Tuesday, June 19, 2018

የጥበብና የጸሎት ጉዞ ወደ አሥመራ

የጥበብና የጸሎት ጉዞ ወደ አሥመራ

ከላይ የምታዩት፣ እኔና ባልደረቦቼ አሥመራ ላይ፣ እንዳ-ማሪያም (ቅድስት ማሪያም ቤተክርስትያን) ፊትለፊት፣ (በቅስት የገባው ደግሞ ከረን)፣ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መጀመር ትንሽ ቀደም ብሎ፣ የተነሳነው ፎቶ ነው። ጦርነት የዘጋውን ጎዳና ሰላም እንደከፈተው እዚህች ቦታ ተመልሼ የምስጋና ጸሎት ላደርግ ስመኝ ቆይቻለሁ። ጥበቃው ይህንን ያህል ቢረዝምም እኔም ተስፋ ሳልቆርጥ፤ ምኞቴ እውን ሊሆን የሚችልበት ምልክትም ሳይታይ ብዙ ቆየ። ግን፣ ለምንድነው መሪዎቻችን “ሰላምን ፈርመናል” እስኪሉን እምጠብቀው? ራሴው ወደኤርትራ ተጉዤ ስለሰላም አልዘምርም? መቼም ይህ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖር ኢትዮጵያዊ ከንቱ ህልም ነው እሚመስል። እሺ፣ ብቻዬን አልችለው ይሆናል። እናንተ ብትተባበሩኝስ? የኔ ብጤ ተራ ዜጎችን፣ የፌስቡክ ወዳጆቼን፣ አንቺንና እንተን፣ ማለቴ ነው። ወደኤርትራ ነፃ የጸሎትና የጥበብ ጉዞ አድርገን ለዓመታት የተለያዩ ቤተሰቦች እንዲገናኙ፣ ለሰላም የሚደረገውም ተቋማዊ ጥረት ጉልበት እንዲያገኝ፣ አስተዋፅዖ እናበረክት ዘንድ እንድንተባበር ጥሪ እያደረግሁ ነው። ይህ ለኢትዮጵያዊያንም ለኤርትራዊያንም የቀረበ የመንፈሳዊና የጥበባዊ ጉዞ ጥሪ ነው።   

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲፈነዳ፣ ትግራይ ውስጥ፣ ማይ-ነብሪ በተባለ ቦታ ነበርኩ - በግድብ ሥራ ምክንያት። እኔና ባልደረቦቼ ባንደ ተራ በሚመስል ንጋት ማልደን ለሥራ ስንነሳ የታንክና ከቶም አይተናቸው የማናውቃቸው የከባድ መሳሪያዎች ቅፍለት ሲግተለተል ተመለከትንና ምፅዓት የመጣ ያህል ደነገጥን። ለካስ ምሽት ላይ፣ ወይም ንጋት አካባቢ፣ ወዳጆች በነበሩት ኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል ጦርነት መፈንዳቱ ታውጆ ኖሯል!

የጦርነት ነጋሪቱ በተሰማበትና የጦሩ ቅፍለት በታየበት በዚያ ቀን ምሽት፣ የመንደር እናቶች ተሰባስበው፣ በማይ-ነብሪ አሸዋማ መሬት ላይ በጉልበትና በክርናቸው እየዳሁ፣ ሕማሙና ከተጋጠ ጉልበትና ክርናቸው የሚዝረበረበው ደም ሳያግዳቸው፣ እስከሌሊት “ምምህላል” (ምሕላ) አደረጉ፦ “አቤቱ፣ ይህንን ድንገት የፈነዳ ጦርነት ያዝልን! በጣዕር ማጣጣም የጀመርነውን ሰላም መልሰህ አትንጠቀን! ከእሳት የተረፉ ልጆቻችንን እንደገና እሳት አትሞጅርብን! ተማለለን፣ አቤቱ ተማለለን!” እያሉ። የእኒያ እናቶች እምነትና የጸሎት ብርታት እማያምኑ ጓደኞቼንም ሳይቀር ለጸሎት አስጎነበሰ።

ሊፈነዳ በማስገምገም ላይ ያለን ጦርነት እንዲህ ስቀርብ ያ የመጀመሪያዬ ነበር። ተቃርኖው አስደነቀኝ! እዚህ፣ እኚህ እናቶች ጦርነቱ እንዳይነሳ ዕምባና ደም ያፈስሳሉ። እጉኑ ደግሞ ሌሎች ኃይሎች ለጦርነቱ ዕምባና ደም ለመገበር ይጎርፋሉ። ማይ ነብሪ ትንሽ የገጠር ከተማ ነች። በትልቋ ኢትዮጵያ ውስጥ ስንቶች ተመሳሳይ ጸሎት እያደረጉ ይሆን? ያን ያህል ደምና ሕማም የተገበረው ጸሎት ጦርነቱን አለማስቀረቱን አስቤ፣ “ጸሎት ብላሽ! አወይ የባከነ የዋህነት!” አላልኩም። ይልቅ፣ ያ ጸሎት ከሁለቱም ወገኖች ለረገፉት የትዬሌሌ ነፍሳት ስርየት፤ ጦርነቱ ለሰበራቸው ልቦችና ቤተሰቦችም ፅናት፣ እንደሰጠ ማሰብ መረጥኩ እንጂ። ለኔ፣ የጸሎት ኃይል፣ ልክ እንደጥበብ ኃይል፣ ከቶም አይከሽፍም፤ አይባክንምና።        

ከዚህ ክስተት ትንሽ ቀደም ብሎ (ሐምሌ 1988)፣ እኔና የውሃ-ማቆር ሥራ ባልደረቦቼ ለልምድ ልውውጥ በሚል፣ ኤርትራን የመጎብኘት ዕድል ገጥሞን ነበር። አሥመራ የደረስነው ባንዲራ መውረጃ ሰዓት አካባቢ ነበር። እኛ ቀድመን እንዳለፍን ለካስ በሌላ መኪነ በርቀት ይከተሉን የነበሩ ባልደረቦቻችን በወታደሮች ተይዘው ጣቢያ ወርደው ኑሯል። በኋላ እንደነገሩን፣ “እንዴት ባንዲራ በመውረድ ላይ እያለ መኪና ታንቀሳቅሳላችሁ?” የሚል ነበር ምክንያቱ። ባልደረቦቻችን፣ እንግዳነታቸው ታውቆ ያለብዙ ችግር ተለቅቀው ተቀላቀሉን።

በበነጋው ጉብኝታችንን ስንጀምር እኔ (በስዕሉ እንደሚታየው) ባህላዊ ሸማ ለብሼ፣ በባርኔጣዬም ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ጥብጣብ አድርጌ፣ ወጣሁ። ጠንቃቃ ጓደኞቼ፣ ኤርትራዊያን “ይህ ባንዲራ” የሰጣቸው ቁስል ገና ስላልሻረ ባንዲራውን ሲያዩ ሊቆጡ ይችላሉና እንዳወልቀው መከሩኝ። እኔም፣ “እነሱ ባንዲራቸውን እንዲያ ሲያከብሩ የኔን ባንዲራ ለምን አያከብሩም?” በሚል ስሜት፣ ምክራቸውን እንዳልሰማሁ ሆኜ አሳለፍኩት። ለሳምንት ያህል የኤርትራን ገጠርና ከተማ ስንጎበኝ፣ ባለባንዲራ ባርኔጣዬ አብራኝ ነበረች። ለአገራዊ ጥላቻ መግለጫ ባንዲራ ማቃጠል በተለመደባት ዓለማችን ይህን ማሰቤ የዋህነት ሊመስል ይችል ይሆናል።  

የጓደኞቼ ስጋት ግን እውን አልሆነም። የትኛውም ኤርትራዊ ባንዲራዬን እንዳወልቅ አልጠየቀኝም፤ የመከፋት ስሜትም አላሳየኝም። እንዲያውም፣ አንዲት ኢትዮጵያዊት አሮጊት ቀርበውኝ፣ ባንዲራቸውን በአደባባይ በማየታቸው የተሰማቸውን ደስታና አገራቸውንም ለማየት ያላቸውን ምኞት አንጀት በሚያባባ መልክ ገለፁልኝ። በተረፈ፣ የኤርትራ ቆይታችን በዚህች ባንዲራና በየሆቴሉ እንሰማቸው በነበሩ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች የታጀበና የወዳጅነት ስሜት የተሞላው ነበር። ካለፈው መቋሰል በኋላም ኤርትራዊያን የኢትዮጵያን ሙዚቃ ያንን ያህል መውደዳቸው ደስ ይላል። አንዳንዶቻችን ከኤርትራዊያን ጎን ሆነን ጸሎት እንዳደረግን ሁሉ በምንጋራውም ሙዚቃም አብረናቸው ጨፍረናል። ቢያንስ ይህች ገጠመኜ፣ በኤርትራዊያንና በኢትዮጵያዊያን መካከል የተፈጠረው ወቅታዊ መቃቃር፣ ሁለቱን ሕዝቦች ያስተሳሰራቸውን ጥልቅ የደም፣ የእምነትና የጥበብ ማተብ ሊበጥስ እንደማይችል የነበረኝን እምነት አፅንታልኛለች።  

ኋላ ለትምህርት ቻይና ስደርስ የተቀበለኝ እዩኒቨርሲቲው ቀድሞ ደርሶ የነበር ኤርትራዊ ነበር። ያ ኤርትራዊ፣ ያውም የቀድሞ የነፃነት ታጋይ፣ ኋላም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ላይ የተሳተፈ ተዋጊ፣ በአንድ ዶርም ውስጥ ለሁለት ዓመታት ያህል አብሮኝ ቆየ። የእኔንና የዚያን ኤርትራዊ ወዳጄን ግንኙነት እንደተላጠ ሙሉ ብርቱካን ብናስብ፣ የግንኙነታችን ብሔራዊና ፖለትካዊ ገፅታ የብርቱካኑን አንድ ብልት ያህልም አይሆንም። የዚያ ወዳጄ ቀልድና ቁምነገር፣ በኔ ጉትጎታ ይነግረኝ የነበረው የጦርነት ውሎው አሳዛኝ ተረኮች፣ እንጋራቸው የነበሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ዘፈኖች፣ አብረንም እንደግማቸው የነበሩ ጸሎቶች፣ በልባችን የሆነ ጥግ ተሰውሮ ሊኖሩ የሚችሉን የአብሮኛነት ግርዶሾች ሳያስወግዱልን አልቀረም። ለሁለታችንም፣ የይቅርታና የመረዳት ጎዳና ተፈጥሮአዊውና የተሻለው የሙሉነት ምርጫ ነበር።

ስለ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትና የሰላም ጉዳይ በተነሳ ቁጥር፣ ልክ እንደማይ ነብሪ እናቶች በዕምባና በደም ግብር ሰርክ ስለሚጸልዩ የትየሌሌ ወላጆች አስባለሁ - የተለዩአቸውን ልጆቻቸውን ገፅታ ለቅፅበትም እንኳ ለማየት እየጠበቁ ጸሎታቸው ምላሽ ሳያገኝ በቀቢፀ-ተስፋ ወደየመቃብሮቻቸው የሚወርዱ የትየሌሌ ወላጆችን። በኤርትራ ውስጥ በጸሎትና በሙዚቃ ታጅቤ ያሳለፍኳቸውን ደሳስ የሚሉ ጥቂት ቀናት አስባለሁ። አስመራ ላይ እንዳገኘኋቸው እናት ከሁለቱም ወገን ወደየቀዬ ወደአገራቸው እሚመለሱባትን ዕለት ሞት በሚፈታተነው ተስፋ  የሚጠባበቁ ግለሰቦችን አስባለሁ። ቻይና እንዳገኘሁት ኤርትራዊ ወዳጄ አቁሳይ ትዝታዎቻቸውን አሸንፈው ከሚለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉንን የግንኙነቶቻችንን መሠረቶች ለመጨበጥ ዝግጁ የሆኑ፣ ብርቱና ምሉዕ ሰብዕና ያላቸውን፣ ብዙ ሰዎች አስባለሁ።

እርግጥ ነው፣ የኔ ተሞክሮና ትዝታ ከብዙዎች ነፍስ-አብጠርጥር ተሞክሮና ትዝታ ጋር ሲነፃፀር እጅግ እምንት ነው። ቢሆንም ግን፣ ይህች ልንቁስ መሳይ ትዝታዬ በሁለቱም አገሮች ውስጥ ብዙ ሰዎች የልብ-ለልብ ግንኙነትን እየናፈቁ እንደሁ ለማየት ከበቂ በላይ ነች። ይህች ትዝታዬ፣ እንዲህ እያልኩ ለመጠየቅም ከበቂ በላይ ነች፦ በአገሮች መካከል ያለ ግንኙነት የሕዝቦችና የግለሰቦችም ግንኙነት ጭምር አይደለምን? ይህ ሰብዓዊ ግንኙነት ጨርሶ የሌለ እስክመስል ድረስ ድምጽ የተነፈገው ለምንድነው? እኛ፣ ራሳችንን ‘ሃይማኖተኛ ሕዝብ፣ አማኝ ሕዝብ፣’ እያልን ከቁሳዊነት አንፃር ሳይሆን ከመንፈሳዊነት አንፃር ለመግለፅ የምንፈልግ ሕዝቦች አይደለንምን? የማንነታችን ትንሹ ክፍል ሰብዓዊም ሆነ አገራዊ ግንኙነቶቻችንን እንዲገዛና እንዲመራ እምንፈቅደው ለምንድነው? ኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ሰብዓዊ ገፅታን ከፍ ያለ ሕዝባዊ መገለጫና ኃይል እንዲያገኝ ብናደርግ ለሰላም የሚደረገውን ተቋማዊ ጥረት አያግዝ፣ አያፋጥን ይሆን?

ስጀምር እንዳልኳችሁ፣ ለኢትዮ-ኤርትራ የሕዝብ-ለሕዝብ ግንኙነት ጉልበት ለመስጠት፣ በዚህም የተለያዩ ቤተሰቦች እንዲገናኙና በመንግስታቱ መካከል ለሚደረገው የሰላም ጥረት እገዛ ለማድረግ፣ ለሰላም መንፈሳዊና ጥበባዊ ጉዞ እናደርግ ዘንድ እንድትተባበሩኝ ጥሪ ይዤ ቀርቤአለሁ። ይህንን ሃሳብ ለረጅም ጊዜ እያምሰለሰልኩት ብቆይም ከዚህ ቀደም ጊዜው የደረሰ መስሎ አልተሰማኝም ነበር። በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትራችን የተገለፀው የፖለቲካ ፈቃደኝነት ሃሳቡን እውን ለማድረግ ጊዜው መድረሱን አመለከተኝ። እነሆ፣ ሃሳቤ ይህ ነው፦

እኔና ይህንን ሃሳብ የሚደግፉ የፌስ-ቡክ ወዳጆቼና የወዳጆቼ ወዳጆች፦
   1.  ከየትኛውም ሃይማኖትና ዕምነት ከ500 እስከ 1000 ያህል ግለሰቦች ወደኤርትራ የጸሎትና የጥበብ ጉዞ ለማድረግ ፈቃደኝነታቸውን እንዲገልፁ እንጠይቃለን። (ይህ ጉዞውን ለማድረግ የሚነሱ ሰዎች ቁጥር ብቻ ነው) በኤርትራም ውስጥ ለተመሳሳይ ዓላማ ወደአዲስ አበባ ለመጓዝ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች እንዲተባበሩ በፌስቡክና በሌሎች ማኅበራዊ ድረ-ገፆች እንጠይቃለን

    2. የሚፈለገውን ያህል ድጋፍ እንዳገኘን፣ ጥረታችንን በጋራ እናደራጃለን፣ እናቅዳለን ከሁለቱም አገሮች ከያኒያንንና ሌሎች ባለተፅዕኖ በጎ-ፈቃደኞችንም እያሳተፍን፣ የመንግስታቱን የሚመለከታቸው ተቋማት ትኩረት ለማግኘት እንሠራለን።

   3. ቀጥሎም ከሚመለከታቸው የሁለቱም መንግስታት ተቋማት ፈቃድ እናገኛለን፤ የአፍሪካ አንድነት፣ የተባበሩት መንግስታትና፣ ሌሎች ለሰላም የሚሰሩ አካላትም አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲያደርጉልን እንጠይቃለን

    4. በኦፊሴል ቀነ-ቀጠሮ ይዘን፣ አስፈላጊ ከሆነ በአፍሪካ ሕብረት ወይም በተባበሩት መንግስታት የሰላም ሃይል ታጅበን፣ ወደኤርትራ ታንኮች ለጦርነት በሄዱበት ጎዳና ላይ እኛ ለሰላም ሕዝባዊ የጸሎትና የጥበብ ጉዞ እናደርጋለን በእንዳ-ማሪያም ፊትለፊት ወይም በተመረጠ ሌላ ቦታ ላይ ከሁሉም ሃይማኖቶች ከተውጣጡ ኤርትራዊያን ጋር የጸሎት፣ የጥበብና የወዳጅነት ውሎ እናደርጋለን።

    5. በምላሹም፣ ለሰላም ጉዞው ፈቃደኝነታቸውን የገለፁ ኤርትራዊያን አብረውን ወደአዲስ አበባ ይመጡና በመስቀል አደባባይ ወይም በሌላ በተመረጠ ቦታ ላይ ተመሳሳይ የጸሎት፣ የጥበብና የወዳጅነት ውሎ አድርገው ወዳገራቸው ይመለሳሉ።

   6. የሁለቱ ሕዝቦች የተናጋ ወዳጅነት ተጠግኖ ሰላማዊ ትስስሩ በፅኑ መሠረት ላይ እንደገና እስኪገነባ ድረስ ይህንን የእምነትና የጥበብ ጉዞና ውሎ በየዓመቱ ወይም በየሁለት ዓመቱ ማድረግ እንቀጥላለን።  

ይህንን ሃሳብ የምትደግፉና፣ በሰላም ጉዞውና በዝግጅቱ ላይም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለመሳተፍ የምትሹ፣ ወዳጆቼ “ላይክ” እና ለየወዳጆቻችሁም “ሼር” በማድረግ ድጋፋችሁን እንድትገልፁ እጠይቃለሁ። የምናገኘው ድጋፍ እየጨመረ ሲሄድ ከተባባሪዎቻችን መካከል ጉዞውን ለማደራጀትና ለመምራት የሚሹ በጎ ፈቃደኞችን ከየሙያ ዘርፉ፣ ከየሃይማኖቱም፣ በጋራ እንመርጣለን። እነዚህ በጎ-ፈቃደኞች፣ የትም ቦታ ይሁኑ፣ ፌስቡክንና ሌሎች ማኅበራዊ ድረ-ገፆችን ተጠቅመው ከያሉበት (ከየቤታቸው) አስተዋፆዎቻቸውን ያበረክታሉ። ጉዞው እውን እንደሚሆን እርግጠኛ ሆነን ዝግጅቱ የሙሉ ጊዜ ሥራ እስከሚጠይቅ ድረስ ሁላችንም በትርፍ ጊዜዎቻችን ለዚህ የሰላም ኅብረት እንተጋለን። (አውቃለሁ፣ ሰላም የትርፍ ጊዜ ሥራ አይደለም። የሙሉ ጊዜና የሙሉ ልብ ሥራ ነው። በየቤታቸሁ ሆናችሁ ሙሉ ልባችሁን ከሰጣችሁን ያ ሙሉ ልብ ሙሉ ጊዜን ይፈጥርልናል ጊዜ ስጋት አይሆንም። ብቻ፣ በፀሎታችሁም፣ በየጥበቦቻችሁን አብራችሁን ሁኑ።)   

ይህ የሰላም ጥረት ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ሃሳቡን ለየትኛውም ድርጅት ወይም መገናኛ ብዙሃን አላካፈልኩም። ሃሳቡን የሚደግፉ ድርጅቶችና መገናኛ-ብዙሃን ለዚህ ጥሪ ምላሽ እንደሚሰጡ፣ ለውጥኑ ስኬትም የየድርሻቸውን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ፣ አምናለሁ። እነሱም እንደግለሰብ ጓደኞቼ ሁሉ ገፁን ላይክና ሼር በማድረግ እንዲተባበሩን እጠይቃለሁ።

በቅድሚያ ግን፣ እስቲ፣ እያንዳንዳችን በግል ለሰላም ምን ማድረግ እንደምንችል እናሳይ እስቲ፣ የፌስቡክ ወዳጅነት ምን ያህል የሰላም ጉልበት ሊኖረው እንደሚችል እናሳይ! ለምታደርጉት ድጋፍ በሁለቱ ሕዝቦች ጊዜያዊ መለያየት ያለምርጫቸው ተነጣጥለው በሚቸገሩ ቤተሰቦች ስም በቅድሚያ ምስጋና አቀርባለሁ! እንግዲህ በእንግሊዝኛው ምሕፃረ ቃል ጂፕ (JEEP – the Journey of Ethiopian and Eritrean People for Peace) ያልኩት ሕዝባዊው የጥበብና የእምነት ጉዞ ይህ ነው። በጦርነት ጊዜ ለጎርበጥባጣ መንገድና ለአስቸጋሪ መልክዓምድር እንደተሰራችው ጂፕ መኪና፣ የኛም ጂፕ ጎርበጥባጣና አስቸጋሪ ጎዳናን መጠበቅና ለዚያ መዘጋጀት አለበት። ይፍጠንም ይዘግይም ጂፓች፣ ጎዳናዋ ምንም ያህል አቀበትና ማጥ የበዛበት ቢሆንምን፣ የሰላም ጉዞዋን በድል ትወጣዋለች። ሰላም!

2 comments:

  1. ስንቅነህ ወዳጄ!

    ፀሎት ከሚለው ሃሳብ በስተቀር የሰላም ጉዞውና የጥበብ ግንኙነቱ ሸጋ ነው። ፓለቲካ ያቡካካውን ነገር እራሱ ፓለቲካው ያስተካክለው፣ እንጂማ የትም በተገናኘንበት አለም እንኳን ከኤርትራዊያን ጋር ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ሰዎች ጋር በመልካም ግንኙነት እንኖራለን!

    ጓደኛህ በረከት
    ከደቡብ ኮሪያ

    ReplyDelete
  2. Thank you Bereket. I agree with you. And, for me, prayer is also a form of art, a refined kind if done the right way. So, we will give the chance for those who choose to express themselves with prayers.

    ReplyDelete