Sunday, October 25, 2015

የእናትህ/ሽ ኃይል ምንጩ ምንድነው?

እያንዳንዱ ሰው ሊናገረው የሚሻው ታሪክ ኣለው፡፡ ኣብዛኛው ሰው ስለእናቱ የሚናገረው ታሪክ ኣለው፡፡ ሴታዊት (https://www.facebook.com/Setaweet-336495249877408) በመጪ ፕሮግራማቸው ላይ እናገር ዘንድ ዕድሉን ሰጡኝ፡፡ እምናገርበት ርዕስ ገና ኣልተወሰነም፡፡ በበኩሌ፣ በሥራዎቼ በማሰስ ላይ ስላለሁት የሴቶች ኃይልና ሚና ብናገር ደስ እንደሚለኝ ሃሳብ ኣቀረብኩ፡፡ “ካች ዩር ተንደር/Catch Your Thunder፣” ሕንዴኬን፣ ሳባን፣ እና ኒያቢንጊን ስለመሳሰሉ ኃያል ሴቶች ዳግመ-ትንሳዔ የሚያወራ ተረክ ነው፡፡ ስለሴቶች ያለኝ ዕይታ በኣመዛኙ የተቀረፀው በእናቴ፣ በኣያቴ፣ እና በእምነቴ ነው፡፡ በሥራዎቼ ውስጥ እናቶቼ ላሳደሩብኝ ተፅዕኖዎች ሰፊ ባህላዊ መሠረት ለማግኘት እየሞከርኩ ነው፡፡ እናቴ በብዙ ሰዎች የተወደደች የብዙዎች እናት ነበረች፡፡ ሃይማኖትና የኑሮ ደረጃ ሳይለይ ብዙዎች ወዳጆቿ ነበሩ፤ የጎዳና ላይ የኔብጤዎችን እና ኣስፈራሪዎችን ጨምሮ፡፡ የተፅዕኖዋም ልኬት የተወዳጅነቷን ያህል እንደሁ ኣስባለሁ፡፡ ግን፣ እሷ የታወጀላት ግብረሰናይ ወይም የሆነ ማኅበር መሪ ኣልነበረችም፡፡ በቃ፣ እናት ነበረች፡፡ በቤት ውስጥም ቢሆን ተፅዕኖዋ የሚከወነው በእናታዊ መንገዶቿ ነበር፡፡ የሷ ባህሪያት ዛሬ እንደሞዴል በምንወስዳቸው ሴት መሪዎቻችን ውስጥ ይታያሉ? በትንሹ፡፡ ዛሬ፣ ከሌሎች ባህሎች የሴትነት ሮል ሞዴሎች (የሚና ተምሳሌቶች) ወደኛ ባህል ሲሰርጉ እናያለን፡፡ ብዙዎቻችን እነዚያን ሞዴሎች በቤታችን እና በመንደራችን ውስጥ ከምናውቃቸው ልባም/ኃያል ሴቶች ጋር ለማጣጣም ይከብደናል፡፡ ብዙውን ጊዜ፣ “መገናኛ ብዙሃን ሊጭኑብን ከሚፈልጉት የሴትነት ሞዴል የተለየ ሞዴል ኣያስፈልገን ይሆን እንዴ?” ብዬ ኣስባለሁ፡፡ ያ ከረጅም ግዜ ጀምሮ ልፈታው ጥረት በማድረግ ላይ ያለሁትን እንቆቅልሽ ሰጠኝ፡- ኃያል ሴት፣ ልባም ሴት፣ የተሰራችው ከምንድነው? ኃይሏ መተግበር ያለበትስ እንዴት ነው? የምፅፋቸው ታሪኮች እኔ ጠንካራ በምላቸው ሴቶች የተሞሉ ናቸው፡፡ ኣንተም/እንቺም ኃያል የምትላ/ያት ሌላ ዓይነት ሴት፣ ልትናገረ/ሪው እምትሻ/ሺው ሌላ ታሪክ መኖሩ እርግጥ ነው፡፡ ይህንን ታሪክህ/ሽን ልታጋራ/ሪን ብትችል/ዪ መልካም እንደሚሆን አሰብኩ! ምናልባት ኣማራጭ የሴትነት ሞዴሎችን ማግኘት እንችል ይሆናል፡፡ ምናልባትም የሴታዊት ውይይታችን በዚህ ዳብሮ ሊቀርብ ይችል ይሆናል፡፡ በዚህ ብንጀምርስ፡ የእናትህ/ሽ ኃይል ምንጩ ምንድነው? ወይም፣ ጥንካሬዋ እምን ላይ ነው? ከዚህ በመነሳት፣ በሴት መሪዎቻችን ውስጥ ማየት የምትፈልገ/ጊው ባህሪይ ምንድነው?

No comments:

Post a Comment