Wednesday, January 22, 2014

ይህ ነበር መንፈሱ…

ስለጥንቱ መንፈስ፣
ስላለፍኩበቱ፣ 
ስለልጅነቴ፣
ስለረኝነቴ፣
ስለቆጡ ቤቴ፣
ኣንጎርጉር፣ ኣንጎርጉር፤
ኣዚም፣ ኣዚም ኣለኝ።
ቀኔ ወጀብ በዝቷት፣
በህይወት ባህር ላይ፣
ተናጠች መሰለኝ።  


ይህ ፅሁፍ በ96 ውስጥ (መሰለኝ) በኣዲስ ኣድማስ ጋዜጣ ላይ የወጣ ፅሁፍ ነው። ኣስር ዓመት መሆኑም ኣይደል? ዓመቱ እንዴት ይሮጣል ጎበዝ! ከኳንተም የጥናት ክበብ ኣካሄድ ትንሽ ለየት የሚል የጥበብ ምሽት ላይ ተገኝቼ የከተብኩት ነው። በዚያን ጊዜ የነበረውን መንፈስ በጥቂቱም ሊያሳይ ይችላል። የኳንተምን ስሜት የያዙትን ደግሞ ሰሞኑን እሰቅልላችሁዋለሁ። 

የኣርምሞ ንጋቶች፣ የግጥም ከሰዓቶች፣ የጥበብ ምሽቶች


በየጀማው ለምን እንደምሰየም እሚያውቅ ሰው የለም።  መደበቅ ፈልጌ ሳይሆን ከልቡ የጠየቀኝ ስለሌለ ነው።  

“ዛሬ ማታ በቀ… ትምህርት ቤት፣ ካም’-ፋየር ኣለ።” ኣለኝ ባልንጀሬ።  “በእሳት ዙሪያ ግጥም ይነበባል፤ ዜማ ይንቆረቆራል፤ ሂስ ይደረደራል፤ … ።  ትሄዳለህ?”
“እሽ።”
“በዚህ ትምህርት ቤት ቀን ቀን ህፃናጽ ይማሩበታል፤ ማታ ማታ ደግሞ ጠቢባን ይጠበቡበታል።  ደስ ኣይልም?”
 “ደስ ይላል።”

ኣሁን ኣሁን ይህ ልማድ እየበረከተ መጥቷል።  በየጥጋጥጉ የኣርምሞ ንጋቶች፣ የግጥም ከሰዓቶች፣ የጥበብ ምሽቶች ብቅ፣ ብቅ እያሉ ነው።  በከተማችን የጥንታዊ ግሪካዊያንና የሱፊዎች መንፈስ ያረበበበት ባህታዊ ሳይሰብክ ኣይቀርም።  ፅድቅ በዚህ በኩል ኣለ ባይባል ኖሮ ባበሻ ምድር ይህ ትጋት ከዬት ይመጣ ነበር? ለፍልስፍና?

እኔም ከሁለት ሶስቱ ታድሜኣለሁ።  ኣልዋሽም፣ ደፋር ኣላገኘሁም።  የነኣፍላጦንን [የፈላስፋ ስም] ቡችላ የገባችበት ገብቶ የቀበረችውን ለመፈንቀል ደፍሮ የተከተለ ኣላየሁም።  ኣንድ ልባም ለማግኘት ሌላ ሶስት ሺ ዘመን መጠበቅ፣ ሶስት ሺ ዘመን መፈለግ ሳይኖርብን ኣይቀርም።  (ፈረደበት ይህ ሶስት ሺ!)

መጅኑን የሚባል ኣፍቃሪ ነበር ኣሉ።  በላይሊ ፍቅር ኣቅሉን የሳተ ኣፍቃሪ።  ላይሊ ጠፋችበትና የፍለጋው ግለት ኣነሁልሎት ልክ መርፌ እንደጣለች መነኩሲት በየሸጡ፣ በየጉድባው ያስሳት ጀመር።  ኣፈር ሲያበጥር ያየው ተገርሞ፡-

“ማጅኑን ሆይ! ምንድነው እምትሰራው?” ቢለው
“ላይሊን እየፈለግሁ ነው። ”  
“ኣዬ ዕብደትህ! ላይሊ ንፅህት ነፍስ ናት፤ እንደምን ትቢያ ውስጥ ትፈልጋታለህ?”
ኣፍቃሪው መጅኑን እንዲህ መለሰ፡-
“ሁሉም ቦታ እፈልጋታለሁ፤
በእርግጠኝነት፣ ኣንድ ቦታ ኣገኛታለሁ። ”

የዚህ ፅኑ ፍለጋና ናፍቆት ድምፅ ከኛም ዘንድ በቅርቡ ተደምጦ ነበር፡-
“እልፍ ተጉዘን ዛሬ ኣንተን ኣገኘን፤
ሰላም ላንተ ይሁን፣ ፈላስፋችን!” ብንለው፣
 “የለ፣ የለ፣ እኔ ተረት ነኝ።” ኣለና ወደ ተረት ዓለሙ ኣፈገፈገ - ኣገፋሪ እንደሻው ዘብሄረ ሸዋ። ያንን መናፍቅ መነኩሴም (ዘርኣ ያዕቆብ) ጠይቀነው ቢሆን ኖሮ እንዲሁ ይመልስልን ነበር፡-
“የለ፣ እኔ ካህን ነኝ። ”
 ባይሆንማ ኖሮ በእርሱ እግር የተተካ ኣንድ እንኳ ኣይገኝም ነበር?

በእንዲህ ያለ ትህትና ውስጥ ፍልስፍና ልትኖር ኣይቻላትም።  የፍርሃትና የመማሰል ባህል በነገሰበት ማህፀንም ሳትረገዝ ትጨነግፋለች።  በእውነት ያፈቀሯት መርዝን ኣዋዝተውባት ተግተውላታል።  ምሷ ያ ነው።  ፍቅረ-ጥበብ - እሳት፣ ኣፈቃረ-ጥበብ - የእሳት እራት።  መንገዷም ያ ብቻ ነው።  መቼም በህይወት ውስጥ ፈላስፋ ከሌለ በምናብ ፈጠራ ውስጥ ፈላስፋ ሊኖር ኣይችልም።  ናፍቆቱ ገደለን!

ለዚያ ነው ወዳጄ “ጠቢባን ይጠበቡበታል፤” ሲል የቀልድ እንዳይመስል ስሜቱ ጥረት ያደረገው።  እኔም “የምር በሆነ” በሚል የመስገብገብ ስሜት ነው ያደመጥኩት።  ጠንካራ ምኞት መሆንን ይወልድ የለ?

* * *

ፅልመት እጁን ሲዘረጋ ከጭስ ይታገል የነበረው እሳት በኣፍላ ስሜት ተንቦገቦገ።  ጥላው በየሰው ገፅ ላይ ዕብድ መንፈስ የሚደንስ ኣስመሰለ።  በሚንበለበለው እሳት ዙሪያ ሶስት ደርዘን የሚሆኑ ጉብል ከሸበላ ተሰባጥረው ታድመዋል።  በቁጥር ሴቶች ይበዛሉ።  ነፃነት ኣለ ማለት ነው።  ሴትን ወደ ጥበብ የሚያቀርባት ነፃነት ካለ መልካም ዘመን እየመጣ ስለመሆኑ መተንበይ ነቢይ ኣያስብልም።  ውካታው በመካከላቸው የነገሰውን ሰላም የረበሸው ኣይመስልም።  ለዝግጅቱ እንግዳ ነኝ።  በታዳሚው መካከል እየተፈጠረ ባለው የወዳጅነት ድር ገና ኣልተያዝኩም ነበርና በዝምታ የብቻዬን ሃሳብ ኣደራ ጀመር።  በውካታው መካከል ያለው ሰላም ለቁዘማዬ ተመቸኝ።

እሳቱ ተንቀለቀለ።   
ብረት-ምጣድ ተጣደበት።  
ጥብስ ተንቸሰቸሰበት።  
ተጋራነው።  (ኣርሶ፣ ኣርሶ ሲበቃው የታረደ በሬ ነው መሰል ስጋው ያለፋል። )
ጥብሱን እያመነዠክን የኣስተባባሪውን የመግቢያ ንግግር ኣደመጥን።  መቼም በእንዲህ ዓይነት ዝግጅቶች ኣከባቢ “… ጊዜያችንን በኣልባሌ ቦታ ከምናጠፋ … ” የምትልን መቅድምና ማሳረጊያ የተወራረደ ኣያጣትም።  እና፣ ይህ የተሻለ የጊዜ ማሳለፊያ መሆኑ ነው።  ፈራሁ -  “… በጊዜ ውስጥ ማለፍ …” የሚል ነገር በቋንቋችን ውስጥ የለም።  (እኛ ተራምደነው ባለፍንበትና ጊዜ ጭርምትምቱን በወጣ!)

ቀልድ ጥሩ ነው - ያለመተዋወቅን በረዶ ያቀልጣል።  ኣንዲት ጉብል በኦርጅናሌ ዳንስ የታጀበ ኦርጅናሌ ቀልድ ቀለደችና በሳቅ ፈረስ ወደ ግጥም ኣምባ ደረስን።  ሰዓሊ እንደሆነ እማውቀው ልጅ ምንጭ ጠቅሶ ኣንዲት ግጥም ኣነበበ፡-

“ጥበብን ኣቅፌ፣
እውቀትን ደግፌ፣
ከህይወት እሳት ዳር
እጄን ኣሙቄኣለሁ፤
እሳቱ ሲጠፋ፣
ብርዱ ሲያንሰራፋ፣
ጨርቄን ማቄን ሳልል፣
እሰናበታለሁ። ”

ተጨበጨበ።  ግጥሙን ለጥቆ ኣንዱ በዕብድ ድምፁ ዘው ብሉ፣ “ደረቅ እንጨት ሞጅሩበት ኣቦ፤ ኣታቀዝቅዙን! …”  ኣለ።  ሳቅና ጭብጨባ ተዋጣለት።  
ግጥም ተደገመ።  
ተጨበጨበ።  
ተሰለሰ።  
ተጨበጨበ።  
ዘላጋ ወግ ብጤ ተነበበ።  
ተጨበጨበ።

ፈራሁ።  ፍልስፍና ራሷ ድንጉጥ ናት።  የጭብጨባ ጩሀት ባለበት ዝርም ኣትል።  በእውነት ፈራሁ!

በየጣልቃው ሙዚቃ ኣለ።  ወጣት ባለዋሽንት ተነስታ የብረት ዋሽንቷን ኮረኮረች።  ዜማዋ ጭራውን እየነሰነሰ የሽምፅ ጋለበ።  የተሳፈሩበት ኣልጠፉም።  ዓይኔን በኣግዳሚው ዙሪያ ኣሽከረከርኩ።  ወጣት ቆነጃጂት ይበዛሉ ብዬ የለ? ያምራሉ።  ሁሉም ያምራሉ።  በቁንጅናቸው ይመሳሰላሉ፤ በዕድሜኣቸው ይመሳሰላሉ፤ የተመሰጡ በመምሰላቸው ይመሳሰላሉ፤ … ።  ይህ ስልጣኔ ኣንድ ዓይነት ውበት ይሆን የሚቀፈቅፈው?

እነሱ በሙዚቃው እኔ በነሱ ተመሰጥን።  ለመመሰጥ ትንሽ የፈጠኑ መሰለኝና ፈራሁ።  እንዲህ ያለው ምሳጤ በሌጣ ባህር ላይ የእንግልል ዝርግት እንደማለት ነው።  (ስስ ነፃነት ኣለው። ) ባህሩ ግን ኣያሰጥምም።  ስትቆይ ባህር ላይ መተኛትህንም ትረሳለህ።  ስትነቃ ምንም ውሃ ኣላረጠበህም።  ኣንተ የሌለህበት ጊዜ ኣለፈ ማለት ነው።  

ሞዛቂዋ ልጓሙን በመላ፣ በመላ እየያዘች ፈረሷን ኣቆመችው።  ትልቅ ጭብጨባ ሆነ።  መልካም ነው።  ወደፊት በፈረሷ ላይ ደምንና ህማምን ትጭንበታለች።  ኮቴው የማይነጥፍ፣ ለሉጋም የማይሸነፍ ኮርማ ይወጣዋል።  የነኣፍላጦን ፈረስ ምድር ወረደ ማለት ነው።  ዘለዓለም እየጋለበ የሚኖር ፈረስ …

እንደባህታዊ የተሸረበ ልጅ ተነሳና ረጂም ቀልድ ቀለደ።  የክት የሚመስሉ ረጃጅም ሳቆች ተመዝዘው ተንተገተጉ።  ከጋሙ የነፍስ ወለላዎች የሚፈነጣጠቁ ሳቆች።  (“ቀልድ ጥሩ ነው፤ ቀላዋጭ ስሜትን ያባርራል። ” ይላል ባልንጀሬ።)  

* * *

ሳልጠብቀው ኣባነነኝና “...የት ነበርክ?” ኣለኝ ወዳጄ።  
“እንዴት ጠየቅህ?”
“ላለህበት ጊዜ ባዕድ ሁነህ ባልተወለዱ ጊዜዎች ውስጥ ስትባዝን ኣየሁሃ!”
ይህ እንግዲህ እርሱ ስለኔ ከማያውቃቸው ነገሮች ኣንዱ ነው፡- እኔ ያልኖርኩበት ዘመንና ቦታ የለም።  
“ኣንተስ እዚሁ ነበርክ?” ኣልኩት።    
“ቀልጆቹን ወድጃቸዋለሁ። ” ኣለኝና በደረቁ እንደተለመደው የተቀነፈ ሃሳብ መረቀበት።  “(ቀልድ ጥሩ ነው፤ ኣሁንህን እንድትኖር ያደርግሃል። ”

እኔና ባልንጀሬ፡-

ኣንድ ጣሪያ እንጋራለን።  ከበላዬ የርሱ ኣልጋ ኣለ።  ኣንዳንዴ ከበታቼ ይሆናል። በመሃል ኣንድ ለሚስቶቻችን የተተወ ቦታ ኣለ። ብዙውን ጊዜ ልብሱ ኣልጋዬ ላይ ይገኛል። የኔም የሱ ላይ።  ልብሳችንን ያገኘንበት ኣልጋ ወይም ኣልጋችን ላይ ያገኘነውን ልብስ የየራሳችን እናደርገዋለን።  እማንጋራቸው ሚስቶቻችንን ብቻ ነው።  ምክንያቱም ሚስቶች ኖረውን ኣያውቁም።  ፍለጋ ላይ ነን።  (“እማፈቅራት ሚስት ባገኝ ላለማጋራት እሰስት ይሆን?” እያልኩ ባሰብኩ ቁጥር፣ “ላባቴ መቅደስ ቀናተኛ ነኝ።” ምናምን እምትለዋ ኪዳናዊት ጥቅስ ትታወሰኛለች።) ኣዎን ፍለጋ ላይ ነን።  በዚህ እንመሳሰላለን። በብዙ ነገሮች እንመሳሰላለን። ምናልባትም እምንለያየው በዕድሜ ብቻ ነው።  የኔ ስንት እንደሆነ ኣላውቅም።  የእርሱ ግን ስልሳዎቹ ውስጥ ነው።  

ህልማችንም ይመሳሰላል። ተደራርበን ስለምንተኛ ይሆናል። በየሰከንዶች፣ በየቅፅበቶች ውስጥ ልንደጋገም እምንችል ሰዎች እንዳይደለን ከነቃን ቆይተናል። (በጅረት ውስጥ ማን ሁለቴ ሊቆም ይችላል?) (ሁለት ሰከንዶች ኣንድ፣ ወይም በሁለት ሰከንዶች ውስጥ ኣንድ ዓይነት እንደሆኑ የሚሰማቸው ሰዎች ኑሮኣቸውን እያባከኑ ነውና ይባንኑ!)

ይህ ወገኛ ጥበብ ይደገም፡- እያንዳንዷ በራሪ ቅፅበት በነፍሴ ላይ ሺ ኣሻራ ኣትማ እንደምታልፍ ኣውቃለሁ።  ከኣላፊው ባህር ፈለግ መጭለፍ የቻልኩትን በመዝገበውሎዬ ላይ ኣንቆረቁረዋለሁ።  ባልንጀሬም እንዲሁ።  ከትቤ ስተኛ ወይም የተኛሁ ስመስል ባልንጀሬ መዝገበውሎዬን ያነብበዋል።  ከወደደው ቃል ያኖራል።  ከጠላውም ሂስ ይቀርፃል።  ምንም ስሜት ካልሰጠው ግን ማንበቡንም ይረሳዋል።  እኔም እንደዚሁ።  ከጥበብ ምሽቱ መልስ ይህን ፅፌ ነበር፡-

የኣበው ሱባኤ ጥበባቸውን ወደነፍሳቸው ባህር ኣዘቀጠ።  በዚህ የህይወት ደለል ላይ የገድል ዋርካዎች ኣቆጠቆጡ።  በነዚህ ዋርካዎች ፍቅር የወደቁ ልጆቻቸው ኣድባሮቻቸው ኣደረጉኣቸው።  ተጠለሉባቸውም።  ኣባቶቻቸው ያለፉባቸው የደምና የህመም ጎርፎች፣ የብርድና የሃሩር ዶፎች ሳይነኳቸው ኣለፉ።  ሺህ ዘመናት ተዝለግልገው ነጎዱ - ኣዲስ ዋርካ ኣልበቀለም።  

እንደ ኣገፋሪ እንደሻው ዘብሄረ ሸዋ ወደተረት ዓለም የዘለቁ ደፋር ፈሪዎች የተቀበረውን የጥበብ ከፈን፣ የጥበብ ቡትቶ መዝዘው ኣወጡልን። (ይህም ከሞት ብብት ውስጥ ህይወትን እንደመፈልቀቅ ተቆጠረላቸው - እንደዘመናዊ ገድል።) የመጡልን ቡትቶዎች ብቻ ስለሆኑ ስለተሰወረው ጥበብ ከሚነግሩን ነገር ይልቅ የማይነግሩን በለጠ።  (ኣድናቂም፣ የተረት ውበቱ ነው።ብሎ ተደመመ። ) የሚሉን  ስለሌለም ወደ ህልም ዓለም ይዘውን ሸመጠጡ።  የጦፍን ህልመኞች ሆነነው ኣረፍን!

የኣበው ቅርስ ህልመኞችን ቀፈቀፈ። የዘመኑ ህማም ህልመኞችን ቀፈቀፈ። ድንበር የለሹ ስልጣኔ ህልመበኞችን ቀሰቀሰ። ባህር የነበረው ጥበብ ውቂያኖስ ሆኖ ተናወጠ።  በኣንድ ኣካልና በኣንድ ደብር ብቻ የምገለጥበት ዘመን ኣበቃ!’ ብሎም ኣመጠ።  ይህን ያወቀ ጠቢብነቱን ኣወቀ።  ... ተመስገን ለዚህ ስድ ዘመን! ኣሜን!”

ማልጄም ሆነ ኣርፍጄ ብነቃ ቀድሜ እምፋጠነው ወደ መዝገበውሎዬ ነው።  ባልንጀሬ ምን ኣኑሮልኝ ይሆን? ስገልጠው ከምሽቱ ማስታወሻዬ ግርጌ የወዳጄን ቃል ኣገኘሁ።  እንዲህ ይለል፡-

በመጋም ላይ ያለው ረመጥ ፈንድቶ የተቀጣጠለ-‘ለት ይህ ደረቅ ከያኒና መናኒ ሁላ ወዮለት! ይህ ህልመኛ ትውልድ ድንገት የባነነ-‘ለት የነኣፍላጦን ድርሳን ወዮለት! ... እንኳን ዛሬ ተወለድን! ኣሜን!”


ወዷቸዋል ማለት ነው የቅፅበቶቼን ክታቦች... 

No comments:

Post a Comment