“ድንቄም ጥበብ!” አለ አሉ አያ ኤሊ!
(አፍሪካ፣ ሴታዊነትና ጥበባችን - የአንድ ደብተራ እይታ)
ስለምን መናገር እንዳለብኝ በግልጽ አልተነገረኝም። ሴትና ሥነ-ጽሑፍ? ሴትና ጥበብ? ደግነቱ፣
የራሴን ሥራዎች መሠረት አድርጌ እንድናገር ነጻነት ተሰጥቶኛል። ይህ፣ “ለመሆኑሴት ምንድናት?” “ጥበብስ?” ወደሚል ሙያዊ ትንታኔ
ውስጥ እንዳልገባ ያግዘኛል። ያንን ልተንትን ብልም ትምህርቱ የለኝም። Simone de Beauvoir የተባለች ፈረንሳዊት ፈላስፋ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ 900 መቶ ገፅ ያለው መጽሐፍ ጽፋለች።
ያንን መጽሐፍ ማንበብ ጀመርኩና ይበልጥ ድንግርግሬን ቢያወጣው ተውኩት።
የBeauvoirን መጽሐፍ አንብቤ ባልጨርስም ሴትንና ወንድን መለየት የሚያቅተኝ ግን አይመስለኝም
- በማየትም፣ በዳበሳም። ቢያንስ ኢትዮጵያዊ፣ ከኢትዮጵያዊም አማርኛ ተናጋሪ፣ ስለሆንኩ በህዋሶቼ ብቻ ሳይሆን በልቦናዬም ከሚገባው
ሴቱንና ወንዱን እለያለብዬ አስባለሁ። ለምሳሌ፦
እውቀት ወንድ፣ ጥበብ ደግሞ ሴት ነች። ስጋ ወንድ፣ ነፍስ ሴት ነች። ሞት ወንድ፣ ሕይወት ሴት ነች። ኑሮ ወንድ፣ ዕጣ-ፈንታ ሴት ነች። ድንበር ወንድ፣ አገር ሴት ነች። ሰማይ ወንድ፣ ምድር ሴት ነች። ጦርነት ወንድ፣ ሰላም ሴት ነች። ፀብና ጥላቻ ወንድ፣ እርቅና ፍቅር ሴት ናቸው። እግዚአብሔር
ወንድ፣ ገነት ሴት ነች። ምድራዊ
መንግስት ወንድ፣ ሰማያዊ መንግስት ሴት ነች። የእግዚአብሔር
ሕግ ወንድ፣ የአምላክ ፈቃድ ደግሞ ሴት ነች።ተሳሳትኩ
እንዴ? ምነው፣ “መንግስትህ ትምጣ፣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን፣” እያልንም አይደል እምንፀልይ?
እንግዲህ ሥራዎቼን የማንበብ ዕድል የገጠማችሁ፣ ሴት ገፀ-ባህሪያቶቼን
ለምን ረቂቅና ጠንካራ ሰብዕና እንደማላብሳቸው ከዚህ አተያይ መገመት ሳትችሉ አትቀሩም። የ”ስድሰተኛው ሃጢአት”ዋ ሰዓሊ፣ የ”ኤላን
ፍለጋ”ዋ ኩዬ፣ “የስሳዬ ልጆች” ማሜ፣ ንፍቀ-ክበብ፣ ሁለቱ ቢራቢሮዎችና የመጨረሻዋ ቅጠል፣ የ”Catch
Your Thunder” ሁለቱ አያንቱዎች በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሑፍ ውስጥ ከሚታዩ እጅግ። እጅግ ጥቂት ልሁቅ ሴት ገፀ-ባህሪያት መሃል ይቆጠራሉ
ብዬ ብሟገት እማሸንፍ ይመስለኛል። ይህንን የፈለገ አንብቦና መርምሮ እንዲፈርድ ትቼ ”Catch Your
Thunder፡ Rendezvous With the End” የተሰኘው መጽሐፌ
ስላለው አተያየ-ፆታ ጥቂት ልበል።
“ካች ዩር ቴንደር” ትረካውን እንዲህ ብሎ ይጀምራል፦
‘Men can only see half the face of women…’
(p. 3)
“ወንዶች ማየት የሚችሉት የሴቶችን ግማሽ ገፅ ብቻ ነው። …”
በሌላ ቦታ ደግሞ እንዲህ ይላል፦
‘Africa
was supposed to be a continent of women leaders. Alas, men wouldn’t give them
the chance.’ P. 270
“አፍሪካ
በመሠረቱ የሴት መሪዎች ምድር ነበረች። የሚያሳዝነው ግን፣ ወንዶች ዕድሉን ሊሰጧቸው አልቻሉም።”
“ካች ዩር ቴንደር” በዋና ጭብጥነት፣ ዛሬ ዓለማችንንም አፍሪካንም ከአዘቅት ውስጥ የጣላትን
ወንዳዊ ሥልጣኔ በተጠማ ፅዋ (Thursty Cup) ይመስለውና ያንን ባዶ ፅዋ ሞልቶ አፍሪካንም ዓለምንም የሚያድነው ወይን ከሴቶች
መምጣት እንዳለበት ይሟገታል።
ከዚህም ባሻገር፣ የአፍሪካ መልክዓ-ምድር ሲፈጠርም ሴታዊ መልክና ባኅሪይን ተላብሶ የተፈጠረ
እንደሆነ ሥዕላዊ ማስረጃ በመስጠት የፍንጠዛ (fantasy) መላምት
ያቀርባል።
እኚህ ሁሉ ወግና አባባል ለማሳመር ብቻ የተባሉ አይደሉም። እኔ የማላምንበትን አልጽፍም። ከላይ
ባጭሩ ያጋራሁዋችሁ እውነቶቼ በአመዛኙ በእምነቴና በባህላዊ ገፀ-ምድራችን ላይ ባደረግሁት ኪናዊ ሃሰሳና ማሰላሰል የደረስኩባቸው
ድምዳሜዎቼ ናቸው።
መጽሐፎቼን ያነበባችሁ እንደምታውቁት በጥበብ ሥስራዎቼ በባህላዊ ገፀ-ምድር (Cultural
Landscape) ንባብ ላይ አተኩራለሁ። ሙያዬ ሥነ-አዝርዕትና የመልክዓ-ምድር ሥነ-እነፃ (Landscape Architecture) መሆኑ ለዚህ አግዞኛል። ”Landscape Architecture” እና ”Cultural Landscape” እንደሙያም እንደጽንሰ-ሃሳብም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ
አዲስ ናቸው። “Cultural Landscape” ባጭሩ፣ ከተፈጥሮና ከባህል መስተጋብር የተገኙ ቅርሶችን - ግዑዙንም
ረቂቁንም - የሚመለከት ጽንሰ-ሃሳብ ነው። እንደብራና ተነብቦ አንደምታ የሚበጅለት ረቂቅነት ስላለው ነው፣ “Cultural Landscape”ን “ባህላዊ መልክዓ-ምድር” ከማለት ይልቅ፣ “ባህላዊ ገፀ-ምድር”
በሚል መተረጎም የመረጥኩት።
በዚህ ጽንሰ-ሃሳብ ላይ ከዚህ የበለጠ ሙያዊ ትንታኔ አልሰጥም።
ይልቅ፣ ከ”ካች ዩር ቴንዴር” ጥቂት አናቅፅትን በመጥቀስ፣ ባህላዊ ገፀ-ምድርን ማንበብ ለምን እንደሚያስፈልግ፣ ይህም ሴትን፣ ጥበብንና
የአፍሪካን ትንሳዔ በሚመለከት ባጋራኋችሁ ድምዳሜ ላይ እንዴት እንዳደረሰኝ ለማሳየት ልሞክር። መጽሐፉ እንግልዝኛ ስለሆነ ቀድሜ
በእንግልዝኛ ጠቅሼ በግርድፉ በአማርኛ እተረጉመዋለሁ።
1.
“ካች ዩር
ቴንደር” ስለተፈጥሮና ስለሰው ግንኙነት ምን ይላል?
‘Sacredness
writes itself … Our world shaped itself long before it started to shape us.
What we believe and live by are written on it long before we started to believe
and live. Those who know the earth and the sky are tales could still read that.
The land thinks. The land impresses its thoughts on us. Sacredness writes
itself…’ P. 229
“ቅድስና
ራሱን ይፅፋል… ምድራችን እኛን ከማበጃጀቷ እጅግ ቀድማ ራሷን አበጃጅታለች። እምንኖርባቸው ሃሳቦችና እምንመራባቸ እምነቶች እኛ
መኖርና ማመን ከመጀመራችን በፊት በእርሷ ላይ ተነቅሰዋል። ምድርና ሰማይ ተረቶች ናቸው። ይህንን የሚያውቁ ጠቢባን ዛሬም ከምድርና
ከሰማይ ገጽ ላይ ጥበብ ያነብባሉ። መሬት ታሰላስላለች። መሬት ሃሳቦቿን በኛ ላይ ታትማለች። ቅድስና ራሱን ይፅፋል…”
“ካች ዩር ቴንዴር” እንዲህም ይለናል፦
‘Water
stores your soul-print. Trees store your soul-print. The road stores your
soul-print. You may not see it, but when you go back to a tree you shed your
tears under, or your laughter, the tree claps for joy. The road that knows you
rises up to welcome you. The rock smiles. The water ripples. The land
blooms." P. 228
“ዉሃ የነፍስሽን
ማሕተም ያኖራል። ዛፎች የነፍስሽን ማሕተም ያኖራሉ። የተራመድሽበት መንገድ የነፍስሽን ማሕተም ያኖራል። አንች አታዪው ይሆናል እንጂ፣
ዕምባሽን በጥላው ውስጥ ወዳፈሰስሺበት፣ ወይም ፈንዲሻ ሳቅሽን ወደረጨሽበት፣ ዛፍ ተመልሰሽ ስትሄጂ፣ ዛፉ በፍንደቃ ያጨበጭብልሻል።
የሚያውቅሽ ጎዳና የዱካሽን ቅርበት ሲሰማ ሊቀበልሽ ቀና፣ ቀና ይላል። አለቱም ገጽሽን ሲያይ በፈገግታ ይፈካል። ውሃውም በናፈቀው
ገፅታሽ የውልብታ ኃይል በደስታ ማዕበል ይናወጣል። እምታስታውስሽ ምድርም እንዳየችሽ
እምብርቷን ገላልጣ በፀደያዊ ፍካት ትፈግጋለች።”
2. ሴቶች እንዴት ለምድርም ለጥበብም ቅርብ ሆኑ?
ሀ. በግብርና
ሕይወት ውስጥ ያሉ እናቶቻችንን ውሎና ክህሎት እንመልከት። ወንዶች በአመዛኙ በሰፋፊ እርሻዎችና በውስን የገበያ ሰብሎች ላይ ሲያተኩሩ፣
ሴቶች ግን ለጤናውም ለቅመሙም፣ ለሽታውም ለማጌጫውም፣ ለዕለት ጉርሱም ለስዕለት ግብሩም፣ በሚሆኑ የጓሮ አትክልቶች ላይ ያተኩራሉ።
ይህ፣ ለዘመናችን እጅግ አስፈላጊ የሆነው የ”Genetic diversity” እውቀትና ክህሎት እነሱጋ እንዳለ ያሳየናል።
ለ. ከምድር
መላቀቅን (Transcendence) በሚያስተምሩ ክርስትናንና እስልምናን በመሳሰሉ መጤ እምነቶች ውስጥ የወንዶች መሪነትና “የጥበብ”
የበላይነት ጎልቶ ይታያል። እኚህ ሃይማኖቶች በየደረሱበት ለእናት ተፈጥሮ መልካም እንዳላደረጉ የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች አሉ። በአንፃሩ፣
“ባዕድ አምልኮ” ብለን በምንኮንናቸው፣ ከተፈጥሮ ጋር በሕብር አብሮ የመኖርን አስፈላጊነት በሚያሳዩትና፣ ከወንዙና ከተራራው፣ ከወቅቶች
መለዋወጥም ጋር በተቆራኙት እሬቻን፣ አቴቴን፣ አድባርን፣ በመሳሰሉ አገር-በቀል እምነቶች ውስጥ ሴቶች ከፍ ያለውን ሚና ይጫወታሉ።
ይህ የሚያጎናፅፋቸው ልዩ ክህሎትና ጥበብም ዛሬ ምድር አብዝታ እምትፈልገው ነው።
ሐ. ሴቶች፣
በአካላዊና በሥነ-ሕይወታዊ ሂደቶቻቸው ላይ በሚከሰቱ ለውጦች ምክንያት (የወር አበባ፣ እርግዝና፣ መውለድ፣ ማጥባት፣ ማሳደግ፣ ወዘተ)፣
ለአካባቢያዊና ወቅታዊ ለውጦች፣ ለሽታውም ለድምፁም፣ ለብርዱም ለሙቀቱም፣ ለቁርቋሬውም ለልስላሴውም፣ ለብርሃኑም ለፅልመቱም … ቅርብ
ናቸው። ይህም ሥነ-ሕይወታዊና ሥነ-ልቦናዊ ስሱነት (sensitivity) ይፈጥርባቸዋል። ለአንድ-አይነትነት፣ ሲከፋም (አይሞቀው፣
አይበርደው እንዲሉ) ለስሜት ድንዛዜ፣ ከተጋለጠው የወንዶች ሥነ-ሕይወታዊና ሥነ-ልቦናዊ ተፈጥሮና ዝንባሌ አንፃር ይህ ስሱነት ሴቶችን
ለጥበብ ቅርብ ያደርጋቸዋል።
እነዚህ የአተያየ-ጾታ ሚናዎች ኤኮኖሚያዊ ስነ-ልቦናዊና ማኅበራዊ ዋጋቸው እንዲኮስስ መደረጉ
እውነተኛ ዋጋቸውን ከቶም አያሳንስም። የጾታን እኩልነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ትገል ውስጥ የእነዚህን ሚናዎች ዋጋ ማሳደግ እንጂ
ሴቶች እነዚህን መሰል ሚናዎች እንዲተውአቸው ማድረግ ተገቢ አይመስለኝም። ይህ ግን በእነርሱ ምርጫ እንጂ እንደባህላዊ ወይም ተፈጥሮአዊ
ግዴታ የሚጫንባቸው መሆን የለበትም። በዚህ በተለወጠ ዘመናችን ወንዶችም በእንዲህ አይነት ሚናዎች ላይ ሊሳተፉ እንደሚችሉ የማያከራክር
ሆኖ።(መልካም ወዳላደረጉ ተራምደን ወዳለፍንባቸው መንገዶች የኋሊት እንመለስ ማለት እንዳልሆነም ግልጽ ሆኖ።)
“ካች ዩር ቴንደር” ከላይ የጠቀስኳቸውን አይነት ብዙ የባህላዊ ገፀ-ምድር ንባቦችን መሠረት
በማድረግ እንዲህ ይላል፦
‘I
think, women are closer to the spirit of the land and see. Their feet are
fairer on the road than that of men. They sing and dance the memory of the
ancient tale in their silence and utterance, in their stillness and movement.
The land responds to them better.’ P. 270
“ይመስለኛል፤
ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ለምድር መንፈስ ቅርብ ስለሆኑ ረቂቅ ሚስጥራትን ማየት ይችላሉ። የእግሮቻቸው ዳናም እንደወንዶች እርምጃ ጎዳናውን
የማያቆስል ልስሉስ ነው። የጥንታዊውንም ምድራዊ ጥበብ ትዝታ በዝምታቸውም በንግግራቸውም፣ በእርጋታቸውም በእንቅስቃሴያቸውም ውስጥ
ያዜሙታል፤ ይደንሱታልም። ምድሪቱ ለእነርሱ ፈጣን ምላሽ ትሰጣለች።”
3. አፍሪካ ለምን፣ “በመሠረቱ የሴት መሪዎች ምድር” ተባለች?
“ካች ዩር ቴንደር” የአፍሪካን ሴት መሪዎች ሚና ከቅርብ ዘመኗ እቴጌ ጣይቱ ጀምሮ እስከ ጥንታዊያኑ
ህንዴኬዎችና ክሊዮፓትራዎች ድረስ ይዳስሳል፤ በምናውቃቸው የታሪክ መጽሐፍት ውስጥ ብዙ የማይወራላቸውን ሴት መንፈሳዊና የጦር መሪዎቻችንንም
ያነሳሳል። ለምሳሌ፦ የወራሪውን የጀርመን ጦር በጀግንነት የተዋጋጉትን፣ ከላይኛው የኩሽ ምድር ተነስተው በኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና ኮንጎ
ልሳነ-ምድር ውስጥ የሚመላለሱትን ኒያቢንጊዎች፣ የሎቬዱን የዝናብ ንግስቶች፣ የዙሉላንዷን ናንዲ፣ የስዋዚዎችን ሌዲ ኤሌፋንት፣ የሾናዋን
ምቡያ ንሃንዳ፣ የአንጎላዋን ንዚንጋ፣ የአሻንቲዎችን ያ አሳንታዌ፣ የሃውሳዎችን ጉምሱዎች፣ ወዘተ… በማንሳት፣ እኚህ ሴቶች ታሪካቸው
ባይፃፍም የአፍሪካ እውነተኛ መሪዎች እንደነበሩ በመሟገት፣ የዛሬዎችን እንስት ጀግኖች ከእነዚህ እመው መናፍስት ወራሾች ውስጥ ለማግኘት
ይሞክራል።
በነገራችን ላይ ይህ መጽሐፍ ስለአፍሪካዊ ቤተሰባዊ አንድነት ነው የሚዘምረው። እንዲህ እያለ፦
‘I came
out of the Sea; tanned my skin in the molten stones of the Danakil; flowed down
the Great Rift of my thick lips; stretched westward across the desert of my
forehead; walked down the prairies of my chest; deep into the Congo of my
heart; far down the Kalahari of my feet. I am a soul of thousand faces. I am a word
of thousand versions. Redemption!’ P. 198
“ከቀዩ
ባሕር ዕምብርት ፈለቅሁ፤ በዳናኪል ቅልጥ አለቶች ቆዳዬን አጠየምኩ፤ በወፋፍራም ከናፍሮቼ ስምጥ ሸለቆ ቁልቁል ፈሰስኩ፤ በግንባሬ
(ሰሃራ) በረሃ በኩል ወደምዕራብ ተንጠራራሁ፤ በደሬቴ የሳር ምድር ተንደረደርድሬ እልቤ ኮንጎ ውስጥ ጠልቄ ገባሁ፤ ወደእግሮቼ ካላሃሪም
አቆልቁዬ ዘለቅሁ። እኔ ሺህ ፊት ያለኝ አንድ ነፍስ ነኝ። እኔ ሺህ ዲቃላ ያለኝ አንድ ቃል ነኝ። (እኔ አፍሪካ፣ እኔ አፍሪካዊ
ነኝ!) ትንሳኤ!”
ይህም የውህደትና የአንድነት እይታ ለሴቶች ይበልጥ የቀረበ ሴታዊ (Feminine) እይታ ነው።
4. (በመጨረሻም) አፍሪካ ለምን ሴት ተባለች?
ከ”ካች ዩር ቴንደር” ዋና ገፀ-ባኅሪያት አንዱ የሆነው ጎዳና ወይም ታማ፣ ከላይ የጠቀስኩላችሁን፣
የዓለማችንን የተንጋደደ ሥልጣኔ የሚወክለውን “የተጠማ ፅዋ”
(The Thirsty Cup) ምስጢር ለማወቅ፣ ፅዋውንም እንደወይን ሞልተው አፍሪካንም ዓለማችንንም ከጥፋት የሚታደጉትን የአፍሪካዊ
ሴት ጀግኖች ማንነት ለማወቅ፣ ከቢሾፍቱ ሃይቆችና ከእንጦጦ ተራራ ተነስቶ፣ የሶፍ ኡመር ዋሻን፣ ዬሃን፣ አክሱምን፣ ወዘተ… ወደመሳሰሉ
የአፍሪካ ታላላቅ የገፀ-ምድር ቅርሶች እየሄደ ምድሪቱ ምስጢሩን እንድትፈታለት ይማፀናታል። ለምሳሌ አክሱም ላይ ደርሶ እንዲህ ይላል፦
“What was your secret, O Hendeke of the untouchable fame! What the source of your strength, O you queen of the undying flam! What was your anger for, O Yodit of the unyielding seed! What did you hide from the temptations of the King, that master of a thousand concubines, O Sheba of the peerless wisdom!” P. 276
“የአይደረስበቱ
ዝና ሕንዴኬ ሆይ፣ ምስጢርሽ ምን ነበር? አንች የማይከስመው ነበልባል ንግስት ሆይ፣ የብርታትሽ ምንጭ ምን ነበር? የማይሞተው
(ይሁዳዊ) ዘር ዮዲት ሆይ፣ ቁጣሽ ስለምን ነበር? የወደር አልባው ጥበብ ሳባ ሆይ፣ ከዚያ የሺ እቁባቶች ጌታ፣ ከዚያ (ይሁዲ)
ንጉስ ብልጠት፣ የሰወርሽው ሚስጢር ምን ነበር?”
ጎዳና፣ በሌሎች ገፀ-ምድሮች አማክሎ አሶሳ ይደርስና፣ አሁን የህዳሴ ግድብ በሚዘረጋበት የጉባ ተራራ ላይ ተቀምጦ፣ እግሮቹን በቅዱሶቹ የበርታ አለቶች ላይ አንተርሶ፣ አባይ ስውሩን ድንበራችንን ተሻግሮ፣ “ብሉ ናይል” በሚል አዲስ ስም ተጠምቆ፣ የኑቢያን ምድር እየባረከ የፈርኦኖችን ምድር ሊያረሰርስ ሲገሰግስ እየተመለከተ እንዲህ ይላል፦
"O
Cleopatra! What is the secret that you hid from him who claimed to love you;
from him who made you queen when you are already one; from him who told you
that you are white when you are black and comely - as black and comely as your
sister of River Abbai; … as black and comely as the soil that bore you; [and as
black and comely as the tents of Kedar and the curtains of
Solomon.]?" P. 277
“ክሊዮፓትራ
ሆይ! ከዚያ፣ እንደሚያፈቅርሽ ከተናዘዘልሽ ቄሳር የደበቅሽው ሚስጥር ምን ነበር? ከዚያ አንቺ ቀድሞም ንግስት ሆነሽ ሳለ፣ አነገስኩሽ
ካለሽ ቄሳር የደበቅሽው ሚስጥር ምን ነበር? ከዚያ፣ አንቺ ጥቁርና ውብ ሆነሽ ሳለ ነጭ እንደሆንሽ ከነገረሽ ቄሳር፤ እንደእህትሽ
እንደአባይ ልጅ ጥቅሩና ውብ ሆነሽ ሳለ ‘ነጭ ነሽ’ ካለሽ ቄሳር፤ እንዳበቀለሽ አፈር ጥቁርና ውብ ሆነሽ ሳለ፣ ‘ነጭ ነሽ’ ካለሽ
ቄሳር፤ እንደ ቄዳር ድንኳኖችና እንደሰሎሞን መጋረጃዎች ጥቁርና ውብ ሆነሽ ሳለ፣ ‘ነጭ ነሽ’ ካለሽ ቄሳር የደበቅሽው ሚስጥር ምን
ነበር?”
ይህንን እንዳለ አንድ የበረሃ መንፈስ ይገለጥለትና እንዲህ ይለዋል፦
"That she is made pregnant with fire and gave birth
to water." P. 277
“ሚስጥሩማ፣ እርሷ በእሳት መንፈስ ጸንሳ ውሃ መውለዷ
ነው።”
በአሶሳው ጫማ ሰፊ ልጅ አካል የተገለጠው መንፈስ ይህንን ብሎ ይህች ምድር ቅድስት ስለሆነች ጎዳና የቆሸሹ ጫማዎቹን
እንዲያወልቅ ይነግረዋል። ጎዳናም
ምድሪቱ ለምን ቅድስት እንደሆነች ይጠይቀዋል። መንፈሱ መልሶ እንዲህ ይላል፦
"Don't
you see the secrets of the heavens written on it - a Tablet of the gods? Fire
it takes from out the sea and water it gives back." P. 278
“የሰማያት
ሚስጢራት የተፃፉባት የአማልክቱ ታቦት እንደሆነች አይታይህምን? ከባህሩ እሳት ተቀብላ ያንን እሳት ወደውሃነት ለውጣ መልሳ ለባህሩ
ትሰጣለች።”
ጎዳና ወደየረር ተራራዎች ሄዶ የዳናኪል ረባዳንና የኢርታ-አሌን ነፋሊት በአይነልቦናው ሲያይ፣
ያ የአሶሳ መንፈስ የነረገው ሚስጥር ትርጉም ግለፅ ሆኖ ይታየዋል። እሳት፣ በጎመራ ነፋሊት መልክ ከቀይባህር ማፀን ተነስቶ፣ በታላቁ
የስምጥ ሸለቆ በኩል ወደቪክቶሪያ ሃይቅና በዙሪያው ወዳሉ ተፋሰሶች ይወርድና፣ ኢየሱስ ውሃውን ወደወይንነት እንደለወጠው፣ በጥቁሩ
አፈር ወደውሃነት ተለውጦ፣ በናይል ዴልታ በኩል ተመልሶ ወደወጣበት ባሕር ይፈስሳል።
እንግዲህ አፍሪካ፣ በእሳት መንፈስ ፀንሳ የውሃን መንፈስ የወለደች እንስት መሆኗም
አይደል? “ለዚያ ነው አፍሪካ የሰው ዘርም የቀዳማይ ሥልጣኔም ማሕፀን ለመሆን የበቃችው፤” ይለናል “ካች ዩር ቴንደር”። [ይህንን
ከሃይማኖታዊ ምሳሌ ጋር ስናነጻጽረው፣ ለሙሴ የተገለፀውን ነበልባላዊ መንፈስ በከሰተው ቁጥቋጦ (ዕፀ-ጳጦስ) የሚመሰለው የቅድስት
ድንግል ማሪያም ማሕፀን፣ እሳት የሆነውን ቅዱስ-መንፈስ በውስጡ ከስቶ የሕይወት ውሃ የሆነውን ኢየሱስ እንደሰጠን ሁሉ፣ የአፍሪካ
ምድርም እሳት የሆነውን የሰው መንፈስ ስጋ ነስቶ ለምድር የሰጠ ማሕፀን ነው ማለት ነው። ያም አፍሪካን ሌላኛዋ ዕፀ-ጳጦስ ያደርጋታል።]
“አንበሶች ታሪካውን መፃፍ እስከሚጀምሩ የእነርሱ ታሪክ በአዳኞቻቸው ገድል የተሞላ ይሆናል፤”
የሚል አፍሪካዊ አባባል አለ። አንድ አፍሪካዊ ተረት ልንገራችሁና ሃሳቤም ንግግሬንም ልቋጭ።
ጠቢቡ ኤሊ ፍጥረታትን እየተዘዋወረ ስለጥበባቸው ይጠይቃቸዋል። ጥንቸል ስለፈጣን ሯጭነቷ አውርታ
ስታበቃ፤ ኤሊው፣ “ድንቄም! ተረጦና ተሞተ!” ብሏት ያልፋል። ሸረሪትም ስለጥበቧ፣ ስለፈትልና ሽመናዋ አብዝታ ካወራች በኋላ፣ አያ
ኤሊ፣ “ድንቄም! ተሸመነና ተሞተ!” ብሎ ያልፋል። ዛፉም፣ ስለፍሬው ማማርና ጣዕም ተንትኖ ሲያበቃ፣ “ድንቄም! ተፈራና ተሞተ!”
ብሎት ይሄዳል አያ ኤሊ። የምድርን ጥበብ አብዝቶ የሚያውቀው ኤሊ ፍጥራኑን ሁሉ እንዲህ እየጠየቀ፣ “ድንቄም!” እያለ በራሳቸው
እንዳይኮሩ ያደርጋቸዋል።
እንደኔ እይታ፣ በራሳቸው ጥበባዊ ብቃት ሞገስን የተጎናጸፉ ኢትዮጵያዊ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች እጅግ
ጥቂት ናቸው። አብዛኛዎቹ ሥራዎች በዘመን አጋጣሚዎችና ኃይሎች ግፊት የክብር መንበር ላይ ይፈናጠጣሉ። እኝህ ጊዜ ያነሳቸው ሥራዎች፣ ይፍጠንም ይዘግይም፣ ጊዜ እንደሚጥላቸው
እርግጥ ነው። ዛሬ የጥበቡን ዓለም በጉልበትም በብልጠትም የተቆጣጠሩት ወንዶች፣ ወንዳዊነትና ሌሎች ከዘመኑም ከጥበቡም ጋር የማውይሄዱ
ውስን አተያዮች ናቸው። ይህ የጥበብ እግረ-ሙቅ ነው። ቢያንስ ሴቶቻችን፣ በዚህ ጽሑፍ አጭር ዳሰሳ እንዳየነው፣ ከምድር ጋር ያላቸው
ጥብቅ ቁርኝት የሰጣቸውን ጥበብ የማውጣት ዕድሉን አግኝተው ጥበባችንን ወደምሉዕነት እስከሚያሸጋግሩት ድረስ፣ የዛሬውን ግማሽ ጥበብ፣
“ድንቄም! ተከየነውና ተሞተው!” እያልን በተስፋ እንጠብቃለን።
አመሰግናለሁ!