መግደላዊት ማርያም
ሴተኛ ኣዳሪ ኣልነበረችም!
የስህተቱ መጀመሪያ
ጳጳስ ግሪጎሪ (Pope Gregory) ናቸው ኣሉ። እኝህን ካህን ያምታታቸው ደግሞ ሰባት የሚሆኑ ማርያሞች በወንጌል ውስጥ መጠቀሳቸው
ነው። በእርሳቸው የ591ዓ.ም ስብከት ምክንያት ቅድስት መግደላዊት ማርያም የተሳሳተ ማንነት ሰለባ ተደረገች። በክርስትና የጠዋት
ታሪክ ውስጥ የሴቶችን የመሪነት ሚና ለማኮሰስ ይደረግ ከነበረው ጥረት ጋር ተዳምሮ ይህ ስብከት እንደእውነት (በካቶሊኩም፣ በኦርቶዶክሱም፣
በፕሮቴስታንቱም) ቤተክርስቲያናት ተስተጋባ። ክብር ጎደፈ፤ ታሪክም ተፋለሰ። እንጂማ፣ በወንጌል ውስጥ ኣንድም ቦታ መግደላዊት ማርያም
ሴተኛ ኣዳሪ ነበረች የሚል ቃል የለም። ስህተቱንም እውነቱንም ጥቂት ጥቅሶችን እየጠቀስን እንይ፡
በወንጌል ውስጥ መግደላዊት
ማርያምን ቀድሞ የሚያስተዋውቀን ሉቃስ ነው (ሉቃ. 8፡ 1-3)። ይህ ምዕራፍ ሉቃስ ኢየሱስን በሽቱ ስለቀባች ኣንዲት ሃጢኣተኛ
ሴት ከተረከ በሁዋላ የሚከተል ነው። የጠቀስናቸው ካህን መግደላዊት ማርያምን ያምታቱት ከዚህች ባለሽቱ ሴት ጋር ነው። እንዲህ ብለው፡
”ሉቃስ
ሃጢኣተኛ የሚላት ያች ሴት፣ ዮሐንስ ደግሞ ማርያም የሚላት፣ እሷ ሰባት ኣጋንንት የወጡባት ሴት እንደሆነች እናምናለን። እኚህ ሰባቱ
ኣጋንንት የሚወክሉት ርክሰት እምንላቸውን ነገሮች ሁሉ ካልሆነ ሌላ ምንን ሊሆን ይችላል? … ወንድሞች ሆይ፣ ያች ሴት ከዚያ ቀድም
ያንን ሽቱ በሃጢኣት ስራዋ ጊዜ ኣካሏን ለመቀባት ትጠቀምበት ነበር።”
ይህንን ከዬት ኣመጡት ኣባው? ወንጌሉን
በትኩረት ስናይ ሉቃስ ቀድሞ የጠቀሳት ሃጢኣተኛ ሴት መግደላዊት ማርያም እንዳይደለች ግልፅ ይሆናል። ሉቃስ በምዕራፍ 7 መጨረሻ
ግድም ስለዚች ሴት ከተረከ በሁዋላ በምዕራፍ 8 መጀመሪያ ላይ መግደላዊት ማርያምን እንደኣዲስ ያስተዋውቃታል፡ ”… ከደዌ ተፈውሰው
የነበሩ ኣንዳንድ ሴቶች፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም፣ …” (ሉቃ. 8፡2) ወንጌላዊው መግደላዊት
ማርያምን ከጥቂት ዓረፍተነገሮች ቀድሞ ካነሳት ስሟ ካልተጠቀሰው ሴት ጋር ኣለማያያዙና መግደላዊት ማርያምን እንደኣዲስ ማስተዋወቁ
እርሷ ከዚያች ሴት ጋር ኣንድ እንዳይደለች ኣያሳይም? ጳጳሱን ካምታቱኣቸው ነገሮች ኣንዱ ኢየሱስን በሽቱ ስለቀቡ ሴቶች የተነገረው
ተረክ መብዛቱ ይሆን ይሆናል፡
1. ከላይ ያየነው (ሉቃስ 7፡ 36-50)፡ ቦታው ኣልተጠቀሰም (በገሊላ)፣ ቤቱ የለምፃሙ የሲሞን፣ ባለሽቱዋ
ሴት - ስሟ ያልተጠቀሰ፤
2. ማቴ. 26፡ 6-12፡ ቦታው በቢታኒያ፣ ቤቱ የለምፃሙ የሲሞን፣ ባለሽቱዋ ሴት - ስሟ ያልተጠቀሰ፤
3. ማር. 14፡ 3-9፡ ቦታው በቢታኒያ፣ ቤቱ የለምፃሙ የሲሞን፣ ባለሽቱዋ ሴት - ስሟ ያልተጠቀሰ፤
4. ዮሐ. 12፡ 1-8፡ ቦታው በቢታኒያ፣ ቤቱ የኢየሱስ ወዳጆች የነበሩት የኣልዓዛር፣ የማርያም፣ እና የማርታ።
የባለሽቱዋ ሴት ስም፣ ማርያም (ይህችኛዋ የቢታኒያ ማርያምም መግደላዊት ማርያም ኣይደለችም - ዮሐ፡ 11፡ 1-4)።
5. በሁሉም ወንጌላት ውስጥ የኢየሱስን መቃብር የወረደ ኣካል በሽቱ ለማበስ ከሄዱ ሴቶች ውስጥ መግደላዊት ማርያም
በቀዳሚነት ተጠቅሳለች።
እንግዲህ መግደላዊት ማርያም ኢየሱስን
በሽቱ ከመቀባት ጋር ተያይዞ በግልፅ የተጠቀሰችሁ ኢየሱስ ከተሰቀለ በሁዋላ ብቻ ነው። ያኔ ደግሞ በኣካል ኣላገኘችውም፣ ኣልቀባችውምም።
ያ እርሷን እግሩን በሽቶ ከቀባችዪቱ ሴት ጋር ኣንድ ኣድርጎ ለማንበብ ምን መሠረት ይሰጣል?
በኣንፃሩ፣ ወንጌላት ሁሉ መግደላዊት
ማሪያምን እጅግ በከበረ ኣገላለፅ ያነሱኣታል፡
1. መግደላዊት ማርያምና ሌሎች ሴቶች ክርስቶስን በየሄደበት ሁሉ ይከተሉትና በገንዘባቸውም ያገለግሉት ነበር።
(ሉቃ 8፡2)
2. ወንዶች ደቀመዛሙርት ሁሉ ሲሸሹ (ማቴ. 26፡56) መግደላዊት ማርያም ከሌሎች ሴቶች ጋር በኢየሱስ የስቃይና
የስቅላት ሰዓት ኣብራው ነበረች። (ማቴ. 27፡56፣ ማር. 15፡40፣ ሉቃ. 23፡ 55፣ ዮሐ. 19፡25)
3. በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ብቻዋን (በሌሎች ወንጌላት ከሌሎች ሴቶች ጋር፣) የኢየሱስን ባዶ መቃብር ለማግኘት
ቀዳሚዋ ነች። (ማቴ. 28፡10፣ ሉቃ. 24፡10፣ ዮሐ. 20፡2)
4. በዮሐንስና በማርቆስ ወንጌላት ውስጥ ብቻዋን (በሌሎች ውስጥ ከሌሎች ሴቶች ጋር) የኢየሱስን የተነሳ ኣካል
ለማየት ቀዳሚዋ ናት። (ማቴ. 28፡29፣ ማር. 16፡9፣ ዮሐ. 20፡11)
5. የክርስቶስን ትንሳዔ ለሌሎች ታበስር ዘንድ ተልዕኮ የተሰጣት ብቸኛዋ ሴት ናት። (ዮሐ. 20፡15)
6. በወንጌል ውስጥ የሴቶች ስም በተነሳ ቁጥር በኣብሳኛው ቀድሞ የሚጠቀሰው የእርሷ ስም ነው። ይህ ከሌሎች
ሴቶች ሁሉ ይልቅ ያላትን የከበረ ደረጃ ኣያመለክትም?
እንግዲህ መግደላዊት ማርያም ወንጌል ይህንን ያህል ክብር የሚሰጣት ክርስትና ግን የሚገባትን
ክብር የነፈጋት ቅድስት ሴት ነች። እርሷ ሴተኛ ኣዳሪ እንደነበረች የሚያመለክት ምንም ማስረጃ በወንጌል ውስጥ የለም። በማወቅም
ይሁን ባለማወቅ እንዲያ ትታይ ዘንድ ምክንያት ለሆኑት ለጳጳስ ግሪጎሪ፣ ”ማነው ምንትስ?” የሚለውን የፀጋዬ ገ/መድህንን ግጥም
ጋብዘን ለዛሬ በዚህ እናብቃ። በሚቀጥለው ጦማሬ፣ ”እውን መግደላዊት ማሪያም የኢየሱስ ሚስት ነችን?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ
እሞክራለሁ።እነሆ የመግደላዊት ማርያም ወንጌል ገፅ 8
No comments:
Post a Comment