ሞኞች ሆይ፣ ኑና እንደዱሮኣችን እንሁን!
ምስር ብላ እንዳትሉኝ፣ “የምስራች!” ኣልልም። ሲያቅረኝ ውሎ ያድራል ምስር የበላሁ ለታ።
እንኩ፣ እንዲሁ ዜናውን ልንገራችሁ፦ (የለ፣ ይቅርታ፣ ከዜናው በፊት መሟሟቂያ ነገር ላስቀድም።) ይህንን፣ በትንሽ በትልቁ መርገምት
ያፈረና የሰከረ ዘመን፣ ይህንን ያለማቋረጥ በሚያርፍነት ጡጫ ያለልክ የነሰረ ዘመን፣ በማወደስ ልንደርደር። ይህ የቸርነት ዘመን
ነው። ኣንዳንድ ግልፅ እውነቶች ልብ ልንላቸው ኣስታዋሽ ይሻሉ። ልነግራችሁ ወዳለው እውነት ያነቃኝ ኣንድ ወዳጄ ነው። ኣዎ፣ ይህ
የፀጋ ዘመን ነው። ቀድሞ፣ ኣንድ መፅሃፍ ፍለጋ ቤተመፅሃፍት እንሄድና “ወጥቷል፣ ሳምንት ተመለሺ፤” እንባላለን። ዛሬ፣ ኣምስትና
ኣስር ሺ መፅሃፍት በኪሳችን ይዘን እንዞራለን። ቀድሞ ደብዳቤ ፅፈን ፖስተኛው በሰላምና በቶሎ እንዲያደርስልን እንጸልያለን። ዛሬ፣
ኣንድ ገፅ ሳናባክን፣ ቦስጣም ቴምብርም ሳንል፣ በቅፅበት ውስጥ፣ ካሻን ባለሙ ሁሉ፣ እንነበባለን። ቀድሞ፣ ቄስ ትምህርት ፍለጋ
ኣድማስ ኣሳብረን ዓመታት እንዋትታለን፤ ዛሬ፣ ቄሱንም መጣፉንም፣ እየጓዳችን እናገኛለን። እውነት ነው፤ ይህ የቸርነት ዘመን ነው።
ልጨምር?
ቀድሞ፣ እንግሊዘኛ፣ ወይ ፈረንሳይኛ፣ ወይ ቻይኒኛ ኣለመቻላችን የማወቅ ግሮሮኣችንን እንቅ
ኣርጎ ይይዝብን ነበር። ዛሬ፣ ማንኛውንም ቋንቋ በቅፅበት ተርጉመን ሚስጢር እንፈለፍላለን። የኛዋ ግዕዝ ዛሬም እዚያ ኣለመድረሷ
ይህን ሃሰት ኣያደርገውም። የኛን የቤት ስራ ማን ሊሰራልን ኖሯል? ግዕዝ ቀርቶ የፈርዖኖች፣ የማያዎች፣ እንዲያውም የኣትላንቲሶች
የሚስጢራት መፅሃፍት እንኳ ሳይቀሩ እንዳማለሉን ይቀራሉ የሚል ስጋት የለኝም። እንዲያው የቀድሞ ዘመናችን የንፍገት ባህሪይ ኣልላቀቀን
ብሎ በስስት ውስጥ ሊያስኖረን ይታገለናል እንጂ፣ እርግጥ ነው፣ እጉያችን ያሉ ቀርቶ፣ ተሰረቁብን፣ ጠፉብን፣ እምንላቸው የብራናም
ሆነ የዲንጋይ መፅሃፍቶቻችን በየቤታችን ይገኛሉ፣ በየጣታችን ፈቃድ ውስጥ ይሆናሉ። ትንሽ ጊዜ ብቻ፣ ትንሽ ጊዜ።
ዛሬ፣ እደ“ንጉስ” እያሱ በቁም እስር ውስጥ ያለ፣ ያለከልካይ በየኣገሩ ይዞራል። ዛሬ፣
ትንፍሽ እንዳይል የተበየነበት፣ ያለገደብ ይናገራል። ዛሬ፣ “ቤት እሰራበት ቀርቶ እቀበርበት እፍኝ መሬት ኣገኝ ይሆን?” ብሎ እሚሰጋ፣
የኔ ቢጤ እንደ ሰማይ ድንበር የለለው ቀላድ ይወርሳል፣ ከሰለሞንም ቤተመቅደስ የከበረ ህንፃ ይገነባል። (ለግዜው፣ ያ ቤቱ ከብርድ
ባያድነውም።) “የምድር የተናቁና የተረሱቱ ሁሉ ታላቅና ገናና ይሆናሉ፤ ለጥበባቸውም፣ ለሃይላቸውም፣ ለግዛታቸውም ልክ ኣይኖራትም፤”
የሚል ትንቢት ከነበር፣ ያ ትንቢት የተነገረው ስለዛሬና ስለኛ ነው። እነሆ ዓለማችን በየዓመቱ፣ እንዲያውም በየዕለቱ፣ ሺ ሰለሞኖችን
እየወለደች! ባምስት ኣሶች ኣምስት ሺ ሰዎች የመጥገባቸው ተዓምር ስንት ዘመን ተሰበከ? እነሆ ዛሬ፣ ልናወድሰው ከምንችለው በላይ
በተዓምራት የታጨቀ የተዓምር ዘመን መጣ! ኣንዳንዴ ሳስበው፣ እንዲህ በኣንድ ቀንና ዓመት ውስጥ፣ ሺ ቀናትና፣ ዓመታት መኖር እየቻልን፣
ዕድሜዓችንን እንደቀድሞው በ365 ቀናት ኣንዴ መቁጠራችን ኣግባብ ነው? እላለሁ። ለነገ ታሪክ ፀሃፊዎች፣ እነማቱሳላ ኣይደሉም በዓለም
ላይ ብዙ የኖሩት። እኛ፣ የዚህ ዘምን ሰዎች ነን። እና፣ እንደጥንቱ 365 ቀኖቻንን በኣንድ ዓመት ብቻ እንዴት ይሰፈሩ? እንዲህ፣
ጓዳችንን ሳንለቅ፣ ሲያሻን በላስቬጋስ፣ ሲለን በሃቫና ኩቫ ውለን እያደርን፣ እንደቀድሞው ባንድ ኣገር ዜግነት መጠራታችንስ ኣግባብ
ነው? “ያገርህ ሰዎች፣ እንዲህ በዘርና በሰፈር ተከፋፈለውና ታጥረው ሲናቆሩ እያየን ኣንተ እንዲህ ትላለህ፤” ኣትበሉኝ። ይህ፣
በዚህ በፀጋ ዘመን የኛ ውድቀት ነው። እንነሳለን። ትንቢት መናገሬ ኣይደለም። እውነት ነው። ይህ፣ እኛ ምን ብንጠብ፣ ምን ብንታጠር፣
መሆኑን እማናስቀረው እውነት። እንነሳለን፣ ልዩነታችንንም ውበታችን እናደርጋለን። እኛም’ኮ የእግዚኣብሄር፣ እኛም’ኮ የዘመናችን
ልጆች ነን!
ይህ ረጅም መንደርደሪያ ነው። ግን፣ ኣዎ፣ ይህ የቸርነት፣ ይህ የብርታት ዘመን ነው።
ማድረግ ለምንችለው ነገር ገደብ የለውም። እነሆ ዜናው፦ ዛሬ፣ ኣዲስ የፍልስፍና ትምህርት ቤት ተከፍቶልናልና እንኳን ደስ ያለን!
በኳንተም የጥናት ክበብ ላይ ዳግም ነፍስ የመዝራት ምጥ ኡቡንቱ ’ና ፑልቶ የሚል ስም ያንጠለጠለ ኣድስ የድረገፅ
(ጦማር?) ተማሪ ቤትን ከነቃጭሉ ዱብ ኣርጓልና፣ ኑ፣ እንደዱሮኣችን ኣብረን እንፈላሰፍ! (ስንት ዘመን ኪራይ ቤት ፍለጋ ዋተትን?
ያውም እንዲያ በግድግዳ የታጠረ፣ ሃምሳ ነፍሳትን ብቻ ተቀብሎ፣ ሞልቷል! እሚያስብል ስንዝር ክፍል ፍለጋ!)
በነገራችን ላይ፣ ቢያንስ ለኳንተሞች፣ ቢያንስ ስለኳንተም ለሚያውቁ ወዳጆች፣ ቢያንስ በኳንተማዊያን
ነፃነት ለተቃኘች ነፃ ነፍስ፣ “እንፈላሰፍ፣” ብሎ ግብዣ በ“ይራቅ!” እሚያስማትብ ኣይደለም። እንዲያ፣ በስንቱ ተፈላስፈንበት!
“ሞኞች ሆይ” መባሉስ ነገር ነገር ኣይሸት ይሆን? ይህ የሚያስቆጣው፣ ይህችን ጥሁፍ ሊያነባት ኣይጀምርም ብዬ በማመን ወደጉዳዬ
ልዝለቅ።
ያ፣ የኛ (የኳንተሞች) ልክፍት ኣልተጋብቷቸው የነበሩ ኣሳቢዎቻችን፣ ድሮም፣ “ምን ኣተርፍ
ብላችሁ?” ይሉን ነበር። ዛሬም ይህችን ጥሪ ሲሰሙ፣ “ምን ልታተርፉ?” ይሉን ይሆናል ድጋሚ።
በልጅነቴ እጎረቤቴ አባ ገገግ እሚባሉ እሳት የላሱ፣ እሳት የሆኑ ባለክራር ነበሩ። (የእውነተኛ
ሰው እውነተኛ ስም ነው ኣባ ገገግ። ላከብራቸው ነው በስማቸው የጠራሁ። ደግሞም፣ የርሳቸውን ታሪክ፣ “ደበላ” ወይም “ደባልቄ”
እሚባል ስም ተሸክሞት ስንዝር ሳይራመድ ሊወድቅ ይችላል ብዬ ሰጋሁ።) ክራር ኣክርረው እየሸጡ፣ እዚያች እቤታችን ጎን በነበረች
ግራር ስር በዜማቸው ገበያቸውን እየጠሩና እያደሩ፣ የኔብጤዎችንም ከእንቅልፍም ከድብርትም እየቀሰቀሱ፣ ቀን ተቀብለው ቀን ሲሸኙ
ይኖሩ ነበር፣ ኣባ ገገግ። ዛሬ መቃብራቸው ዝም ብሎ ዝም ኣስባላቸው’ንጂ (በኔ ብጤዎች ውስጥ ዛሬም እየተናገሩት ያለው ሳይቆጠር)፣
እሳቸው ኣማልለው ያልጠሯቸው፣ ነካክተውና ተራርበው ያላቀበጧቸው፣ ኣሳስቀውም ያልሸኟቸው ቀናት ነበሩ ብል ኣሳንሳቸዋለሁ። ሰፈራችን
ሁሉም ዓይነት ሸቀጥ እሚሸመትባት የመሸታ ሰፈር ነበረችና፣ ከኣባ ገገግ ህይወት ላይ፣ ያድባሯን መርገምት፣ የሰውን ሃሜት ቀንሼ
ሳስበው፣ የተማረች ነፍስ ይዘው ኖረው የተማረች ነፍስ ይዘው ያለፉ እንደሁ ይሰማኛልና እንዲያው ለልማድ ያህል፣ “ነፍሳቸውን ይማር!”
ብዬ ልቀጥል።
ባለክራር ኣዝማሪ ነበሩ ብላችሁ፣ “እስቲ ተግጥማቸው ኣቅምሰን፣” እንዳትሉኝ ፈራሁ። መልካም
ግጥምን ሊያደንቅ ኣስቦ፣ “እሚዘመር፣” እሚል መምህር እመንገዴ ላይ ገጠመኝ ሰሞኑን። ያ ከግጥም ከፍታዎች ኣንዱ ደረጃ ይሆናል
- የዘማሪውም የመዝሙሩም ዓይነት ብዙ ሊሆን ቢችልም። የኣባ ገገግ ግጥምና ዜማ እንዲያ ያለ ኣይደለም። ምን እሚሉት ምትሃት እንዳለው
እንጃ፣ ልቦናን ልክ ወንፊትን እንደሚዘልቅ ውሃ ዘልቆ ከነፍስ ጥልቀት ውስጥ ሰጥሞ እሚቀር ዓይነት ነው። ግጥምና ዜማቸው ስለፍቅር
ሳይሆን ፍቅርን ራሱን፣ ስለዕምባ ሳይሆን፣ ዕምባን ራሱን ስለሆነ ይሆናል። (እሰይ፣ ትንሽ ግነት ጥሩ ማምለጫ ሰጠኝ።) እና፣ ከኣባ
ገገግ ግጥሞች፣ እንደ ኣዝማች እሚደጋግሟት ስንኝ ብቻ ናት ትዝ እምትለኝ፡- “ያ ገገጉ፣ ጋንጋድርሹ!” ምን ማለት እንደሆነች ኣላውቅም።
ስላልገባችኝም ይሆናል ከዓዕምሮዬ ተሰንቅራ መቅረቷ።
ኣባ ገገግ ድሮም ቀልብ ሰራቂ፣ ጨዋታ ሰራቂ ነበሩ። እነሆ፣ ዛሬም ትዝታ ሰራቂ ሆነው፣
እኔን ብቻ’ንጂ ኣታውራ እያሉኝ ነው። “ዓለም ጥብርብርታ፣ የሳሙና’ረፋ”ን ማዜም ይወዱ ነበር እሳቸው። ታዲያ፣ ዓለምን ሲወዷት
የብቻ ነው! ሰርክ እንደዘመሩላት እቅፏንም ሙቀቷን፣ ማዕጠንቷንም ቅባቷንም፣ … ሳይጠግቡ ነው ያለፉ - በ99ኛቸው (በኔ ስሌት)።
ዓለምን እያሙና እያሳጡ መቅኒዋን ሲያጣጥሙ በመኖር አባ ገገግ ብቸኛ ሰው እንዳይደሉ እሚያስብ ካለ በኣንድ ምህዋር ላይ ነን። በኣጥቢያውም
በሰበካውም “ዓለም ከንቱ፣ የከንቱም ከንቱ፤” እያሉ፣ በሃሳብም በድርጊትም ዓለምን እንደዋዋቴ እያኘኩ በሚኖሩ ጻድቃን መሃል ነው
ያደግነው። የዚህ የግፏት እቀፏት ኑሮ-ጥበብ ምንጩ እምን እንደሁ ለማወቅ ስንማስን፣ ያው መልካሙ መጣፍ እንደሁ ደረስንበት። ኣይዋሽም
ይባላልና ያ መጣፍ፣ “ይህችን ውብ ዓለም ከነቱ ማለቱ ለምን ይሆን?” ብለን ጠየቅን። (ኣንድ፡ ፍልስፍና ሳይነጋ ተጀመረ።)
“ለምን ይሆን? ለምን ይሆን? …” እያልን መልስ ፍለጋ ምናባችንን ስናስጋልብ፣ ለዓለም
ዝማሬዎቿና ቅኔዎቿ፣ ለህይወት ርቅቀቷና ሚስጢራቷ ልባችንን እንድንከፍት ነው እንዲህ የሚለን መጣፉ፣ እንዲያ የሚሉን መምህራኑ።
የሚል ሹክታ ተወደወዳኛው የደረሰን መሰለን። (ፍልስፍና በልጅነት ኑሯችን ውስጥ እንደዋዛ ራሱን እያሰረገች እንደሁ ልብ ይሏል።)
… ቅኔ ሞገሷ ዕምባ ነው። ይህ ፍልስፍና ኣይደለም፤ ቢያንስ ያበሻ ምድር እውነት ነው።
ዝቅ ቢባል የኔ-ቢጤውና ሙሾ ኣውራጇ፣ ከፍ ቢባል መነኩሴውና ባህታዊዋ፣ በዕምባ ያጎመሩትን የቅኔ አዝመራ ሲመግቧት ለኖረች ምድር፣
ይህች የዕምባ ኣድባር ላፈራቻቸው ልጆቿም፣ ይህ በርግጥ እውነት ነው። ኣዎ፣ (ኣጋነንህ ወይም ዋሸህ እሚል ካለ ሲሻው ይክሰሰኝ
እንጂ) ያበሻ ቅኔ፣ ያበሻ ሚስጢር፣ ያበሻ ዝማሬም ምንጯ ዕምባ፣ መፍሰሻዋም የዕምባ ፈለግ፣ መኖሪያዋም የዕምባ ሸለቆ ነው። ወይም፣
እናጠቃልል ከተባለ፣ ዕምባ ቋንቋ ሆና ስትገለጥ፣ ቅኔ ሆና ትዘመራለች። እና ታዲያ እኚያ፣ “ምን ኣተርፍ ብላችሁ?” እሚሉን ጠያቂዎች፣
ይህንን እያወቁም፣ “ከዓለም ደስታዋና ምቾቷ ይልቅ፣ በዕምባዋ ላይ ልብን መጣል ሞኝነትም ኣይደል?” ይሉንም ይሆን?
ነው’ንጂ! ሞኝነት ነው። ኋላስ ምን ሊባል? ያም ኣይደል ትርፉ ታዲያ - ሞኝ መሆን?
ጥያቄ እንጂ መልስ እማይሰጠን ያ መልካም መጣፍስ ቢሆን፣ “ሞኝ ሁኑ” ኣይደል እሚለን? በሞኝነት እንጂ በብልጠትማ ማን ገነትን
ወረሰ? እንኳን ገነትን ምድርንም የወረሷት ሞኞች ናቸው። ኣልሰሜ ካለ፣ “እንዴት?” ይበል። ቢያንስ፣ ስለዚያ፣ “የኮክ ፍሬ ለምን
እምድር ወደቀ?” ብሎ የጅል ጥያቄ ስለደነቀረው የኔብጤ እሚያውቁ ይህን ኣይጠይቁም። ኮክም ሆነ፣ በለስም ሆነ፣ ኣጋምም ሆነ፣ እንቆቆ፣
በስሎ ሲያበቃ ወደ ምድር መውደቁ ምን ይደንቅና ያስጠይቃል? ጠየቀ ግን ያ፣ ኒውቶን እሚሉት ወፈፌ። ጠይቆም ኣላበቃ፣ ደረስኩበት
ያለውን መልስ ኣለእፍረት ላለሙ ሁሉ ጮክ ብሎ ተናገረ። ተሳለቀበት ታዲያ ሰው በዚያ በጅል ግብሩ? እንዲያውም! እስቲ ተኣዳም ዘር
እርሱ ታገኘው ሞገስ እሚተካከል ሞገስ ያገኘ ስንቱ እንደሁ ለማስላት እሚሻ ጣቶቹን ቆጥሮ ይንገረን። እና ታዲያ፣ ዓለምን የወረሷት፣
ዓለምን ያስገበሯት፣ እነማን ናቸው? … ሞኞችና የሞኝ ውላጆች ኣይደሉ?
ኣሌ የለውም ጃል፣ ትርፉ ቅኔ ነው ህይወት። ትርፉ ዝማሬ ነው ህይወት። ውበቱ ዕምባና
ሞኝነት ነው ኑሮ። ሌላ ሌላውማ፣ ጠቢቧ እመቤት ወ/ሮ ቦጋለች እንደሚሉት፣ ሲሞላ ቦርጭ፣ ሲጎድል እከክ ነው። የዓለምም ጣዕም በቅጡ
እሚገለጠው ይህ ምስጢር ለገባቸው ለእነ ኣባባ ገገግ ብቻ ሳይሆን ይቀር ብላችሁ? ለዚያም ኣይል 99 ዓመታት ኣንብተውባትም፣ ኣልበዋትም፣
ንጠው በቅቤዋ፣ ኣፍለተው በኣሬራዋ ሲያገሱ ኖረውም ሳይጠግቧት እሚለይዋት?
ፈጣሪ ምድርንና ሰማይን ፈጥሮ ሲያበቃ፣ ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃምን ሆነ። ሰው፣ ኢንተርኔትን
(መረጃመረብ?) ፈጥሮ ሲያበቃ፣ እውቀት ይሁን! ኣለ፤ እውቀት ሊሆንም ጀመረ። ዘመኑ፣ እነሆ ድንበር የለሽ ኣደራሽ ሰጠኋችሁ፤
እያለን ነው። ሲሻችሁ ዝሩበት፣ ሲሻችሁ እጨዱበት፣ ሲሻችሁ ጋልቡበት፣ ሲሻችሁም ተጫጩበት ኣልያም ተንጫጩበት፣ እያለን! እኛ ብንፈላሰፍበት
የቱ ከልካይ ይኖራል? ወዳጆቼ ሆይ፣ ይህችን ዓለም ናቅ ኣርገን እንዳሻን እምናወጋበት የፍልስፍና ትምህርት ቤት ተከፍቶላችሁዋልና፣
ኑ! ኣብረን ወደ ልጅነታችን፣ ወደ ጅልነታችን፣ ወደ ፍልስፍናችን እንመለስ። ሌላውማ፣ ያው፣ እትዬ ቦጌ እንደሚሉት …
(ኳንተም የጥናት ክበብን የማያውቋት በጥቂቱም ያውቋት ዘንድ፣ የሚያውቋትና የናፈቋት፣
ትዝታዋ መነሳሳትን ይፈጥርላቸው ዘንድ፣ ስለክበቧ የከተብኳትን ኣጭር ታሪክ፤ በወቅቱ የነበረው ድባብ በውስጤ የፈጠረው ስሜት ያዋለዳቸውን
ኣንዳንድ መጣጥፎችም፣ በዚሁ ሰሌዳችን ላይ ቀስ በቀስ እሰቅልላችሁዋለሁ። እስከዛሬ በደረቅ ወረቀት በምድረ-ሃበሻ ስለበተንኳቸው
ሥራዎቼም የመግቢያም የመውጫም ዓይነት ቅምሻም በዚሁ ሆደሰፊ ሰሌዳችን ላይ ኣኑሬኣለሁ። ማንበብ የሚሻ መነሳሻ ያድርጋቸው፣ ያነበባቸውም
መከለሻ። ኣንብባችሁ ጥያቄ ኣለኝ ያላችሁኝ፣ እማንስማማበት ብዙ ጉዳይ ኣለም ያላችሁኝ፣ እነሆ በሩ ተከፍቷልና ጥያቄዎቻችሁንም ሃሳባችሁንም
ኣጋሩን። እናንተስ እጃችሁ ከምን? … ዘራችሁ ይብዛ! www.opulto.blogspot.com
I am so happy that I say today nothing except: Congratulation!
ReplyDeleteThank you Beti!
ReplyDeleteCongratulations on the opening of this blog! I enjoyed reading every bit of this article. This is really a wonderful place to keep the discourse going. More than a few blogs/discussions these days make simplistic analysis of what is a complex system of thought. In so doing, they carry a risk of either trivializing a particular system of thought/group or unjustly elevating others (myself included). Any discourse of cultures, in my humble view, needs to involve what Alain Locke describes as a deep conviction that there is equivalence among civilizations. As you may agree, this understanding of equivalence does not rule out constructive self-critique. So, I hope to see many old and new faces here, cheers!
ReplyDelete