ኣፍሪካዊ
ፈ፟ላ፟ስነት ኣለ?
ካለ፣ ኣፍሪካዊነቱ
እምኑ ላይ ነው?
ኣፍሪካዊ
ሆነም ኣልሆነ፣ ፈ፟ላ፟ስነት ከነጭራሹ ለምን ያስፈልገናል?
ለመሆኑስ፣
ፈ፟ላ፟ስ/ፈ፟ላ፟ስነት ማለትስ ምን ማለት ነው? ከእሳቤው ትርጉም እንጀምር፡-
ፈ፟ላ፟ስ (ብዙ ቁጥር፣ ፈ፟፟፟፟ለ፟ስት)፦ “ፈለሰ፣” “ፈላስፋ፣” እና “ፈለሰፈ” ከሚሉት ቃላት የትርጉምም የድምፅም ድቅል የተፈጠረ ቃል ነው። ሁለመናዊ ኣተያይና የህይወት መንገድ ያለውን ሰው ያመለክታል። (እዚህ ከተሰጠው ተጨማሪ ትርጓሜ ጋር) ፈለሰ ማለት፦ ኣንድም፣ ተሰደደ፤ ወጣ፤ ሄደ፤ ማለት ነው። ኣንድም፣ መነኮሰ፤ መነነ፤ ዓለም በቃኝ ኣለ፤ ማለት ነው። ኣንድም፣ ፈለሰፈ፤ ኣገኘ፤ ፈጠረ፤ ማለት። ኣንድም፣ ተፈላሰፈ፤ ከ“ፕሌቶ ሸለቆ” ለቅቆ፣ መጥቆ ታየ፤ ማለት ነው። ፈ፟ላ፟ስ፣ የሃሳብ ስደተኛነትን (መናኒነትን/ ተማላይነትን/ መንፈሳዊነትን)፣ ፈላስፋነትንና ሳይንቲስትነትን ያጣመረ ነፃና ሁለመናዊ ኣተያይ ያለው ሰው፣ ነው። “ነፃ ኣሳቢ” ሲባል ነፃነቱ እስከምን ድረስ ነው? ሊባል ይችል ይሆናል። በምዕራቡ ዓለም ሳይንስና ሚዲያ የብዙ ሰዎችን የማሰብ ነፃነት ገድበዋል። በምስራቁ ደግሞ ባህልና ሃይማኖት። ከነዚህ የእግረ-ልቦና ጋጦች ውጭም የማሰብ ነፃነት ያለው ሰው ነው ፈ፟ላ፟ስ። በዘመኑ ባብዛኛው ሰው ተቀባይነትን ካገኘ ኣስተሳሰብና ኣኗኗር ወጣ ያለ ሃሳብና ኣኗኗር ያለው ብቻ ሳይሆን ልማድን ሊሞግትና ሊያሳድግ ነፃነቱንም ሆነ ፍትሁን እማይገድብ፣ ፍለጋውንም እማያቆም ሰው ነው ፈ፟ላ፟ስ። (ኦ’ታም
ፑልቶ፣ የሲሳዬ ልጆች/ኬክሮስና ኬንትሮስ ገጽ 364-365)
በእንግሊዘኛው፣
“የእግረ-ኣቧራማው ፈላስፋ መንገድ/The
Dao of the Dusty Foot Philosopher” በኣማሪኛው ደግሞ “የፈ፟ላ፟ሱ/ሷ
መንገድ፣” ያልኳትን የኪስ መጽሐፌን በማስተዋወቅ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ልሞክር:-
“ፈ፟ላ፟ሳዊ
ህይወት (ጉዞ) ቅንጦት ኣይደለም፤ የምሩጣን ሰዎች ብቻ የኑሮ መላም ኣይደለም። ኣለነፍስ የተፈጠረ
ሰው የለም። ከያንዳንዱ ሰው ጋር ኣብራ እምትፈጠረው ነፍስ፣ በዚያ ሰው ማንነት ውስጥ ኣንድ ወይም ሌላ ዓይነት
መንፈሳዊ ጥማት ታኖራለች። ፈ፟ላ፟ሳዊ ጉዞ (ፍለጋ)፣ እያንዳንዱ ሰው፣ በየትም ቦታና የታሪክ ዘመን ውስጥ፣ በየትኛውም የህይወቱ
የዕድገት ደረጃ የሚያደርገው [ራስን (ህልምን) የማሟላት] ግለ-ጉዞ
ነው። ግን፣ ኣንዳንዶቹ በነቃዔ-ልቦና (ኣስበውና ኣቅደው) ሲያደርጉት፣ ሌሎች ግን ሳያስቡት ይኖሩታል።
…” (ኦታም ፑልቶ፣ ሺ የፍቅር ዲቃላዎች፣ ገፅ፡ Xiii)
የዚህ እይታ
ኣንዱ ኣንደምታ ይህ ነው:- የትኛውም ባህል፣ በውል ታስቦበትም ሆነ ሳይታሰብበት ያደገ፣ የራሱ የፈ፟ላ፟ሳዊነት መንገድ ኣለው
- ያ መንገድ እንደታዋቂ የፈ፟ላ፟ሳዊነት ኣስተምህሮቶች በስርዓት የተደራጀ ባይሆንም እንኳ። “የፈ፟ላ፟ሱ/ሷ መንገድ፣”
ባልኳት መጽሐፍ ውስጥ ያቀረብኳቸው፣ የፈ፟ላ፟ሳዊ ፍለጋ ወይም የግለ-ጉዞ
ደረጃዎች፣
ሺ የፍቅር ዲቃላዎች/ A Thousand Versions of Love በተሰኘው መፅሃፌ ውስጥ
በኣማሪኛ ተርጉሜ ያቀረብኳቸው የጥንታዊ ቻይናዊያን የጥበብ ታሪኮች ያዋለዷቸው ናቸው። ሃሳቡን ያዋለዱት እነዚያ የቻይና ተረኮች ቢሆንም በዚህ መልክ ለማደራጀት
የሞከርኩት ፈ፟ላ፟ሳዊ መራሄ-ህይወት ግን የቻይናዊያን የህይወት መላ ነው ማለት ኣይደለም። ይልቅ፣ የኣፍሪካዊነትን መንፈስ ተላብሶ፣
ወይም በየትኛውም ባህል ውስጥ ያለ የትኛውም ሰው ሊጠቀምበት በሚችል መልኩ ተደራጅቶ፣ የቀረበ እንጂ። እኔ ግን፣ በብዙ ምክንያቶች
መንገዱን፣ ኣፍሪካዊ የፈ፟ላ፟ስነት መንገድ፣ ልለው እመርጣለሁ።
እንደኔ እይታ፣
ኣፍሪካዊ ፈ፟ላ፟ስነት
ተግባራዊ ፈ፟ላ፟ስነት ነው - ኣፍሪካዊያን፣ ኣርብቶና ኣርሶ ኣደርም ይሁኑ ካህንና ወታደር፣ ቀለም ቀመሶቹም ይሁኑ ቃላዊያን፣ ኖረው የደረሱበት፣ ደርሰውበትም
የሚኖሩት መላ-ህይወት። ይህ፣ ሂደቱ (ፍለጋው) ከውጤቱ (ከመብቃቱ) ተነጣጥሎ የማይታዩበት መንገድ ነው። ንፁህ ኣፍሪካዊ መንገድ፣
ላይባል ይችላል፤ እንዲያ የሚባል መንገድ የለምና። በሌላ ባህል ያልተበረዘ ንፁህ ባህልም ሆነ ፍልስፍና የለምና። ለኣንድ ለተወሰነ
ኣስተምህሮት ወይም መላ-ህይወትም ኣይገብርም። እኛ ኣፍሪካዊያን፣ ምናልባትም ከሌሎች ኣህጉራት ህዝቦች በበለጠ፣ የሰውን ልጅ ኣዕምሮኣዊና
መንፈሳዊ መንገዶች፣ በኣብዛኛው ኖረን ኣይተናቸዋል። ብዙ ሰዎች ሊሉት እንደሚወዱት፣ እኛ ለውጥ እማንሻ ኣይደለንም። እርግጥ ስንቀበል
ቀስ ብለን ቢሆን ነው። መንገዳችን ያ፣ ኑሮአችን የሰጠችን ጥበባችንም ያ ይሆናል። ኣዎ፣ ኣፍሪካዊው ተጓዥ (በረሀኛ) ያልረገጠው
የሃሳብ ምድር የለምና
እግሮቹ ቆሽሸዋል። ያኚው ቆሻሻ እግሮች ግን፣ የየደረሱበትን ምድር ምርጥ የጥበብ ጣዝማ ኣንስተዋል። ኣፍሪካዊ የፈ፟ላ፟ስነት መንገድ እንዳለ የምንስማማ
ከሆነ፣ ያ ከነዚህ ሁሉ ጣዕመን (የህይወት ተሞክሮዎች) ውህደት ነጥሮ የወጣ መሆን ኣለበት። ሁለመናዊ በሆነው የኣፍሪካ ገንቦ ውስጥ፣
በቁሳዊና በመንፈሳዊ፣ ከሞት በፊትና ከሞት በሁዋላ ባለ ህይወት፣ ወዘተ... መካከል ዋልታዊ
ክፍፍል በማይፈጥረው፣ ልክ ኡቡንቱ
(Ubuntu) እንደሚባለው
ኣፍሪካ-በቀል ክባዊ የህይወት መላ ባለ፣ ምሉዕ የህይወት ገንቦ ውስጥ፣ ነጥሮና ተጨምቆ የወጣ። ይህ፣ በስሎ እንዳበቃለት ጠጅ ያለ ኣይደለም። የሚኖሩትና
ህይወት ያለው ፍልስፍና በመሆኑ፣ ልውጠቱን እማያቆም፣ በቆየና በተለወጠም ቁጥር ብስለቱንና ጣዕሙን እንደሚጨምር ወይን እንጂ። እንግዲህ፣
የእግረ-ኣቧራማው ፈላስፋ መንገድ እንዲህ ካሉት መንገዶች
ኣንዱ እንደሆነ ኣስባለሁ።
ምናልባት
መንገዱ ከሌሎች መንገዶች ሊለያይ ቢችልም፣ ግቡ ግን ኣንድ ነው - ያ በሁሉም ነፍስ ጥልቀት ውስጥ የተዘረጋው፣ ፍጡር ሁሉ በጋራ
እሚዋኝበት የእውነትና የውበት ውቂያኖስ። እተራራ ጉልላት ላይ መውጣት ጀምረህ፣ ከተራራው ግርጌ ሽቅብ ማዝገም ከጀመርህ፣ የመረጥከው
መንገድ በምስራቁ በኩል ያለውንም ይሁን በምዕራቡ፣ በሰሜኑ በኩል ያለውንም ይሁን በደቡቡ፣ ያ እምብዛም ለውጥ ኣያመጣም። እርምጃህን
ካልገታህ እጉልላቱ ላይ ትደርሳለህ። የትኛውም ዓይነት የፈ፟ላ፟ስነት መንገድ የሚያመራው ወደዚያ የኣንዲዮሽ ጉልላት፣ ወደዚያ የውበትና
የእውነት ውቂያኖስ ነውና። ኣፍሪካዊያን በረሀኞችም ሲጨልፉ የኖሩት ከዚያው የጋሪዮሽ ግዛተ-ልቦና ነው።
እና ታዲያ
ልዩነቱ ምንድርነው? እሚል ቢኖር መልሱን ቀድሜ ተናግሬ የለ’ንዴ? እላለሁ።
ለኣፍሪካዊው በረሀኛ፣ ኣንድነት ግቡ ብቻ ኣይደለም፤ ህይወቱም፣ መንገዱም ነው። የለ፣ እንዲህ ኣላደርግም፤ ያያቶቼ መንፈስ
ይቆጣል፤ ነው እሚል ኣፍሪካዊው፤ በህይወትና በሞት መካከል ድንበር ኣይስልም። የለ፣ ኣላማትም፤ ኣልሰርቃትም፣ እሷ ባታየኝ
መንፈሷ ያየኝ የለ?
ነው እሚል ኣፍርካዊው፤ በራሱና በሌላው መሃል ድንበር ኣይስልም። የቀየዬ ሸንጎ እንዳላደርግ ወስኖ የለ? ኣላደርገውም፤
ማንም ባያየኝም ኣላደርገውም። ለምን በራሴና በቤቴ ላይ ጎሜ (መርገምት - ጋሞኛ) ላምጣ? ነው እሚል
ኣፍሪካዊው፤ በግለሰብና በማህበረሰብ፣ በቤቱና በሌሎች ተቋማት መሃል ድንበር ኣይስልም። የዓይኔ ሽፋን ተንቀጠቀጠ፣ እንግዳ
ሊመጣልኝ ነው፤ ስቅ ስቅ ይለኛል፣ ማን ኣነሳኝ ይሆን? ልቤ ድንግጥ
ድንግጥ ይልብኛል፣ የሩቅ-ኣገር ወዳጄን ምን ኣግኝቶት ይሆን? ነው እሚለው
ኣፍሪካዊው፤ በዚህና በዚያ፣ በኣሁንና በወደፊት መካከል ድንበር ኣያበጅም። ለራሱ ምታትም ሆነ ለሆዱ ቁርጠት ጤናዳምና ዝንጅብል
ቆርጥሞ ሲያበቃ፣ ማንን ጎድቼ፣ ማንን ኣድምቼ ይሆን ይህ የመጣብኝ? ያባቴ ከራማ
ይቅር ይበለኝ! ነው እሚለው ኣፍሪካዊው። በቁሳዊና በመንፈሳዊ ፈውስ መሃል ድንበር ኣይስልም። ዘርቶ ኣርብቶ፣
ለውጦ ሸምቶ ሲያበቃ፣ መርቁልኝ፤ ኣመስግኑልኝ፤ ነው እሚለው ኣፍሪካዊው። ላቤ ያፈራው፣ ገንዘቤ የገዛው ብቻ ይበቃኛል፤
እነደሚለው ዘመነኛ፣ ቁሳዊ ሃብትን ከመንፈሳዊ ሃብት ነጥሎ ኣያይም ኣፍሪካዊው። ዘፈኑና ጭፈራው፣ ቅርፃ-ቅርፁና ስዕሉ ውበትና ስሜት ብቻ ኣይደሉም ላፍሪካዊው፤
ፈውሱና ውዳሴውም ናቸው። ኣፍሪካዊው፣ መልክዓ-ምድሩንና መልክዓ-ሰማዩን፣ እፅዋት እንስሳቱን፣ በተረት መቃን ኣስውቦ፣ በፍቅርም
በኣምልኮም እልቡና እነፍሱ ውስጥ ነው እሚያኖረው። እውጪው ያሉ፣ ማርና ወተት፣ ቂጣና ቅልጥም ሲያሻው ብቻ የሚበረብራቸው፣ የጥቅም
ቀልቀሎዎቹ ብቻ ኣይደሉም። ይህች ሃሳብ ኣንዴ ትደገም፣ እንደቄብ ቅልጥም ትቆርጠም:- ለኣፍሪካዊው፣
ምድሩና ሰማዩ፣ እፅዋት እንስሳቱ፣ ልክ በኣምልኮው ቀስቶት፣ በእምነቱ ኣድርቶት፣ ተልቡ እንዳኖረው የአስተዳደር ስርዓቱ፤ ልክ በምርቃትና
በእርግማኑ ኣላቁጦት፣ በተረቱም በንግርቱም ቀምሞት፣ ከነፍሱ እንዳተመው የፍትህ ስርዓቱ፣ እልቡ ውስጥ ያሉ፣ ከነፍሱ የሰረፁ፣ የማንነቱ
ድርና ማግ ናቸው። ...
የኣፍሪካዊውን
መንገድ ከሌላ ኣቅጣጫ ከሚመጡልን መንገዶች ጋር ሳላነፃፅር ባልፍ እምለው ግልፅ ላይሆንልኝ እንደሚችል ሰጋሁ። እኔ ፈላስፋም ሳይንቲስትም
ኣይደለሁምና ማነፃፀሬን እማደርገው ፈላስፋም ሳይንቲስትም ካልሆኑ የኔ-ብጤ ተራ ኣሳቢዎች ኣንፃር ነው። ሰሞነኛ የሆኑትን የነዚህን
ኣይነት ሰዎች ጽሑፎች ሳነብ በልቤ ታለው የኣፍሪካዊው ፈ፟ላ፟ስ መንገድ እያነፃፀርኩ እጠይቃለሁ።
ኤካርት ቶሌ
(Eckhart
Tolle)፣ ስሜትንና ኣዕምሮን ከሂሊናና ከንቃት፣ ኣሁንን ከነገና ከትናንት፣ ነጣጥሎ የብቃት መንገድ
ይህች ነች፤ ሲለኝ፣ ባፍሪካ ምድር በተሰራች ነፍሴ፣ እንዲህ ያለው ክፍልፍሎሽ እሚቻልና እውነት ነውን? እላለሁ። ሃሳብን ከሃሴትም
ከብራሄም ኣቃርኖ ሾላ በድፍን ሊያጎርሰኝ ሲሞክርም፣ ምን ማለቱ ይሆን? እላለሁ። ኣትጠይቅ እሚለኝን
ካህንም ሆነ ኣታስብ የሚለኝን ብልጣብልጥ የጎሪጥ እማይ ጠረጠር ኣፍሪካዊ ነኝና።
ፓውሎ ኮሎ
(Paulo
Coelho) እና ሄርማን ሄስ (Hermann Hess) ገፀባህሪዎቻቸውን
ከበረሃ ኣሸዋውም፣ ከወንዙም ኣናግረው፣ ብቃት ይህች ነች፤ ሲሉኝ፣ ያ ሙሉ ዕድሜ በፈጀ ጉዞኣቸው የደረሱበት መነጋገር
ምን ኣፈራ? እላለሁ።
ኣለፍሬ ማረስን እርግማን ሳደርግ የኖርኩ ኣፍሪካዊ ገበሬ ነኝና። ባገኛቸውም ልላቸው እመኛለሁ:- ስታደርገውና
ስትደርስበት ታውቀዋለህ፤ ስትሉኝ፣ ገነትን ከኣፍሪካዊ መንደሬ ኣውጥቷትና ከማትታይ ሰማይ ባሻገር ደብቋት፣ ስትሞት ታገኛታለህ፤
እንደሚለኝ ካህን ኣልሆናችሁምን? ቢያንስ በቃን ከምትሉት ከናንተ እሚጨበጥ ፍሬ ሳላይ፣ ተጓዘው
በምትሉኝ መንገድ ሁሉ መኳተን-መንከራተቱስ ለምኔ?
ማህበሩንና
ዕድሩን ከግላዊ ህይወት ነጥለው፣ መታዘዝንም ከነፃነት ኣኳርፈው፣ ይህች ናት ኣርነት፤ ሲሉኝ፣ እውን ኣርነት ማለት ምን ማለት ነች? እላለሁ።
የሄርማን ሄስ ገፀ-ባህሪይ ሲዲሃርታ፣ ከሁሉም ዓይነት ጥፋትና ርክሰት በነፃነት ስም ተዘፍቆ ሲያበቃ፣ ሁሉንም ነገር መሞከር መልካም፣ ሁሉም ህይወት ሸጋ፣ መሆኑን “ማወቁን” የብራሄውና የብቃቱ ቁንጮ ሲያደርግ፣ በዚያ ሁሉ ንቃቱ፣ የሱ መስረቅና
መሰሰን የወንድም የእህቱን መንገድ እንዲያሰናክል እንዴት ኣልታየውም? እላለሁ።
እኔ እኔ የሆንኩት፣ እኛ እኛ በመሆናችን ነው፤ በሚል ጥበብ የተገራሁ ጦሳና ንጉኒ ነኝና።
በእውነት
ነፃነት ምንድርናት?
ቁሳዊውን
ህይወትና ዕውቀት ከመንፈሳዊው ህይወትና ዕውቀት ነጥሎ የከረመው ዓለም፤ ያ
የደረሰበትን ስልጣኔ፣ እናንተም እንደኔ ሁኑ፤ ለሚለው ስብከቱ እንደ ማስረጃም እንደ መደለያም፣ ሲያቀርብ
የኖረው ዓለም፤ የያዝነው መንገድ ለኛም የተሟላ ደስታን እንዳላመጣልን ነቅተናል፤ በሚሉቱ ዘመናይ ካህናቱ “ራዕይና ብራሄ”
በኩል፣ ወደናቃት መንገድ ተመልሶ፣ እነሆ ይህች ናት መንፈሳዊነት፤ ይለኛል። በነዚያ ካህናት ቃላት ውስጥ ቅንነትን ላይጠፋ
እንደሚችል ቢሰማኝም፣ ያሳደጋቸው ነገሮችን በዋልታዊ ክፍፍል (polar dichotomy) የማየት ዝንባሌ እየተፈታተናቸው ሳይ፣ እውን
ደርሰንባታል እሚሉትን ብራሄና ብቃት ደርሰውባታልን? እላለሁ። መድረኩንም፣ ምስባኩንም
የተቆጣጠሩት ዲያቆኖቻቸው፣ በገበያዊ ብልሃታቸው እንድከተላቸው ሲያግባቡኝ፣ እስቲ፣ በፈጠራችሁ፣ ከምስባካችሁ ኣንዴ ውረዱና
ስለመንፈሳዊነት ልብ-ለልብ እንነጋገር፤ እላለሁ። በወርካውም በጎጆውም ውስጥ ከናት ካባቶቼ፣ ከእህት ከወንድሞቼ ጋር ክብ
ተቀምጬ ድቡሼ (ምክክር - ጋሙኛ) ሳደርግ ያደግሁ ጋሞና ቦረን ነኝና። እነሱ ታዲያ ያኔ ፊታቸውን ያጠቁሩብኛል፤ ልባቸውን
ያዞሩብኛል፤ ስሜታቸን ይቆለምሙብኛል፤ ወይም የዕውቀትና የልቀታቸውን ምጥቀት ሊያሳዩኝ ሺ ድርሳን ይጠቅሱብኛል። የኔኑ ድርሳንም
ጨምሮ! እኔም ራሴን እምጠይቅ ኣይነት፣ ነፃነታችሁ፣ በድልድዩ ግራ ወገን ላለመውደቅ እጅግ ሲጠነቀቅ፣ በቀኙ ወገን እንደወደቀ
ተጓዥ ኣላደረጋችሁምን? እላቸዋለሁ። ነፃ ያልወጣችሁ ነፃ ኣውጪዎች መሆናቸሁም ኣይደል?
መንገዱ ይህን
ያህል ቢለያይም ያው መድረሻው ኣንድ እንደሁ ነው እሚታሰብ - ኣንድነት። ኣዎ፣ ራስን (ግላዊነትን) የፍጥረት ሁሉ መጀመሪያም፣
መጨረሻም ኣድርጋ እምትጀምር ጉዞም ከኣንድነት ግዛት ልታደርስ ትችላለች። ኣደጋው፣ እዚያ ላታደርስም መቻለሏ ነው። ራሱን እንደ
እግዚያብሄር የሚያይ፣ በሁለንተና የትኛውም ጥግ ቢደርስ የራሱን ነፀብራቅ ብቻ የሚያይ፣ የራሱን ድምፅ ገደል ማሚቶ ብቻ የሚሰማ
“እኔ”ን ልትፈጥርም ትችላለች። (40 ጠብታዎች፣ ሙላት 3) የለም፣ ኣፍሪካዊው መንገድ እንደጠቀስኩት ዘመንኛ መንገድ
ዓለሙን ዋልታ ለዋልታ ኣይከፋፍልም። ኣንድነት እጉዞው መጨረሻ ላይ የሚደረስበት ብቃት (ኒርቫና) ብቻ ኣይደለም ላፍሪካዊው። እውነቱም፣
እምነቱም እበረሃ ውስጥ የተተከለች፣ በዓመትና በሰንበት እንደቅንጦት የሚጎበኛት ዛፍ ኣይደለችም ላፍሪካዊው። ይልቅ፣ እግቢው ውስጥ
ተክሎ ያሳደጋት፣ ወጥቶ ገብቶ ማረፊያው፣ ማልዶ ኣምሽቶ ምግብ መድሃኒቱ እሚያደርጋት ጥላ ከለላው እንጂ። ይህንን ኣንብቦ፣ ኣለቅጥ
ኣጠቃለልህ ኣያ! ኣፍሪካዊውን ሁላ ባንድ እርቦ ሰፈርከውሳ! አወይ ሎዢክ ኣለማወቅ! ኣወይ ግልብ ማጠቃለያ! እሚለኝ ይኖር ይሆን? ካለ፣ የቱ ኣፍሪካዊ ባህል
ከዚህ ውጭ እንደሁ ንገረኝና፣ ኣብረን ይግባኝ እንበል፤ እለዋለሁ። ደሞም፣ ልብ ይባልልኝ፣ ከላይ፣ ዘመንኛው መንገድ፣ ነው ያልሁት።
ጥንታዊቷ መንገድ፣ ባፍሪካም በሌላውም ዓለም፣ ኣንድነት መመሪያዋ፣ ኣንድነት መድረሻዋ ነበር። ይህንንም ኣሌ እሚል ካለ፣ እሱንም፣
“ዋልታ ለዋልታ
ለመደልደል
ምን ኣስመዘዘህ
ዕጣ?
አብረን ይግባኝ
እንበል
መጣፍ ኣጣቅስ
እማኝ ኣምጣ!”
እለዋለሁ።
(40 ጠብታዎች፣ ኣብረን ይግባኝ እንበል)
እኛ ዘመናዊያን
ታዲያ፣ ይህንን ያፍሪካዊ መንገድና ህይወት፣ ከንቱ እምነት፣ ባዕድ ኣምልኮ፤ ብለን፣ ፈርደንና ረግመን፣ ኣስክደነው ስናበቃ፣ በየልካችን
የሰፋነውን የኣዋቂነትና የስልጡንነት፣ የጠቢብነትና የፅድቅ ካባ ተጎናፅፈን፣ ገዝፈንና ደምቀን ታየን። እምነቱን ስንነጥቀው፣ ተረቱን
ስናስረሳው፣ በእርግጥ እያደረግን ያለነው፣ እሱንና ምድሩን ማፋታት እንደሁ ልብ ኣላልን ይሆን? ተፈጥሮን ከልቡ ኣውጥተን ውጭ፣ ኣስተዳደሩንና ፍትሑን ከልቡ ኣውጥተን
ውጭ፣ እምነቱንም ገነቱንም ከልቡ ኣውጥተን ውጭ! ይህን እያደረግን ደግሞ፣ ማንነት፣ ብለን፤ ኣፍሪካዊነት፣
ብለን፤ ቅርስ፣ ብለን፤ ... መፈክር እንጽፋለን፣ ፕሮጄክት እንነድፋለን፣ ፈንድ እናሳድዳለን። እኔስ ተስፋ ኣደርጋለሁ:-
ኣፍሪካዊው ወንድሜ በኛ ጩሀት ዝም ኣለ እንጂ ማንነቱን ገና ኣልረሳም። ቃሉና መንፈሱ ኣረመጠ እንጂ ገና ኣልጠፋም! ፍልስፍናው
በኛ ብዕርና ብራና ሊታሰር እጅግ ረቀቀ እንጂ ከልቡ መቅደስ ተሰድዶ በመካነ-ቅርስ ውስጥ ኣልመሸገም።
እና ኣሁን፣
በኛ ምክንያትነትም ይሁን በዘመኑ ሩጫና ቁንጥጫ ሰበብ፣ ይህ የእግረ-ኣቧራማው ፈላስፋ፣ የፈ፟ላ፟ሱ፣ መንገድ፣ የባለሙዚዬሞችና የባለድግሪዎች መቆለጳጰሻ
ብቻ መስሎ ቢታይ ያስገርማል? ተቃርኖው
ግን፣ ይህ መላ-ህይወት ለኣፍሪካ ብቻም ሳይሆን ለሌላው ዓለምም ይበልጥ የሚያስፈልግበት ጊዜ ቢኖር ኣሁን መሆኑ ላይ ነው።
ከመቻቻል ባሻገር፣
በሰመረች ህብር እሚኖር ትውልድ ለመቅረፅ፣ ከሙስናና ከስንኩል ባህሪያት ሁሉ የነፁ ዜጎችንና ተቋማትን ለማፍራት ከፈለግን፣ ስራው ዛሬውኑ፣
ስራው ከየቤቱ መጀመር እንዳለበት ሁሉም የሚስማማ ይመስለኛል።
ኣፍሪካዊ
ባህል በመሰረቱ መንፈሳዊ ባህል ነው። በኣፍሪካ ምድርና ህዝብ ውስጥ ዘላቂ ለውጥን ለማነሳሳትና ለማራመድ የሚሞክሩ የተሃድሶ ጥረቶች
ሁሉ፣ ይህንን የባህላችንንና የማንነታችንን ገፅታ ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ኣለባቸው። በኣፍሪካዊው ታሪክ፣ ስሜትና ሕይወት ውስጥ
ስራቸውን በሰደዱ ተረቶችና እውነቶች ላይ የተመሰረተና ያን ህቡዕ ቅርስ ለላቀ ፍሬ የሚያበቃው፣ ሁለመናዊ፣ የሰመረ ህብር ያለው፣ እና ያለማቋረጥ ሊያድግ የሚችል
ንፅርዖተ-ዓለም እጅግ ያስፈልገናል።
(ምንጭ፡- ኦታም ፑልቶ፣ የፈላሱ መንገድ፡ ከሺ የፍቅር ዲቃላዎች የተወለደ፤ ገጽ 90-100)
(ምንጭ፡- ኦታም ፑልቶ፣ የፈላሱ መንገድ፡ ከሺ የፍቅር ዲቃላዎች የተወለደ፤ ገጽ 90-100)
No comments:
Post a Comment