Wednesday, April 16, 2014

ሰማሀኝ? መቀሌም የትውልድ መንደሬ ናት!

“ኣንት ቆሻሻ እንደሆንክ ቢያይም፣ ዝናብ መዝነቡን ኣያቆምም

ያነባሁም ለታ፣
የፈገግሁም ለታ፣
የተበትሁም ለታ፣
ትህትና’ንደጉንጉን የበተንሁም ለታ፣
ጥላቻ ቋጥሬ የታመምኩም ለታ፣
በፍቅር ሰክሬ የዘመርኩም ለታ፣
ይህች ፅጌረዳ፣ መፍካቷን መሽተቷን፣ ኣታቆምም ይሀው። 
እኔም ተፈጥሮዬን፣ ለመኖር ስጀምር፣ ህቅ ይለኛል ምነው?


ጉልቻ እኔ ከመወለዴ በፊትም ጉልቻ ነበር። ስለዚያ እኔ ምንም ማድረግ ኣልችልም። ማድረግ እምችለው ነገር ግን ኣለ። … ይህችን ጥበብ የሰጠችኝ፣ በህይወቴ ውስጥ እንደታላቅ ምሰሶ የቆመች፣ ኣንዲት ሳምንት ነች። ያው፣ እንደሌሎች ሳምንታት ሁሉ ሰባት ቀናት ናቸው ያሏት። ያኝ ቀናት ግን ሰባት የመቅደሴ ኣውታሮች ናቸው። ይህች የህማማት ትዝታዬ፣ ይህች የትንሳኤ ስጦታዬ ነች። እነሆ፦


ሰማሀኝ? መቀሌም የትውልድ መንደሬ ናት!

ህማማት። 1987 ዓመተ-ም.ህ.ረ.ት። ኣዋሳ። ሰባት ወር የዘለቀ ጉዳይ ነበረኝ። የቅጥር ጉዳይ። ያለስራ ዓመት ከጠበቅሁ በሁዋላ ወቅቱ ያቀረበልኝ ኣማራጭ የወረዳ የተፈጥሮ ሃብት ፅ/ቤት ሃላፊ ተብዬ መሎ ወረዳ መውረድ ነበር። እምፈልገው ስራ ነበርና ሹመት ለመቀበል ኣላቅማማሁም። ዓመት ሰራሁ። የዘመኑ ገምጋሚዎች ዓመቴን ኣብጠለጠሉብኝ። እነሱ መናገር የፈለጉትን ተናገሩ። እኔም መናገር ያለብኝን ተናገርሁ። ከዚያ በሁዋላ ኣብረን መቀጠል እንደማንችል ግልፅ ሆነ። በፍቅሩ የጣለኝ ቦታ ነበር። ግን ምንም ማድረግ ኣልቻልኩም። በቃ፣ ሥራ ለቀቅሁ። እነሆ ሰባት ወር። ስንት ከንፈር መምጠጥ ተቋቁሜ፣ ቅጠሩኝ ብዬ ስመላለስ። ህማማት። 1987 ዓመተ-ምህረት፣ ኣዋሳ።

በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኣንድ ክፍል ውስጥ። ከክፍሉ ሃላፊ ፊት ቆሜኣለሁ። እሱ ወንበሩ ላይ ዘና ብሎ ተቀምጧል። ሽቅብ ያየኛል። ቁልቁል ኣየዋለሁ። እኔ እማየው እሱን ብቻ ኣልነበረም። እማየው የተረጋገጠ ተስፋዬንም ነበር። ይህ ሁሉ ምልልስ ዛሬ መቋጫ ያገኛል። ኣቤት፣ ስንቴ ተመላለስኩ! ለቤርጎና ለምግብ ስንት ገንዘብ ኣፈሰስኩ!

ከኔ ጋር ኣንድ ጉዳይ የነበራቸው ብዙ ብጤዎቼ ቅጥር ጨርሰው ስራ ይጀምራሉ። እንዴት እንዳሳኩ እጠይቃቸዋለሁ። ይነግሩኛል።

"እንዲህ’ኮ ማድረግ ነበረብህ! ቀላል ነበር’ኮ ጉዳዩ!"

በእያንዳንዱ መምጣቴ እርግጠኛነት ይዤ ነበር ኣዋሳ እምገኝ። ሳምንት ኣስራ ኣምስት ቀን ቤርጎ ተቀምጬ፣ ቢሮ ተመላልሼ፣ እንኳን ጉዳዬን ማስፈፀም ቀርቶ፣ ኣግኘው የተባልኩትን ሰው ሳላገኘው እመለሳለሁ። ባለስልጣናቱ ላለመገኘት ሁልጊዜም ምክንያት ኣላቸው። ኣንዳንዴ፣ ተሳክቶልኝ ተፈላጊውን ሰው ኣግኝቼና እንደማይሆን ሰምቼ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ማንንም ሳላገኝ ገንዘቤን ጨርሼ እመለሳለሁ። ያኔ ታዲያ፣ መልካም ዜና እሚጠብቁ ቤቶቼን ማየት ሲያስፈራ!

ከኔ በሁዋላ ሌላ ሰው ተቀጥሮ ሲመጣ ኣይና እንደገና እጠይቃለሁ። እንደገናም ይነግሩናል። እንደገናም እሄዳለሁ። እንደገናም ያለፍሬ እመለሳለሁ። ጓደኞቼ ያልነገሩኝ መንገድ እንዳለ ማሰብ የጀመርኩት ቆይቶ ነው።

ተስፋ ኣልቆረጥኩም። ያለው ኣማራጭ ተስፋ ማድረግ ብቻ በሆነበት ሰዓት ተስፋ በዘፈቀደ ኣይቆረጥም። ደግሞም፣ ተስፋ መቁረጥ ብርታት ይጠይቃል ኣንዳንዴ። ልቤ ብርቱ ኣልነበረችም መሰል ያኔ።

እንደገና፣ ወይ በሬዲዮ፣ ወይ በጋዜጣ፣ ወይ በወሬ ኣንድ ተስፋ ያዘለ ነገር እሰማና እሄዳለሁ ወዳዋሳ፤ ወደ ተስፋዋ ምድር። የተዘጋ በር ይገጥመኛል። የተዘጋ ኣንደበት፣ የተዘጋም ልብ ይገጥመኛል። ኣፎች የሚከፈቱት ከንፈር ለመምጠጥ ብቻ ይሆንብኛል። እመለሳለሁ።

ሰባት ወር። ኣሁን ታዲያ እማያጠራጥር ነገር ይዤ ነው የመጣሁት። የዞኑን ሃላፊን እራሱን ኣግኝቼው ነበር ከመምጣቴ በፊት። በስንት ደጅ ፅናት!

"ጥፋቱኮ ያንተ ነው።" ብሎኛል እሱም፤ "የት መሄድ እንዳለብህ እንኳ ኣታውቅም። ዝም ብለህ ጊዜህን ታባክናለህ? ኣትጠይቅም?" ብሎኛል።  

ግልፅ ነው። ይህ ሁሉ ጊዜ የባከነው በራሴ ጥፋት ነው። ደግነቱ፣ በመጨረሻ የት መሄድ እንዳለብኝ፣ ማንን ማናገር እንዳለብኝ ኣውቄኣለሁ። የተባልኩትን ሰው ታላገኘሁ ብዬ ሶስት ቀን ጠብቄኣለሁ። እነሆ፣ ኣሁን እፊቱ ቆሜኣለሁ። ተስፋዬ ግዘፍ ነስቶ፣ ሰው ሆኖ እየታየኝ። "ተስፋ ኣለመቁረጥ እንዴት መልካም ነው!" እያስባለኝ።  

ጉዳዬን ኣብራራሁኝ። የተባልኩትን ተናገርኩኝ። የላከኝንም ኣሳወቅሁኝ። እውነት ነው፣ ይህ ሁሉ ባላስፈለገ። እምጠይቀው ግልፅ ነው። እምጠብቀውም ግልፅ። ዘመኑ ያ መብቴ መሆን ኣለመሆኑን እንድጠራጠር ቢያረገኝም፣ ኣዎ፣ ማብራሪያ እማይሻ ጉዳይ ነው ጉዳዬ።

"ልክ ነህ፤" ብሎ ጀመረ ሰውዬው። "ትክክለኛው ቦታ ነው የመጣሀው። ኣሁን ግን፣ በጀቱ ገና ስላልፀደቀ ኣንድ ሶስት ወር ያህል …"  

ከዚያ በሁዋላ የተናገረውን ኣላስታውስም። የሆነ ታላቅ መበጠስ በውስጤ ተበጠሰ። ተስፋዬ ነበር። ያኔ ልቤ ብርታት እንዳላት ኣወቀች መሰል፤ ተስፋዋን ጧ! ኣድርጋ በጠሰች።  

ለካስ ተስፋ ድንገት ሲቆረጥ ደም ኣይደለም እሚወጣው። ዕምባ ነው ለካስ! የዕምባ መዓት። ኩራትም የለም በዚያ ሰዓት። ተደብቄ ኣነባበት ጓዳ ልፈልግ፣ ብሎ ቅንጦትም የለም በዚያ ሰዓት። "ወንድ ብቻውን ነው እሚያነባ፤" ብሎ ምክር ኣይታወስም በዚያ ሰዓት። ተስፋ ድንገት ሲቆረጥ እንዲያ ነው ለካስ። ጥልቅ በሆነ ዝምታ ውስጥ ዕምባ ግድቡን ይጥሳል ፀጥ ካለ ነፍስ እየተንሿሿ ይወርዳል። የት እንደተቆመም ተረስቶ!   

"በማልቀስ’ኮ እሚሆን ነገር የለም፣" ሲለኝ ይሰማኛል የክፍሉ ሃላፊ።
ስራ እንዲሰጠኝ እማነባ መስሎታል።
"በዕምባ እሚሆን የለም፣ ወዳጄ።"
ዕምባዬ ልመና መስሎታል።
"ዕምባ ምንም መፍትሄ ኣያመጣልህም።"  
ለራሴ እማነባ መስሎታል።

ምናልባት፣ ያነባሁት ለርሱ ነበር። ያነባሁት ለዘመኑ ነበር፣ ምናልባት። ዕምባዬ ምህረት ነበር፣ ምናልባት። በዚያች ሰዓት እያንዳንዱ ሰው ቅድስና እንዳለው ተገልፆልኝ ነበር፣ ምናልባት። እያንዳንዱ ሰው ለቅፅበት ታህልም ራሱን ለዓለም ሃጢዓት እንደሚሰዋ ታይቶኝ ነበር፣ ምናልባት። ዓለም መንፃቷን እምትጎናፀፈው እያንዳንዱ ሰው በሚያዋጣት የዕምባ ጠብታ እንደሆን ተሰምቶኝ ነበር፣ ምናልባት። ዕምባዬ የወረደው የሆነ ያልታወቀ ትንቢት ለማሟላት ነበር፣ ምናልባት። ለዚህ ሁሉ ምንም ማረጋገጫ የለኝም። ይህንን ግን ኣውቃለሁ - ያነባሁት ለራሴ ኣልነበረም።

ይህንንም ኣውቃለሁ - ዕምባዬ ቃል ነበረ። ያ ባለስልጣን የገባውን ያህል ኣነበበ። እኔ የራሴን ኣንደምታ መደረት ኣላሻኝም። ፊቴን ኣዙሬ ከቢሮው ወጣሁ። …       

ሰዎች፣ "ሚስጢር ለሚስጥረኛ ነው እሚነገር፤" ሲሉ እሰማለሁ። እኔ ምስጢረኛዬ ማን እንደሆን እስተዛሬ ሳላውቅ ኣለሁ። ያን ቀን ግን ኣንዲት ሚስጥረኛ ኣግኝቼ ነበር። ኣረፋፈዴን እያሰብሁ ያማረ ሆቴል ውስጥ ሻይ እጠጣለሁ። ምኔ እንደሳባት እንጃ። በምን ወሬ እንደጀመረንም እንጃ። ያስተናገደችኝ ልጅ፣

"ዛሬ ከሰዓት እረፍት ነኝ። ለምን ኣብረን ቤት ኣንሄድም? ቡና ኣፈላልሃለሁ። ከፈለግህም ጫት እንቅማለን።" ኣለችኝ።  

ከዚያች ሰዓት በፊት ተገናኝተን እምናውቅ ኣይመስለኝም። እማላውቀው ሰው ጋር ለመቀራረብ ድፍረት ያለኝ ኣልነበርኩም። ግን፣ ከሰዓት ራሴን እመደቧ ላይ ኣገኘሁት። ያኔ ነው እሷ ምስጢረኛዬ እንደሆነች ያወቅሁት። እና፣ ላደርግ ያሰብኩትን ነገርኳት፦

"ልሄድ ነው። ደቡብን ጥዬ ልሄድ ነው።"
"ወዴት?"
"እንጃ፣ ምናልባት ወደ ኣፋር። ምናልባት ወደ ጋምቤላ። ምናልባትም ወደ ትግራይ።"  

በእውነቱ፣ ለኔ የትኛውም ምንም ልዩነት ኣልነበረውም። እርግጠኛ የሆንኩት ወደ ቤት እንደማልመለስ ብቻ ነው። እዚህ እምጠብቀው ምንድነው? ከዚህ ኣካባቢስ እምለምነው ምንድነው? ብሄድ እሚቀርብኝስ ምንድነው? ያዶላ ወርቅ የኔ ነው?   

ያችን ሚስጥረኛዬን ስሟን እንኳ የጠየቅሁዋት ኣይመስለኝም። ከሳምንት በሁዋላ ደግሜ ባያት ኣላስታውሳት ይሆናል። በሆነ የቅፅበታት መጠላለፍ ልብ ለልብ ተገናኘን። ልብ ለልብ ኣወጋን። እና፣ ተለያየን። ኣሁንም ግን ልቤ ውስጥ ነች። ይሁን፣ … ያ ይበቃል።

በዚያን ቀኑ ተነገወዲያ ታዲስ ኣበባ ወደ መቀሌ የሚሄድ ኣውቶብስ ላይ ተቀምጬ ተገኘሁ። ኤላን ፍለጋ ውስጥ ይህ ቃል ኣለ፦  

"ወደ ኣባያ ነበር መሄድ የነበረበት። እግሮቹ ግን ወደ ጫሞ ይመሩታል። ኣልታገላቸውም። ዝም ብሎ ተከተላቸው። እግር ኣለምክንያት በመንገድ ኣትወስንም። …" (ገፅ 232)

ሁለት ሰው በሚያስቀምጥ ወንበር ላይ ነኝ። በመስተዋቱ በኩል። እጎኔ ኣንድ ተጋዳላይ ተቀምጧል። ኣውቶብሱ ውስጥ ጫጫታ ይጨፍራል። በኔ ውስጥ ግን ዝምታ ነግሷል። ለምን የመቀሌን ትኬት እንደቆረጥኩ ኣስባለሁ። …

ያ የለውጥ ዘመን ነበር። ለምደን የቆየናቸው ነገሮች ሁሉ እንዳልነበሩ ሆነው ነበር። እናያለን ብለን ያላለምናቸውንም ነገሮች ኣየን። የረጋው ጊዜ ድንገት ነው የተናጠው። ከዚያ ውስጥ የወጣው ግን ቅቤ ብቻ ኣልነበረም።

ጓደኞቻችን ተለወጡብን። ጓደኛ ነበሩ። ያም ብዙ ነገር ማለት ነበር። ተለወጡ። ብሔር ሆኑ። ፓሪቲ ሆኑ። ያ መለወጥ ከልባችን ኣንዳች ነገር ቦጭቆ ወሰደ። ኣዲስ የህመም ዓይነት ኣወቅን።

መታወቂያችን ላይ ኣዲስ ቃል እንድንፅፍ ተገደድን። ብሄር። ብሄራችን የቱ እንደሁ ለማወቅ ኣታካች ፍለጋ ያደረግንም ነበርን። የኛ ምርጫ ብቻ በቂ ኣልነበረም። ባካባቢ መወለድ፣ ባካባቢ ማደግ፣ ያካባቢን ቋንቋና ባህል ማወቅ ብቻ በቂ ኣልነበረም። ኣካባቢውን ፍፁም መውደድና ራስን ለዚያ ለመስጠት ማዘጋጀት በቂ ኣልነበረም። ባንድ ክፍል ውስጥ ይማሩ፣ ባንድ ዶርምና ፍራሽ ይተኙ፣ ባንድ መደብ ላይ ይቅሙ፣ ባንድ ኣፍም ይናገሩ፣ … የነበሩ ወዳጆች ብሄር ሆነው፣ ፓሪቲ ሆነው፣ ጩቤ ሲማዘዙ መስክረን ነበር። "እንዴት ራሳቸውን ይህን ያህል ያዋርዳሉ?" ብለንም ፈርደን ነበር። እነሆ ዛሬ፣ ያው የብሄር ጥያቄ በየመታወቂያችን መጣ። እነሆ ዛሬ፣ ያው የብሄር ጥያቄ፣ የሌለ በር ከፋች፣ የተከፈተ በር ዘጊ፣ ሆኖ መጣ። ሌላም ብዙ ቀድሞ እማናውቀው ነገር ሆነ። እና፣ ዘር መርጠን ተቀየምን። ዘር መርጠን ቂም ቋጠርን። …

የለ፣ ያ የተናጠ ጊዜ ቅቤ ብቻ ኣልነበረም ያፈለቀው። 

ልብ ሳልለው፣ በልቤ ዙፋን ላይ ጥላቻ ነግሶ ኣገኘሁት። ድፍን ጥላቻ ነበር። ያ ህመሙን ኣብሶታል። "ለማፍቀር ምክንያት ማግኘት ከባድ ነው፤" እሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ። ለኔ ግን የከበደኝ ለመጥላት ምክንያት ማግኘት ነበር። እምደረድረው ምክንያት ሁሉ በቂ ሆኖ ኣይገኝም። በተለይ ለዚያ ጥላቻዬ ምክንያት ማግኘት ኣቃተኝ። ልቤ ውስጥ ያለውን ኣዝማሚያ ኣውቀዋለሁ። ህዝብን ወደመጥላት እያጋደለ ነው። ወዴት እየወረድኩ ነው? የሰው ዘር ሁሉ ኣፍቃሪ ነበርኩ። በ’ርግጥ፣ ቀድሞ ያን ለራሴ ነግሬ ኣላውቅም። ጎዳና ላይ ወጥቼም፣ "የሰው ዘር ሆይ፣ እወድሃለሁ!" ብዬ ለፍፌም ኣላውቅም። ኣሁን ልቤ ውስጥ ያለው ህመም እሚነግረኝ ኣንድ እውነት ኣለ። ያ ተፈጥሮዬ ኣይደለም። ጥላቻ ከቶም ተፈጥሮዬ ኣይደለም። በተለይ ህዝብን መጥላት። ግለሰቦች መጥፎ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዴት ኣንድ ህዝብ መጥፎ ሊሆን ይችላል? እንዴት በህዝብ ላይ ቂም ይያዛል? …

እና፣ በዚያች ጥዋት፣ በዚያ ኣውቶብስ ውስጥ ሆኜ፣ በጫጫታ በታጀበው ዝምታዬ ውስጥ ኣድፍጬ፣ ይህንን ኣስባለሁ።

ሌሎች ነገሮችንም ኣስባለሁ። ከኮሌጅ እንደወጣሁ ለራሴ የመቶ ሃያ ዓመት ዕቅድ ነድፌ ነበር። እዚያ ውስጥ ለኣራት ለኣምስት ዓመታት ገዳም ገብቶም የገዳምን ህይወት ማየት፣ ትምህርቱንም መቅሰምም ኣለበት። ያ ዕቅዴ ኣሁን ባሰብኩት መንገድ እየሄደ ኣይደለም። ትግራይ የገዳማት ምድር ነው። ቋንቋውም ለግዕዝ ቅርብ ነው። ምናልባት የመቀሌን ትኬት ባስቆረጠኝ ምክንያት ውስጥ ያም ምክንያት ይኖራል። 

ህይወት የራሷ ፈለግ ኣላት። የኤላን ፍለጋው ኩሴ፣ "ያለምክንያት እግር በመንገድ ኣትሰለጥንም፤" ያለው ያንን እያሰበ ይሆናል። ህይወት ለምን ባንድ ኣቅጣጫ እንደመራችን ሺ ምክንያቶች መደርደር እንችል ይሆናል። ነገር ግን፣ ሁል ጊዜም እኛ እማናውቃቸው ሌሎች ሺ ምክንያቶች ይኖራሉ። በዚያ ጉዞዬ ውስጥ፣ "ይህን የትግራይ ህዝብ ቀርቤ ማወቅ፣ ቀርቤ መረዳት ኣለብኝ፤" የሚል ዓይነት ምክንያት ደምቆ ይሰማኝ እንደነበር ኣስታውሳለሁ። በልቤ ጥልቀት ድምፃቸውን ኣጥፍተው የተደበቁ ምክንያቶች የቶቹ ይሆኑ? …   

ልቤ ውስጥ ታላቅ ደስታ ነበር። ድፍን ፍርዴን ለመስበር ኣንድ እርምጃ ወስጃለሁ። ያ ከወዲሁ የነፃነት ስሜት ኣጎናፅፎኛል። እጎኔ ያለው ተጋዳላይ ደግሞ ብዙ ነገር ያወራኛል። ልብ ለልብ ለመነጋገር ረጅም ጊዜ ኣልወሰደብንም። ከተራመድኩት የከረምኩትን ኣንድ መንገድ ዳግም እየተራመድኩ ነበር። ሰዎችን እንደግለሰብ የመቅረብ መንገድ። እንደግለሰብም ስሜቴን ገልጬ ስሜታቸውን የማድመጥ መንገድ። እዚያ ውስጥ የሆነ ተፈጥሮኣዊ፣ የሆነ ትክክል ነገር ኣለ። በዛፎች በተሰመረ የእግር መንገድ ላይ በእርካታ የመራመድ ያህል ነው። ስሜት ውሃልኩን ሲያገኝ ይታወቃል። 

የመቀሌ መንገድ ሁለትና ሶስት ቀን ነበር የሚፈጀው ያኔ። ለመተዋወቅ ሰፊ ዕድል ኣለ። ዙሪያዬ ብዙ ሰዎችን ኣወቅሁ። ኣባቶች እንደ ኣባት፣ እናቶች እንደ እናት፣ ወጣቶችም እንደ እህትና ወንድም ይቀርቡኛል። እዚያ ውስጥ ምንም ማስመሰል የለበትም። ተጋዳላዩ እሚያወራኝ ታሪኩ ውስጥም ምንም ማስመሰል የለበትም። በእምነት ኣንድ ኣይደለንም። በታመምንለት፣ በደማንለትም ምክንያት ኣንድ ኣይደለንም። በየተቀበልነው ህማም ጥልቀትም ኣንድ ኣይደለንም። ሁለታችንም ግን ኣንድ የሆኑትን ያኝን ሰብዓዊ ስሜቶች እናውቃቸዋለን። ቢያንስ በዚያ ኣንድ ነን። ያ በመሃከላችን የሚፈጥረው ድልድይ ሰፊ ነው። ጎን ለጎን በነፃነትና በወንድማማችነት ስሜት ልንራመደው እንችላለን።

ያ ተጋዳላይ ለኔ ግለሰብ ነበር። የለም፣ ፓሪቲ ኣይደለም። የለም፣ ብሄር ኣይደለም። እሱ፣ ከሆነ ከማያውቀው ሰው ጋር፣ ኣንድ ተራ ጉዞ ተጓዘ። ለኔ ግን፣ ታላቅ መንቃትን ሰጠኝ። ካውቶቡሱ ስንወርድ ተለያየን። ስሙንም፣ መልኩንም ኣላስታውስም። ትዝታው ግን ከነፍሴ ተሸምኖ ይኖራል።      

ረፋድ ከሰዓት ላይ ነው መቀሌ የደረስነው። ከቤት ወደ ኣዋሳ የወጣሁት ላጭር ቀን ነበር። ኣንድም የተረጋገጠውን የስራ ዕድል ወዲያው እንደምጨርስ ስለገመትኩ። በተጨማሪም፣ የበዓል ወቅት ስለሆነ በዓሉን ቤት ተመልሼ እንደማከብር ስለታሰበ። የያዝኩት ገንዘብም ብዙ ኣልነበረም። ኣዋሳ ላይ ሶስት ቀን፣ ኣዲስ ኣበባ ኣንድ ቀን ኣድሬኣለሁ። ትኬት ለመቁረጥ ስሄድ ዘጠና ብር ነበር በእጄ። ለትኬት ስልሳ ብር ከፈልኩ። ሰላሳ ብር ቀረኝ። እመንገድ ላይ ምን በልቼ፣ እንዴት እንዳደርኩት ኣሁን ኣላስታውስም። ወይ ከሹፌሮች ጋር፤ ወይ ባምስትና በስድስት ብር ማደሪያና ምግብ ኣግኝቼ ነበር። መቀሌ ስገባ ሃያ ኣራት ብር እጄ ውስጥ ነበር። ይህ ግን፣ ምንም ስጋት ኣላሳደረብኝም።

መቀሌን ስረግጥ በሁለቱ የጉዞ ቀናቴ ይሰማኝ የነበረው ሃሴት ጉልላቱ ላይ ደርሶ ነበር። ይህች ወደ ነፃነት የወሰድኳት ትንሽዬ እርምጃ ናት። ለልቤ ያመጣችው ሃሴት ግን ከስፍር በላይ ነበር። ከረጅም መለየት በሁዋላ ኣገሬ የተመለስኩ ነበር የመሰለኝ። እንዲያውም በሰፈሬና በመንደሬ ያለሁ። ኣንድ እማቀውን ሰው ድንገት ባገኝ፣ በሩቁ ብቻ እጄን ኣውለብልቤ እማልፍ። በቃ፣ እዚያው፣ በቦታዬ የተገኘሁ። ሰዎችም ሁሉ እማውቃቸው፣ ነበር የመሰለኝ። ያን ስሜት መቼም ድጋሚ እማገኘው ኣይመስለኝም። ምናልባት ስሞት እንደገና እኖረው ይሆናል። ነፍሳችን እምትመኘውን ደጋግማ መኖር ትችላለች ኣሉ ስንሞት።

እኔ ከመወለዴ በፊትም ጉልቻ ጉልቻ ነበር። ከሞትኩ በሁዋላም ጉልቻ መሆኑን ይቀጥል ይሆናል። እኔ በዚያ ምርጫ የለኝም። ይህንን ግን መምረጥ እችላለሁ፦ መቀሌም ምድሬ፣ መቀሌም መንደሬ ናት። 

ቤርጎ ሳይሆን በመኖሪያ ቤት ውስጥ ለተደረደሩ ኣልጋዎች ስድስት ብር ከፍዬ ኣደርኩ። ያ ቅንጦት ነው በ’ርግጥ። ግን፣ ከተማዋን ተዟዙሬ እስከማያት እንዳደረግሁት መስዋዕትነት ነው የቆጠርኩት። ማምሻውን በቀጣዮቹ ቀናት ማደሪያ የሚሆነኝን ቦታም ኣገኘሁ። እራት ኣንድ ሁለት ብር ሳያነሳብኝ ኣልቀረም። ምን ይደረግ!

በበነጋው በጠዋት ተነስቼ የሄድኩት መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ነበር። ያን እማላውቀውን መንገድ ስጓዝ በልቤ ኣንድ ሰው ነበሩ፦ ዶክተር ምትኩ። የዓለማያ ኣስተማሪዬ ነበሩ። ያኔ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት። ተራ የተማሪና ያስተማሪ ግንኙነት ነበረን። ቢያዩኝ እሚያስታውሱኝም ኣልመሰለኝም። ቢሆንም፣ እማውቀው ኣንድም ነፍስ በሌለበት ምድር ያች ትንሽ መተዋወቅ ወደ’ሳቸው ልትስበኝ ብርታት ነበራት።

እዩኒቨርሲቲው በር ደርሼ ዘበኛውን ኣናገርሁት፦  
"ኣዎ፣ እዚህ ናቸው።" ኣለኝ። "ዛሬ ያው ስራ ስለማይገቡ፣ ነገ መጥተህ ልታገኛቸው ትችላለህ።"
"ዛሬ ለምንድነው ሥራ እማይገቡት?"
"ዛሬ ሰንበት ኣይደል?"

ገረመኝ። ቀኑን እንኳ ረስቼዋለሁ። በጉዞ ብዛት ቀኑ እንደጠፋብኝ ነግሬው፣ ኣመስግኜው መንገድ ስጀምር፣ "በጭራሽ!" ኣለኝ ዘበኛው። "ይህን ያህል ተጉዘህ መጥተህማ ሳታገኛቸው ኣትሄድም። መኖሪያ ቤታቸው እዚሁ ግቢ ውስጥ ነው። እቤታቸው እወስድህና ኣግኝተሃቸው ሂድ።"

ላብራራለት ሞከርኩ፦ የመጣሁት በራሴ ምክንያት ነው። እሳቸው ጭራሹኑ ላያውቁኝም ይችላሉ።እንዲሁ ላገኛቸው ፈለግሁ እንጂ ጉዳዬም ከሳቸው ጋር ኣይገናኝም። …

እምቢ ኣለ ግን እሱ። ሁኔታው ትህትና ውስጥ ኣስገባኝ። እየከበደኝ ለሱ ብዬ በጅ ኣልሁ። ይዞኝ ሄደ ቤታቸው። እዚያም ተመሳሳይ ነገር ገጠመኝ። በሩን የከፈተችልን ሴት ዶ/ር ምትኩ እቤት እናዳሉ፣ ግን እንደተኙ ነገረችን። ልመለስ ስል፣ በጭራሽ! ኣለች እሷም በተራዋ። ለሷም ሁኔታውን ማብራራት ኣላዳነኝም። እንደገና እየከበደኝ እሽ ኣልኩኝ። ገባሁና ተቀሰቀሱ።

"ዓለማያ ነበርክ ኣይደል?" ኣሉኝ እንዳዩኝ። ስላስታወሱኝ ደስ ኣለኝ። ጉዳዬን ሰምተው ሲያበቁ፣
"ቃል እምገባልህ የተዘጋጀ ነገር የለም። ነገ መመለስ ከቻልክ ግን የተወሰኑ ቦታዎች ደዋውዬ ልጠይቅልህ እችላለሁ። ትግራይ ሁሉም ሰው በሰላም ሰርቶ እሚኖርበት ቦታ ነው። ጠንካራ ሰራተኛ እስከሆንክ ድረስ እሚያገኝህ ክፉ ነገር ኣይኖርም።"

ቃላቸው ብቻ ኣይደለም ተስፋ የሰጠኝ። በተለይ፣ ተጀምሮ እስቲጨረስ የተስተናገድሁበት የወዳኝነትና የፍቅር ስሜት ነው። በሳቸው ብቻ ሳይሆን በገጠሙኝ ሰዎች ሁሉ። ስመለስ፣ "በእውነቱ፣ ምድሬ ይህች ነች።" እያልኩ ነበር።

መሸና ወዳዲሱ ማደሪያዬ ሄድኩ። ሚካኤል ቤተክርስቲያን በረንዳ ላይ ነበር። ሽርጤን ተከናንቤ ተጠቅልዬ ተኝቻለሁ። ሌሊት ላይ፣ ሁለት ሰዎች ቀሰቀሱኝ - ኣንድ ኣዛውንትና ኣንድ ልጅ።

"ማነህ? … እዚህ ምን ኣመጣህ?" ኣሉኝ።

ነገርኳቸው። ግን፣ ስለማንነቴ ምንም ማስረጃ ኣልነበረኝም። መታወቂያ ኣልነበረኝም። ጊዜያዊ ዲፕሎማ ብቻ። ያ ደሞ ፎቶ የለው፣ ምን የለው። መጠየቄ ኣናደደኝ፣ እኔ። ግንፍል ብዬ፣

"ለምንድነው እምትመረምሩኝ? ይህ የእግዚኣብሔር ቤት ኣይደል’ንዴ? ማንኛውም መንገደኛ ሊያድርበት ኣይችልም?"

ረጋ ብለው ሁኔታውን ሊያብራሩልኝ ሞከሩ። ይህ እንደ መሃል ሃገር ኣይደለም። ብዙ ነገሮች ኣልፈዋል በዚህ ክልል ውስጥ። ያልታሰቡ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ለክፋት ኣይደለም የጠየቁኝ። … ቀስ በቀስ ተረጋጋሁ። ቀስ በቀስ ተግባባን። በመጨረሻም፣ እደወል ቤት ውስጥ ገብቼ ከልጁ ጋር እንዳድርም ፈቀዱልኝ። ካርባምንጭ ለመጣ ሰው መቀሌ ብርዳም ነው። ልጁ የራሱን ኣንሶላ ደረበልኝ። ሰላማዊ ምሽት ኣሳለፍኩ። ያ ልጅ እማላውቀው ወንድሜ ነበር። ኣወቅሁት ያኔ።

ሰኞ ዕለት እንደታሰበው ዶ/ር ምትኩን ኣገኘሁዋቸውና የተወሰኑ ቦታዎች ደዋውለው የት የት መሄድ እንዳለብኝ ነገሩኝ። የዚያኑ ዕለት ኣምስት የቢሮ ሃላፊዎችን ኣገኘሁ። ያ ኣዋሳ ሰባት ወር ተመላልሼ ካገኘሁት የሃላፊ ቁጥር ይበልጥ ነበር። ምን ዓይነት ልዩነት ነው? እሚያስገርመው ቁጥሩ ብቻ ኣይደለም። ግንኙነቱ ሌጣ ግንኙነት ኣልነበረም። በቀና ስሜት የተሞላ ነበር። ኣንድ ምሳሌ ይህንን ያሳይልኛል፦

ሳርት ወደተባለ ኣዲስ መስሪያ ቤት ሄድኩኝ። (ያ ሁዋላ ለሶስት ዓመታት የሰራሁበት መስሪያ ቤት ነው።) ያገኘኝ ልጅ (ገብረመድህን) እንዲህ ኣለኝ፦

"ሃላፊው ኣሁን የለም። ለጥቂት ሳምንታት ኣይመለስ ይሆናል። ኣዲስ የጥናት ቡድን እያዋቀርን ባንተ ሞያ ብቻ ሰው ጎድሎን ነበር። ጥሩ ጊዜ ነው የመጣሀው። የሚወስነው ግን እሱ ስለሆነ የማስረጃህን ፎቶኮፒ ኣስገባና ካንድ ከሁለት ሳምንት በሁዋላ ተመለስ።"

ኣንድ ሁለት ሳምንት ለመቆየት ምንም ነገር የለኝም። እየጠየቅሁት ያለሁት በሙያዬ ለመስራት ኣይደለም። ማንኛውንም የቀን ስራ ነው። እነሱ የግድብ ስራ ስለሚሰሩ ለኔ የሚሆን የቀን ስራ እንደማያጣ እርግጠኛ ነበርኩ። ያን ስነግረው ፊቱ ሲለዋወጥ ታየኝ፣ ገብረመድህን። ዓይኖቹ ደመና ሲለብሱ፣ ዕምባ ሲያፈልቁም ታየኝ። የሱ ዕምባዎች ከኔም ዓይኖች የዕምባ ጨሌዎችን ፈነቀሉ።

ይህ ኣስገራሚ ነገር ነው። ከዚህ ቀደምም የቀን ስራ ጠይቄ ኣልተሳካልኝም። እኔና ጓደኛዬ፣ ተሾመ፣ ያለስራ መቀመጥ ቢያሰለቸን ወደ ኣዋሽ ጥጥ ለቀማ ለመሄድ ወሰንን። ያኔ፣ ኣርባምንጭ ላይ ምዝገባ ነበር። እኛ ግን ሲሌ-ወራ-ጋሞ በተባለው ጣቢያ ላይ ለመመዝገብ መከርን። ኣርባምንጭ የሚያውቀን ሰው ብዙ ስለሚሆን። ስሌ ላይም እኔን እሚያቁኝ ሰዎች ብዙ ሊሆኑ ስለሚችሉ ተሾመ ሄዶ ሁለታችንንም እንዲያስመዘግብ ተስማማንና ሄደ። ማታ ሳይመዘገብ ተመለሰ። "ለምን?" ብለው፣

"እምቢ ኣሉኝ ባክህ። እያሾፍክብን ነው፤ ኣሉኝ። ኣንተን የመሰለ ሰው እንዴት ቀን ስራ ይሰራል? ኣሉኝ። ብለምናቸው ጭራሹኑ ተናድደው ኣስወጡኝ።"

እግዚኣብሔር ይመስገን ብርቱ ኣካል ኣለኝ። እግዚኣብሔር ይመስገን እማይሞት ተስፋ ኣለኝ። እግዚኣብሔር ይመስከን ሆዴ በንፍሮም በዶሮም እኩል ይሞላል። እና፣ ኑሮዬን ከሸለቆ ውስጥም፣ ከተራራ ላይም ከመጀመር እሚያግደኝ ምን ነገር ኣለ? ያን ግን ያኝ ሰዎች ኣልተረዱም። ትክክሉ እነሱ እሚያስቡት ብቻ እንደሆነ ኣመኑና ያችንም ዕድል ከለከሉን። ወደ መቀሌ ስመጣ ማንኛውንም ስራ ሰርቼ ህይወቴን እንደማቀና ኣምኜ ነበር። እነሆ፣ ያው ጥያቄዬ ሌላ ዓይነት የስሜት ክር ነካ።  

(ያ ኣንብቶ ያስነባኝ ልጅ፣ ያኔ ኮሞሮስ ደሴት ውስጥ በወደቀው ኣውሮፕላናችን ህይወቱ ኣልፏል። ያን ኣደጋ ባሰብኩት ቁጥር ኣስበውና፣ "በዚያ ውስጥ ቢያንስ ኣንድ ደግ ሰው ነበር፤" እላለሁ።) 

በዚያኑ ቀን የግብርና ቢሮ የሁለት መቶ ኣርባ ብር ጊዜያዊ ስራ ሰጠኝ። የቢሮ ሃላፊው ኣቶ ብርሃነ በዚያው በትህትና በተሞላ የደግነትና የወዳጅነት ስሜት ነበር ያስተናገዱኝ። ያም ሆነ ግዜያዊ ቅጥሬ ከጠየቅሁት በላይ ነበር። ከዚያ በሁዋላ የሆነው ሁሉ ታሪክ ብቻ ነው።  

እንግዲህ ይህ ሁሉ የሆነው በኣንድ ሳምንት ውስጥ ነበር። ሰኞ ኣዋሳ ገባሁ። በሚቀጥለው ሰኞ መቀሌ ላይ ስራ ኣገኘሁ። ያገኘሁት ስራ ብቻም ኣልነበረም። በነዚያ ሰባት ቀናት ብዙ ነገሮች ሆኑ። ብዙ ዓይነት ሰዎችም ገጠሙኝ። በመንገዴ ያገኘሁዋቸው ያኝ ሰዎች ሁሉ ግለሰቦች ነበሩ። ፓሪቲ ኣይደሉም። ዘር ኣይደሉም። ግለሰቦች። ግንኙነታችንም በግል ደረጃ ነበር። በዚያ ደረጃ ፍቅር ሰጥተን ፍቅር መቀበል እንደምንችል ኣስታወሱኝ። ያ ወደዘነጋሁት ተረት ኣነቃኝ። ያ ወደ ተፈጥሮዬ መለሰኝ። ያ በሰው ልጅ ላይ የነበረኝን እምነት ኣፀናልኝ። ሰባት የህማማትና የትንሳኤ ቀናት። ኣዳኝ!    

ደቡብ ላይ የገጠሙኝን ባለስልጣናትም የተገናኘሁት በግል ደረጃ ነበር። እነሱም ያንኑ ደግነት፣ ያንኑ የወዳጅነትና የፍቅር ስሜት ሊያሳዩኝ ምርጫ ነበራቸው። በሆነ ምክንያት ያንን ሊያደርጉ ኣልቻሉም። ያ ግን ሰብዓዊነቱ እውስጣቸው የለም ማለት ኣይደለም። እንዲህ ያለው ስሜት ኣንድ ቦታ ተፈብርኮ በፓርቲ የሚታደል እንዳይደለ ኣውቃለሁ። ያሳደገኝ ተረት እንደሰው ምን ያህል የተሳሰርን እንደሆንን ነው ሲነግረኝ የኖረው። ያ የተናጠ ጊዜ ያንን ተረታችንን ኣስረሳን መሰል፣ በግዜያዊ ስሜት ያን ልንቁስ የድር ህብር በጣጠስነው መሰል፣ በምትኩ የፈጠርነው ኣዲስ ተረታችን ሊያስተሳስረን ጉልበት ኣጣ መሰል፣ በልባችንም በቃላችንም መቃቃር ደምቆ ተሰማ። ሃይማኖታችን ኣንድ ሊያደርገን ጉልበት ኣጣ። ሃገርም ኣንድ ልታደርገን ጉልበት ኣጣች። ሰው መሆንም ኣንድ ሊያደርገን ጉልበት ኣጣ።  

ያ የህማማት ገጠመኜ፣ ይህ የዝንጋዔ ዘመን ሊነጥቀኝ ከነበር ከዚያ ጥንታዊ የተረት ማህፀን፣ እንደገና ኣዋለደኝ። ቦታው ደግሞ መቀሌ ነበር። እና፣ ባልተፈጠረና ባልተፈጠርኩለት ኣጥርና ድንበር ደልድሎኝ፣ ያለተፈጥሮዬ እንድኖር የሚሰብከኝን የዘመኔን ጎበዝ እንዲህ እለዋለሁ፦ "ሰማሀኝ? መቀሌምኮ የትውልድ መንደሬ ነች!"

በቅርቡ ኣውስትራሊያ ደርሶ የተመለሰ ወዳጄ የገጠመውን ነገረኝ። የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ነው ልጁ። ቤተ-ክርስቲያን መሄድ ፈለገና ጠየቀ። ጓደኞቹ፣ ጥያቄውን በጥያቄ መለሱለት፦   

"ወደየትኛው ነው መሄድ እምትፈልግ? ወዳማራ ኦርቶዶክስ? ወደትግሬ ኦርቶዶክስ? ወይስ ወደኦሮሞ ኦርቶዶክስ?"  

"በዚህ ዘመን እንዲህ ባለ የክፍፍል ኣረንቋ ውስጥ መዘፈቅ ኣያሳዝንም?" ኣለኝ ወዳጄ።

እኔ ታዲያ፣ ይህ ወገኔ፣ ይህ ዘመኔ፣ የገባበትን እንዲህ ያለውን ነገር ሳስብ ሁሌ እምጠይቀው፣ "ሰውን በግል ደረጃ፣ በሰውነቱ ብቻ፣ እሚቀርቡበትን ኣጋጣሚ ሳያገኙ ቀርተው ይሆን?" እያልኩ ነው።

እርግጥ ነው፣ ያ ኣይሆንም። ይህ የቡራኬ ዘመን ነው። የፈጣሪ ችሮታ ከየትኛውም ዘመን ኣብልጦ የዘነበበት ዘመን ነው ይህ። እንኳን የራስን ወገን፣ እንኳን የራስ ሃይማኖትን ምዕመን ለመቅረብና ለማወቅ ቀርቶ፣ ከሺ ኣድማስና ከሺ ምዕራፍ ርቆ ያለን ነፍስ ልብ ለልብ ለማውጋት የነበረውን ገደብ በሙሉ ማለት ይቻላል ኣንስቶልናል ዘመኑ። እና፣ … በዚህ በተቀደሰው ዘመኔ ውስጥ፣ ይህ ወገኔ ምን ነካው? ያውም ኣውስትራሊያን፣ ያውም ኣውሮጳን፣ ያውም ኣሜሪካን በመሰለ ቦታ እሚኖረው ይህ ወገኔ ምን ነካው?

ኣንዲት ኣፍሪካዊት ኣባባልም ትታወሰኛለች ደሞ፦
"ኣንት ቆሻሻ እንደሆንክ ቢያይም፣ ዝናብ መዝነቡን ኣያቆምም።"
ይህ የፈጣሪ ቸርነት ነው። እኔ ምን ፅልመትን ብመርጥ ፀሃይ መውጣቷን ኣታቆምም። እኔ ምን ጥላቻን ባራግብ፣ ኣእዋፍት መዘመራቸውን ኣያቆሙም። እኔ ምን ኣፍንጫዬን ብይዝ፣ ፅገሬዳ መዓዛዋን መናኘት ኣታቆምም። ይህ የፈጣሪ፣ ይህ የተፈጥሮ ደግነት ነው።

ደግሞ ይህንን ኣውቃለሁ፦ ከፀሃይም፣ ከኣእዋፍትም፣ ከፅገሬዳም የከበርኩ የእግዜር ስራ ነኝ፣ እኔ። የፍጥረት ሁሉ ቁጨት ነኝ እኔ።   

ትርጉሙ፣
የፍጥረት ቁጨቱ
በኔ ላይ ካረፈ።
እንዳይተረተር፣
ከርሬ ልቋጠር።         ኣርባ ጠብታዎች፣ ቁጨት፣ ገፅ 24

የፍጥረተ-ዓለም ትርጉምና ቁጨት የሆንኩት እኔ፣ ይህንን ብኩርናዬን የሁዋሊት ጥዬ፣ በርክሰት ውስጥ ለመኖር እንደምን እመርጣለሁ? ያውም በዚህ የፈጣሪ በረከት ያለከልካይ በሚወርድልኝ፣ ያለ ዳኛ፣ ያለእረኛ በሚታደለኝ ዘመን! … ድሮ፣ ድሮ፣ ለጥፋት ዘንቦ ነበር ኣሉ ዝናቡ። ኣሁን ግን ያ ዝናብ (እውነት እንበለው እውቀት፣ ሳይንስ እንበለው ቴክኖሎጂ) እሚዘንበው ሊያጠፋኝ ሳይሆን ሊያነፃኝ እንደሆን ኣውቃለሁ። መንፃት ምርጫ ነውና እኔ እምቢኝ እል ይሆናል። ዝናቡ ግን መዝነቡን ኣያቆምም። ፈጣሪ፣ በኔ እምቢታ፣ ፍጥረትን ሁሉ ኣይቀጣምና። እኔ፣ ምን በሃጥዓት፣ ምን በኣመፃ ብኖር፣ በውስጤ ያለውን መልካምነትም ኣያጠፋም እርሱ። እውስጤ ያኖረውን የራሱን እስትንፋስ ይወዳልና እርሱ። ያን የእርሱን ብርሃን ከኔ ብቻ ውስጥ እንኳ ቢያጠፋ የፍጥረቱ ቁጨት ይበተን፣ የነበረውም እንዳልነበር ይሆናልና። እሱ እያንዳንዱን ፍጡሩን በሃያል ጥበቡ ከሌላ ከየትኛውም የፍጥረቱ ቤተሰብ ጋር በስውር ህብር ኣስተሳስሮ መስርቷልና። ኣዎ፣ በከበበኝ ጥቀርሻ ብርሃኔ ምን ቢደበዝዝ፣ እኔ በእርሱ በኩል ሁሌም እምንጨለጨል ጧፍ ነኝ። ኣያጠፋኝም!

ኣበቦች ኣብበው ሳይ፣ ኣዕዋፍት ሲዘምሩ ሳደምጥ፣ ፋፋቴ ሲንሿሿ ስሰማ፣ የጥቁር ኣፈር ሽታ ባፍንጫዬ ሲገባ፣ ፈገግ እላለሁ። ይህችን ታህል መልካምነት ሁልጊዜም እውስጤ ኣለች። ለፍጥረት እማልነፍገውን ፈገግታ ለወንድሜ ከቶም ኣልነፍግም። የትኛውም ሰው፣ በየትኛውም ቦታና ጊዜ፣ ያችን ታህል ብጣቂ መልካምነት ሊያደርግ እንደሚችልም ኣውቃለሁ። እኔ፣ እማልከስም ብርሃን ነኝ። እሱም እማይከስም ብርሃን ነው። እኔ፣ የህይወት ኣጋጣሚዎች ኣሸንፈውኝ፣ ዛሬ ክፉ መስዬ እታይ ይሆናል። ነገም ስቆጣ፣ ሳማና ሳደማ እገኝ ይሆናል። በውስጤ ግን፣ በነፍሴና በልቤ ግን፣ ጥሩ ሰው፣ ብሩክ ሰው ነኝ እኔ።

ፊቶች ይረሳሉ። ቆይቶ፣ ያኔ፣ በዚያ የመቀሌ ምካኤል የደወል ቤት ውስጥ፣ ኣንሶላውን ያዋሰኝን ልጅ መቀሌ ኣየር-ማረፊያ ኣገኘሁት። ኣድጎ ነበርና ኣላወቅሁትም። እሱ ግን ኣወቀኝ። መናገር የተሳነው ነው ልጁ። በምልክት ቋንቋ ማንነቱን ኣብራራልኝ። ማንነቴንም ነበር የነገረኝ። ኣስታወስኩት። ኣዎ፣ ዛሬ በመንገዴ እሚገጥሙኝን ነገ እንደዚያ ልጅ፣ እንደዚያች ምስጢረኛዬ፣ እንደዚያ ተጋዳላይ፣ … እረሳቸው ይሆናል። በእውነቱ፣ ያችን ደግነት የሰራልኝ ቀጥሎ መንገዴን እሚያቋርጥ ማንኛውም ሰው ሊሆን ይችላል። እና፣ ፊት ማስታወስ፣ ስም መጥራት፣ ምን ይበጀኛል? እና፣ ሃይማኖት መለየት፣ ዘር መቁጠር ምን ይበጀኛል? እና፣ ፓርቲ መሸንሸን ሃብት ማስመዘን ምን ይበጃል? … ሳገኘው፣ ያገኘሁት ሰውነቱንም ሰውነቴንም እንደሁ ማሰብ ኣይበቃኝም? ከየትኛውም ዓይነት ኣንድነት ያ ኣይጠነክርም? ከየትኛም ዓይነት የመለያየት ምክንያት ያ ኣይጠነክርም?   


እውነት ተብለው በምድር የተነዙ ብዙ እውቀቶች ኣሉ። የእኛን ምርጫ ሳይጠይቁ፣ ተሰርተውና ተወስነው የቆዩንና የሚቆዩን ብዙ ነገሮች ኣሉ። ጉልቻ እኔ ከመፈጠሬ በፊትም ጉልቻ ነበር። ስለዚያ እኔ ምንም ማድረግ ኣልችልም። ይህንን ግን እችላለሁ፦ እኔ ከእምነትም መርጬ ኣምናለሁ። ከእውቀትም መርጬ ኣውቃለሁ። ከቃልም መርጬ እናገራለሁ። በመንገዴ በሚገጥመኝ ብጤዬ ሁሉ ውስጥም ራሴው ውስጥ ያለውን እማይከስም መልካምነት ለማየት እተጋለሁ። ኣዎ፣ እማይከስም። ይህ ተስፋ ብቻ ኣይደለም። ይህ እውቀት ነው። ይህ እውነት ነው። በልቤ መዳፍ ውስጥ ጨብጬ የያዝኳትን ይህችን ብጣቂ እውነት ሊነጥቀኝ የሚችል ማንም የለም። መ.ቼ.ም!  

3 comments: