Sunday, November 15, 2015

የመግደላዊት ማርያም ወንጌል ገጽ 9

የዮሐንስ ወንጌልም የመግደላዊት ማርያም ወንጌል ነው?  
ይህ እጅግ ኣስደንቆኛል። እናንተንም እንደሚያስደንቃችሁ እርግጠኛ ነኝ። ባለፈው፣ መግደላዊት ማርያም የኢየሱስ ፍቅረኛ በመሆን ኣለመሆኗ ጥያቄ ላይ እንደምፅፍ ቃል ገብቼ ነበር። ይህ ኣሁን ያገኘሁት ምስጥር ከዚያም ይልቅ ኣስገራሚ ሆኖ ስላገኘሁት ነው ያንን ለግዜው ያቆየሁት። እኔ እምብዛም የመጽሐፍቅዱስ ደጋሚ ኣይደለሁም። ይህንን ያህል ያፈጠጠ ጉዳይ ዓይኔ ሥር ተደብቆ ሲያልፈኝ መክረሙ ግን “ኣጀብ!” ኣስብሎኛል። ቢያንስ ሲጠይቁ ኣለመስማቴ!
ሰሞኑን ባጋጣሚ የገባሁበት የመግደላዊት ማርያም ጉዳይ ኣስገራሚ የኣድቬንቼር ዓለም ሆኖ ኣገኘሁት። የትኛውንም የዕውቀት ዘርፍ እጣታችን ጫፍ ላይ ላመጣው ዘመን ምስጋን ይግባው! ባለሞያ ኣይደለንም ብለን ከፍለጋ ሳንገታ በመረጥነው የዕውቀት ዘርፍ የቻልነውን ያህል እንጓዝ ዘንድ ጎዳናውን ክፍት ኣድርጎልናል ዘመኑ። እሸት የደረሰለት ያገሬ ገበሬ፣ “እነሆ ቅመሱልኝ!“ እንደሚል፣ እኔም ኣጭር ጉዞዬ ያስጠረጠረችኝን እሸት “እነሆ“ ለማለት ወግ ሆኖ ኣገኘሁት። መቼም ፍለጋ የየራስ ነው። ይህ የዘመኑ ዕድል ግን የሁላችንም ነው። “ቄሱም ዝም፤ መፅሃፉም ዝም!“ እምንልበት ዘመን ካበቃ ሰነበተ። ቄሱ ከተለጎሙ መጽሐፉን እምናናግርባቸው እልፍ ቁልፎች በየጣሪያችን፣ በየጣታችን ሥር ናቸው። ኣማኞች እንደሚሉት ፍርድ የእግዚኣብሔር ነው። እግዚኣብሔር ደግሞ ሚዛኑን በየልባችን ኣኑሯል። የቱም ነፍስ በሌላው ነፍስ ተጠያቂ ኣይሆን ዘንድ የየግል ፍለጋ የዘመኑ ግዴታ ሆኗል። ለኔ፣ ይህ የፍለጋዬ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ ኣይደለም። በመግደላዊት ማርያም ዙርያ ያለው ታሪክ እጅግ ኣጓጊና መሳጭ ነው። ሃሰሳዬ ይቀጥላል። በየራሳችሁ መንገድ በፍለጋው መጀመሪያም መሃልም ሆነ መጨረሻ ላይ ያላችሁ፣ ምናልባት በዚህ መንገድ ኣላለፋችሁ እንደሁ፣ እነሆ የተደነቅሁበት የሰሞኑ ግኝት፡
“የዮሐንስ ወንጌል ደራሲ መግደላዊት ማርያም ናት፤“ ይላል ከድረገፅ ያገኘሁት ኣንድ የጥናት ወረቀት። “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?“ ኣልኩኝ ይህንን ርዕስ እንዳየሁ። ፀሃፊው ማስረጃውን በኣመዛኙ ከዚያው ከዮሐንስ ወንጌል መምዘዙ የመደነቄ መጀመሪያ ሆነ።
የዮሐንስ ወንጌል ከሌሎች ወንጌላት በብዙ መልኩ የተለየ ነው። ከሌሎች ወንጌላዊያን ይልቅ ለኢየሱስ ቅርብ የሆነና በመንፈሳዊ ዕይታውም ከፍተኛ ደረጃን የተቀዳጀ ሰው እንደፃፈው ይታወቃል። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደሚስማሙበት የዚህ ወንጌል ደራሲ ኣይታወቅም። ቀድሞ፣ ደራሲው ሐዋሪያው ዮሐንስ (የዘብዲዮስ ልጅ) እንደሆነ ይታሰብ ነበር። ለዚያ እምነት የተገኘው ማስረጃ፣ Irenaeus የተባሉ የሁለተኛው ክፍለዘምን ጳጳስ የልጅነት ትዝታ ብቻ ሆኖ ተገኘ፡ “በልጅነቴ ጳጳስ Polycarp ነግረውኝ ነው፤“ ያሉት። ይህ እምነት እውነት እንዳይደለ ብዙ ኣጥኚዎች ይስማማሉ። ከነዚህ ውስጥ የወንጌሉ ትክክለኛ ደራሲ በዚያው ወንጌል ውስጥ በተደጋጋሚ የተጠቀሰው ክርስቶስ እጅግ ይወደው የነበር ደቀመዝሙር ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ወንጌሉ ራሱ ያንን ይመሰክራል። ያ ደግሞ ሐዋሪያው ዮሐንስ ኣይደለም።  
ካስደነቁኝ ነገሮች ኣንዱ እንግዲህ ይህ ነው። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ለክርስቶስ ከሌሎች ደቀመዛሙርት ሁሉ ይልቅ የቀረበ፤ ከኢየሱስ ጥምቀት ጀምሮ ይከተለው የጀመረ፣ ነገር ግን ስሙ ሆን ተብሎ በሚመስል መልኩ ያልተጠቀሰ፣ ኣንድ ምስጥራዊ ደቀመዝሙር መኖሩ ነው። ይህ ደቀመዝሙር ክርስቶስን ያን ያህልከ ይቀርበው ከነበር፣ ስሙ ኣለመጠቀሱ ለምን ይሆን? ትሉ ይሆናል። ያ የኔም ጥያቄ ነበር። መልሱ ከምር፣ “ወይ ግሩም!” ኣስብሎኛል። ስለ መግደላዊት ማርያም ከማውራታችን በፊት፣ ይህ ደቀመዝሙር ከክርስቶስ ጋር ምን ያህል ይቀራረብ እንደነበር ለማሳየት እርሱ የተጠቀሰባቸውን ኣናቅፅት ማየት ግድ ይለናል (ረዘም ያሉ ጥቅሶችን በትዕምርተ-ጥቅስ ቀንፌ ስለማሳጥራቸው ለተሟላ መረጃ መፅሃፍቅዱሳችሁን መግለፅ ይኖርባችሁ ይሆናል)፡
1.       ዮሐ 1፡ 35-40 - "…[መጥምቁ] ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ቆመው ነበር፣ ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ - እነሆ የእግዚኣብሔር በግ ኣለ። ሁለቱ ደቀመዛሙርት ሰምተውት ኢየሱስን ተከተሉት። …" ምናልባትም እኚህ ኢየሱስን ኣውቀው የተከተሉ የመጀመሪያ ደቀመዛሙርት ናቸው። ቀድመው መሲሁ እንደሚመጣ ኣውቀው ሲፈልጉት የነበር ይመስላል። በኢየሱስ ግብዣ ወደ እርሱ ቤት ሄደው ኣብረውት ዋሉ። ከነዚህ ሁለት ደቀመዛሙርት ኣንዱ እንድርያስ እንደሆነ ዝቅ ብሎ ተጠቅሷል። የሌላው ማንነት ኣልተጠቀሰም። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ይህ ስሙ ያልተጠቀሰው ሰው ገና የኢየሱስ ደቀመዝሙር መሆኑ ነበርና፣ "ኢየሱስ የሚወደው ደቀመዝሙር" ኣልተባለም። ቢሆንም፣ በሌሎች ቦታዎች ላይ "ኢየሱስ የሚወደው" የተባለው ይኸው ሰው እንደሆነ ኣንዳንድ የመፅሃፍቅዱስ ኣጥኚዎች ያምናሉ።
2.       ዮሐ. 13፡ 23-26፡ "ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀመዛሙርቱ ኣንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ/… there was leaning on Jesus’ bosom one of his disciples, whom Jesus loved…(King James Bible)" እነሆ ተወዳጁ እዚህ በግልፅ ተጠቀሰ። ስሙ ግን ኣሁንም ተዘልሏል። ያን ተወዳጅ ጴጥሮስ በዓይኑ ጠቅሶት የሚከዳው ማን እንደሁ ኢየሱስን እንዲጠይቅ ይጠይቀዋል።
3.       ዮሐ. 18፡15-16፡ ኢየሱስ ለእስር/ለጥያቄ ከተያዘ በሁዋላ፣ "ስሞዖን ጴጥሮስም፣ ሌላውም ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። …" ያ ደቀመዝሙር በሊቀካህናቱ ዘንድ የታወቀ ስለነበር፣ በእስር ቤቱ በር ላይ ጴጥሮስ ተከልክሎ ሲቀር እርሱ ገብቶ ይመለስና በረኛዋን ኣስፈቅዶ ጴጥሮስን ያስገባዋል። እዚህ ላይ፣ ይህ ደቀመዝሙር "ተወዳጁ" ተብሎ ባይጠራም፣ ስሙን ለመጥቀስ ያልተፈለገ በሚመስል መልኩ፣ "ሌላውም ደቀመዝሙር" ተብሎ ታልፏል። ይህም ሰው ያ ኢየሱስ የሚወደው ደቀመዝሙር እንደሆነ የጥናቱ ኣቅራቢዎች ያስባሉ።  
4.       ዮሐ. 19፡25-27፡ "… ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በኣጠገቡ ቆመው ባየ ጊዜ …" እናቱን ለዚያ ይወደው ለነበረው ደቀ መዝሙር ኣደራ ሰጠ፤ ደቀመዝሙሩም ይዟት ወደቤቱ ሄደ። እዚህ ቦታ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ መግደላዊት ማርያም እና ያ ተወዳጅ ደቀመዝሙር በኣንድ ጊዜ ኣንድ ላይ የነበሩ ሁለት የተለያዩ ሰዎች እንደሆኑ ተጠቅሰዋል። ግን፣ ይህንን ጥቅስ በትኩረት ያየ የሆነ ስህተት እንዳለበት ይረዳል። በዚህ ላይ ወደሁዋላ እንመለስበታለን።
5.       ዮሐ. 20፡ 1-11፡ "… መግደላዊት ማርያም … ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሉ ኣየች። እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ …" ኢየሱስ መነሳቱን ትነግራቸዋለች። ጴጥሮስና ተወዳጁ ደቀመዝሙር ሮጠው ወደመቃብሩ ይሄዳሉ፤ ኢየሱስንም ያጡታል። በእነዚህም ጥቅሶች ውስጥ ተወዳጁን ደቀመዝሙር በስም ላለመጥቀስ ጥንቃቄ የተደረገ ይመስላል። ተወዳጁ ደቀመዝሙርና መግደላዊት ማርያም በኣንድ ላይ እንደነበሩ ለሁለተኛ ጊዜ ተጠቅሷል። ይህ ሁኔታ የተገለፀባቸውን ጥቅሶ በትኩረት ብናይ ልክ እንደላይኛው (ተ.ቁ. 4) ሁሉ እዚህም የሆነ የተፋለሰ ነገር እንዳለ ይታያል። በዚህ ላይም ቆየት ብዬ እንመለስበታለሁ።
6.        ዮሐ. 21፡7 - ጴጥሮስና ሌሎች ደቀመዛሙርት ዓሳ በማጥመድ ላይ ሳሉ ኢየሱስ ይገለጥላቸዋል። ሌሎች ደቀመዛሙርት ማንነቱን ኣላወቁም። "…ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር ጴጥሮስን ጌታ እኮ ነው ኣለው።" በእዚህ ቦታ የተገለጠላቸውን ኢየሱስ ያ ተወዳጅ ከጴጥሮስም ቀድሞ ኣወቀው። ጴጥሮስ ራቁቱን ስለነበር (በሃፍረት ይሁን በድንጋጤ ኣይታወቅም፤) ተሸፋፍኖ ራሱን ወደሃይቁ ወረወረ።
7.       ዮሐ. 21፡20-23 - "ጴጥሮስ ዞር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀመዝሙር ሲከተለው ኣየ፡ እርሱም ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ - ጌታ ሆይ ኣሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው ያለው ነበር።" ጴጥሮስ የዚህን ደቀመዝሙር መከተል ያልወደደው ኣይነት፣ "ጌታ ሆይ፣ ይህስ እንዴት ይሆናል?" ብሎ ኢየሱስን ይጠይቀዋል። ኢየሱስም፣ ኣንተ ስለሱ ምን ኣገባህ? ዝም ብለህ እኔን ተከተለኝ፤ በሚል ድምፀት ይመልስለታል፡ "እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን ኣግዶህ? ኣንተ ተከተለኝ…" ይህ የኢየሱስ ሚስጥራዊ ኣገላለፅ ያ ተወዳጅ ደቀመዝሙር በስጋም ሕያው ሆኖ እንደሚኖር ሌሎች ደቀመዛሙርት እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል።
8.       ዮሐ. 21፡ 25 - ይህ ከላይ የተጠቀሰውን በዚያ ተወዳጅ ደቀመዝሙር ላይ የተደረገውን ውይይት የሚከተል ጥቅስ የወንጌሉ ፀሃፊ ያ ተወዳጅ እንደሆነ ይናገራል፡ "ስለ እነዚህም የመሰከረ፣ ይህንንም ጽፎ ያለ ይህ ደቀመዝሙር ነው፤ ምስክሩም እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።"
ይህ ተወዳጅ የዘብዲዮሱ ዮሐንስም፣ ይሁዳም፣ እንዳይደለ ግልፅ ማሳያዎች ኣሉ። እርሱ፣ ከኢየሱስ ጥምቀት እስከእርገቱ፣ ከዚያም በመንፈስ ተገልፆ ሌሎቹን ደቀመዛሙርት ባፅናናበት ጊዜ ሁሉ ከኢየሱስ ጋር ነበር። ይህ ሰው በስም ከተጠቀሱት ከኣስራሁለቱ ደቀመዛሙርት ከየትኛውም ጋር ኣንድ ተደርጎ የተጠቀሰበት ቦታ የለም። ሁሉም ቦታ፣ "ሌላው ደቀመዝሙር፣" ወይም "ክርስቶስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር፣" በሚል ብቻ ነው የተጠቀሰው። በቅድስናውና ለኢየሱስ ባለው ቅርበት ከጴጥሮስም ሆነ ከሌሎች ደቀመዛሙርት ሁሉ የላቀ እንደሆነ በግልፅ ይታያል። ማህበራዊ ግንኙነቱና ተፅዕኖውም ከፍተኛ መሆኑ በእስርቤቱ በር ላይ የሆነው ታሪክ ያሳረዳል። ታዲያ እንዲህ ያለ "የወንጌል ኮከብ" ሊባል የሚችል ደቀመዝሙር ስሙ መደበቁ ለምን ነው? ኢየሱስ ስም ኣልባ ኣስራሶስተኛ ደቀመዝሙር ነበረው? ከ12ቱ ደቀመዛሙርት እንደኣንዱ እንኳ ኣልተቆጠረም። ከሌሎች መብለጥ ያሳንሳል? ወይስ የሆነ ድብቅ ሚስጥር ወይም ሴራ ኣለ? ምናልባት ያ ተወዳጅ ሴት ስለሆነ ይሆን? ለኢየሱስ በኣካልም ጭምር የነበረው ቅርበት ልክ እንደልዩ ምልክት ከኣንዴም ሁለቴ መጠቀሱን (በእራት ላይ የኢየሱስን ደረት ተደግፎ/ተጠግቶ መቀመጡን) በዛሬ ዓይን ስናይ፣ ያ ሰው ሴት እንደሆነ ያስጠረጥረናል። ከሌሎች ደቀመዛሙርት እንደኣንዱ ያልተቆጠረውና ስሙ ያልተጠቀሰው በዚያ ምክንያት ይሆን? እና ሴት ከነበር ለምን በታሪኩ ውስጥ እንደወንድ ተገለፀ? እውን የሆነ ስህተት ኣልያም ሴራ ኣለ?   
የጥናቱ ባለቤቶች፣ ሆን ተብሎ የተሰራ ሴራ ኣለ፤ ነው እሚሉት። ወንጌላትንና ሌሎች የታሪክ መዛግብትን መሠረት ኣድርገው፣ በወንድ ፆታ የተገለፀው ይህ ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር በእርግጥ መግደላዊት ማርያም እንደሆነች ያስረዳሉ። እንዲያ ከሆነ ደግሞ፣ የዮሐንስ ወንጌል ደራሲ እርሷ ነች ማለት ነው። (ድሮ፣ በእጁ የፃፈ ብቻ ሳይሆን ትምህርቱን በቃል ያስተላለፈም እንደደራሲ ይቆጠር የነበር ቢሆንም፣ በወንጌሉ መጨረሻ ላይ ያለው መደምደሚያ ወንጌሉን ያ ተወዳጅ ጻፈው ነው እሚል። ያ የመደምደሚያ ዓረፍተነገር የሌላ ሰው ሊሆን ይችላል።) እንዲያ ከሆነ፣ ኣሁን የምናነበው የዮሐንስ ወንጌል ኦሪጅናሌው ኣይደለም ማለት ነው። ምክንያቱም መግደላዊት ማርይም ሴትም ወንድም መሆን ኣትችልም። የሆነ ሰው ወንጌሉን ኤዲት ኣድርጎታል (ኣርትዖት ሰርቶበታል) ማለት ነው። ግን ግን፣ ይህንን ሙጉት እንቀበለው ቢባል እንኳ ያንን ለውጥ ያደረገው ሰው ኣንዳንድ ቦታ የማርያምን ስም ሲያወጣና ፆታዋን ሲቀይር፣ በሌላ ቦታ ለምን እንዳለ ተወው? በተጨማሪም፣ መግደላዊት ማርያም እና ያ ተወዳጅ በኣንድ ቦታ በኣንድ ላይ ተገኝተው የነበር ሁለት ሰዎች እንዴት ሊሆኑ ቻሉ? ለነዚህ ጥያቄዎችም መልስ ኣላቸው የዚህ ጥናት ባለቤቶች። በተለይ መግደላዊት ማርያምና ያ የኢየሱስ ተወዳጅ እንደሁለት ሰው የቀረቡባቸው ቦታዎችን ወንጌሉ ተቀይሯል ለሚለው ሙጉታቸው እንደ ግልፅ ማስረጃ ነው እሚያቀርቡት። ምክንያቱም ቢያንስ በነዚህ ሁለት ቦታዎች ያልተገቡ ለውጦች እንደተደረጉ የሚያሳዩ የማያከራክሩ የኣተራረክና የመዋቅር ስህተቶች ኣሉ። እኚህ ሰዎች የሚሉት እውነት ከሆነ፣ የወንጌል ምሁራንም ሆነ ቤተክርስቲያናት ሊመልሱት የሚገባቸው ታላቅ ጥያቄ ይደነቀርባቸዋል ማለት ነው። 

በእኔ ሚዛን የነዚህ ሰዎች ማስረጃ ኣሳማኝ ነው። ያንን ያመነ ሰው ደግሞ፣ መግደላዊት ማርያም የትኛውም ደቀመዝሙር ሊስተካከለው ከሚችለው በላይ የከበረ ደረጃ እንደነበራት ያምናል። እነዚህ ማስረጃዎች እናንተንም ያሳምኑ እንደሁ ኣይታችሁ ትፈርዱ ዘንድ፣ ወይም የመልስ መከራከሪያ (counter argument) ታቀርቡ ዘንድ፣ ማረጋገጫዎቹን በቀጣዩ ጦማሬ ኣስነብባችሁዋለሁ። የለም ማስረጃውን ባይናችን ማየትና የራሳችንን ጥናት ማድረግ ኣለብን ካላችሁ፡ ይህ ፅሁፍ የተመሠረተበት የጥናት ወረቀት እነሆ፡ R.K. Jusino, 1998፡ Mary Magdalene: Author of the Fourth Gospel?

Wednesday, November 11, 2015

የመግደላዊት ማርያም ወንጌል ገፅ 8

መግደላዊት ማርያም ሴተኛ ኣዳሪ ኣልነበረችም!
የስህተቱ መጀመሪያ ጳጳስ ግሪጎሪ (Pope Gregory) ናቸው ኣሉ። እኝህን ካህን ያምታታቸው ደግሞ ሰባት የሚሆኑ ማርያሞች በወንጌል ውስጥ መጠቀሳቸው ነው። በእርሳቸው የ591ዓ.ም ስብከት ምክንያት ቅድስት መግደላዊት ማርያም የተሳሳተ ማንነት ሰለባ ተደረገች። በክርስትና የጠዋት ታሪክ ውስጥ የሴቶችን የመሪነት ሚና ለማኮሰስ ይደረግ ከነበረው ጥረት ጋር ተዳምሮ ይህ ስብከት እንደእውነት (በካቶሊኩም፣ በኦርቶዶክሱም፣ በፕሮቴስታንቱም) ቤተክርስቲያናት ተስተጋባ። ክብር ጎደፈ፤ ታሪክም ተፋለሰ። እንጂማ፣ በወንጌል ውስጥ ኣንድም ቦታ መግደላዊት ማርያም ሴተኛ ኣዳሪ ነበረች የሚል ቃል የለም። ስህተቱንም እውነቱንም ጥቂት ጥቅሶችን እየጠቀስን እንይ፡
በወንጌል ውስጥ መግደላዊት ማርያምን ቀድሞ የሚያስተዋውቀን ሉቃስ ነው (ሉቃ. 8፡ 1-3)። ይህ ምዕራፍ ሉቃስ ኢየሱስን በሽቱ ስለቀባች ኣንዲት ሃጢኣተኛ ሴት ከተረከ በሁዋላ የሚከተል ነው። የጠቀስናቸው ካህን መግደላዊት ማርያምን ያምታቱት ከዚህች ባለሽቱ ሴት ጋር ነው። እንዲህ ብለው፡
”ሉቃስ ሃጢኣተኛ የሚላት ያች ሴት፣ ዮሐንስ ደግሞ ማርያም የሚላት፣ እሷ ሰባት ኣጋንንት የወጡባት ሴት እንደሆነች እናምናለን። እኚህ ሰባቱ ኣጋንንት የሚወክሉት ርክሰት እምንላቸውን ነገሮች ሁሉ ካልሆነ ሌላ ምንን ሊሆን ይችላል? … ወንድሞች ሆይ፣ ያች ሴት ከዚያ ቀድም ያንን ሽቱ በሃጢኣት ስራዋ ጊዜ ኣካሏን ለመቀባት ትጠቀምበት ነበር።”
ይህንን ከዬት ኣመጡት ኣባው? ወንጌሉን በትኩረት ስናይ ሉቃስ ቀድሞ የጠቀሳት ሃጢኣተኛ ሴት መግደላዊት ማርያም እንዳይደለች ግልፅ ይሆናል። ሉቃስ በምዕራፍ 7 መጨረሻ ግድም ስለዚች ሴት ከተረከ በሁዋላ በምዕራፍ 8 መጀመሪያ ላይ መግደላዊት ማርያምን እንደኣዲስ ያስተዋውቃታል፡ ”… ከደዌ ተፈውሰው የነበሩ ኣንዳንድ ሴቶች፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም፣ …” (ሉቃ. 8፡2) ወንጌላዊው መግደላዊት ማርያምን ከጥቂት ዓረፍተነገሮች ቀድሞ ካነሳት ስሟ ካልተጠቀሰው ሴት ጋር ኣለማያያዙና መግደላዊት ማርያምን እንደኣዲስ ማስተዋወቁ እርሷ ከዚያች ሴት ጋር ኣንድ እንዳይደለች ኣያሳይም? ጳጳሱን ካምታቱኣቸው ነገሮች ኣንዱ ኢየሱስን በሽቱ ስለቀቡ ሴቶች የተነገረው ተረክ መብዛቱ ይሆን ይሆናል፡
1.       ከላይ ያየነው (ሉቃስ 7፡ 36-50)፡ ቦታው ኣልተጠቀሰም (በገሊላ)፣ ቤቱ የለምፃሙ የሲሞን፣ ባለሽቱዋ ሴት - ስሟ ያልተጠቀሰ፤
2.       ማቴ. 26፡ 6-12፡ ቦታው በቢታኒያ፣ ቤቱ የለምፃሙ የሲሞን፣ ባለሽቱዋ ሴት - ስሟ ያልተጠቀሰ፤
3.       ማር. 14፡ 3-9፡ ቦታው በቢታኒያ፣ ቤቱ የለምፃሙ የሲሞን፣ ባለሽቱዋ ሴት - ስሟ ያልተጠቀሰ፤
4.       ዮሐ. 12፡ 1-8፡ ቦታው በቢታኒያ፣ ቤቱ የኢየሱስ ወዳጆች የነበሩት የኣልዓዛር፣ የማርያም፣ እና የማርታ። የባለሽቱዋ ሴት ስም፣ ማርያም (ይህችኛዋ የቢታኒያ ማርያምም መግደላዊት ማርያም ኣይደለችም - ዮሐ፡ 11፡ 1-4)።
5.       በሁሉም ወንጌላት ውስጥ የኢየሱስን መቃብር የወረደ ኣካል በሽቱ ለማበስ ከሄዱ ሴቶች ውስጥ መግደላዊት ማርያም በቀዳሚነት ተጠቅሳለች።
እንግዲህ መግደላዊት ማርያም ኢየሱስን በሽቱ ከመቀባት ጋር ተያይዞ በግልፅ የተጠቀሰችሁ ኢየሱስ ከተሰቀለ በሁዋላ ብቻ ነው። ያኔ ደግሞ በኣካል ኣላገኘችውም፣ ኣልቀባችውምም። ያ እርሷን እግሩን በሽቶ ከቀባችዪቱ ሴት ጋር ኣንድ ኣድርጎ ለማንበብ ምን መሠረት ይሰጣል?
በኣንፃሩ፣ ወንጌላት ሁሉ መግደላዊት ማሪያምን እጅግ በከበረ ኣገላለፅ ያነሱኣታል፡
1.       መግደላዊት ማርያምና ሌሎች ሴቶች ክርስቶስን በየሄደበት ሁሉ ይከተሉትና በገንዘባቸውም ያገለግሉት ነበር። (ሉቃ 8፡2)
2.       ወንዶች ደቀመዛሙርት ሁሉ ሲሸሹ (ማቴ. 26፡56) መግደላዊት ማርያም ከሌሎች ሴቶች ጋር በኢየሱስ የስቃይና የስቅላት ሰዓት ኣብራው ነበረች። (ማቴ. 27፡56፣ ማር. 15፡40፣ ሉቃ. 23፡ 55፣ ዮሐ. 19፡25)
3.       በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ብቻዋን (በሌሎች ወንጌላት ከሌሎች ሴቶች ጋር፣) የኢየሱስን ባዶ መቃብር ለማግኘት ቀዳሚዋ ነች። (ማቴ. 28፡10፣ ሉቃ. 24፡10፣ ዮሐ. 20፡2)
4.       በዮሐንስና በማርቆስ ወንጌላት ውስጥ ብቻዋን (በሌሎች ውስጥ ከሌሎች ሴቶች ጋር) የኢየሱስን የተነሳ ኣካል ለማየት ቀዳሚዋ ናት። (ማቴ. 28፡29፣ ማር. 16፡9፣ ዮሐ. 20፡11)
5.       የክርስቶስን ትንሳዔ ለሌሎች ታበስር ዘንድ ተልዕኮ የተሰጣት ብቸኛዋ ሴት ናት። (ዮሐ. 20፡15)
6.       በወንጌል ውስጥ የሴቶች ስም በተነሳ ቁጥር በኣብሳኛው ቀድሞ የሚጠቀሰው የእርሷ ስም ነው። ይህ ከሌሎች ሴቶች ሁሉ ይልቅ ያላትን የከበረ ደረጃ ኣያመለክትም?
እንግዲህ መግደላዊት ማርያም ወንጌል ይህንን ያህል ክብር የሚሰጣት ክርስትና ግን የሚገባትን ክብር የነፈጋት ቅድስት ሴት ነች። እርሷ ሴተኛ ኣዳሪ እንደነበረች የሚያመለክት ምንም ማስረጃ በወንጌል ውስጥ የለም። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እንዲያ ትታይ ዘንድ ምክንያት ለሆኑት ለጳጳስ ግሪጎሪ፣ ”ማነው ምንትስ?” የሚለውን የፀጋዬ ገ/መድህንን ግጥም ጋብዘን ለዛሬ በዚህ እናብቃ። በሚቀጥለው ጦማሬ፣ ”እውን መግደላዊት ማሪያም የኢየሱስ ሚስት ነችን?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እሞክራለሁ።

እነሆ የመግደላዊት ማርያም ወንጌል ገፅ 8


Saturday, November 7, 2015

የመግደላዊት ማሪያም ወንጌል - ገፅ 7

ከ30 የማያንሱ ወንጌሎች ነበሩ ኣሉ። (ታሪክንም እንደተረት “ኣሉ“ ብለው ቢያወሩት ሳያምርበት ይቀራል?) በ4ኛው ምዕተ-ዓመት በኒቂያ የተሰባሰቡ ካህናት ዛሬ “ኣዲስ ኪዳን“ በሚል እምናውቃቸውን ኣራቱን ወንጌላትና መልዕክቶች መርጠው፣ “የኢየሱስን ትምህርት የሚወክሉቱ እኚህ ናቸው!“ ብለው ወሰኑ። ያኔ ክርስትና ዛሬ በምናውቀው መልክ ተበጀ። ያ ጉባዔ ባይኖር ኖሮስ? ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ኣንዱ ይህ ነው፦ ኣሁን ወደኣማርኛ መልሼ ላጋራችሁ የጀመርኩት ወንጌል ከቅዱሳን ኣናቅፅት እንደኣንዱ ተቆጥሮ ይሰበክ፣ ይመለክ ነበር። በተጨማሪም፦ የዓለም ታሪክ፣ የዕውቀት ታሪክ ልዩ ይሆን ነበር። ሴትነትም፣ ፆታዊ ፍቅርም ይበልጥ ይከበር ነበር። በእርግጥ የሆነው ግን ይህ ነው፦ ከኒቂያ ጉባዔ በሁዋለ የተመረጡት ወንጌላት በኣንድ መድበል ተጠረዙ። የቀሩት ተወገዙ፣ ተገነዙ። እናም፣ ያልተመረጡቱ ወንጌላት በኣብዛኛው ሲጠፉ ጥቂቶቹ በሌሎች መዛግብት ውስጥ በእግረ-መንገድ መልክ ተጠቅሰው በስም ብቻ ከመቃብር በላይ ቆዩ። ከ2000 ዓመታት የመቃብር ህይወት በሁዋላ፣ በባለፈው ምዕተ ዓመት ተዘንግተው ከነበሩ ወንጌላት ውስጥ የጥቂቶቹ ቅጂዎች በየኣጋጣሚው ተገኝተው ዳግመ-ትንሳዔን ተቀዳጁ። ከነዚህ ውስጥ እ.ኤ.ኣ በ1947ዓ.ም የተገኙት “የቀይ ባህር ጥቅልሎች“ እና “የናግ ሃማዲ ላይብራሪ“ በመባል የሚታወቁቱ ጥንታዊ መዛግብት የክርስትና ታሪክ በዓዲስ ዓይን ይታይ ዘንድ ትልቁን ኣስተዋፅዖ ኣድርገዋል።  እርግጥ ነው፣ ይህ ክርስትናን ኣልቀየረውም፤ ኣይቀይረውምም። ምክንያቱም ክርስትና መፅሃፍ ቅዱስ ብቻ ኣይደለም። ታሪክም ጭምር ነው። ባህልም ጭምር ነው። ተቋምም ጭምር ነው። ስልጣንም፣ ሃብትም ጭምር ነው። ይበልጥ ብልጣብልጥ ለሆኑቱ፣ እማይነጥፍ የጥገት ላም። እንደቆዳ ቀለም፣ መለያም መኩሪያም ጭምር ነው ክርስትና። እስከነጥቅሱ፣ “ነብር ዥጉርጉርነቱን ኣይቀይርም!“ ነው መልሱ። ቅዱሳን ቃላቱ የዚህ ውስብስብ ሥርዓት ኣንድ ገፅታ ብቻ ናቸው። ቃላት ከምድር ቀርቶ ከሰማይ ቢወርዱም ክርስትናን ኣይቀየርም። 


ይህ የመግደላዊት ማሪያም ወንጌል በ1896ዓ.ም. ኣከባቢ በግብፅ ውስጥ በኮፕቲክ ቋንቋ ተፅፎ ከተገኘ ፓፒረስ የተወሰደ ነው። ወንጌሉ ተሟልቶ ባይገኝም ስለክርስትና የጠዋት ታሪክና ስለመግደላዊት ማሪያም ኣዳዲስ ነገሮችን እናውቅ ዘንደ በቂ መልዕክቶችን ይዟል። ለመሆኑ፣ መግደላዊት ማሪያም ማን ናት? መግቢያዬን ላለማርዘም ይህንን ጥያቄ በሚቀጥሉት ጦማሮቼ ብመልሰውስ? ባጭሩ ግን ይህንን ልበል፦ ይህችን እንስት ኣዲስ ኪዳን በሽርፍርፉ ጠቅሷታል። የክርስትና ታሪክ ኣዛብቶ ስሏታል። በዚህ ወንጌሏ ውስጥ እርሷ እኛ ከሰጠናት ስም ይበልጥ ቅድስት፣ ከፃፍንላት ታሪኳም በላይ ንፅህት ነች። 

በከፊል የተገኘው የመግደላዊት ማሪያም ወንጌል የተለያዩ የእንግልዝኛ ትርጉሞች ኣሉት። ከነዚህ ውስጥ እኔ ያነፃፀርኩት ሶስቱን ብቻ ነው። ይህ የኔ ትርጉም በኣመዛኙ የተመሠረተው በJean-Yves Leloup (1997) የእንግልዝኛ ትርጉም ላይ ቢሆንም ኣንዳንድ ዓረፍተነገሮችን ለራሴም ለኣንባቢዎቼም ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ ሌሎችን ትርጉሞች ተጠቅሜኣለሁ። ከዛሬ ጀምሮ የወንጌሉን የኣማርኛ ትርጉም የማሰላሰያ ቀናትን እየዘለልኩ ገፅ በገፅ ኣቀርብላችሁዋለሁ። እንደኣስፈላጊነቱ ስለተጠቀምኩባቸው ቃላትና ሃረጎች ማብራሪያ እሰጣለሁ። ይህ የመጀመሪያው ገፅ (ገፅ 7) ነው። መድረኩ ለጥያቄም ለኣስተያየትም ክፍት ነው።

Thursday, November 5, 2015

The Holiest Sinner

A Quote from Catch Your Thunder: Rendezvous With the End

ፍፁም ቅዱሷ ሃጥዓተኛ

ከሜሮን ጋር ሻይ ቡና እያልን ስለመንፈሳዊነት (mysticism) ስናወጋ መግደላዊት ማሪያም ተነሳች። “ካች ዩር ተንደር” በህትመት ሂደት ላይ ነበር ያኔ። ከረቂቁ ላይ ይህችን ቅድስት የሚያነሳን ኣንድ ምዕራፍ ኣነበብኩላት። (ከታች በስዕሉ ላይ የጠቀስኩትን።) በሌላ ጊዜ ስንገናኝ ሜሮን “የመግደላዊት ማሪያም ወንጌል“ (በእንግሊዝኛ) የሚለውን የJean-Yves Leloup መፅሃፍ ኣዋሰችኝ። እንዲህ በቀላሉ ኣገኘዋለሁ ብዬ ያላሰብኩት መፅሃፍ ነበር። “ተባረኪ ኣቦ!” ብዬ ተቀበልኳት። መፅሃፉን ሳነብበው ስለመግደላዊት ማሪያምም ሆነ ስለክርስትና ኣላውቃቸው የነበሩ ብዙ ነገሮችን ኣገኘሁበት። ይህ ክርስትና ብዙዎቻችን ከምናስበው ውጪ ብዙ ድብቅ ታሪኮች እንዳሉት እና ኢየሱስ ያስተማረው ክርስትና እኛ ጋ ሙሉ በሙሉ እንዳልደረሰ ከሚያሳዩ መፅሃፍት ኣንዱ መሆኑ ነው። “ፍፁም ቅዱሷ ሃጥዓተኛ“ የሚለው ሃሳብ ይህንን መፅሃፍ ከማንበቤ በፊት የነበረኝ ዕይታ ነበር። ኣሁን ግን ሃጥዓተኛነትን ከመግደላዊት ማሪያም ጋር ኣገናኝቶ ማሰብም ራሱ “ይቅር በለኝ!“ የሚያስብል እንደሁ ተረድቻለሁ። (እዚህ በተለይ በክርስትና ተረክ ተፅዕኖ የተበጀውን የቀድሞ ዕይታዬን ለማሳየት ብቻ ተጠቀምኩበት።) በሚቀጥሉት ጦማሮቼ ከጠቀስኩላችሁ መፅሃፍ ያገኘሁዋቸውን ኣንዳንድ ነገሮች ወደኣማርኛ መልሼ ላጋራችሁ ተዘጋጅቻለሁና ተጋበዙ፣ ተገባበዙልኝ። እተረጉመው ዘንድ የስህን (ዶ/ር) ቀና ግፊት ጉልበት ሆኖኛልና ለሜሮንና ለእርሷ ምስጋና!

Sunday, November 1, 2015

ድህነት ታሪክ የለውም

ድህነት ሕይወት የለውም። ድህነት ታሪክ የለውም። ቅርስም ውርስም ኣይደለም ድህነት። ጥላህ እንጂ ማተብህ ኣይደለም ድህነት። ስላጣህ ደሃ ነኝ፣ ትንሽ ነኝ ኣትበል። በሙሉ ልብ በብርሃኑ ላይ ከቆምክ ድህነት ኣብሮህ ኣይኖርምና። ለድህነት ሕይወትም ልብም እምትሰጠው ኣንተ ነህ። ለእርሱ የገበርከውን ሕይወት ያህል ኣንተ ሕይወት ታጣለህ። ራስህ ሞተህ ድህነት እንዲኖር እምትፈቅድ ኣንተ ማነህ? በፈጠረህ፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ ኣትበለኝ!