመሆኑ የቀረቡ ማረጋገጫዎች

ክርስትና በመሰረቱ የሴቶች እምነት ነበር። ወንዶች ኣያያዙን ሳያውቁት ነጠቋቸውና እንዳይሆን፣ እንዳይሆን ኣደረገጉት አንጂ። እስቲ ኣስቡት፡ ከወንጌል ታሪክ ውስጥ መሳጩ ታሪክ የሴቶች ታሪክ ነው። ከፅኑ የኢየሱስ ተከታዮች ውስጥ ዋናዎቹ ሴቶች ነበሩ። ኢየሱስንና ተከታዮቹን በገንዘባቸውም ጭምር ይደጉሙ የነበሩት ሴቶች ነበሩ። በኢየሱስ የእንግልትና የስቅላት ጊዜ ወንዶች ደቀመዛሙርት በሙሉ ፈርተው ሲሸሹ በፅናት ኣብረውት እስከመጨረሻው የቆሙት ሴቶች ነበሩ። እርሱ ከተቀበረም በሁዋላ መቃብሩን ለመጎብኘት የሄዱ፣ በሽቱም ሊያጥኑት ያሰቡ፣ ሴቶች ነበሩ። ኢየሱስ ከሙት በተነሳ ሰዓትም በመጀመሪያ ያናገራቸው፣ ለወንዶች ደቀመዛሙርት የትንሳዔውን ብስራት እንዲያውጁ ተልዕኮ የተሰጠው፣ ለሴቶች ነው። ወንዶች ደቀመዛሙርት ትንሳዔውን ለመቀበል ተጠራጥረው ሲያንገራግሩ በእምነታቸው ፀንተው የቆሙት ሴቶች ናቸው። ሴቶች ኣዲስ የተገለፀውን እምነት እንዲያ በነፍስና በልባቸው የመቀበላቸው ምስጥር ዛሬ የምሁራን መነጋገሪያ ነው። ክርስቶስ ሴቶችን እጅግ ስላከበረ ይሆን? የወቅቱ የኣይሁድ ካህናትና ምዕመናን፣ የእርሱ ደቀመዛሙርትም ጭምር፣ በኣድራጎቱ ሲያንጎራጉሩ፣ እርሱ ሴቶችን፣ በተለይም ከተናቀው እና ከተበደለው ወገን የሆኑትን፣ በእኩልነት መንፈስ ያነጋግር፣ ይፈውስ፣ ኣብሮኣቸውም ይመገብ፣ ያንን ፍቅሩን ለመመለስ የሚያደርጉትን መስዋዕትነትም በፍቅራዊ ደግነት ይቀበል ነበር። በእውነቱ፣ እርሱ ለሴቶች እጅግ ርህሩህና በምህረት የተሞላ ነበር። ይህንን ሁሉ ስናይ፣ ኢየሱስ እውነቱን በተለይ ለሴቶች በኣደራ እንደሰጠው እናስበለን። እና ታዲያ፣ ክርስትና እንደምን ከሴቶች እጅ ወጣ? ኣንዳንዴ ሳስበው፣ ‘ሴቶች ክርስትናን ባይነጠቁት ኖሮ፣ የመስቀል ጦርነትን፣ “The Inquisition”ን፣ “Ku Klux Klan”ን፣ “The Witch Hunts”ን፣  “Lord’s Resistance Army”ን የመሳሰሉ ክርስቲያናዊ መርገምት ምድርን ይጎበኙኣት ነበር ወይ?’ እላለሁ።
በባለፈው ጦማሬ በከፊል ያስነበብኳችሁ የጥናት ውጤት፣ “ወንጌልም እኮ ይነጠቃል፤ ይሰረቃል!” ይለናል። “የመግደላዊት ማርያም ወንጌል ተነጥቆና ተቀይሮ ለዮሐንስ ተሰጠ!“ ይለናል። “’በዚያ ወንጌል ውስጥ፣ ‘ኢየሱስ ይወደው የነበረው፣’ ‘በእራት ጊዜ በኢየሱስ ደረት ላይ ተደግፎ የነበረው፣’ ‘እናቱን በኣደራ ሰጠው’“ የተባለለት፣ ምን ፆታው ተቀይሮ በወንድ ቢገለጥም ያ ደቀመዝሙር በእርግጥ መግደላዊት ማርያም ነበረች!“ ይለናል። “የዚያ ወንጌል ኦርጂናሌው በጠዋቱ የሃዋርያት ቤተክርቲያን ተፅዕኖ በመቀየሩ እንጂ፣ መፃፉ ራሱ የሚመሰክረው እውነት ይህ ነው፤ ወንጌሉ ስለመቀየሩም ግልፅ የሆኑ ማረጋገጫዎች ኣሉ!“ ይለናል። በዚህ ፅሁፍ የመጀመርያ ክፍል፣ በቀጣይነት የዚህን ሙጉት ማረጋገጫዎች እንደማቀርብ ቃል ገብቼ ነበር። ማረጋገጫዎችን ከማየታችን በፊት ኣንድ ጥያቄ ለመመለስ ልሞክር፡ ጥንታዊያኑ የሐዋርያት ቤተክርስቲያናት መሪዎች ወንጌሉን በእርግጥ ለውጠውት ከሆነ፣ በዚህ ቅዱስ መፅሃፍ ላይ ይህንን ዓይነት ጥፋት ያመጡ ዘንድ ሊያነሳሱኣቸው የቻሉ ነገሮች ምንድር ናቸው?
የጥንት ቤተክርስቲያናት ወንጌሉን ለመለወጥ ኣስገድደዋቸዋል የሚባሉ ነገሮች
ከክርስቶስ እርገት በሁዋላም ሴቶች ኣዲሱን የክርስትና እምነት በማስፋፋት ሁነኛ ሚና እንደነበራቸው የታሪክ መረጃዎች ያመለክታሉ። “የጳዉሎስና የቴክላ ሥራ/Acts of Paul and Thecla“ የተሰኘው ፅሁፍ እንደሚያመለክተው ሴቶች እንደ ወንድ ደቀመዛሙርት ሁሉ በየቦታው እየተዘዋወሩ ወንጌሉን ያስፋፉና እምነቱን ለመቀበል የፈቀዱትን ሰዎችም ያጠምቁ ነበር። ወቅቱ ግን በሴቶች ላይ ታላቅ ገደብ ይደረግ የነበረበት ወቅት ነበር። በተለይ ያላገቡ ሴቶች እንደልቅና ጋጠዎጥ ይታዩ ነበር። መግደላዊት ማርያም መለያዋ ቦታ እንጂ ቤተሰብ (ኣባት፣ ባል፣ ወንድም፣ ወዘተ) ኣለመሆኑ ላጤ እንደነበረች ያመለክታል። ይህ፣ በሐዋርያቱ እና ገና በመደራጀት ላይ ባለው የክርስቲያን ቤተሰብ ዘንድ ኣሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ እንደነበር መገመት ኣያዳግትም። በሁዋላ በመግደላዊት ማሪያም ላይ ለተፈጠረው የተዛባ ኣመለካከትም ላጤነቷ ኣስተዋፅዖ ያደረገ ይመስላል።
በኣይሁድም ሆነ በወቅቱ ይገዙኣቸው በነበሩቱ ሮማዊያን ማህበራዊ መዋቅር ውስጥ ያልታቀፉቱ የኢየሱስ ተከታዮች፣ ምንዝርና ባለስልጣን የሌለበት፣ ሁሉም እኩል የሚታይበት፣ ትንሽ ማህበረሰብ ነበር። ክርስቶስ ካረገ በሁዋላ ግን የኣመራርና የስልጣን መዋቅር ጉዳይ ጥያቄ ሆኖ ተነሳ። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ያ ትንሽ የክርስቲያን ማህበረሰብ ወደተለያዩ ቡድኖች ተከፋፈለ። ከነዚህ ውስጥ ዋናዎቹ ጴጥሮስን እንደመሪ የወሰደው የሐዋርያቱ ቡድን እና የተለያዩ ትንንሽ ቡድኖች የነበሩት በኣጠቃላይ ግን “ግኖስቲክስ“ በመባል የሚታወቀው፣ በኣመዛኙ መግደላዊት ማርያምን እንደመሪ የወሰደው፣ ቡድን ነበር። (ግኖስቲኮች፣ ባጭሩ፣ “እግዚኣብሔር እውስጣችን ኣለ፤” በሚለው እምነት መሠረትነት መዳን ራስን፣ ውስጥን፣ ከማወቅ ይመጣል ባዮች ናቸው። ኢየሱስም ያስተማረው ያንን እንደሁ ያምናሉ። ጠፍተው የተገኙቱ ወንጌላት በኣብዛኛው የግኖስቲኮች ወንጌላት ሲሆኑ ይዘታቸው ከምናውቃቸው ወንጌላት ለየት የሚለው ለዚያ ነው።) ዓመታት ሲያልፉ ከተወዳዳሪ የክርስትና ቡድኖች መሃል የሐዋርያቱ ቤተክርስትያን ኣሸናፊነት እየተረጋገጠ መጣ። የቤተክርስትያኒቱ መሪዎች፣ የተከፋፈለውን የክርስቶስ ቤተሰብ ለማዋሃድ ወጥ የሆነ ቅዱስ መፅሃፍ እንደሚያስፈልግ ኣምነው፣ በሚቀጥሉት ሦስት ምዕተዓመታት በብዙ ጉባዔዎች፣ ውይይቶች፣ ውዝግቦችና ግጭቶች ውስጥ ሃያሰባቱን የኣዲስ ኪዳን መፅሃፍት መረጡ። በዚህ ሂደት ቤተክርስቲያኒቱ ከተቀበለቻቸው መርሆዎች ጋር የማይጣጣሙ የሚመስሉ ነገሮችን የያዙ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው የግኖስቲኮች ወንጌላት፣ ደብዳቤዎችና ታሪኮች በመናፍቅ መፅሃፍትነት ተፈርጀው ተወገዙ፤ እንዲወድሙም ተደረገ። ከነዚህ መፅሃፍት መጥፋት ጋር፣ በግኖስቲኮች ዘንድ ከኢየሱስ ቀጥሎ እንደመሪ ትታይ የነበረችው የመግደላዊት ማርያም ስምም እየደበዘዘ መጣ።
በሐዋርያት ቤተክርስቲያን፣ በተለይም በካቶሊክ፣ ጴጥሮስ ስልጣኑን ከኢየሱስ የተቀበለ የሐዋርያት ቤተክርስትያን መሪ እነደሆነ ተቆጠረ። በእርሱ ወንበር ላይ የሚቀመጡ የሮማን ካቶሊክ ጳጳሳትም ያው የክርስቶስ ስልጣን ተቀባይ እንደሆኑ ታመነ። በዚህ ውስጥ የመግደላዊት ማርያም የሐዋርያነት እና የበላይነት ጉዳይ የጴጥሮስን እና የወራሾቹን ጳጳሳት ስልጣን መለኮታዊነት ከጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆነ። ስለዚህም የመግደላዊት ማርያምን ክብርና ሞገስ የሚያጎድፍ ዘመቻ ማካሃድ ወንጌላትን ከማጥፋት ጎን ለጎን የሐዋርያት ቤተክርስቲያን ኣንደኛው የትግል መስመር ሆኖ ወጣ። ማርያም የኢየሱስን ትንሳዔ እማኝ፣ ይህንንም ለሐዋርያቱ ታበስር ዘንድ ተልዕኮ የተሰጣት፣ በመሆኗ “Hyppolytus“ የተሰኙ በሁለተኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻ ኣከባቢ የነበሩ ጳጳስ፣ “የሐዋርያት ሁሉ ሐዋርያ” የሚል የክብር ስም ቢሰጧትም ከእርሳቸው ቀጥሎ የመጡት ጳጳስ ይህንን ስላጣጣሉት የጳጳስ ሂፖሊተስ ምስክርነት በመግደላዊት ማርያም ላይ የተያዘውን ዘመቻ በመግታት በኩል ኣስተዋፅዖው እምብዛም ነበር። ዘመቻው በእርሷ ላይ ብቻ ኣልነበረም። በሴቶች የኣመራርና የኣገልግሎት ሚና ላይም ጭምር እንጂ። ለምሳሌ፣ በኣንደኛው ምዕተዓመት መጨረሻ ላይ የሮሙ ካህን ክሌሜንት እና በሁለተኛው ምዕተዓመት የኣፍሪካ ቤተክርስቲያናት ጳጳስ ተርቱሊያን፣ ሴቶች በቤተክርስቲያናት ውስጥ ምንም ዓይነት ኣገልግሎት እንዳይሰጡና በመሪነትም ቦታ ላይ እንዳይቀመጡ ኣዘዙ። በኣራተኛው ክፍለዘመን፣ “Apostilic Constitution“ የተሰኘው ደንብ፡ “ከመፀለይና ስብከትን ከማድመጥ በስተቀር፣ ሴቶቻችን በቤተክርስቲያን ውስጥ እንዲያስተምሩ ኣንፈቅድም፤“ የሚል ክልከላ ይዞ ወጣ።
የመግደላዊት ማርያምን ሞገስ ለማጣጣል በቀጥታ በእርሷ ላይ የተደረጉ ስብከቶች እና የተፃፉ ፅሁፎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሁሉንም እዚህ መጥቀሱ ይህንን ፅሁፍ ኣለቅጥ ያረዝመዋል። (ዝርዝር የሚፈልጉ ከዚህ ፅሁፍ መጨረሻ ላይ የተጠቀሱትን ዋቢዎች ይመልከቱ።) በኣጠቃላይ ግን፣ እርሷን ከሌሎች የወንጌል ሴቶች የማትለይ (ተራ) ሴት እንደሆነች ለማሳየት፣ ማንነቷንም ከሌሎች ሴቶች ጋር ኣምታቶ ለማቅረብ፣ ክርስቶስ ከሰባት ኣጋንንት ፈወሳት በሚለው ታሪክ ላይ በማትኮር ሃጥዓተኛነቷን ለማጉላት፣ የመሳሳት ምክንያት ተደርጋ ከምትታየው ከሄዋን ጋርም ኣንድ እንደሆነች ለማሳመን፣ የኢየሱስንም ትንሳዔ ለመመስከር የማትበቃ ሴት እንደሆነች ለማሳየት፣ ከትንሳዔው በሁዋላ ኢየሱስ፣ “ኣትንኪኝ፣ ገና ወደኣባቴ ኣልሄድኩም፤” ያላት በሃጥዓቷ ምክንያት እንደሆነ ለማሳመን፣ ወዘተ የሚጥሩ ነበሩ። የቤተክርስቲያን ኣባቶች የማርያም መግደላዊትን ምንነት በተመለከተ ውስብስብ ስነ-መለኮታዊ ትንታኔ ውስጥ ገቡ። ይህንን ኣምስት ምዕተ-ዓመት የዘለቀ ዘመቻ ማሳረጊያ ያበጁለት ጳጳስ ግሪጎሪ ናቸው፡ በኦፊሴል፣ “መግደላዊት ማርያም፣ ሉቃስ የጠቀሳት ሴተኛ ኣዳሪዋ ሴት እንደሆነች እናምናለን!” በማለት።  
እንግዲህ የግኖስቲኮችን ፅሁፎች ለማጥፋት፣ ሴቶች በኣጠቃላይ፣ በተለይም መግደላዊት ማርያም፣ በክርስትና ውስጥ ያላቸውን ክብርና ቦታ ለመንጠቅ፣ ከተደረገው የከረረ እና የተራዘመ ዘመቻ ኣንፃር መነሻችን የሆነውን የ“ዮሐንስ“ን ወንጌል ጉዳይ እናስብ። ኣጥኚዎቹ እንደሚነግሩን፣ ይህ ወንጌል በጠዋቱ የክርስትና ታሪክ ውስጥ በመጀመሪያ በግኖስቲኮች ዘንድ ይበልጥ የታወቀና የእነርሱም እንደሆነ የሚቆጠር ነበር። (በወንጌሉ ላይ የተገኘው እጅግ ጥንታዊው ኣንደምታ የግኖስቲኮች ኣንደምታ ነው።) እንደተባለው፣ “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር፣“ በሚለው ስም-የለሽ ደቀመዝሙር ምትክ የመግደላዊት ማርያምን ስም ተክተን ብናነብ ያ በወንዶች ደቀመዛሙርት እና በጴጥሮስ መለኮታዊ መሪነት በሚያምኑት ሐዋርያዊያኑ ቤተክርስቲያናት ዘንድ የሚፈጥረውን ሥነ-መለኮታዊ ፈተና እናስብ። ይህ ከሆነ፣ እነዚያ ቤተክርስቲያናት ወንጌሉን የራሳቸው ካደረጉት በሁዋላ፣ ይዘቱን ለማስተካከል መገደዳቸው እንደማይቀር ግልፅ ይሆናል።
ወንጌሉን የለወጡ ሰዎች ለምን የመግደላዊት ማርያምን ስም ሙሉ በሙሉ ኣላወጡትም?
የሆነ ሰው ወንጌሉን ለውጦታል፣ የመግደላዊት ማርያምን ስም “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር፣“ በሚል ተክቶታል፣ ፆታውንም ወደወንድ ቀይሮታል፤ የሚለውን ምጉት ብንቀበል፣ ያ የለወጠው ሰው ለውጡን ለምን በከፊል ብቻ ኣደረገው? ለምን የመግደላዊት ማርያምን ስም ከሁሉም ቦታ ኣላወጣውም? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል።
መልሱ ቀላል ነው፤ ይላሉ የጥናቱ ኣቅራቢዎች። የዮሐንስ ወንጌል በሐዋርያኑ ቤተክርስቲያናት ተቀባይነት ከማግኘቱ በፊት የሉቃስ፣ የማርቆስና የማቴዎስ ወንጌላት በሰፊው ይታወቁ ነበር። በነዚያ ውስጥ ደግሞ በኢየሱስ የስቅላት፣ የቀብርና የትንሳዔ ሰዓት መግደላዊት ማርያምን ጨምሮ ሌሎች ሴቶች በቦታው እንደነበሩ በግልፅ ይናገራል። ኦርጂናሉን ወንጌል የቀየረው ሰው ከሌሎች ቦታዎች ላይ የማርያምን ስም ሊያወጣና በወንድ ሊለውጣት ቢቀልለውም ስለኢየሱስ ስቅላትና ትንሳዔ ከሚያወሩ ጥቅሶች ውስጥ ማውጣት ኣይችልም ማለት ነው። ይህንን ማድረግ ስላልቻለ፣ ለዋጩ ሌላ ዘዴ ተጠቅሞ እነዚያን ጥቅሶች ቀይሮኣቸዋል። ምን በማድረግ? “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር፣“ ከመግደላዊት ማርያም የተለየ ሰው መሆኑን ለማሳየት በነዚያ ተረኮች ውስጥ ያንን ስም-ኣልባ ደቀመዝሙር በጣልቃነት በማስገባት እርሱና ማርያም በኣንድ ቦታና ጊዜ በኣንድ ላይ የተገኙ ሁለት ሰዎች እንደሆኑ ለማሳየት መሞከር! ማርያምና ያ ደቀመዝሙር በኣንድ ላይ የተገኙት በነዚህ የስቅላት እና የትንሳዔ ቦታዎች ብቻ መሆኑ ይህ ምጉት ምክንያታዊ እንደሁ ያመለክታል። ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ፣ ለዋጩ የሌለ ሰው ጣልቃ ማስገባቱን የሚያመለክቱ ከሌላ ወንጌል ጋር የመጣረስ፣ የትረካ፣ እና የመዋቅር ስህተቶች በነዚህ ሁለት ቦታዎች ብቻ መኖራቸው ነው። ይህም፣ ቢያንስ እነዚያ ጥቅሶች ስለመቀየራቸው ግልፅ ማስረጃ ይሆናል።
1.      ወንጌሉ የማርያም ስለመሆኑ ወንጌላዊ ማረጋገጫዎች
ጥቅሶች በመለወጣቸው የተፈጠሩ ስህተቶች
ሀ. በኢየሱስ ስቅላት ሰዓት ወንድ ደቀመዝሙር በቦታው ኣልነበሩም፡
የሉቃስ፣ የማርቆስና የማቴዎስ ወንጌላት በኢየሱስ ስቅላት እና ቀብር ወቅት ኣብረውት የነበሩት ተከታዮች ከገሊላ የመጡ ሴቶች ብቻ እንደሆኑ ነው የሚገልፁት። (ሉቃ. 23፡49፤ 23፡55፤ ማር. 15፡40-41፤ 45፤ ማቴ. 27፡55) እኚህ ወንጌላት ወንዶች ደቀመዛሙርት በቦታው እንደነበሩ ኣይጠቅሱም። ይህም ወንዶቹ ደቀመዛሙርት በሙሉ ጥለውት እንደሸሹ (ማቴ. 26፡56) ከሚናገረው ጥቅስ ጋር ስምም ነው። ነገር ግን፣ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር በስቅላቱ ወቅት ከመስቀሉ ሥር እንደነበር ይናገራል። ይህ ደቀመዝሙር እንደተባለው ወንድ ከሆነ ቃሉ ከሌሎች ወንጌላት ጋር ኣይጣጣምም።  
ለ. በዮሐ. 19፡25-27 ያለው የተፋለሰ ትረካ ስህተት እንዳለ ያሳያል፡
በሚቀጥሉት ሁለት ዓረፍተነገሮች ውስጥ ያለውን መፋለስ እንመልከት፡ "በኢየሱስ መስቀል ኣጠገብ እናቱ፣ የእናቱም እህት፣ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፣ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር። ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በኣጠገቡ ቆመው ባየ ጊዜ እናቱን፡- ኣንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ፤ ኣላት።"
ፀሃፊው በሁለተኛው ኣረፍተነገር በመስቀሉ ስር ከነበሩ ሴቶች ስለኣንዱ ነው የሚያወራው? ከሆነ፣ያ ደቀመዝሙር ሴት ነው ማለት ነው። ካልሆነ ግን፣ በመጀመሪያው ዓረፍተነገር ውስጥ ያልነበረን ደቀመዝሙር ኢየሱስ በሁለተኛው ዓረፍተነገር ውስጥ ያየዋል ማለት ነው። ይህ ሰው ከዬት መጣ? እንዲህ ያለስ ኣተራረክ ልክ ይመስላል?
ሐ. ጴጥሮስ ብቻውን ነበር ወይስ ከሌላ ሰው ጋር?
ሉቃስ ኢየሱስ በተቀበረ ማግስት ጴጥሮስ መቃብሩ መፈንቀሉን ሰምቶ ወደመቃብሩ የሮጠው ብቻውን እንደሆነ ይተርካል። (24፡12) ማቴዎስና ማርቆስ ይህንን ኣይጠቅሱም። የዮሐንስ ወንጌል ግን (ዮሐ. 20፡ 1-11) ወደመቃብሩ የሮጡት “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር፣“ እና ጴጥሮስ መሆናቸውን ይናገራል። ሉቃስ ያልጠቀሰው ያ ደቀመዝሙር እዚህ ከዬት መጣ? ይህ ደቀመዝሙር በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ጣልቃ መግባቱ ከታች እንደምናየው የትረካ ስህተትም ኣምጥቷል።  
መ. መግደላዊት ማርያም ወደመቃብሩ ተመልሳ ነበር?
በዮሐ. 20፡ 1-11 ወደመቃብሩ በተደረገው የሩጫ ተረክ ውስጥ መግደላዊት ማርያም ለጴጥሮስና ለስም-ዓልባው ደቀመዝሙር የመቃብሩን መፈንቀል ከነገረች በሁዋላ ጴጥሮስና ያ ደቀመዝሙር ወደመቃብሩ ሮጡ ቢልም ስለመግደላዊት ማርያም ወደመቃብሩ መመለስ ኣይናገርም። ጴጥሮስና ስም ኣልባው ደቀመዝሙር ወደመቃብሩ ውስጥ እንደገቡ በሚናገር ሰዓትም መግደላዊት ማርያም የት እንደነበረች ኣይናገርም። መጨረሻ ላይ፤ ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ነበር፤ (20፡11) ይላል። ማርያም ወደመቃብሩ እንዴትና መቼ ተመለሰች? ተራኪው ይህንን እንዴት ዘለለው? ከጥቅስ 2 እስከ 10 ውስጥ የተጠቀሰው ተወዳጅ ደቀመዝሙር እርሷ እንደሆነች ካሰብን ግን ይህ የትረካ መፋለስ ኣይኖርም።
ሠ. ኣመኑ ወይስ ኣላመኑም? ያመነው ማነው? ያላመነውስ? 
ከላይ በተጠቀሰው ተረክ ውስጥ ሌላው የተምታታ ነገር፣ “በዚያን ጊዜ ኣስቀድሞ ወደ መቃብሩ የመጣውም ሌላ ደቀመዝሙር ደግሞ ገባ፣ ኣየም፣ አመነም፤ ከሙታን ይነሳ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና ኣላወቁም ነበርና።“ (20፡ 8-9) የሚለው ጥቅስ ነው። ይህ ጥቅስ ምንድነው የሚለው? ‘ኣመነ’ ነው ወይስ ‘ኣላመነም’? ከላይ ስም-ኣልባውን ደቀመዝሙር ‘ኣመነ’ ካለ፤ ከታች ‘ኣላወቁም/ኣላመኑም’ የሚለው ጴጥሮስንና ማርያምን ነው? ማርያም ግን ኣይታ ኣምናለች። ይህ፣ ወንዶች ደቀመዛሙርት የክርስቶስ ትንሳዔ ሲነገራቸው እንዳላመኑ ከሚናገሩት ከሌሎች ወንጌላት ተረክ (ማቴ. 28፡17፣ ማር. 16፡9፣ ሉቃ. 24፡11) ጋር ለማመሳሰል የተደረገ ያልተሳካ ጥረት ይመስላል። ማርያም ኣየች ኣመነችም፤ ጴጥሮስ ግን ስላላወቀ ኣላመነም ቢል የሰመረ፣ ከሌሎች ወንጌላትም ጋር የሚስማማ ትረካ ይሆን ነበር።
2.      ታሪካዊ ማረጋገጫዎች
‘የዮሐንስ ወንጌል የተፃፈው በመግደላዊት ማርያም ነው’ ለሚለው ምጉታቸው ኣጥኚዎቹ ያቀረቧቸው የታሪክ መረጃዎች ባጭሩ የሚከተሉት ናቸው፡
ሀ. ኣራተኛው (የዮሐንስ) ወንጌል ከሰባ ዓ.ምህረት በፊት ስለነበሩት የኣይሁድ ባህሎችና ቦታዎች ከሌሎች በተሻለ ትክክለኛ መረጃ ይሰጣል። ይህም፣ በወቅቱ በነበረ የዓይን ምስክር እንደተፃፈ ያመለክታል።
ለ. ኣራተኛው ወንጌል በቅርቡ ከዋሻ ውስጥ በተገኙት የግኖስቲኮች ወንጌላት ጋር በይዘት፣ በተለይ በመግደላዊት ማርያም እና በጴጥሮስ መካከል የነበረውን የፍኩኩር ግንኙነት በሚመለከት፣ የሚመሳሰል ነው። (ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር በብዙ መንገድ ከጴጥሮስ በልጦ መገኘቱ ጴጥሮስን ቅናት ውስጥ እንደከተተው ከዚህ ቀደም ኣይተናል።)
ሐ. ኣራተኛው ወንጌል ለሴቶች የሚሰጠው ክብር የግኖስቲክ ወንጌላት ለሴቶች ከሚሰጠው ክብር ጋር ይመሳሰላል። በተለይ ስም-ኣልባውን ደቀመዝሙር በመግደላዊት ማርያም ተክተን ካነበብን ይህ ይበልጥ ግልፅ ይሆናል።
ማሳረግያ፡
የዮሐንስ ወንጌል፣ በዜብዲዮሱ ልጅ በዮሐንስ ተፃፈ የሚለውን እምነት ዛሬ የመፅሃፍቅዱስ ምሁራንም ሆኑ ኣንዳንድ ቤተክርስቲያናት ኣይቀበሉትም። ‘እና ማን ፃፈው?’ ለሚለው ጥያቄ ደግሞ፣ ወንጌሉ ራሱ ‘ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር ፃፈው፣’ ብሎ ይመልሳል። ይህ ሚስጥራዊ ደቀ መዝሙር ማነው? ይህ ደቀመዝሙር መግደላዊት ማርይም ልትሆን እንደምትችል ወንጌላዊም ሆነ ታሪካዊ መረጃዎችን ጠቅሰን ኣይተናል። እንዲያ ከሆነ፣ የ’ዮሐንስ’ በሚል ስም እምናውቀው ወንጌል በእርግጥ የመግደላዊት ማርያም ነው ማለት ነው። ለካስ፣ ወንጌልም ይሰረቃል! ይህ ባይሆን ኖሮ፣ ኢየሱስና ወንጌላት ለሴቶች ይሰጡት የነበረውን ክብር የቤተክርስቲያናት ታሪክ ባያጎድፈው ኖሮ፣ ዓለም ሰቆቃዋ ምን ያህል በቀለለ ነበር!

1. R.K. Jusino, 1998፡ Mary Magdalene: Author of the Fourth Gospel?

2. Janice Meighan “Mary Magdalene, Partner or Prostitute: An in-depth study of the transformation of Mary Magdalene in church history” York University Research Paper, (2005) 

No comments:

Post a Comment