Friday, January 24, 2014

ይህ ነበር ታሪኩ…

እኔ ቃል ኣላውቅም።  
ስተርክ የሰሙኝ፣
“ይህን ኣላወራሽ፣ ይህን ኣልነገርሽም፣ ምኑን ታሪክ ፃፍሺው? ምኑንስ ዘገብሺው?” ብለው ይከሱኛል።
“የኖርኩት ኑሮዬን፣ ያየሁትም ባይኔ፣ ዝክሬም በራሴው ልብ፣ እኮ ነው፤” ብላቸው፣
“እና ያ ታሪክ ነው? እና ያ እውነት ነው? እና ያ ቅርስ ነው? ትዝታ ነው በዪው፤” ብለው ያርሙኛል።
እኔ ቃል ኣይገባኝ፣ እኔ ቃል ኣላውቅም።
እሄው …
ትዝታን ከታሪክ፣ ታሪክን ከተረት፣ እውነትን ከስሜት ኣለሁ ስቀላቅል።


ከታች እምታነቡት ታሪክ ምንጭ የፈሱ መንገድ (The Dao of the Dusty Foot Philosopher) ነች።ይህ በዚያች መፅሃፍ ውስጥ እንደ ኣፔንዲክስ (ትርፍ ኣንጀት?) የገባ ታሪክ ነው። ሌላው፣ በኪስም በልቦናም ይዘውት ሊዞሩ የሚመኙት ዓይነት ዝማሬ ነው። ይህ፣ መፃን ከመግዛት ኣያድናችሁም።   

ኳንተም የጥናት ክበብ
      - የጋሪዮሽ ሃሰሳ ጥበብ
ኣጭር ቅኝት

የኳንተም የጥናት ክበብ ታሪክ፣ የፍቅር ታሪክ ነው። ፍቅር እንደ እንቅልፍ ነው። ዳር ዳር ሲል እንጂ ሲወስድ ሰዓት ኣያስመዘግብም። (ያይን ፍቅር የሚሉት ዓይነት ካልሆነ በቀር። አረ እሱም ቢሆን!) ታዲያ፣ የፍቅር ታሪክ መጀመሪያ ኣለው ይባላል? ኣለው ከተባለና ኳንተምም መጀመሪያ ካለው፣ የመጀመሪያው ዘር የተዘራው ኣዲስ ኣበባ ውስጥ ኣይደለም። መቀሌ ነው። የኳንተም ንቁ ተሳታፊዎች ከነበሩት ውስጥ እንኳ ይህንን የሚያውቅ ስንቱ ይሆን?

ቆይ፣ ቆይ፣ እኔን ማን የፍቅር ካህን ቢያረገኝ ነው ስለፍቅር ድንጋጌ በመስጠት ይህን ታሪክ የጀመርሁ? ይልቅ፣ ኣርባ ጠብታዎች ተብለው በኔም በወዳጆቻቸው ልቦናም እንደጠብታ በዝምታ ከሚሰጥሙ ጭልታዎቼ ኣንዷን መንደርደሪያዬ ላድርግ። ያ ልለው ያሰብኩትን ባጭሩ ይልልኛልና፡

ሕቡዕ ኣሻራዎች
ባልተመደረከው፣ ባልታየው ትውኔ
ባልተተነተነው፣ ኢ-ክቱብ ድርሳኔ
ባልተሸነሸነው፣ ኢ-ሥፉር ዘመኔ
እልፍ ጣት አርፎብኝ፤
በማን ወጣሁ ልበል፣ በማን ተቀረፅኩኝ?
(ኣርባ ጠብታዎች፣ ገፅ 19)

ሰው ተብለን የኑሮ ድርሳናችንን ስንጀምር፣ በገዛ ራሳችን የህይወት ብራና ላይ እኛ ሳናውቀው የሚፃፍ ታሪክ ኣለ። እኛ በንቃት ያልተወንነው ተውኔት፣ በንቃት ልንተነትነው እማንችለው ድርሳን፣ ጊዜ ሸንሽነን፣ ዘመን ሰፍረን እማንቋጥረው ገድል ኣለ። ይህ በተለይ የነፍሳችን ታሪክ ነው። በነፍስ ዓለም በኛ ላይ ማን ተፅዕኖ እንዳሳደረብንና እያሳደረብን እንደሁ ልናውቅ ኣንችልም። ምናልባት በሂማሊያ ተራሮች የዓለት ስንጥቅ ውስጥ ሱባኤ የያዘ መነኩሴ ይሆናል። ምናልባትም እገበያችን ውስጥ ትከሻችንን ገጭቶ ይቅርታም ሳይለን ያለፈ ወጠምሻ። በዚህ ሕቡዕ ሕይወታችን ውስጥ ስንት ጣቶች ዓሻራቸውን ኣሳርፈውብን ይሆን? በኤላን ፍለጋ/የዓዞ ኮሌጅ ውስጥ ዋና ገፀ-ባህሪይው ኩሴ፣ የኤላን ፍቅር ከህፃንነቱ ጀምሮ እልቡ ማን እንዳኖረ ግራ እንደገባው ሁሉ፣ ኣንዳንዴ በማናውቀው ምክንያት በኣንድ ነገር ፍቅር ተጠልፈን እንገኛለን።

መቀሌ ላይ፣ ከ1985-1989ዓ.ም ባሉት ዓመታት ውስጥ፣ ከየኣቅጣጫው የተሰባሰቡ፣ ስለጊዜና ቦታ፣ ስለሳይንስና ሃይማኖት፣ ስለጥበብና ፍልስፍና፣ ማውራት እሚወዱ የኔብጤዎች፣ ተፈላላጊ ነፍሶችን ከሉጋም በሚስበው በዚያ ሕቡዕ ክር ተሳስበው ነው መሰል፣ ተገናኙ። ሲያድለኝ፣ እኔ ከነዚያ ውስጥ ኣንዱ ነበርኩ። ለሳምንታትም ሆነ ለወራት፣ “ግድብ ሰርሂና ሸዊት ንበልዕ/ግድብ ሰርተን እሸት እንበላለን!” እያልኩ ከትግራይ ገበሬዎችና ሌሎች ብጤዎቼ ጋር ለግድብ ስራ የሚመች ቦታ ኣሰሳ የትግራይን ሸለቆና ጋራ ስወጣና ስወርድ እቆይና መቀሌ ስመለስ እኝህን ወዳጆቼን ኣገኛለሁ። ስለግዜና ስለቦታ፣ ስለህልምና እውን፣ ስለእምነትና እውቀት፣ እናወራና ነፍሴን በሃሳብ፣ ስሜቴን በሃሴት ሞልቼ፣ ተጋዳላይ በሸበጡ ወደተራመዳቸው የትግራይ ገጠሮች እኔ ዘመናይ ጃንቦ (ጫማ) ኣድርጌ እዘምታለሁ።

ኑሮ በራሷ ቅያስ ቦረናም ኣቆርም ኣድርሳኝ ስመለስ እነዚያን ጓደኞቼን ኣዲስ ኣበባ ላይ ኣገኘሁዋቸው። መቀሌ ሳለን ትሰማን የነበረች ያች የመንፈስ ከፍታ ታወሰችን መሰል፣ እንዲያው ለምን ተሰባስበበን ስለሃይማኖትም ስለሳይንስም እምናወራበትን ክበብ ኣንጀምርም? ተባባልን። እና፣ ኣምስት (ትግራይ ኣንድ ላይ ከነበርነው፣ ካሚል ዲኖ፣ ኣብረሃም መሐሪ፣ እኔና ሌሎች ኣሁን ስማቸውን እማላስታውሳቸው ሁለት ኣዲስ ተጋባዦች) ሆነን፣ ላሰብነው ጥናትና ውይይት የሚስማማ የመሰለንን መፅሃፍ (የሩሂ ተቋም መፅሃፍ) መርጠን፣ ፒያሳ ላይ፣ በዶ/ር ኤሊያስ ይትባረክ ቤት ጥናት ጀመርን። ይህ የሆነው፣ ወሩን በማላስታውሰው የ95ዓ.ም ኣንድ ምሽት ላይ ነበር። ሃሳቡ፣ ለኣንድ ሰዓት በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ፣ ለኣንድ ሰዓት ደግሞ በሳይንስ ላይ ለመወያየት ነበር። ስንጓዝ ግን፣ የመንፈሳዊ ጉዳዩ ሁኔታ ተሳታፊዎችን ነፃ ኣላደርግ ኣለ። ስለዚህ፣ ለጊዜው ያንን ትተን በሳይንስ፣ በፍልስፍና፣ በጥበብ፣ ወዘተ ዙሪያ መመላለስ ጀመርን። ኣንድም፣ በውይይቱ ነገረ-ሳይንስ ጎልቶ ስለወጣ፣ በተጨማሪም የውይይቱ ኣካሄድ የሁሉንም ሰው ነፃ ኣስተዋፅዖ የሚያበረታታ ስለነበር፣ ክበቡ ኳንተም የጥናት ክበብ/Quantum Study Circle ተባለ። ከዚያ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ቦታው ተቀይሮ ኣምስት ኪሎ፣ በኣቶ ይርዳውና ወ/ሮ ገነት ቤት ለጥቂት ጊዜ ቀጠለና፣ ከሰው ብዛት ኣንፃር ቦታ ችግር ሆኖ፤ በዚህም ላይ ሌሎች ምክንያቶች ተጨምረውበት፣ ውይይቱ ለጥቂት ወራት ቆመ።

ኳንተም ለጊዜው ብትቆምም ተሳታፊዎች ግን በየምክንያቱ መገናኘታቸውን ኣልተውም። ያገናኙን ከነበሩ ምክንያቶች፣ ወሎ ሰፈር፣ በቱ ዊንግስ ኣከደሚ ውስጥ ይዘጋጅ የነበረው ካምፕ-ፋየር (የእሳት ዙሪያ የጥበብና የጨዋታ ምሽት) ኣንዱ ነበር። በመሃል፣ በጥር ወር 1996 ዓ.ም.፣ ኣርባ ጠብታዎች የግጥም መድበል፣ መንትያዋን The Big Turbulence ይዛ ወጣች። ከያዘቻቸው ግጥሞች ኣንዱን፣ ሥነ-ህላዌ፣ በሃሳባቸው ጥልቀት እጅግ ያስደንቁኝ ለነበሩቱ ለያሬድ (ያኔ የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ)፣ ለያብባል (ያኔ የፊዝክስ የመጀመሪያ ድግሪ ተማሪና ኣሁን መቀመጫውን ጣሊያን ኣድርጎ የጠፈርን ሚስጢር እየፈለፈለልን በኣውሮፓ የጠፈር ጥናት በኩል ለዓለማችን ድንቅ ኣስተዋፅዖ በማድረግ ላይ ያለ፣ ወጣት ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት - ኮዝሞሎጂስተ) እና ለሌሎች የኳንተም ተሳታፊዎች ማስታወሻ ኣድርጋ። እና፣ መፃፏን ለማስተዋወቅም፣ የቋጠረችውን ስንቅ ለማጋራትም፣ ከኳንተም ተሳታፊዎች ያገኘሁዋቸውን ጥቂቱን እና ሌሎች ጓደኞቼንም ጋበዝሁና 16 ሆነን ስታዲዬም፣ ቶታል ህንፃ ላይ፣ ኣቶ ጌታቸው ታዬና ወ/ሮ ቤተሊሄም ቤት፣ በኳንተም ላይ ድጋሚ ሕይወት የዘራችውን የመጀመሪያ ውይይት ኣደረግን። ከዚያ በሁዋላ፣ ኳንተም የጥናት ክበብ፣ በኣስደናቂ ፍጥነት ብዙ ወጣቶች በናፍቆት የሚጠብቋት የውይይትና በሃሳብ የመሞያያ ክበብ ሆነች። በየሳምንቱ ኣርብ ምሽት፣ በኣማካይ 60 ወጣትና ጎልማሶች፣ ተማሪዎችም ሆኑ ሰራተኞች፣ የጥበብ ሰዎችም ሆኑ ኣድናቂዎች፣ የተማሩም ያልተማሩም፣ እሚተዋወቁም እማይተዋወቁም፣ ተገናኝተው በጋራ በተመረጡ ርዕሶች ላይ ነፃ ውይይት የሚያደርጉባት ተናፋቂ ክበብ። የዚህች ክበብ ተሳታፊዎች የነበሩ ተመሳሳይ ፕሮግራሞችን በመቀሌና በኣርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ለመጀመር ሙከራ ኣደረጉ። እንዲህ እያለ የኳንም ህልውና እስከ 1997 ግንቦት ወር ምርጫ ዘለቀ። ምርጫውን ተከትሎ በተነሳው ችግር መሰባሰቡን ለጊዜው ኣቆምን። ቆይቶም ድጋሚ ጀመርነው። ግን፣ እኔም በሌላ የህይወት ጥሪ ካድማስ ባሻገር ኣመራሁ፤ ያብባልና ሌሎች ንቁ ተሳታፊዎችም በትምህርትና በስራ ጉዳይ ኣገር ውስጥም ሆነ ካገር ውጭ ተበታተኑ፤ እንሰባሰብባት የነበረችው ቤትም (ያች ገነታችን) ባለቤቷን ቀየረች። ኳንተም ግን እነሆ ኣሁንም በየልባችን ኣለች። (በየግል በተገናኘን ቁጥር፣ ... መቼ ይሆን ኳንተምን ድጋሚ እምንጀምር? እየተባባልን። ተደጋግሞ እሚጠየቅ ጥያቄ መልስ ሳያገኝ አይመክንም መቼም። ይህ ተስፋ ነው።) 

ተመሳሳይ ፕሮግራሞችን መጀመር ለሚያስቡ፣ ተሞክሮኣችን እይታ ቢሰጥ፣ የኳንተም ስኬት ከዬት እንደመነጨ የሚሰማኝን ላጋራ። ኳንት ኣንድ ባለቤት ኣልነበራትም፤ ተሳታፊዎች ሁሉ ባለቤቷ ነበሩ። ልዩ ኣስተባባሪም ኣልነበራትም፤ ከተሳታፊዎች በልቡ መነሳሳት ያደረበት ማንኛውም ያስተባብር ነበር። ከስምም፣ ከገንዘብ ጋር የተሳሰረች ኣልነበረችም። ቤቱ ኪራይ የማይከፈልበት፣ ከኣቶ ጌታቸው በጎ ፈቃድ፣ ቤተሰባቸውም ያቀርቡልን የነበሩት ሻይና ዳቦም ከነሱው ደግነት ብቻ የመነጩ ነበሩ። በትምህርትም፣ በዕድሜም፣ በጥበብም የበላይ ነኝ የሚል ኣልነበረባትም። ሁሉም በፍፁም ነፃነት የተሰማውን የሚናገርባት ነበረች። የፖለቲካም የሃይማኖትም ወገናዊነት ኣልነበረባትም። የሁሉንም እይታ፣ ያለተፅዕኖም፣ ያለብያኔም ታስተናግድ ነበር። የርዕስም ውስንነት ኣልነበረባትም። ተወያዮች ያወያዩናል ያሏቸው ርዕሶች ሁሉ ያለከልካይ ይነሱ ነበር። (ኣቤት፣ በነዚያ ሁለት ከምናምን ዓመታት ውስጥ ስንት ርዕሶች ተነሱ! ውበት፣ እግዚኣብሄር፣ ህልም፣ ድሃነት፣ ፍቅር፣ ጋብቻ፣ ኳንተም፣ ኬዎስ/ቱማታ፣ ፍትህ፣ ስንቱ!) ርዕሶችን የሚወስን ልዩ ኣካልም ኣልነበረም። ለሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት ሳምንታት ርዕሶች የሚመረጡት በጋራ ነበር። በተመረጡ ርዕሶች ላይ የመንደርደሪያ ሃሳብ የሚያቀርቡ ሰዎችም ከሁሉም ተሳታፊዎች በራስ ፈቃደኝነት ይመረጣሉ። ሃሳቡ፣ ማንኛውም ሰው፣ ህትመቶችንም ሆነ ድረ-ገፆችን ኣንብቦም ይሁን ሰው ጠይቆ፣ በየትኛውም ርዕስ ላይ መሰረታዊ ዕውቀት ሊያገኝ ይችላል፤ የሚል ዓይነት በመሆኑ፣ የሚነሱ ርዕሶች ምንም ያህል ከባድ ቢሆኑም፣ ባለሙያ ወይም ምሁር ፍለጋ ኣይኬድም። የትኛውም የፈቀደና ጊዜው ያለው፣ ከየኣቅጣጫው በርዕሱ ላይ የሚነሱ ሃሳቦችን ኣሰባስቦ መጥቶ፣ የ15 ደቂቃ የመንደርደሪያ ሃተታ ያቀርባል። ከዚያ፣ በኣቅራቢውና በኣንድ ፈቃደኛ ኣወያይ ኣማካኝነት፣ ለሁለት ሰዓታት ያህል በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ውይይት ይካሄድበታል። ክበቡ ባልተፃፈ ህጉ የሚያበረታታው፣ እያንዳንዱ ሰው እውነትን በራሱ ዓይንና እውቀት መርምሮ እንዲፈርድ ስለሆነ በየትኛውም ጉዳይ ላይ ባለሙያ ኣንጋብዝም። (ኣንድ ጊዜ ብቻ፣ በጃዝ ሙዚቃ ላይ ተወያይተን ስናበቃ፣ ኣርቲስት ሙላቱ ኣስታጥቄን እንደጋበዝን ኣስታውሳለሁ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ኣንድ የሥነ-ምጣኔ ዶክተር፣ በማህበራዊ ፍትህ ላይ ባደረግነው ውይይት ተሳትፈው ለቀጣዩ ሳምንት በዚያው ርዕስ መወያያ ይዘው ሊቀርቡ ጠይቀው ኣቅርበዋል።) ኣንዳንዴ፣ ውይይቱ ሲነሽጠንና የመፃፍ ጊዜውንና ኣቅሙን ስናገኝ በተነሱ ጉዳዮች ላይ በተለይ ለኔሽን ጋዜጣ እንፅፍ ነበር። ኣንዳንድ ጉዳዮች በጋዜጣው ላይም ለሳምንታት ያወያያሉ። በዚህ በኩል ለኔሽን ጋዜጣና የዚያ ጋዜጣ ኣዘጋጆች ከነበሩት ለዓለማየሁ ገላጋይ ምስጋና ማቅረቡ ተገቢ ነው።

ለኣርቲስት ብርሃኑ መኮንን ምስጋን ይግባውና፣ ውይይቱ ከሞላ ጎደል በመቅረፀ-ድምፅ ተይዞ ኣሁንም በህዋችን ውስጥ ህያው ሆኖ ኣለ። ይህ፣ ለተሳታፊዎችም ሆነ ላልተሳተፉባቸው የሆነ ቁምነገር መያዙ ኣይቀርምና በሆነ መንገድ ለሚፈልገው ሁሉ ለማድረስ ጥረት እናደርጋለን። እኔም በዚህ ኣጋጣሚ፣ ከዚህ የኳንተም ውይይት ጋር በተያያዘ፣ በጋዜጣ ላይ የፃፍኳቸውን፣
 የኣርምሞ ንጋቶች፣ የግጥም ከሰዓቶች፣ የጥበብ ምሽቶች (ኣዲስ ኣድማስ ጋዜጣ - ይህንን ሰሞኑን ሰቅዬላችሁዋለሁ።)  
 ሴትና እሳት  (ኔሽን ጋዜጣ)
 ስድስተኛው ሃጢዓት (ኔሽን ጋዜጣ)
እና፣ ኣስቤ ሳይሞላልኝ ቀርቶ ያኔ ኣልፃፍኳቸው የነበሩትን፣ እንደ
 የሚ/ር ሽሮዲንገር ድመት
 ድሮና ዘንድሮ - ሰውና ዝንጀሮ
 የአንዲት ትንኝ ህይወትና የወ/ሮ ቦጋለች ፍልስፍና
ያሉትንና ሌሎችንም መጣጥፎች ያካተተ ኣንድ መድበል ለኣንባቢያን ጀባ እንደምል ቃል ልግባ። (ከኳንተም ተሳታፊዎች ከኳንተም የጥናት ክበብ ጋር በተያያዘ በዚህ መድበል ውስጥ መጣጥፉን ማውጣት የሚፈልግ እጁን ያውጣ!) 

ከላይ መግቢያዬ ያደረግሁዋትን ግጥሜን መደምደሚያዬም ላድርጋት። በዚህ የኳንተም ክበብም ሆነ በሌላ በተያያዙም ባልተያያዙም ኣጋጣሚዎች፣ ሕቡዕም ግልፅም ኣሻራዎቻችሁን ያሳረፋችሁብኝ የነፍሴ ወዳጆች ሆይ፣ ከቶም ኣልረሳችሁም። ህልማችው ተህልሜ፣ ሃሳባችሁ ተሃሳቤ፣ ቃላችሁ ከቃሌ ላይፈታ ተሸምኗልና።

መውጫ

ይህችን የኳንተም የጥናት ክበብ ታሪክ በብሎጋችን ላይ ልሰቅልላችሁ ሳዘጋጅ፣ በኣጠቃላይ ታሪክ ስለምንለው ጉዳይ በውስጤ ይመላለሱ የነበሩ ጥያቄዎች ከላይ መግቢያዬ ያደረግሁዋትን ግጥም ኣዋለዱልኝ። እነኝህ ጥያቄዎች ቢያንስ በከፊል በናንተም ልቦና ውስጥ መመላለሳቸው ኣይቀርምና፣ የሆነ ሃሳብ ወይም የሆነ መልስ ኣስፀንሰዋችሁ ከሆነ፣ የደረሳችሁበትን ታካፍሉን ዘንድ ከጥያቄዎቼ ከፊሉን የኳንተም የጥናት ክበብ “ታሪክ” መውጫ ላድርግ፡- ሳይንቲስቶች፣ ኣያቶቻችን በሚሊዬን ለሚቆጠሩ ዓመታት ይህችን ምድር እንደተረማመዷት ይነግሩናል። ያገሬ ሰዎች፣ ከመቼ፣ እና ለምን ከዚያ፣ መቁጠር እንደጀመሩ ባይገባኝም፣ የሶስት ሺ ዘመን ታሪክ እንዳላቸው በኩራት ይተርኩልኛል። ያን ቁጥር እሚያሳንስባቸው የመሰላቸውንም ይቆጣሉ። ቻይናዊያን ኣንዳንዴ የሰባት ሺ ዓመት ታሪክ፣ በኣብዛኛው ደግሞ የኣምስት ሺ ዓመት ታሪክ፣ ኣለን፣ እያሉ የሚያወሩትን ስሰማ ከርሜ ነው የመጣሁት። ያም፣ ታሪክ መቁጠር የሚጀመረው ከዬትና ለምን ከዚያ? እሚለውን ጥያቄዬን ኣጠናክሮብኛል። ሰሞኑን ጀምሬ በማንበብ ላይ ያለሁት የEoin Colfer ልቦለድ ታሪክ፣ Artemis Fowl፣ (ግሩም መፅሃፍ ነው፤ ኣንብቡት)፣ ውስጥ ዋና ገፀባህሪይው ኣርቴሚስ ፎውል፣ “If I win, I’m a prodigy. If I lose then I am mad. That’s the way history is written.” ይለኛል። ኣስሬ፣ በሲሳዬ ልጆች/ኬክሮስና ኬንትሮስ ውስጥ፣ የሰው ልጅ ታሪክ በፈስ የተሞላ ነው፤ እሚለው ለዚያ ይሆን እንዴ? እውን የሰው ልጅ ታሪክ በፈስ የተሞላ ነው? … የዩኒቨርሲቲ ኣንደኛ ዓመት የታሪክ መምህሬ ሙሉ ልጅነቴን ስደግመው የኖርኩትን ከኢትዮጵያ ታሪክ ደማቅ ርዕሶች ኣንዱን (የግራኝ መሃመድ ወረራ) ኣርሜ እንዳነብ ኣሳምኖኛል። ከኣስርና ኣስራ ኣምስት ዓመታት በፊት ይሆናል፤ በሆነ መፅሄት (ኢትዮጲስ ወይም እፎይታ መሰለኝ) ላይ፣ ከታሪክ ምሁሩ ከዶ/ር ላጲሶ ጌ. ደሌቦ በተጠቀሰ የኣገር ፍቅር ስሜት የታሪክ ምሁር ኣያደርግም በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ታሪክ ፀሃፍት እንደሆኑ ስንሰማ ስላደግናቸው ሰዎች ታሪክ ፀሃፊነት ጥያቄ የሚያስነሳ ሃሳብ ይዞ ኣንብቤኣለሁ። የኢትዮጵያ ታሪክ፣ በተለይም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ታሪክ፣ በኣመዛኙ በተረት ላይ የተመሠረተ ነው። በኤላን ፍለጋ/የኣዞ ኮሌጅ ውስጥ ዋናው ገፀባህሪይ ኩሴ፣ “ለካስ በእውነት ስር ላይ ያቆጠቆጠች ተረትም ኣለች? … ስሯን ስለማናይ ይሆን ተረቱን ሁሉ ከንቱ ተረት እምናደርግ?” ይላል። ይህ እንደመልስ ይቆጠር? … ኣሁንም ግን ይህ ታሪክ እሚሉት ነገር ኣይገባኝም። እስቲ የገባው የገባውን ያህል እንዲገባን ሊያደርግ ይሞክር።     

No comments:

Post a Comment