Friday, August 17, 2018

አፍሪካ፣ ሴታዊነትና ጥበባችን - የአንድ ደብተራ እይታ


“ድንቄም ጥበብ!” አለ አሉ አያ ኤሊ!

(አፍሪካ፣ ሴታዊነትና ጥበባችን - የአንድ ደብተራ እይታ)

ስለምን መናገር እንዳለብኝ በግልጽ አልተነገረኝም። ሴትና ሥነ-ጽሑፍ? ሴትና ጥበብ? ደግነቱ፣ የራሴን ሥራዎች መሠረት አድርጌ እንድናገር ነጻነት ተሰጥቶኛል። ይህ፣ “ለመሆኑሴት ምንድናት?” “ጥበብስ?” ወደሚል ሙያዊ ትንታኔ ውስጥ እንዳልገባ ያግዘኛል። ያንን ልተንትን ብልም ትምህርቱ የለኝም። Simone de Beauvoir የተባለች ፈረንሳዊት ፈላስፋ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ 900 መቶ ገፅ ያለው መጽሐፍ ጽፋለች። ያንን መጽሐፍ ማንበብ ጀመርኩና ይበልጥ ድንግርግሬን ቢያወጣው ተውኩት።
የBeauvoirን መጽሐፍ አንብቤ ባልጨርስም ሴትንና ወንድን መለየት የሚያቅተኝ ግን አይመስለኝም - በማየትም፣ በዳበሳም። ቢያንስ ኢትዮጵያዊ፣ ከኢትዮጵያዊም አማርኛ ተናጋሪ፣ ስለሆንኩ በህዋሶቼ ብቻ ሳይሆን በልቦናዬም ከሚገባው ሴቱንና ወንዱን እለያለብዬ አስባለሁ። ለምሳሌ፦
እውቀት ወንድ፣ ጥበብ ደግሞ ሴት ነች። ስጋ ወንድ፣ ነፍስ ሴት ነች ሞት ወንድ፣ ሕይወት ሴት ነች። ኑሮ ወንድ፣ ዕጣ-ፈንታ ሴት ነች። ድንበር ወንድ፣ አገር ሴት ነች። ሰማይ ወንድ፣ ምድር ሴት ነች። ጦርነት ወንድ፣ ሰላም ሴት ነች። ፀብና ጥላቻ ወንድ፣ እርቅና ፍቅር ሴት ናቸው  እግዚአብሔር ወንድ፣ ገነት ሴት ነች። ምድራዊ መንግስት ወንድ፣ ሰማያዊ መንግስት ሴት ነች የእግዚአብሔር ሕግ ወንድ፣ የአምላክ ፈቃድ ደግሞ ሴት ነች።ተሳሳትኩ እንዴ? ምነው፣ “መንግስትህ ትምጣ፣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን፣” እያልንም አይደል እምንፀልይ?
እንግዲህ ሥራዎቼን የማንበብ ዕድል የገጠማችሁ፣ ሴት ገፀ-ባህሪያቶቼን ለምን ረቂቅና ጠንካራ ሰብዕና እንደማላብሳቸው ከዚህ አተያይ መገመት ሳትችሉ አትቀሩም። የ”ስድሰተኛው ሃጢአት”ዋ ሰዓሊ፣ የ”ኤላን ፍለጋ”ዋ ኩዬ፣ “የስሳዬ ልጆች” ማሜ፣ ንፍቀ-ክበብ፣ ሁለቱ ቢራቢሮዎችና የመጨረሻዋ ቅጠል፣ የ”Catch Your Thunder” ሁለቱ አያንቱዎች በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሑፍ ውስጥ ከሚታዩ እጅግ። እጅግ ጥቂት ልሁቅ ሴት ገፀ-ባህሪያት መሃል ይቆጠራሉ ብዬ ብሟገት እማሸንፍ ይመስለኛል። ይህንን የፈለገ አንብቦና መርምሮ እንዲፈርድ ትቼ ”Catch Your Thunder፡ Rendezvous With the End”  የተሰኘው መጽሐፌ ስላለው አተያየ-ፆታ ጥቂት ልበል።   

“ካች ዩር ቴንደር” ትረካውን እንዲህ ብሎ ይጀምራል፦

‘Men can only see half the face of women…’ (p. 3)
“ወንዶች ማየት የሚችሉት የሴቶችን ግማሽ ገፅ ብቻ ነው። …” 

በሌላ ቦታ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ 

‘Africa was supposed to be a continent of women leaders. Alas, men wouldn’t give them the chance.’  P. 270
“አፍሪካ በመሠረቱ የሴት መሪዎች ምድር ነበረች። የሚያሳዝነው ግን፣ ወንዶች ዕድሉን ሊሰጧቸው አልቻሉም።”

“ካች ዩር ቴንደር” በዋና ጭብጥነት፣ ዛሬ ዓለማችንንም አፍሪካንም ከአዘቅት ውስጥ የጣላትን ወንዳዊ ሥልጣኔ በተጠማ ፅዋ (Thursty Cup) ይመስለውና ያንን ባዶ ፅዋ ሞልቶ አፍሪካንም ዓለምንም የሚያድነው ወይን ከሴቶች መምጣት እንዳለበት ይሟገታል።
ከዚህም ባሻገር፣ የአፍሪካ መልክዓ-ምድር ሲፈጠርም ሴታዊ መልክና ባኅሪይን ተላብሶ የተፈጠረ እንደሆነ ሥዕላዊ ማስረጃ በመስጠት የፍንጠዛ (fantasy)  መላምት ያቀርባል።

እኚህ ሁሉ ወግና አባባል ለማሳመር ብቻ የተባሉ አይደሉም። እኔ የማላምንበትን አልጽፍም። ከላይ ባጭሩ ያጋራሁዋችሁ እውነቶቼ በአመዛኙ በእምነቴና በባህላዊ ገፀ-ምድራችን ላይ ባደረግሁት ኪናዊ ሃሰሳና ማሰላሰል የደረስኩባቸው ድምዳሜዎቼ ናቸው።
መጽሐፎቼን ያነበባችሁ እንደምታውቁት በጥበብ ሥስራዎቼ በባህላዊ ገፀ-ምድር (Cultural Landscape) ንባብ ላይ አተኩራለሁ። ሙያዬ ሥነ-አዝርዕትና የመልክዓ-ምድር ሥነ-እነፃ (Landscape Architecture) መሆኑ ለዚህ አግዞኛል። ”Landscape Architecture” እና ”Cultural Landscape” እንደሙያም እንደጽንሰ-ሃሳብም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ አዲስ ናቸው። “Cultural Landscape” ባጭሩ፣ ከተፈጥሮና ከባህል መስተጋብር የተገኙ ቅርሶችን - ግዑዙንም ረቂቁንም - የሚመለከት ጽንሰ-ሃሳብ ነው። እንደብራና ተነብቦ አንደምታ የሚበጅለት ረቂቅነት ስላለው ነው፣ “Cultural Landscape”ን “ባህላዊ መልክዓ-ምድር” ከማለት ይልቅ፣ “ባህላዊ ገፀ-ምድር” በሚል መተረጎም የመረጥኩት። 
በዚህ ጽንሰ-ሃሳብ ላይ ከዚህ የበለጠ ሙያዊ ትንታኔ አልሰጥም። ይልቅ፣ ከ”ካች ዩር ቴንዴር” ጥቂት አናቅፅትን በመጥቀስ፣ ባህላዊ ገፀ-ምድርን ማንበብ ለምን እንደሚያስፈልግ፣ ይህም ሴትን፣ ጥበብንና የአፍሪካን ትንሳዔ በሚመለከት ባጋራኋችሁ ድምዳሜ ላይ እንዴት እንዳደረሰኝ ለማሳየት ልሞክር። መጽሐፉ እንግልዝኛ ስለሆነ ቀድሜ በእንግልዝኛ ጠቅሼ በግርድፉ በአማርኛ እተረጉመዋለሁ።

1.      “ካች ዩር ቴንደር” ስለተፈጥሮና ስለሰው ግንኙነት ምን ይላል? 
‘Sacredness writes itself … Our world shaped itself long before it started to shape us. What we believe and live by are written on it long before we started to believe and live. Those who know the earth and the sky are tales could still read that. The land thinks. The land impresses its thoughts on us. Sacredness writes itself…’ P. 229
“ቅድስና ራሱን ይፅፋል… ምድራችን እኛን ከማበጃጀቷ እጅግ ቀድማ ራሷን አበጃጅታለች። እምንኖርባቸው ሃሳቦችና እምንመራባቸ እምነቶች እኛ መኖርና ማመን ከመጀመራችን በፊት በእርሷ ላይ ተነቅሰዋል። ምድርና ሰማይ ተረቶች ናቸው። ይህንን የሚያውቁ ጠቢባን ዛሬም ከምድርና ከሰማይ ገጽ ላይ ጥበብ ያነብባሉ። መሬት ታሰላስላለች። መሬት ሃሳቦቿን በኛ ላይ ታትማለች። ቅድስና ራሱን ይፅፋል…”    

“ካች ዩር ቴንዴር” እንዲህም ይለናል፦

‘Water stores your soul-print. Trees store your soul-print. The road stores your soul-print. You may not see it, but when you go back to a tree you shed your tears under, or your laughter, the tree claps for joy. The road that knows you rises up to welcome you. The rock smiles. The water ripples. The land blooms." P. 228
“ዉሃ የነፍስሽን ማሕተም ያኖራል። ዛፎች የነፍስሽን ማሕተም ያኖራሉ። የተራመድሽበት መንገድ የነፍስሽን ማሕተም ያኖራል። አንች አታዪው ይሆናል እንጂ፣ ዕምባሽን በጥላው ውስጥ ወዳፈሰስሺበት፣ ወይም ፈንዲሻ ሳቅሽን ወደረጨሽበት፣ ዛፍ ተመልሰሽ ስትሄጂ፣ ዛፉ በፍንደቃ ያጨበጭብልሻል። የሚያውቅሽ ጎዳና የዱካሽን ቅርበት ሲሰማ ሊቀበልሽ ቀና፣ ቀና ይላል። አለቱም ገጽሽን ሲያይ በፈገግታ ይፈካል። ውሃውም በናፈቀው ገፅታሽ ውልብታ ኃይል በደስታ ማዕበል ይናወጣል። እምታስታውስሽ ምድርም እንዳየችሽ እምብርቷን ገላልጣ በፀደያዊ ፍካት ትፈግጋለች።”     

2. ሴቶች እንዴት ለምድርም ለጥበብም ቅርብ ሆኑ?
ሀ. በግብርና ሕይወት ውስጥ ያሉ እናቶቻችንን ውሎና ክህሎት እንመልከት። ወንዶች በአመዛኙ በሰፋፊ እርሻዎችና በውስን የገበያ ሰብሎች ላይ ሲያተኩሩ፣ ሴቶች ግን ለጤናውም ለቅመሙም፣ ለሽታውም ለማጌጫውም፣ ለዕለት ጉርሱም ለስዕለት ግብሩም፣ በሚሆኑ የጓሮ አትክልቶች ላይ ያተኩራሉ። ይህ፣ ለዘመናችን እጅግ አስፈላጊ የሆነው የ”Genetic diversity” እውቀትና ክህሎት እነሱጋ እንዳለ ያሳየናል።
ለ. ከምድር መላቀቅን (Transcendence) በሚያስተምሩ ክርስትናንና እስልምናን በመሳሰሉ መጤ እምነቶች ውስጥ የወንዶች መሪነትና “የጥበብ” የበላይነት ጎልቶ ይታያል። እኚህ ሃይማኖቶች በየደረሱበት ለእናት ተፈጥሮ መልካም እንዳላደረጉ የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች አሉ። በአንፃሩ፣ “ባዕድ አምልኮ” ብለን በምንኮንናቸው፣ ከተፈጥሮ ጋር በሕብር አብሮ የመኖርን አስፈላጊነት በሚያሳዩትና፣ ከወንዙና ከተራራው፣ ከወቅቶች መለዋወጥም ጋር በተቆራኙት እሬቻን፣ አቴቴን፣ አድባርን፣ በመሳሰሉ አገር-በቀል እምነቶች ውስጥ ሴቶች ከፍ ያለውን ሚና ይጫወታሉ። ይህ የሚያጎናፅፋቸው ልዩ ክህሎትና ጥበብም ዛሬ ምድር አብዝታ እምትፈልገው ነው። 
ሐ. ሴቶች፣ በአካላዊና በሥነ-ሕይወታዊ ሂደቶቻቸው ላይ በሚከሰቱ ለውጦች ምክንያት (የወር አበባ፣ እርግዝና፣ መውለድ፣ ማጥባት፣ ማሳደግ፣ ወዘተ)፣ ለአካባቢያዊና ወቅታዊ ለውጦች፣ ለሽታውም ለድምፁም፣ ለብርዱም ለሙቀቱም፣ ለቁርቋሬውም ለልስላሴውም፣ ለብርሃኑም ለፅልመቱም … ቅርብ ናቸው። ይህም ሥነ-ሕይወታዊና ሥነ-ልቦናዊ ስሱነት (sensitivity) ይፈጥርባቸዋል። ለአንድ-አይነትነት፣ ሲከፋም (አይሞቀው፣ አይበርደው እንዲሉ) ለስሜት ድንዛዜ፣ ከተጋለጠው የወንዶች ሥነ-ሕይወታዊና ሥነ-ልቦናዊ ተፈጥሮና ዝንባሌ አንፃር ይህ ስሱነት ሴቶችን ለጥበብ ቅርብ ያደርጋቸዋል። 
መ. ማኅበርን፣ ዕድርን፣ ዕቁብን ወዘተ… ብንመለከትም፣ ወንዶች የመሪነቱንና የሆይሆይታውን ሚና ሲጫወቱ ሴቶች ግን ሌሎችን በማገልገል፣ (ለምሳሌ በማብሰል፣ ወዘተ…) እና ቤተሰባዊ ህብረትንና ውህደትን በመፍጠር ላይ ያተኩራሉ። 

እነዚህ የአተያየ-ጾታ ሚናዎች ኤኮኖሚያዊ ስነ-ልቦናዊና ማኅበራዊ ዋጋቸው እንዲኮስስ መደረጉ እውነተኛ ዋጋቸውን ከቶም አያሳንስም። የጾታን እኩልነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ትገል ውስጥ የእነዚህን ሚናዎች ዋጋ ማሳደግ እንጂ ሴቶች እነዚህን መሰል ሚናዎች እንዲተውአቸው ማድረግ ተገቢ አይመስለኝም። ይህ ግን በእነርሱ ምርጫ እንጂ እንደባህላዊ ወይም ተፈጥሮአዊ ግዴታ የሚጫንባቸው መሆን የለበትም። በዚህ በተለወጠ ዘመናችን ወንዶችም በእንዲህ አይነት ሚናዎች ላይ ሊሳተፉ እንደሚችሉ የማያከራክር ሆኖ።(መልካም ወዳላደረጉ ተራምደን ወዳለፍንባቸው መንገዶች የኋሊት እንመለስ ማለት እንዳልሆነም ግልጽ ሆኖ።)  

“ካች ዩር ቴንደር” ከላይ የጠቀስኳቸውን አይነት ብዙ የባህላዊ ገፀ-ምድር ንባቦችን መሠረት በማድረግ  እንዲህ ይላል፦

‘I think, women are closer to the spirit of the land and see. Their feet are fairer on the road than that of men. They sing and dance the memory of the ancient tale in their silence and utterance, in their stillness and movement. The land responds to them better.’ P. 270
“ይመስለኛል፤ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ለምድር መንፈስ ቅርብ ስለሆኑ ረቂቅ ሚስጥራትን ማየት ይችላሉ። የእግሮቻቸው ዳናም እንደወንዶች እርምጃ ጎዳናውን የማያቆስል ልስሉስ ነው። የጥንታዊውንም ምድራዊ ጥበብ ትዝታ በዝምታቸውም በንግግራቸውም፣ በእርጋታቸውም በእንቅስቃሴያቸውም ውስጥ ያዜሙታል፤ ይደንሱታልም። ምድሪቱ ለእነርሱ ፈጣን ምላሽ ትሰጣለች።” 

3. አፍሪካ ለምን፣ “በመሠረቱ የሴት መሪዎች ምድር” ተባለች?
“ካች ዩር ቴንደር” የአፍሪካን ሴት መሪዎች ሚና ከቅርብ ዘመኗ እቴጌ ጣይቱ ጀምሮ እስከ ጥንታዊያኑ ህንዴኬዎችና ክሊዮፓትራዎች ድረስ ይዳስሳል፤ በምናውቃቸው የታሪክ መጽሐፍት ውስጥ ብዙ የማይወራላቸውን ሴት መንፈሳዊና የጦር መሪዎቻችንንም ያነሳሳል። ለምሳሌ፦ የወራሪውን የጀርመን ጦር በጀግንነት የተዋጋጉትን፣ ከላይኛው የኩሽ ምድር ተነስተው በኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና ኮንጎ ልሳነ-ምድር ውስጥ የሚመላለሱትን ኒያቢንጊዎች፣ የሎቬዱን የዝናብ ንግስቶች፣ የዙሉላንዷን ናንዲ፣ የስዋዚዎችን ሌዲ ኤሌፋንት፣ የሾናዋን ምቡያ ንሃንዳ፣ የአንጎላዋን ንዚንጋ፣ የአሻንቲዎችን ያ አሳንታዌ፣ የሃውሳዎችን ጉምሱዎች፣ ወዘተ… በማንሳት፣ እኚህ ሴቶች ታሪካቸው ባይፃፍም የአፍሪካ እውነተኛ መሪዎች እንደነበሩ በመሟገት፣ የዛሬዎችን እንስት ጀግኖች ከእነዚህ እመው መናፍስት ወራሾች ውስጥ ለማግኘት ይሞክራል። 

በነገራችን ላይ ይህ መጽሐፍ ስለአፍሪካዊ ቤተሰባዊ አንድነት ነው የሚዘምረው። እንዲህ እያለ፦

‘I came out of the Sea; tanned my skin in the molten stones of the Danakil; flowed down the Great Rift of my thick lips; stretched westward across the desert of my forehead; walked down the prairies of my chest; deep into the Congo of my heart; far down the Kalahari of my feet. I am a soul of thousand faces. I am a word of thousand versions. Redemption!’ P. 198
“ከቀዩ ባሕር ዕምብርት ፈለቅሁ፤ በዳናኪል ቅልጥ አለቶች ቆዳዬን አጠየምኩ፤ በወፋፍራም ከናፍሮቼ ስምጥ ሸለቆ ቁልቁል ፈሰስኩ፤ በግንባሬ (ሰሃራ) በረሃ በኩል ወደምዕራብ ተንጠራራሁ፤ በደሬቴ የሳር ምድር ተንደረደርድሬ እልቤ ኮንጎ ውስጥ ጠልቄ ገባሁ፤ ወደእግሮቼ ካላሃሪም አቆልቁዬ ዘለቅሁ። እኔ ሺህ ፊት ያለኝ አንድ ነፍስ ነኝ። እኔ ሺህ ዲቃላ ያለኝ አንድ ቃል ነኝ። (እኔ አፍሪካ፣ እኔ አፍሪካዊ ነኝ!) ትንሳኤ!” 
ይህም የውህደትና የአንድነት እይታ ለሴቶች ይበልጥ የቀረበ ሴታዊ (Feminine) እይታ ነው።

4. (በመጨረሻም) አፍሪካ ለምን ሴት ተባለች?

ከ”ካች ዩር ቴንደር” ዋና ገፀ-ባኅሪያት አንዱ የሆነው ጎዳና ወይም ታማ፣ ከላይ የጠቀስኩላችሁን፣ የዓለማችንን የተንጋደደ ሥልጣኔ የሚወክለውን “የተጠማ ፅዋ” (The Thirsty Cup) ምስጢር ለማወቅ፣ ፅዋውንም እንደወይን ሞልተው አፍሪካንም ዓለማችንንም ከጥፋት የሚታደጉትን የአፍሪካዊ ሴት ጀግኖች ማንነት ለማወቅ፣ ከቢሾፍቱ ሃይቆችና ከእንጦጦ ተራራ ተነስቶ፣ የሶፍ ኡመር ዋሻን፣ ዬሃን፣ አክሱምን፣ ወዘተ… ወደመሳሰሉ የአፍሪካ ታላላቅ የገፀ-ምድር ቅርሶች እየሄደ ምድሪቱ ምስጢሩን እንድትፈታለት ይማፀናታል። ለምሳሌ አክሱም ላይ ደርሶ እንዲህ ይላል፦

“What was your secret, O Hendeke of the untouchable fame! What the source of your strength, O you queen of the undying flam! What was your anger for, O Yodit of the unyielding seed! What did you hide from the temptations of the King, that master of a thousand concubines, O Sheba of the peerless wisdom!” P. 276
“የአይደረስበቱ ዝና ሕንዴኬ ሆይ፣ ምስጢርሽ ምን ነበር? አንች የማይከስመው ነበልባል ንግስት ሆይ፣ የብርታትሽ ምንጭ ምን ነበር? የማይሞተው (ይሁዳዊ) ዘር ዮዲት ሆይ፣ ቁጣሽ ስለምን ነበር? የወደር አልባው ጥበብ ሳባ ሆይ፣ ከዚያ የሺ እቁባቶች ጌታ፣ ከዚያ (ይሁዲ) ንጉስ ብልጠት፣ የሰወርሽው ሚስጢር ምን ነበር?”

ጎዳና፣ በሌሎች ገፀ-ምድሮች አማክሎ አሶሳ ይደርስና፣ አሁን የህዳሴ ግድብ በሚዘረጋበት የጉባ ተራራ ላይ ተቀምጦ፣ እግሮቹን በቅዱሶቹ የበርታ አለቶች ላይ አንተርሶ፣ አባይ ስውሩን ድንበራችንን ተሻግሮ፣ “ብሉ ናይል” በሚል አዲስ ስም ተጠምቆ፣ የኑቢያን ምድር እየባረከ የፈርኦኖችን ምድር ሊያረሰርስ ሲገሰግስ እየተመለከተ እንዲህ ይላል፦

"O Cleopatra! What is the secret that you hid from him who claimed to love you; from him who made you queen when you are already one; from him who told you that you are white when you are black and comely - as black and comely as your sister of River Abbai; … as black and comely as the soil that bore you; [and as black and comely as the tents of Kedar and the curtains of Solomon.]?"  P. 277
“ክሊዮፓትራ ሆይ! ከዚያ፣ እንደሚያፈቅርሽ ከተናዘዘልሽ ቄሳር የደበቅሽው ሚስጥር ምን ነበር? ከዚያ አንቺ ቀድሞም ንግስት ሆነሽ ሳለ፣ አነገስኩሽ ካለሽ ቄሳር የደበቅሽው ሚስጥር ምን ነበር? ከዚያ፣ አንቺ ጥቁርና ውብ ሆነሽ ሳለ ነጭ እንደሆንሽ ከነገረሽ ቄሳር፤ እንደእህትሽ እንደአባይ ልጅ ጥቅሩና ውብ ሆነሽ ሳለ ‘ነጭ ነሽ’ ካለሽ ቄሳር፤ እንዳበቀለሽ አፈር ጥቁርና ውብ ሆነሽ ሳለ፣ ‘ነጭ ነሽ’ ካለሽ ቄሳር፤ እንደ ቄዳር ድንኳኖችና እንደሰሎሞን መጋረጃዎች ጥቁርና ውብ ሆነሽ ሳለ፣ ‘ነጭ ነሽ’ ካለሽ ቄሳር የደበቅሽው ሚስጥር ምን ነበር?”
ይህንን እንዳለ አንድ የበረሃ መንፈስ ይገለጥለትና እንዲህ ይለዋል፦

"That she is made pregnant with fire and gave birth to water." P. 277
“ሚስጥሩማ፣ እርሷ በእሳት መንፈስ ጸንሳ ውሃ መውለዷ ነው።”

በአሶሳው ጫማ ሰፊ ልጅ አካል የተገለጠው መንፈስ ይህንን ብሎ ይህች ምድር ቅድስት ስለሆነች ጎዳና የቆሸሹ ጫማዎቹን እንዲያወልቅ ይነግረዋል። ጎዳናም ምድሪቱ ለምን ቅድስት እንደሆነች ይጠይቀዋል። መንፈሱ መልሶ እንዲህ ይላል፦  

"Don't you see the secrets of the heavens written on it - a Tablet of the gods? Fire it takes from out the sea and water it gives back." P. 278
“የሰማያት ሚስጢራት የተፃፉባት የአማልክቱ ታቦት እንደሆነች አይታይህምን? ከባህሩ እሳት ተቀብላ ያንን እሳት ወደውሃነት ለውጣ መልሳ ለባህሩ ትሰጣለች።”
ጎዳና ወደየረር ተራራዎች ሄዶ የዳናኪል ረባዳንና የኢርታ-አሌን ነፋሊት በአይነልቦናው ሲያይ፣ ያ የአሶሳ መንፈስ የነረገው ሚስጥር ትርጉም ግለፅ ሆኖ ይታየዋል። እሳት፣ በጎመራ ነፋሊት መልክ ከቀይባህር ማፀን ተነስቶ፣ በታላቁ የስምጥ ሸለቆ በኩል ወደቪክቶሪያ ሃይቅና በዙሪያው ወዳሉ ተፋሰሶች ይወርድና፣ ኢየሱስ ውሃውን ወደወይንነት እንደለወጠው፣ በጥቁሩ አፈር ወደውሃነት ተለውጦ፣ በናይል ዴልታ በኩል ተመልሶ ወደወጣበት ባሕር ይፈስሳል።
እንግዲህ አፍሪካ፣ በእሳት መንፈስ ፀንሳ የውሃን መንፈስ የወለደች እንስት መሆኗም አይደል? “ለዚያ ነው አፍሪካ የሰው ዘርም የቀዳማይ ሥልጣኔም ማሕፀን ለመሆን የበቃችው፤” ይለናል “ካች ዩር ቴንደር”። [ይህንን ከሃይማኖታዊ ምሳሌ ጋር ስናነጻጽረው፣ ለሙሴ የተገለፀውን ነበልባላዊ መንፈስ በከሰተው ቁጥቋጦ (ዕፀ-ጳጦስ) የሚመሰለው የቅድስት ድንግል ማሪያም ማሕፀን፣ እሳት የሆነውን ቅዱስ-መንፈስ በውስጡ ከስቶ የሕይወት ውሃ የሆነውን ኢየሱስ እንደሰጠን ሁሉ፣ የአፍሪካ ምድርም እሳት የሆነውን የሰው መንፈስ ስጋ ነስቶ ለምድር የሰጠ ማሕፀን ነው ማለት ነው። ያም አፍሪካን ሌላኛዋ ዕፀ-ጳጦስ ያደርጋታል።]

“አንበሶች ታሪካውን መፃፍ እስከሚጀምሩ የእነርሱ ታሪክ በአዳኞቻቸው ገድል የተሞላ ይሆናል፤” የሚል አፍሪካዊ አባባል አለ። አንድ አፍሪካዊ ተረት ልንገራችሁና ሃሳቤም ንግግሬንም ልቋጭ።
ጠቢቡ ኤሊ ፍጥረታትን እየተዘዋወረ ስለጥበባቸው ይጠይቃቸዋል። ጥንቸል ስለፈጣን ሯጭነቷ አውርታ ስታበቃ፤ ኤሊው፣ “ድንቄም! ተረጦና ተሞተ!” ብሏት ያልፋል። ሸረሪትም ስለጥበቧ፣ ስለፈትልና ሽመናዋ አብዝታ ካወራች በኋላ፣ አያ ኤሊ፣ “ድንቄም! ተሸመነና ተሞተ!” ብሎ ያልፋል። ዛፉም፣ ስለፍሬው ማማርና ጣዕም ተንትኖ ሲያበቃ፣ “ድንቄም! ተፈራና ተሞተ!” ብሎት ይሄዳል አያ ኤሊ። የምድርን ጥበብ አብዝቶ የሚያውቀው ኤሊ ፍጥራኑን ሁሉ እንዲህ እየጠየቀ፣ “ድንቄም!” እያለ በራሳቸው እንዳይኮሩ ያደርጋቸዋል።

እንደኔ እይታ፣ በራሳቸው ጥበባዊ ብቃት ሞገስን የተጎናጸፉ ኢትዮጵያዊ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች እጅግ ጥቂት ናቸው። አብዛኛዎቹ ሥራዎች በዘመን አጋጣሚዎችና ኃይሎች ግፊት የክብር መንበር ላይ ይፈናጠጣሉ። እኝህ ጊዜ ያነሳቸው ሥራዎች፣ ይፍጠንም ይዘግይም፣ ጊዜ እንደሚጥላቸው እርግጥ ነው። ዛሬ የጥበቡን ዓለም በጉልበትም በብልጠትም የተቆጣጠሩት ወንዶች፣ ወንዳዊነትና ሌሎች ከዘመኑም ከጥበቡም ጋር የማውይሄዱ ውስን አተያዮች ናቸው። ይህ የጥበብ እግረ-ሙቅ ነው። ቢያንስ ሴቶቻችን፣ በዚህ ጽሑፍ አጭር ዳሰሳ እንዳየነው፣ ከምድር ጋር ያላቸው ጥብቅ ቁርኝት የሰጣቸውን ጥበብ የማውጣት ዕድሉን አግኝተው ጥበባችንን ወደምሉዕነት እስከሚያሸጋግሩት ድረስ፣ የዛሬውን ግማሽ ጥበብ፣ “ድንቄም! ተከየነውና ተሞተው!” እያልን በተስፋ እንጠብቃለን።  
አመሰግናለሁ!

Tuesday, June 19, 2018

የጥበብና የጸሎት ጉዞ ወደ አሥመራ

የጥበብና የጸሎት ጉዞ ወደ አሥመራ

ከላይ የምታዩት፣ እኔና ባልደረቦቼ አሥመራ ላይ፣ እንዳ-ማሪያም (ቅድስት ማሪያም ቤተክርስትያን) ፊትለፊት፣ (በቅስት የገባው ደግሞ ከረን)፣ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መጀመር ትንሽ ቀደም ብሎ፣ የተነሳነው ፎቶ ነው። ጦርነት የዘጋውን ጎዳና ሰላም እንደከፈተው እዚህች ቦታ ተመልሼ የምስጋና ጸሎት ላደርግ ስመኝ ቆይቻለሁ። ጥበቃው ይህንን ያህል ቢረዝምም እኔም ተስፋ ሳልቆርጥ፤ ምኞቴ እውን ሊሆን የሚችልበት ምልክትም ሳይታይ ብዙ ቆየ። ግን፣ ለምንድነው መሪዎቻችን “ሰላምን ፈርመናል” እስኪሉን እምጠብቀው? ራሴው ወደኤርትራ ተጉዤ ስለሰላም አልዘምርም? መቼም ይህ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖር ኢትዮጵያዊ ከንቱ ህልም ነው እሚመስል። እሺ፣ ብቻዬን አልችለው ይሆናል። እናንተ ብትተባበሩኝስ? የኔ ብጤ ተራ ዜጎችን፣ የፌስቡክ ወዳጆቼን፣ አንቺንና እንተን፣ ማለቴ ነው። ወደኤርትራ ነፃ የጸሎትና የጥበብ ጉዞ አድርገን ለዓመታት የተለያዩ ቤተሰቦች እንዲገናኙ፣ ለሰላም የሚደረገውም ተቋማዊ ጥረት ጉልበት እንዲያገኝ፣ አስተዋፅዖ እናበረክት ዘንድ እንድንተባበር ጥሪ እያደረግሁ ነው። ይህ ለኢትዮጵያዊያንም ለኤርትራዊያንም የቀረበ የመንፈሳዊና የጥበባዊ ጉዞ ጥሪ ነው።   

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲፈነዳ፣ ትግራይ ውስጥ፣ ማይ-ነብሪ በተባለ ቦታ ነበርኩ - በግድብ ሥራ ምክንያት። እኔና ባልደረቦቼ ባንደ ተራ በሚመስል ንጋት ማልደን ለሥራ ስንነሳ የታንክና ከቶም አይተናቸው የማናውቃቸው የከባድ መሳሪያዎች ቅፍለት ሲግተለተል ተመለከትንና ምፅዓት የመጣ ያህል ደነገጥን። ለካስ ምሽት ላይ፣ ወይም ንጋት አካባቢ፣ ወዳጆች በነበሩት ኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል ጦርነት መፈንዳቱ ታውጆ ኖሯል!

የጦርነት ነጋሪቱ በተሰማበትና የጦሩ ቅፍለት በታየበት በዚያ ቀን ምሽት፣ የመንደር እናቶች ተሰባስበው፣ በማይ-ነብሪ አሸዋማ መሬት ላይ በጉልበትና በክርናቸው እየዳሁ፣ ሕማሙና ከተጋጠ ጉልበትና ክርናቸው የሚዝረበረበው ደም ሳያግዳቸው፣ እስከሌሊት “ምምህላል” (ምሕላ) አደረጉ፦ “አቤቱ፣ ይህንን ድንገት የፈነዳ ጦርነት ያዝልን! በጣዕር ማጣጣም የጀመርነውን ሰላም መልሰህ አትንጠቀን! ከእሳት የተረፉ ልጆቻችንን እንደገና እሳት አትሞጅርብን! ተማለለን፣ አቤቱ ተማለለን!” እያሉ። የእኒያ እናቶች እምነትና የጸሎት ብርታት እማያምኑ ጓደኞቼንም ሳይቀር ለጸሎት አስጎነበሰ።

ሊፈነዳ በማስገምገም ላይ ያለን ጦርነት እንዲህ ስቀርብ ያ የመጀመሪያዬ ነበር። ተቃርኖው አስደነቀኝ! እዚህ፣ እኚህ እናቶች ጦርነቱ እንዳይነሳ ዕምባና ደም ያፈስሳሉ። እጉኑ ደግሞ ሌሎች ኃይሎች ለጦርነቱ ዕምባና ደም ለመገበር ይጎርፋሉ። ማይ ነብሪ ትንሽ የገጠር ከተማ ነች። በትልቋ ኢትዮጵያ ውስጥ ስንቶች ተመሳሳይ ጸሎት እያደረጉ ይሆን? ያን ያህል ደምና ሕማም የተገበረው ጸሎት ጦርነቱን አለማስቀረቱን አስቤ፣ “ጸሎት ብላሽ! አወይ የባከነ የዋህነት!” አላልኩም። ይልቅ፣ ያ ጸሎት ከሁለቱም ወገኖች ለረገፉት የትዬሌሌ ነፍሳት ስርየት፤ ጦርነቱ ለሰበራቸው ልቦችና ቤተሰቦችም ፅናት፣ እንደሰጠ ማሰብ መረጥኩ እንጂ። ለኔ፣ የጸሎት ኃይል፣ ልክ እንደጥበብ ኃይል፣ ከቶም አይከሽፍም፤ አይባክንምና።        

ከዚህ ክስተት ትንሽ ቀደም ብሎ (ሐምሌ 1988)፣ እኔና የውሃ-ማቆር ሥራ ባልደረቦቼ ለልምድ ልውውጥ በሚል፣ ኤርትራን የመጎብኘት ዕድል ገጥሞን ነበር። አሥመራ የደረስነው ባንዲራ መውረጃ ሰዓት አካባቢ ነበር። እኛ ቀድመን እንዳለፍን ለካስ በሌላ መኪነ በርቀት ይከተሉን የነበሩ ባልደረቦቻችን በወታደሮች ተይዘው ጣቢያ ወርደው ኑሯል። በኋላ እንደነገሩን፣ “እንዴት ባንዲራ በመውረድ ላይ እያለ መኪና ታንቀሳቅሳላችሁ?” የሚል ነበር ምክንያቱ። ባልደረቦቻችን፣ እንግዳነታቸው ታውቆ ያለብዙ ችግር ተለቅቀው ተቀላቀሉን።

በበነጋው ጉብኝታችንን ስንጀምር እኔ (በስዕሉ እንደሚታየው) ባህላዊ ሸማ ለብሼ፣ በባርኔጣዬም ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ጥብጣብ አድርጌ፣ ወጣሁ። ጠንቃቃ ጓደኞቼ፣ ኤርትራዊያን “ይህ ባንዲራ” የሰጣቸው ቁስል ገና ስላልሻረ ባንዲራውን ሲያዩ ሊቆጡ ይችላሉና እንዳወልቀው መከሩኝ። እኔም፣ “እነሱ ባንዲራቸውን እንዲያ ሲያከብሩ የኔን ባንዲራ ለምን አያከብሩም?” በሚል ስሜት፣ ምክራቸውን እንዳልሰማሁ ሆኜ አሳለፍኩት። ለሳምንት ያህል የኤርትራን ገጠርና ከተማ ስንጎበኝ፣ ባለባንዲራ ባርኔጣዬ አብራኝ ነበረች። ለአገራዊ ጥላቻ መግለጫ ባንዲራ ማቃጠል በተለመደባት ዓለማችን ይህን ማሰቤ የዋህነት ሊመስል ይችል ይሆናል።  

የጓደኞቼ ስጋት ግን እውን አልሆነም። የትኛውም ኤርትራዊ ባንዲራዬን እንዳወልቅ አልጠየቀኝም፤ የመከፋት ስሜትም አላሳየኝም። እንዲያውም፣ አንዲት ኢትዮጵያዊት አሮጊት ቀርበውኝ፣ ባንዲራቸውን በአደባባይ በማየታቸው የተሰማቸውን ደስታና አገራቸውንም ለማየት ያላቸውን ምኞት አንጀት በሚያባባ መልክ ገለፁልኝ። በተረፈ፣ የኤርትራ ቆይታችን በዚህች ባንዲራና በየሆቴሉ እንሰማቸው በነበሩ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች የታጀበና የወዳጅነት ስሜት የተሞላው ነበር። ካለፈው መቋሰል በኋላም ኤርትራዊያን የኢትዮጵያን ሙዚቃ ያንን ያህል መውደዳቸው ደስ ይላል። አንዳንዶቻችን ከኤርትራዊያን ጎን ሆነን ጸሎት እንዳደረግን ሁሉ በምንጋራውም ሙዚቃም አብረናቸው ጨፍረናል። ቢያንስ ይህች ገጠመኜ፣ በኤርትራዊያንና በኢትዮጵያዊያን መካከል የተፈጠረው ወቅታዊ መቃቃር፣ ሁለቱን ሕዝቦች ያስተሳሰራቸውን ጥልቅ የደም፣ የእምነትና የጥበብ ማተብ ሊበጥስ እንደማይችል የነበረኝን እምነት አፅንታልኛለች።  

ኋላ ለትምህርት ቻይና ስደርስ የተቀበለኝ እዩኒቨርሲቲው ቀድሞ ደርሶ የነበር ኤርትራዊ ነበር። ያ ኤርትራዊ፣ ያውም የቀድሞ የነፃነት ታጋይ፣ ኋላም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ላይ የተሳተፈ ተዋጊ፣ በአንድ ዶርም ውስጥ ለሁለት ዓመታት ያህል አብሮኝ ቆየ። የእኔንና የዚያን ኤርትራዊ ወዳጄን ግንኙነት እንደተላጠ ሙሉ ብርቱካን ብናስብ፣ የግንኙነታችን ብሔራዊና ፖለትካዊ ገፅታ የብርቱካኑን አንድ ብልት ያህልም አይሆንም። የዚያ ወዳጄ ቀልድና ቁምነገር፣ በኔ ጉትጎታ ይነግረኝ የነበረው የጦርነት ውሎው አሳዛኝ ተረኮች፣ እንጋራቸው የነበሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ዘፈኖች፣ አብረንም እንደግማቸው የነበሩ ጸሎቶች፣ በልባችን የሆነ ጥግ ተሰውሮ ሊኖሩ የሚችሉን የአብሮኛነት ግርዶሾች ሳያስወግዱልን አልቀረም። ለሁለታችንም፣ የይቅርታና የመረዳት ጎዳና ተፈጥሮአዊውና የተሻለው የሙሉነት ምርጫ ነበር።

ስለ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትና የሰላም ጉዳይ በተነሳ ቁጥር፣ ልክ እንደማይ ነብሪ እናቶች በዕምባና በደም ግብር ሰርክ ስለሚጸልዩ የትየሌሌ ወላጆች አስባለሁ - የተለዩአቸውን ልጆቻቸውን ገፅታ ለቅፅበትም እንኳ ለማየት እየጠበቁ ጸሎታቸው ምላሽ ሳያገኝ በቀቢፀ-ተስፋ ወደየመቃብሮቻቸው የሚወርዱ የትየሌሌ ወላጆችን። በኤርትራ ውስጥ በጸሎትና በሙዚቃ ታጅቤ ያሳለፍኳቸውን ደሳስ የሚሉ ጥቂት ቀናት አስባለሁ። አስመራ ላይ እንዳገኘኋቸው እናት ከሁለቱም ወገን ወደየቀዬ ወደአገራቸው እሚመለሱባትን ዕለት ሞት በሚፈታተነው ተስፋ  የሚጠባበቁ ግለሰቦችን አስባለሁ። ቻይና እንዳገኘሁት ኤርትራዊ ወዳጄ አቁሳይ ትዝታዎቻቸውን አሸንፈው ከሚለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉንን የግንኙነቶቻችንን መሠረቶች ለመጨበጥ ዝግጁ የሆኑ፣ ብርቱና ምሉዕ ሰብዕና ያላቸውን፣ ብዙ ሰዎች አስባለሁ።

እርግጥ ነው፣ የኔ ተሞክሮና ትዝታ ከብዙዎች ነፍስ-አብጠርጥር ተሞክሮና ትዝታ ጋር ሲነፃፀር እጅግ እምንት ነው። ቢሆንም ግን፣ ይህች ልንቁስ መሳይ ትዝታዬ በሁለቱም አገሮች ውስጥ ብዙ ሰዎች የልብ-ለልብ ግንኙነትን እየናፈቁ እንደሁ ለማየት ከበቂ በላይ ነች። ይህች ትዝታዬ፣ እንዲህ እያልኩ ለመጠየቅም ከበቂ በላይ ነች፦ በአገሮች መካከል ያለ ግንኙነት የሕዝቦችና የግለሰቦችም ግንኙነት ጭምር አይደለምን? ይህ ሰብዓዊ ግንኙነት ጨርሶ የሌለ እስክመስል ድረስ ድምጽ የተነፈገው ለምንድነው? እኛ፣ ራሳችንን ‘ሃይማኖተኛ ሕዝብ፣ አማኝ ሕዝብ፣’ እያልን ከቁሳዊነት አንፃር ሳይሆን ከመንፈሳዊነት አንፃር ለመግለፅ የምንፈልግ ሕዝቦች አይደለንምን? የማንነታችን ትንሹ ክፍል ሰብዓዊም ሆነ አገራዊ ግንኙነቶቻችንን እንዲገዛና እንዲመራ እምንፈቅደው ለምንድነው? ኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ሰብዓዊ ገፅታን ከፍ ያለ ሕዝባዊ መገለጫና ኃይል እንዲያገኝ ብናደርግ ለሰላም የሚደረገውን ተቋማዊ ጥረት አያግዝ፣ አያፋጥን ይሆን?

ስጀምር እንዳልኳችሁ፣ ለኢትዮ-ኤርትራ የሕዝብ-ለሕዝብ ግንኙነት ጉልበት ለመስጠት፣ በዚህም የተለያዩ ቤተሰቦች እንዲገናኙና በመንግስታቱ መካከል ለሚደረገው የሰላም ጥረት እገዛ ለማድረግ፣ ለሰላም መንፈሳዊና ጥበባዊ ጉዞ እናደርግ ዘንድ እንድትተባበሩኝ ጥሪ ይዤ ቀርቤአለሁ። ይህንን ሃሳብ ለረጅም ጊዜ እያምሰለሰልኩት ብቆይም ከዚህ ቀደም ጊዜው የደረሰ መስሎ አልተሰማኝም ነበር። በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትራችን የተገለፀው የፖለቲካ ፈቃደኝነት ሃሳቡን እውን ለማድረግ ጊዜው መድረሱን አመለከተኝ። እነሆ፣ ሃሳቤ ይህ ነው፦

እኔና ይህንን ሃሳብ የሚደግፉ የፌስ-ቡክ ወዳጆቼና የወዳጆቼ ወዳጆች፦
   1.  ከየትኛውም ሃይማኖትና ዕምነት ከ500 እስከ 1000 ያህል ግለሰቦች ወደኤርትራ የጸሎትና የጥበብ ጉዞ ለማድረግ ፈቃደኝነታቸውን እንዲገልፁ እንጠይቃለን። (ይህ ጉዞውን ለማድረግ የሚነሱ ሰዎች ቁጥር ብቻ ነው) በኤርትራም ውስጥ ለተመሳሳይ ዓላማ ወደአዲስ አበባ ለመጓዝ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች እንዲተባበሩ በፌስቡክና በሌሎች ማኅበራዊ ድረ-ገፆች እንጠይቃለን

    2. የሚፈለገውን ያህል ድጋፍ እንዳገኘን፣ ጥረታችንን በጋራ እናደራጃለን፣ እናቅዳለን ከሁለቱም አገሮች ከያኒያንንና ሌሎች ባለተፅዕኖ በጎ-ፈቃደኞችንም እያሳተፍን፣ የመንግስታቱን የሚመለከታቸው ተቋማት ትኩረት ለማግኘት እንሠራለን።

   3. ቀጥሎም ከሚመለከታቸው የሁለቱም መንግስታት ተቋማት ፈቃድ እናገኛለን፤ የአፍሪካ አንድነት፣ የተባበሩት መንግስታትና፣ ሌሎች ለሰላም የሚሰሩ አካላትም አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲያደርጉልን እንጠይቃለን

    4. በኦፊሴል ቀነ-ቀጠሮ ይዘን፣ አስፈላጊ ከሆነ በአፍሪካ ሕብረት ወይም በተባበሩት መንግስታት የሰላም ሃይል ታጅበን፣ ወደኤርትራ ታንኮች ለጦርነት በሄዱበት ጎዳና ላይ እኛ ለሰላም ሕዝባዊ የጸሎትና የጥበብ ጉዞ እናደርጋለን በእንዳ-ማሪያም ፊትለፊት ወይም በተመረጠ ሌላ ቦታ ላይ ከሁሉም ሃይማኖቶች ከተውጣጡ ኤርትራዊያን ጋር የጸሎት፣ የጥበብና የወዳጅነት ውሎ እናደርጋለን።

    5. በምላሹም፣ ለሰላም ጉዞው ፈቃደኝነታቸውን የገለፁ ኤርትራዊያን አብረውን ወደአዲስ አበባ ይመጡና በመስቀል አደባባይ ወይም በሌላ በተመረጠ ቦታ ላይ ተመሳሳይ የጸሎት፣ የጥበብና የወዳጅነት ውሎ አድርገው ወዳገራቸው ይመለሳሉ።

   6. የሁለቱ ሕዝቦች የተናጋ ወዳጅነት ተጠግኖ ሰላማዊ ትስስሩ በፅኑ መሠረት ላይ እንደገና እስኪገነባ ድረስ ይህንን የእምነትና የጥበብ ጉዞና ውሎ በየዓመቱ ወይም በየሁለት ዓመቱ ማድረግ እንቀጥላለን።  

ይህንን ሃሳብ የምትደግፉና፣ በሰላም ጉዞውና በዝግጅቱ ላይም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለመሳተፍ የምትሹ፣ ወዳጆቼ “ላይክ” እና ለየወዳጆቻችሁም “ሼር” በማድረግ ድጋፋችሁን እንድትገልፁ እጠይቃለሁ። የምናገኘው ድጋፍ እየጨመረ ሲሄድ ከተባባሪዎቻችን መካከል ጉዞውን ለማደራጀትና ለመምራት የሚሹ በጎ ፈቃደኞችን ከየሙያ ዘርፉ፣ ከየሃይማኖቱም፣ በጋራ እንመርጣለን። እነዚህ በጎ-ፈቃደኞች፣ የትም ቦታ ይሁኑ፣ ፌስቡክንና ሌሎች ማኅበራዊ ድረ-ገፆችን ተጠቅመው ከያሉበት (ከየቤታቸው) አስተዋፆዎቻቸውን ያበረክታሉ። ጉዞው እውን እንደሚሆን እርግጠኛ ሆነን ዝግጅቱ የሙሉ ጊዜ ሥራ እስከሚጠይቅ ድረስ ሁላችንም በትርፍ ጊዜዎቻችን ለዚህ የሰላም ኅብረት እንተጋለን። (አውቃለሁ፣ ሰላም የትርፍ ጊዜ ሥራ አይደለም። የሙሉ ጊዜና የሙሉ ልብ ሥራ ነው። በየቤታቸሁ ሆናችሁ ሙሉ ልባችሁን ከሰጣችሁን ያ ሙሉ ልብ ሙሉ ጊዜን ይፈጥርልናል ጊዜ ስጋት አይሆንም። ብቻ፣ በፀሎታችሁም፣ በየጥበቦቻችሁን አብራችሁን ሁኑ።)   

ይህ የሰላም ጥረት ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ሃሳቡን ለየትኛውም ድርጅት ወይም መገናኛ ብዙሃን አላካፈልኩም። ሃሳቡን የሚደግፉ ድርጅቶችና መገናኛ-ብዙሃን ለዚህ ጥሪ ምላሽ እንደሚሰጡ፣ ለውጥኑ ስኬትም የየድርሻቸውን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ፣ አምናለሁ። እነሱም እንደግለሰብ ጓደኞቼ ሁሉ ገፁን ላይክና ሼር በማድረግ እንዲተባበሩን እጠይቃለሁ።

በቅድሚያ ግን፣ እስቲ፣ እያንዳንዳችን በግል ለሰላም ምን ማድረግ እንደምንችል እናሳይ እስቲ፣ የፌስቡክ ወዳጅነት ምን ያህል የሰላም ጉልበት ሊኖረው እንደሚችል እናሳይ! ለምታደርጉት ድጋፍ በሁለቱ ሕዝቦች ጊዜያዊ መለያየት ያለምርጫቸው ተነጣጥለው በሚቸገሩ ቤተሰቦች ስም በቅድሚያ ምስጋና አቀርባለሁ! እንግዲህ በእንግሊዝኛው ምሕፃረ ቃል ጂፕ (JEEP – the Journey of Ethiopian and Eritrean People for Peace) ያልኩት ሕዝባዊው የጥበብና የእምነት ጉዞ ይህ ነው። በጦርነት ጊዜ ለጎርበጥባጣ መንገድና ለአስቸጋሪ መልክዓምድር እንደተሰራችው ጂፕ መኪና፣ የኛም ጂፕ ጎርበጥባጣና አስቸጋሪ ጎዳናን መጠበቅና ለዚያ መዘጋጀት አለበት። ይፍጠንም ይዘግይም ጂፓች፣ ጎዳናዋ ምንም ያህል አቀበትና ማጥ የበዛበት ቢሆንምን፣ የሰላም ጉዞዋን በድል ትወጣዋለች። ሰላም!

JEEP IS CALLING

Art and Prayer Journey to Asmara 



This is a picture taken in front of Enda-Mariam - St. Marry church - in Asmara just before the Ethio-Eritrean war. (The round insert is in Keren). I have been wishing to go back to this spot and pray for joy when peace opens the barred road to Eritrea. It has been a long time waiting. And there is no sign that this will happen anytime soon. But, why wait? Why not make it happen? This seems a sheer wish for an Ethiopian living in Ethiopia. If we the people collaborate, however, there is no reason it won’t happen. I am proposing a prayer and art Journey of Ethiopians and Eritreans for Peace (JEEP), for us to go to Asmara, and for Eritreans to come to Addis Ababa, to pray- and sing-along, and, in so doing, to create an opportunity for divided families to reunite and give impetus for the political peace process.

I was in Tigray, at a village called Mai-Nebri, when the Ethio-Eritrean war broke. Following an ordinary countryside evening, I and my colleagues woke up early (for our fieldwork) to be unpleasantly surprised by caravans after caravans of tanks and other heavy artillery entirely new to us. We later heard the media announce what was happening: war is coming!     

The very evening the war gong sounded that unexpectedly, a number of village mothers gathered, and, walking on their bare knees and hands on Mai-Nebri’s gravelly ground, made prayers deep into the night, unrestrained by the pain and the flood of blood flowing from their knees and hands – pleading God to stop the war that came so suddenly, not to take away the peace they started to enjoy after many years of suffering, and to spare their children that fatefully escaped the previous war. Those mothers’ pious and fervent prayers made even the unbelieving among us to bow down to pray.

That was the closest I experienced a looming war. The contrast was striking! There are these mothers that shed blood and tears so that the war may not come, and there are those forces marching to shed blood and tears for the war. This is a small village. One can only wonder how many more people were praying so fervently nationwide. That this prayer did not stop the war never made me consider it a wasted innocence. On the contrary, as a believer in the potency of prayers, I opted for thinking that it must have contributed for the salvation of the numberless souls slaughtered, and for the strengthening of many hearts and families shattered, by the war.

A few months earlier, I and my colleagues were in Eritrea for a work-related visit. We entered Asmara as evening approached. Members of the Eritrean army stopped our friends following us in another vehicle and took them to their quarter for questioning. As we later learned, the reason was that they were driving when the national flag was being pulled down. Learning that they were visitors, the army released them without much trouble.

When our visit started next morning, I got out in a traditional costume, with a ribbon of Ethiopian flag on my hat. Some of my cautious friends were quick to advise me to remove the flag, afraid that Eritreans may not be too pleased to see the Ethiopian flag in their land as their wounds that ‘this flag’ gave them did not yet heal. I didn't heed their advice, thinking to myself, a people that respects its flag so much should similarly respect the flags of other people; or at least allow other people to show respect for their own flag. You may consider this naiveté, knowing that people burn the flags of other nations to express their anger and they may not spare the person that caries it high when they do. 

For nearly a week, I walked around with the ribbon of the flag on my hat. The fears of my friends did not materialize. No Eritrean, in the city or in the countryside, showed me an unpleasant face because of the flag. In Asmara, an old Ethiopian lady saw the flag and approached me to express her joy to see her flag in public and her wish to return home. Otherwise, our time in Eritrea was entirely in a feeling of fellowship, seasoned by the Ethiopian music that we used to hear in nearly every hotel we visited, at times singing along with Eritreans, as some of us prayed by their side in churches, mosques, or devotional centres. This humble experience was a confirmation to my belief that the incidences of the time are powerless to sever the deeply rooted ties between the two people.    

Later, when I arrived in China for a study, it was an Eritrean guy that received me. This Eritrean, an ex-freedom fighter at that who participated in the later Ethio-Eritrean war as well, was my dorm-mate nearly two years. Our political or nationalistic side was only the smallest, an undefining aspect of our relationship. My friend’s sense of humour, the harrowing recollections of his fighting days that he used to tell me, the traditional music we joyfully shared, and the prayers we chanted together, all of which constituted the greater part of our human interactions, might have helped remove the barriers that could have been hidden in our hearts. The road of forgiveness and understanding was the natural and the most fulfilling choice for us.      

Whenever the issue of the Ethio-Eritrean peace process is mentioned, I think of the many mothers that are praying fervently, like the mothers of Mai-Nebri, for a glimpse on the faces of their beloved and are feeling frustrated thinking their prayer may not be answered. I think of the joyful times I had in Eritrea. I think of individuals on both sides, like the lady I met in Asmara, who endlessly wait with the hope of returning home. I think of people like my dorm-mate who are ready to rise above their painful memories and hold on to the stronger roots that unite than divide us.

Obviously, my experiences and memories are humble compared to the heart-rending experiences and memories of thousands. But they are more than enough to prove to me that there are many people at both sides desiring reunion, despite the anger and redness-of-face in the political realm; more than enough to make me ask: is the relationship between countries not the relationship between people and individuals as well? Why should this human relationship be denied voice to the extent that it appears non-existent? Aren’t we people that prefer to define ourselves spiritually than materially? Why should we allow the smallest part of our being define our personal and national relationships? If we give a greater public expression to the human side of Ethio-Eritrean relationship, couldn’t it energize and help speed up the political peace process?

As I mentioned earlier I am proposing a public movement, born out of my reflections such as the above, to initiate people to people collaborations and enable the political peace process find momentum. I have been thinking of this for quite long. Earlier, the time did not feel right. The political will expressed by our Prime Minister recently suggested to me that this should be the time to try to realize it.

The idea is simple. I, my Facebook friends, and their friends that support this idea will:
·         Ask 500 to 1000 individuals to sign up to make a prayer and art journey to Asmara, and for Eritreans in Eritrea to make a similar journey to Addis Ababa.
·         When we get the required number of supporters from both countries, plan and organized our efforts, involving artists and other volunteer people of influence at both sides, and try to get the attentions of relevant institutions in both countries.
·         Ask the relevant institutions of the two governments to give us permission, and approach AU, the UN, and other concerned organizations to give us assistance we may need.
·         Publicly fix an official date for the journey, and, accompanied by AU and/or UN peacekeeping forces if need be, make the journey of peace on land to hold a prayer vigil and an art and fellowship day with Eritreans of all religions and walks of life in front of Enda-Mariam or another public space.
·         On our return, have the signed-up Eritreans make a similar journey to Addis Ababa and hold the prayer vigil and the art and fellowship day at Maskal Square or at another selected public space.
·         Continue organizing this voyage for peace, this Journey of the Ethiopian and Eritrean for People for Peace, annually or biannually until the broken relationship between the two people is fixed and is re-established on a firmer foundation. 
Friends who support this idea, please ‘like’ and/or ‘share’ it with your friends. As soon as we get reasonable number of supporters, we will choose volunteer organizers in different areas of our work wherever they may be, who mainly work in their spare times from their homes using our Facebook and other social media pages until the time our move requires full time commitment.

With the interest of giving a public base for this peace effort, I did not share the idea with any institution or media. I believe the institutions and the media that support the idea will respond to this call and will make their own contribution to the realization of the JEEP.

First, let us show what we as individuals could do. Let's also show how much social media friendships may mean. I thank all of you who assist this effort in any way you could in the name of those families who suffer the separation they didn’t choose. This is JEEP – the Journey of Ethiopian and Eritrean People for Peace.  Just like the robust vehicle Jeep, created at war time for use on poor roads or open terrain, our alliance should expect, and be prepared for, a hilly and muddy terrain. Sooner or later, JEEP shall conquer its road, however much bumpy that might be! Selam!