Friday, June 26, 2015

ይህ መፅሃፍ ስለምንድነው?

Catch Your Thunder
By: O’Tam Pulto
Publisher: Partridge: A Penguin Company


ይህ መፅሃፍ ስለምንድነው?

(የኣማርኛ ርዕስ ገና ስላላወጣሁለት፣ በደፈናው መፅሃፉ በሚል እጠራዋለሁ። ኣሁንም ሆነ ታሪኩን ካነበበ በሁዋላ ጥሩ ርዕስ የመጣለት ጣል ቢያደርግልኝ በደስታ እቀበላለሁ። ወደፊት በሚመጣው የኣማርኛው ትርጉም ያንን ርዕስ እምጠቀምበት ከሆነ ወረታውን በምስጋና እከፍላለሁ።)

የመፅሃፉ ልባድ የጀርባ ፅሁፍ እንዲህ ብሎ ይጀምራል፡
ይህ የግልጋሜሽ ገድል ኣይደለም። ኣርማጌዶንም ኣይደለም። የማያኖች የዘመን መጨረሻም ኣይደለም። ይህ የማጉዳዎች “The Great Reversal” (ታላቁ ተገላቢጦሽ እንበለው?) ነው። …
ዓለም ስለግልጋሜሽም፣ ስለኣርማጌዶንም፣ ስለኖህ የጥፋት ዘመንም፣ ስለማያኖች 2012ም … ብዙ ኣንብቧል፤ ኣድምጦማል። ስለማጉዳዎች ታላቁ ተገላቢጦሽ ሊያውቅ ቀርቶ እንዲያ የሚባሉ ማህበረሰቦች ስለመኖራቸውም የሰማ ግን ኣይመስልም።  
ማጉዳዎች እነማን ናቸው? ይህ የታሪኩ ኣካል በመሆኑ ስለነሱ በዝርዝር መግለፅ ያስከፍላል። ያ ለግዜው ይቆየን። መኖሪያቸው ግን በታላቁ የምስራቅ ኣፍሪካ ስምጥ ሸለቆ በተሰነጣጠቀው የላይኛው ከንፈር ላይ፣ በጋሞ ከፍተኛ ቦታዎች፣ ከደመናው ጀርባ፣ ከጭጋጉ ባሻገር ነው። ከኣርባ የጋሞ ቤተሰቦች (ከኣርባ ምንጮች) ኣንዱ ናቸው ማጉዳዎች። ከምድራቸው እሚደርስ፣ ደርሶም እሚያገኛቸው ለልዩ ተልዕኮ የተጠራ ብቻ ነው። ኣብሮኣቸው እየኖረም እርሱ ማጉዳ ውስጥ እንዳለ እማያውቅ ብዙ ነው።
ለትልቁ ዓለም ማጉዳዎች የሉም። ወይም፣ ታሪክ የላቸውም። ታሪክ የሌለው ምን ትንቢት ይኖረዋል? ታሪክ የሌለው ምን ድምፅ ይኖረዋል? እንዲህ እየተባለ ታሪክ መዘናጊያ ይሆናል ኣንዳንዴ። ይህችን የመሰለች የከበደች የምፅዓት ትንቢት ከእንዲያ ኣይነት ስም-ኣልባ ቦታ ማን ይጠብቃል? ቀጣይዋ ስንኝ የተቋጠረችው እንዲህ ያለውን የጠቢባን ተብዬዎችንና የጥበብን በመንገድ መተላለፍ ኣስመልክቶ ነው፡-
        “ያንተ ሞራ ሚስጢር፣ ያንተ ኣንጀት ትንቢት፣ መቼ ይናገራል!” ለምን ትለኛለህ?
        “በፋሲካ ምሽት፣ በጌን ታርደዋለህ።” ብዬ የነገርኩህ፣ የጥ…ንቱ ትንቢቴ፣ 
        እጓዳህ ሚስማር ላይ፣ በሰቀልከው ጠቦት፣ ተፈፅሞ’ያየህ!
ምን ብራናን ኣልፈን በጨረር (በኮምፒዩተር) መፃፍና ማንበብ ብንጀምርም በታሪክ ጉዳይ ላይ ዛሬም በድንጋይ ዘመን ውስጥ ነን። ታሪክ ብለን ለመናቅም ፍርድ ለማጓደልም እምንገበዘው ድንጋዩንና ህንፃውን እያየን ነው። ቃል ታሪክ ኣይደለም ለኛ። መንፈስ ታሪክ ኣይደለም። እና፣ “ታላቅ ነበርን፤ ታላቅም እንሆናለን!” እያልን አሁናችንን በተመለከተ እጅ የመስጠታችንን ንግርት በየዕለቱ እናውጃለን። እውነቱ ግን ይህ ነው፡- እኛ ታላቅ ነን። ዛሬም፣ ኣሁንም ታላቅ ነን!
የሆነ ሆኖ፣ የማጉዳዎች የምፅዓት ትንቢት በብራና ላይ የተፃፈ ኣይደለም። በድንጋይና በሸክላም ላይ የተቀረፀ ኣይደለም። እተፈጥሮ እምብርት ውስጥ የተደበቀ እንጂ ነው፡- በሶስቱ ነፋሶች ማህፀን ውስጥ ተሰውሮ ዘመን ያስቆጠረ፤ ከእንስሳት ኣንጀትና ሞራ ግላጭ የተከተበ፤ ከጅረቶች ኣፈሳሰስ፣ ከኣዕዋፍትና ከነፍሳት ኣበራረር የተሰናኘ፤ ማጉዳዎች፣ በተለይም ሙፄዎች፣ “ዋዞ” ወይም “ኣያና” በሚባለው ጥንታዊ ጥበባቸው የተፈጥሮን ግርዶሽ ገልጠው እሚያነብቡት። ይህንን ጥበባቸውን ኣንዳንዶች “የዋዞ ኣምልኮ” ይሉታል። ዋዞ ግን ኣምልኮ ኣይደለም። መንገድ ነው። ጥንታዊ የህይወት መንገድ። ይህ ግልፅ ካልሆነ፣ “ዋዞ ምንድነው?” እሚል፣ “ዛር ምንድነው?” ብሎ ይጠይቅ። “ኣያና ምንድነው? ኣቴቴ ምንድነው? ኣዶካብሬ ምንድነው? ውቃቢ ምንድነው?” ብሎ ይጠይቅ። እነዚህ ስያሜዎች ወዲያው ከሚያጭሩት ምስልና ምላሽ ባሻገር ለመሄድ እምነቱ ፍርሃት ሳይሆን ብርታት ከሰጠው። (ይህ የተወናበደ ዘመን ነው። ቃላትም የተወናበዱ መሆናቸው የሚጠበቅ ነው።)  
እማጉዳ ውስጥ፣ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች፣ የተፈጥሮን ረቂቅ ምልክቶች በእራቁት (በተገለጠ) ዓይናቸው ማየት የሚችሉ ጥቂት ሰዎች፣ የዘመን መጨረሻ እንደ ዘንዶ እየተሳበ ሲመጣ ተመለከቱ። እነሱ፣ “እነሆ ፋና’ልባውም ተናገረ፤” ይላሉ። ፋና’ልባው፣ እንደሉሲፈር የማይልከሰከስና የባጥ የቆጡን የማይቀባጥር፣ የማያስቀባጥር፣ በሰውና በዓለም ጉዳይ ዘመኑ ሳይመጣ ጣልቃ እማይገባ፣ እጅግ ሃያል መንፈስ ነው። የፍፁም ኣርምሞ ጌታ። በፋና’ልባው ዓይን ሲመዘን ሉሲፈር እንቅልፍ ከምትነሳን ትንኝም በልጦ ኣይታይም። እና፣ ፋና’ልባው ተናገረ፤ ይላሉ ማጉዳዎች። ያ ማለት፣ የጊታ ዖላ (የታላቁ ጦርነት) ነጋሪት ተጎሰመ፤ ዕምቢልታውም ተነፋ፤ ማለት ነው።
ጊታ ዖላ በጦርና በጎራዴ፣ በዲሞትፎርና በቦምብ እሚዋጉት ዓይነት ጦርነት ኣይደለም። (እርሱም ሊኖርበት ይችላል እርግጥ።) በዓለም ላይ እየፈራረሰ ያለ ነገር ኣይታይም? ጊዜ ያከበራቸው ተቋማት ከስር-ከመሰረታቸው ተናግተዋል። የሃይማኖቶች ወርካ ተመንግሎ ለመግደርደር ያህል ብቻ ቆሞ ይታያል። የመንግስታት ህልምና ቅዠት ተምታትቷል። ወግና ስርዓት ውላቸው ጠፍቷል። የቤተሰቦች ህብረት ፈርሶ ኣለመተማመንና መቃቃር ነግሷል። ኣባትና እናት ያለሃፍረት ከልጆቻቸው ይሰርቃሉ። ግለሰቦችንም፣ ተቋማትንም፣ መንግስትንም ብናማና ብንተች እነሱን ተክቶ ሊመጣ ስለሚችለው ግን የተረጋገጠ ተስፋ የለንም። ስር ለሰደደው ህመማችን መድሃኒት ያለው ያለ ኣይመስልም። መድሃኒት ኣለን እሚሉን እምነቶችም ተከፋፍለውና ከርረው ከስለትም ብሰው ኣንገት እየቀሉ፤ መንፈስንም ገዝግዘው እያነተቡ ነው። የብዙሃን ደም መፍሰስና መታለል ውጫዊ ገፅታ ብቻ ነው። በእምነት ስም ከሚፈሰው ደም፣ በእምነት ስም ከሚጭበረበረው ሃብት፣ ባሻገር እሳት እንደገባ ጅማት የሚኮማተሩ፣ የሚንጨረጨሩ ነፍሳት ኣሉ። ጊታ ዖላ እንዲህ ነው። እየተዋጋነው እንዳለን ሳናውቅ እምንዋጋው ጦርነት። እየሞትን መሆኑን ሳናውቅ ሞት እምንቀበልበት እንበለ-ህይወት። እየፈረሰ መሆኑን ሳናውቅ መቅደሳችን መቃብራችን የሚሆንበት ምፅዓት። ልባችንም ምድራችንም የጦሩ ሜዳ ናቸው። ማንም ማምለጫ የለውም። ማንም!
በተለመደው ቋንቋ ይህ የመጨረሻው ዘመን ነው። ማጉዳዎች ታላቁ ተገላቢጦሽ ይሉታል። ለምን ቢባል፣ ይህ ትልቁ ትንሽ፣ ትንሹ ትልቅ የሚሆንበት ዘመን ነውና። ይህ፣ የዓለማችን ታላላቅ የስልጣኔና የዕውቀት ስርዓቶች ፈራርሰውና ትብያ ለብሰው ያልታወቁና የተረሱ ጎሳዎች የህይወት መንገድ ዓለምን የሚያጥለቀልቅበት ዘመን ነው። ይህ፣ የነቢያትና የተከበሩ መፅሃፍት ትንቢት እንደተጠበቀው እማይፈፀምበትና የየዋሃንና የህፃን-መሰል ልበ-ንፁሃን ህልም የሚሰምርበት ዘመን ነው። ይህ፣ ከንዩክለር ቦምብና ከጨረር መሳሪያዎች ይልቅ በህፃናትና በበጎች ኣንገት ላይ የታሰረ ቃጭል ሺ ሰራዊትን በፍርሃት የሚያርድበት ዘመን ነው። ተገላቢጦሽ!  
ከምድር ጋር ያላቸውን ጥንታዊ ትስስር ጠብቀው የኖሩ ጥቂቶች ብቻ ጊታ ዖላን በድል ይሻገሩታል። ከጊታ ዖላ በሁዋላ በምትመጣው በኣዲሲቱ ምድርም እነርሱ የእውቀትና የጥበብ ምንጮች ይሆናሉ። ምድር ልትናገር ካለው ኣዲስ ተረክ ጋር ጥንታዊ ተረካቸውን ኣስምረው። እንግዲህ ጊታ ዖላ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ እሚደረግ ጦርነት ነው። በደልና በዳይ ወንዙን ኣይሻገሩ ዘንድ የሚደረግ የሞት-ሽረት ተጋድሎ! ኣልያማ ኣዲሱ ዓለም፣ ኣዲሱ የዓለም ሥርዓት፣ ምኑን ኣዲስ ሆነው!     
ከማጉዳ ውጭ፣ እዚህ ቢሾፍቱ፣ እሆራ ግድም፣ ወይም በምድረ-ሩዋንዳ፣ ወይም በእንቴቤ ዩጋንዳ፣ ኣቴቴ ስትጣራ ተደምጣለች። ይህችን የኛዋን ኣቴቴ ግብፆች ኣሴት ይሏታል። ምዕራባዊያን ደግሞ ኣይሲስ (Isis)። እንግዲህ፣ ያበሻ ምድር ለዓለም ካበረከተቻቸው ታላላቅ ጥበባት የኣቴቴ እውቀት ኣንዱ መሆኑ ነው። ታዲያ፣ ከሌላው ዓለም የወረስናቸው እምነቶቻችንና ማንነታችንም ሳይቀሩ ልዩ ቀለም ኖሮኣቸው እሚታያው ያለምክንያት ነው?
የግፉዓን ኣማልክት የሆነችው ኣቴቴ በዓለም ጩኸት ውስጥ ዝምተኛ ነበረች። ዓለም ዝምታዋን መረዳት ተስኖት ብዙ ቆየ። ስለዚህም ተሰቃየ። አሁን ግን እርሷ ኣርምሞዋን ሰበረች። ይህ ዘመኑ፣ ይህ ዘመኗ ነው! ኣሁን እሷ ሰባቱን የኣፍሪካን ደናሽ ንግስቶች ከተኙበት ለመቀስቀስ እየተጣራች ነው። የተደመጡት ስሞች ግን ሁለት ብቻ ናቸው፡ ኣቴቴ እና ንያቢንጊ። ሌሎች አምስቱ እነማን ናቸው? ቀድመው የነቁቱ ያላደመጡቱንና ያልነቁቱን ፈልገው ማግኘት ኣለባቸው። ፍለጋው ግን ቀላል ኣይሆንም። ማጉዳዎች ኢንዶማ ከሚሏት ከኣፍሪካ ታላቅ ምድር፣ በኣፍሪካም ካሉ የትየሌሌ ኣናሳና የተረሱ ጎሳዎች ውስጥ፣ ያንን ጥንታዊ መንገድ ያልዘነጉ ሰባት ደናግልትን ፈልጎ ማግኘት ቀላል ኣይሆንም። ኢንዶማ ውቂያኖስ ናት። ማተቧን ያልበጠሱቱ እነኛ ደናግልት ደግሞ ኣሳዎች። ከውቂያኖስ ውስጥ ሰባት ልዩ ዓሳዎች ፍለጋ! ብዙዎች በኣቴቴ ወይም በኣይሲስ ስም ይመጣሉ። በምድር ላይም የማይነገርን ሰቆቃም ያስከትላሉ። የኣፍሪካም ሆነ የዓለም ትንሳዔ ያለው ግን በእውነተኞቹ የኣቴቴ ልጆች በኩል ብቻ ነው። በሊቃውንትና በባለፀጋዎች ኣይደለም፤ በምንዱባኖቹና በብዱላኖቹ።   
ከጊታ ዖላ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በኢትዮጵያ ውስጥ ተደብቆ የሚገኝ ኣንድ ሚስጥራዊ ፅዋ ኣለ። ሰባቱ ደናሽ ደናግልት ኣንድ ላይ ሆነው ያንን ፅዋ ማግኘት ኣለባቸው። ያኔ ብቻ፣ ሊጠፋ ያለው የኣፍሪካ ወይም የኢንዶማ ጥንታዊ መንገድ ይህንን የመጨረሻ ዘመን፣ ይህንን የጥፋት ዘመን፣ ይሻገራል። ያለዚያ፣ እኛ ኣፍሪካዊያን ከመጨረሻው ጦርነት በሁዋላ እንደዝርያ ልንቀጥል ብንችልም እንደባህል ግን ኣንኖርም። የጠፋ ማንነት፤ ምንም ኣይነት ብራና ያልከተበው፤ ምንም ኣይነት ሃውልት ያልቆመለት፣ ከገፀ-ምድር የታበሰ ማንነት፣ እንሆናለን። ያ ኣዲስ ዘመን ብራናና ሃውልት ይሉት ነገር ይኑረው ኣይኑረው ማን ያውቃል? ቢኖረውስ ማን ትዝታውን ቋጥሮ፣ “ትዝታዬ ለኔ”ን እያዜመ ገሃነምን ይሻገራል?
ሰባቱን ደናግልት የማግኘቱና የማገናኘቱ ጉዳይ ቀላል እማይሆንበት ሌላ ምክንያትም ኣለ። ስለዚያ ጥንታዊ ፅዋ የሚያውቁት እኚህ የጋሞ ጥበበኞች፣ እኚህ የኦሮሞ ኣቴቴዎች ብቻ ኣይደሉም። ታላቁ ኣሌክሳንደር ወደኣፍሪካ ቀንድ ኣካባቢ ምን ሊፈልግ መጥቶ የኛዋን ህንዴኬን ሊዋጋ ተግደረደረ? ጠቢቡ ሰለሞንስ ከጠቢቧ ሳባ ፍቅር ሰጥቶ ሊወስድ የተመኘው ሚስጥር ምንድነው? ሮማዊያንስ ምስጢሩ ያለው ክሊዮፓትራ ጋር መስሎት ክሊዮፓትራን በፍቅርና በስልጣን ሊደልል ከሞከረው ከቄሳር ጀምሮ፣ በኡምቤርቶና በሙሶሎኒ በኩል ኣድርገው፣ እስከ ዛሬ በዚህች ኩሻዊት ምድራችን ውስጥ እያንዳንዱን ድንጋይ በመፈንቀል የሚማስኑት ምን ፍለጋ ነው? …
ታሪክ አውቆ የሚንሸዋረር ዓይን ነው። ይህንን ኣልመዘገበም። ለነገሩ፣ ይህ ብዕርም ብራናም እሚችለው ተረክ ኣይደለም። ደግነቱ፣ ቀለም እማይከትባቸው፣ መንገድ ግን እማይረሳቸው ግልፅ ምልክቶች ኣሉ። ፅዋው በሃበሻ ምድር ተደብቆ ይገኛል። ኣሁንም ከላይ ያልኩትን ልድገም፡ ታዲያ፣ ይህች የኛ ምድር፣ ይህ የኛ ማንነት፣ ልዩ ቀለም፣ ልዩ ምት፣ ልዩ ቃና ኖሮት እሚታየው ያለምክንያት ነው?
የዚያ ስውር ፅዋ መንፈስ ከጥንትም ጀምሮ ዓለምን ሲያምስ ነው የኖረው። ይህ የመጨረሻ ዘመን ነውና፣ መንግስታትም፣ ሃይማኖታትም፣ ጉልበተኛ ግለሰቦችም በእጃቸው ኣስገብተውት በነገረ-ዓለምም ሆነ በነገረ-ሰማያት የበላይነታቸውን ለመጠበቅ ወይም ኣዲስ የበላይነትን ለመቀዳጀት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በእኛው የይሁዳ ኣንበሳ የሚመራው የዓለም የነገስታት ህብረት ያንን ፅዋ እያደነ ነው። መንግስቱ ኃይለማሪያምም በሚሊታሪና በፓርቲ ልብሱ ስር ተደብቆ በኖረው ሚስጢራዊ ካባው ያንን ፅዋ እያነፈነፉ ነው። ቻይናም በኣፍሪካ ጓዳና ጎድጓዳ ውስጥ ፍለጋዋን አጧጥፋለች። የቢሾፍቱው ጠንቋይ ጃላላና ኣጋሮቹም ወይ ከፅዋው ወይ ከደናግልቱ ጉዳይ ኣላቸው። መጥፋት ተጋርጦበት ሳይፋለም ለመሞት እሚመርጥ ማን ነው? ኣዎ፣ እነዚያ ደናሽ ደናግልት ፈተናቸው ሊታለም ከሚችል በላይ ነው!  
ይህ ጦርነት የምድራዊያን ጦርነት ብቻ ኣይደለም። ሙታንና ግማሽ-ሙታንም ተቀስቅሰዋል። እነሱም ነፃነታቸውን (መዳናቸውን) በመሻት ጊታ ዖላን እንደመጨረሻ ዕድላቸው ወስደውታል። መፈረጃቸውም እያደረጉት ነው። ጦርነቱን ግን እሚቀላቀሉት በኣካል ኣይደለም። ኣካላቸው ድሮ ፈርሶ ከኛ ኣካል ተቀላቅሎ የለ? የኛን የስጋ-ለበሶቹን ኣካል ነው እሚዋሱት። የኛን ልብ ነው የሚገስሱሰት። የኛን መንፈስ ነው የሚወርሱት። ከነቁ ከጥቂቶች በስተቀር፣ ኣብዛኞቻችን ሳናውቀው በነሱ ተይዘን፣ የመረጥነውን መንገድ እየተጓዝን ያለ እየመሰለን የነሱን ጦርነት እየተዋጋን ነው። በየቤተ-ሃይማኖቱና በየቤተ-አምልኮቱ የዚህ ምልክት ኣይታይም? ሰዎች የማይፈቱትን ህልም ሲያልሙ፣ የማይረዱትን ቋንቋ ሲናገሩ እየታየና እየተደመጠ ኣይደል? በኖህ የጥፋት ዘመንም የሆነው ይህ ነው፡- የጥፋት ውሃ ከመውረዱ ኣስቀድሞ ከሰው ዘርና ከሰማይ ሰራዊት ድቅል የተወለዱ ጉዙፋን ፍጥረታት በማይረዷቸው ህልሞችና ቅዠቶች ይሰቃዩ ነበር። ብዙዎቻችን እምንኖርበትና እምናስብበት መንገድስ እውን በሙሉ ልቦናችን፣ እውን በጤናችን ይመስላል? ግድ የላችሁም፣ በስደተኛ መናፍስት ተይዘናል። ገዝፈንም ብንታይ ግዝፈታችን የጤና ኣይደለም። የተዳቀለን እንግዳ ነገር ኣለ። ውሉን በማናውቀው ጦርነት ውስጥ እስከምናምናችን ተዘፍቀናል። ያውጣን ማለት ኣያወጣንም። ማምለጫ የለም!
ይህ ጊታ ዖላ ነው። ይህ የዘመን መጨረሻ ታላቁ ጦርነት ነው። የእያንዳንዱ ነፍስ ወሳኝ ጦርነት። ጦርነቱን የሚመሩት ደግሞ ያኝ ጋቢና የበግ ቆዳ ለብሰው፣ የቀርከሃ በትር ተመርኩዘው፣ ኣህያና በቅሎ እየነዱ፣ ጥንታዊውን የእግር መንገድ በባዶ እግራቸው ሲመትሩት እምናያቸው ጅል መሳይ ደገኞቻችንና ቆለኞቻችን ናቸው። እነሱ ከምድር የወረሷትን ጥንታዊቷን መንገድ ገና አልረሱምና። ይህ በእውቀቱና በእምነቱ ራሱን አብዝቶ የሚያኮራው የትዕቢት ዓለም፣ ይህ የማን-ኣህሎኝ ዘመን፣ ይህ የዶላር ህልም ልቡንም ዓይኑንም የሸፈነበት የቅዠት ትውልድ፣ ሃይል እማ ዘንድ፣ ስልጣንስ እነማን ጋ እንዳለ እንደምን ማወቅ ይቻለዋል?  
ማጉዳዎች እውነታቸውን ነው። ይህ የታላቁ ተገላቢጦሽ ዘመን ነው። ይህም መፅሃፍ የተገላቢጦሹ ጦርነት ዜና-መዋዕል ነው። ወይም፣ የጦርነቱ የመግቢያ ተረክ። ከኣምስት ተከታታይ መፅሃፍት የመጀመሪያው። ታሪክ ብቻ ኣይደለም። ታሪክ ማንን ኣዳነ? ፍልስፍናም ጭምር ነው። ይህ፣ ለሁለትም ለሰባትም ሺ ዓመታት በማይገባን ቋንቋ የተነገረን ፍልስፍና መሞገት ኣለበት! ይህ፣ እንደምርጫ ቀርቦልን ምርጫ የነሳን ሳይንስ መፈተን ኣለበት! ይህ፣ የኛ ባልሆነ ብዕር የተፃፈ ታሪክ ተገልብጦ መነበብ ኣለበት! ይህ በሃሜትና በተረብ የተቀፈደደ ፅሉምና ስሱን ኪነት ከእስሩ መፈታት ኣለበት! በፍርድ ዘመን እሚፈረደው ሰው ብቻ ኣይደለም። እውቀትም ጭምር ነው። ጥበብም ጭምር ነው። ባዲሱ ዓለም ኣዲስ ብራና ነው እሚዘረጋ። በዘመን ኣሻራ እጅግ የቆሸሸው የጥንቱ ብራና ተሸብልሎ ወደጥልቁ ይወረወራል። በኣዲሱ ብራና ላይ እሚፃፈው ቃል እሳቱን ችሎ እሚያልፈው ብቻ ነው።
የነቁቱ ኣይተውታል። የፌዝ ከሚመስለው ከዚህ ዘመን የኑሮ ጭምብል ስር ኣዲስ መንፈስ ተቀስቅሷል። ኣዲስና ኮስታራ ጦርነትም እየተደረገ ነው። የፍርድ ቀን የወሳኝ ምርጫ ቀን ነው። ለማወቅ የሚመርጡ፣ ለመምረጥም የሚያውቁ እነርሱ የበጃቸው ናቸው።

መፅሃፉ ስለዚህ ነው።

1 comment:

  1. ኩላሊት መግዛት ትፈልጋለህ ወይስ ኩላሊትህን መሸጥ ትፈልጋለህ? በገንዘብ ብልሽት ምክንያት ኩላሊቶቻችሁን በገንዘብ ለመሸጥ እድል እየፈለጉ ነው እና ምን ማድረግ እንዳለቦት አታውቁም፣ እንግዲያውስ ዛሬ እኛን ያነጋግሩን እና ለኩላሊትዎ ጥሩ መጠን ያለው $500,000 ዶላር እንሰጥዎታለን። ስሜ ዶክተር ማክስዌል ቺራክ በማውንት አልቬርኒያ ሆስፒታል የነርቭ ሐኪም ነኝ። ክሊኒካችን በኩላሊት ቀዶ ጥገና የተካነ ሲሆን እኛም ኩላሊትን በመግዛት እና በመትከል ህይወት ካለው ለጋሽ ጋር እንሰራለን። የምንገኘው በሲንጋፖር፣ ዩኤስኤ ነው የኩላሊት መሸጥ ወይም መግዛት ከፈለጉ እባክዎን በ ላይ እኛን ለማነጋገር አያመንቱ።

    WhatsApp፡ +1 850 313 7832
    ኢሜል፡ contact@mountalverniahospitals.com

    ምልካም ምኞት
    ዶክተር ማክስዌል ቺራክ

    ReplyDelete