Thursday, March 13, 2014

በረከተ-ቁጣ: ባይገርምህ፣ ከራሴው ሞራ ግላጭ ያነበብኩት ትንቢት ኣለኝ እኔም!

  ባይገርምህ፣ ከራሴው ሞራ ግላጭ ያነበብኩት ትንቢት ኣለኝ እኔም!


Email me if you would like to read @ sinkish@gmail.com 

Monday, March 3, 2014

ኢትዮጵያዊ ኣይጦች ኣያነብቡም!

ትንኝ ላይ ደግነህ፣ ትንኟን ሳታቆስል፣
በሽታህን ገድለህ፣ እፎይ ያልክ ለታ፣
ሰልጥኛለሁ ብለህ፣ ኣታሞህን ምታ!  

ዋሾ ላይ ደግነህ፣ ዋሾውን ሳትገድል፣
ውሸቱን ደምስሰህ፣ እፎይ ያልክ ለታ።
ሰው ሆኛለሁ ብለህ፣ ኣታሞህን ምታ።


ይህችን ፅሁፍ ያድዋ በዓላችንንም፣ ያድዋ ጀግንነታችንንም እያሰብኩ፣ እነሆ፣ በዕለተ-ኣደዋ፣ 2006 ጨረስኳት። ስለጦረኛነት ኣይደለችም። ስለጀግንነት ግን ነች፤ ብል ዕብለት ኣይሆንብኝም። ስላዲስ ዓይነት ጀግንነት። ከረዘመችባችሁ በየርዕሱ እያረፋችሁ ኣንብቧት። እነሆ፦

ኢትዮጵያዊ ኣይጦች ኣያነብቡም!

በደፈናው ባይጦች ላይ ነበር ምርምር ለማረግ የተነሳሁት። ማግኘት የቻልኩት ግን ኢትዮጵያዊ ኣይጦችን ብቻ ነው። በሳይንሳዊው ዘዴ፣ በቂ ናሙና ሳይወስዱ በሙከራው ውስጥ ስላልተካተቱትም መናገር እንደ ግልብ ማጠቃለያ ይቆጠራል። ያ ጥሩ ሳይንስ ኣይደለም። ስለማውቃቸው ኢትዮጵያዊ ኣይጦች ብቻ የደረስኩባቸውን እውነቶች እነግራችሁዋለሁ ዛሬ። በስፖንሰርና በፈንድ እጦት ምክንያት ምርምሬን እስከመጨረሻው ባላዘልቀውም (ይህ የፈንድ ማነቆ እያለ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ጥሩ ሳይንስ መስራት ይቻላል!?) በልቦናዊ የሃሳብ ምርምር (thought experiment) ድምዳሜው ላይ ግን ደርሻለሁ፦ ኢትዮጵያዊ ኣይጦች ኣያነብቡም።

ስለ ኣይጦቻችን ከመናከሬ በፊት ግን፣ ለመንደርደሪ እንዲሆነኝ፣ ስለ ኢትዮጵያዊ ትንኞች፣ ስለ ኢትዮጵያዊ የሌሊት ወፎች፣ እና ስለ ኢትዮጵያዊ ትሁዋኖች፣ ኣወጋችሁዋለሁ። ኣንዴ ጊዜኣችሁን ከፍላችሁኛልና፣ መራርቄ ነው እምሰጣችሁ።

ከመንደርደሪያዬ በፊት የመንደርደሪያ መንደርደሪያ ላስቀድም። ይህ የምርምሬ መላምት ነው፦

ዳርዊን ይሁን ሜንዴል፣ የተቀሰመ ባህሪይ በዘር ኣይተላለፍም፤ ይላል። ውሸት ነው። ድብን ያለ ውሸት! እንዴት ኣትሉም? ትግርኛን ትግሬ ሲጨፍር፣ ወላይትኛን ወላይታ ሲያስነካው ኣይታችሁዋል? የትግርኛን የከበሮ ድለቃ ተከትሎ ወይ ሰለል ወይ ተጎምፀፅ፣ ማለት ማንን ያቅታል! ትሉ ይሆናል። ጭንን እንደተፈጠርንባትና እንደተፈጠርንላት ጥበብ መስበቅ ነው፤ ምን ኣላት ወላይትኛ! ትሉ ይሆናል። ኣሳምራችሁ ኣላያችሁም። በእውነት! ትግሬ በትግርኛ እንደ ጨረቃ እርምጃ ሲንሸራተት፣ ሰበቅ እያረጋት ኣንገቱን፣ መታ እያረጋት ትከሻውን፣ ሰበር እያስባለ ወገቡን፣ ሸብረክ እያረገ ጉልበቱን፣ የቱም የሰለጠነ ደናሽ እንደማያረጋት ያረጋታል - የሆነች ጣዕም፣ የሆነች ውበት፣ የሆነ ቃና ሰጥቷት። ወላይትኛ በወላይታዋ ሸበላ ሲያዝማ፣ ምን ልበላችሁ፣ … ቃል እማይገልፀው ትንግርት፣ ፎቶ እማይይዘው ምትሃት፣ ይታያል። ጋልብ ጋልብ፣ ንጠር ንጠር፣ ብረር ብረር፣ እሚያስብል። ዳንስ ተማርኩ ብሎ ያችን ምትሃት የሚያመጣት የለም፣ እመኑኝ። ዕድሜ ልኩን ደንሶ በማያውቅም ወላይታ ውስጥ ግን ያች ትንግርት ተርምጃውም ትታወቃለች። ታዲያ፣ ያ ምት፣ ያ ስልት፣ ደማቸው ውስጥ ባይኖር ነው? በዘር ባይተላለፍ ነው? በልቦና ባይቀረፅ ነው? … በኔ ይሁንባችሁ፣ እነዳርዊን ተሳስተዋል። (ከፈለጋችሁ ዳንስን እንደቋንቋ ቁጠሩት። ኣንድን ቋንቋ ካደገ በሁዋላ በመማር ያገኛትን ሰው፣ ምንም ያህል የሰላ ተናጋሪ ቢሆን፣ የሆነ ቦታ ተወላጅ ተናጋሪ እንዳይደል ትይዙታላችሁ። ስለ ኣይጦቻችን ያደረግሁትን ምርምር ካነበባችሁ በሁዋላ፣ በዚህ የውርዴ ባህሪይ መላምቴና ድምዳሜዬ መስማማላችሁ ኣይቀርም።) በዚህ በኩል፣ ፈረንሳዊው የኔ ብጤ፣ ላማረክ፣ ነበር ትክክል። እሱ ይህችኑ ነው መስክሮ የሞተ፦ የተቀሰመ ነገር በዘር ይተላለፋል! ደናሽ ኣባት ደናሽ ልጅ ይወልዳል። ኣሽዋፊ ኣባት ኣሽዋፊ ልጅ ይቀርፃል።

የደብተራ ዘነብ፣ መፅሃፈ ጨዋታ ስጋዊ፣ እንዲህ ይላል፦ "ጣዝማ እጅግ ብልህ ናት፤ መሬት ቀዳ ገብታ እንደዚያ ያለ መድሃኒት የሚሆን ማር ትሰራለች። ምነው እናንተ ሰዎች ወይ ከፈጣሪ ወይም ከሰው ብልሃትን ኣትፈልጉምን።" ብልህ ነው ይህ ደብተራ። የጥበብን ምንጭ ኣሳምሮ ኣውቋል፦ ወይ እግዚኣብሄር ነው፤ ወይ ሳይንስ ነው፤ ዕውቀት ማህፀኗ። እነሆ፣ ስለጥበብ ብለን በኢትዮጵያዊ ኣይጦች ስም ስለኢትዮጵያዊ ትንኞች ያለንን ምልከታ በማጋራት እንጀምራለን።

ኢትዮጵያዊ ትንኞች

በትንኝ ገደላ እሚያህለኝ ማንም ኣልነበረም። የዚያ ሚስጥር ምን እንደሁ እማያውቅ ልንገረው፦ያርባምንጭ ልጅ በመሆኔ ነው። ትንኝ ገዳይነት ከደሜ ኣለ። ኣዲሳቤቤዎች ሺህ ዓመት ይህን ጥበብ ቢለማመዱ፣ ከቶም ሊረቱን ኣይችሉም። ተስፋ እንዲቆርጡ፣ ይህንን ከወዲሁ ልንገራቸው፦ ትንኝ ገደላ የኦሎምፒክ ጌም ቢሆን፣ ሜዳሊያው ሁሌም ያርባምንጭ ልጆች ይሆናል። በ’ግር ኳስ ብቻ መሰላችሁ ጉብዝናችን?

ደም መጣጮች ናቸው ትንኞች። ያ ቢበቃቸው መልካም ኣይደል? ከባለወባ ወባ ይዘው ይመጡና ደምሽን ወስደው ወባ ሰጥተውሽ ይሄዳሉ። በተለይ ያች ኣኖፈለስ ጋምቤ እምትባለዋ ያገሬ ትንኝ! (ትውልዷ ጋምቤላ ስለሆነ ነው ኣሉ ያባቷ ስም ጋምቤ የተሰኘው።) በሽታውም ብቻ ቢሆን መልካም ኣይደል? ጩሀታቸው! ንዝንዛቸው! እንዲያው ሴይጣን ራሱ የሚያፏጭ ነው እሚመስል ትንኞቻችን በጆሮሽ ሲያፏጩ። ሴጣን ራሱ! የጠማው ሴይጣን፤ ከነፍስሽ ጉድጓድ ውሃ ኣፍልቆ ሊጠጣ ችክ የሚል ሴይጣን! እንግዲህ ነፍስ ምን ቢቆፈር ውሃ ኣይወጣውምም ኣይደል? ሴጣኑ ታዲያ ይተዋል? ያ ችኮ መንቻካ! … ውይ! ውይ! ውይ! እንዲያው የኢትዮጵያዊት ትንኝ ንዝንዝን እግዜር ኣንዴ ኣሰምቷችሁ የፀጥኛ ምሽትን ውበት በቅጡ ባወቃችሁ! …

ደምሽን መጠው፣ በሽታ ሰጥተውሽ፣ እንቅልፍ ነስተውሽ፣ ይሄዳሉ ትንኞች። (ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው እንቅልፍ ነሺ ነገሮች ሶስት መሆናቸው ነው እንግዲህ፦ ኣንደኛው - ያችው ትንኝ፤ ሁለተኛው - ቡና፤ ሶስተኛው ደግም፣ ሰው! … ኣይ የኢትዮጵያ ነገር! ታልጠፋ ሃብቷ ሰውን ለዓለም መስጠቷ!)

እና፣ ስንት ትንኞችን ገደልሁ መሰለሽ! … ብቃቴ በደምና በማደግ ብቻ የተወረሰ ኣይምሰልሽ! በተግባር ተፈትኖ የሰላ፣ የተሞረደም እንጂ ነው። ስንት ትንኞችን ፈጀሁ፣ ሳላቅራራ፣ ሳላጓራ፣ ሳልፎክር፣ ሳላጎፍር! …

ዘጠነኛ ክፍል ስደርስ ግን ጀግንነቴ ሃጥኣት ሆኖ መጣ! ኣምላክ እንደኔ ኩም ያርግሽ፣ ኩም ኣልኩልሽ! ኣንድ መምህር ነው ይህን ያመጣብኝ። ብታዪው፣ ቅጭጭ ያለ ነገር ነው። ቀይነቱ ደግሞ! ኣፍሮው ደግሞ! ቀይነቱና ኣፍሮው፣ ቅጥነቱንም እጥረቱንም ኣጋንነውበታል። ምን ኣለን መሰለሽ?

"ትንኞች በተፈጥሮኣዊው ስርዓትና በምግብ ሰንሰለት ውስጥ የራሳቸው ድርሻ ኣላቸው። እነሱን ሳንገድል የሚያስተላልፉትን በሽታ ማቆም ስለማንችል ብቻ በተፈጥሮኣዊው ስርዓት ውስጥ ይቅር የማያስብል ጥፋት እያደረስን እንኖራለን!"

ጉድ፣ ኣልኩኝ! ለካስ ሴይጣን ራሱን የገደልኩ መስሎኝ የሴጣን እጅ ሆኜ ቆይቼልሻለሁ! እግዚኣብሄር በብዙ ደግነት ከሚያኖረው ከኔ ወደል ኣካል ውስጥ ያ ጭካኔ እየወጣ፣ ከዚያ በስስት ፈጥሮት በስስት የሚያኖረ ከሚመስል ቀጫጫ ኣካል ውስጥ ትንኝንም ሳይቀር እሚያቅፍ ደግነት መውጣቱስ ኣይገርምም? ምንኛ ምስጋን ኣለው ህይወቱ! በድንጋይ ልቤና በኩይሳ ኣካሌ ዓለምን ኣጉል የከበድኳት፣ ኣጉልም የተጫንኳት መሰለኝ። ምኑ ነኝ! … ኣህ! ምስጋን ኣልባ ገላ!  

እውን እግዚኣብሄር ስህተት ይፈጥራልን? ብዬ ማሰብ ያዝሁ ተዚያ። እስቲ ዙሪያህን ተመልከት። ከእግዚኣብሄር ፍጥረት ቅንጣት እንከን ታገኛለህን? እምትለው ሰማያዊ መጠይቅ ተልቤ ገብታ መውጣትን እምቢ ኣለች። ዙሪያዬን ኣየሁ። በፍጥረት ውስጥ ኣንድም ስህተት ኣላገኘሁም። እግዚኣብሄር በፈጠረው ነገር ደስ እንዳለው ሁሉ እኔም ያን በማስተዋሌ ደስ ኣለኝ። በዙሪያዬ ስህተት ቢኖር የዚያ ስህተት ምንጭ እኔ እንጂ ነኝ ፍጥረት ኣይደለችም፣ ብዬ ኣመንኩ። ትንኞቻችን ህመም ቢሰጡን ያ ህመም ከነሱ የመጣ ኣይደለም። ተፈጥሮ በሰው ልጅ ላይ እምታመጣ ለሚመስለን ለእያንዳንዱ ነገር ሰው ያዛባው፣ ሰው ያበላሸውና ያጠፋው የሆነ ነገር ይኖራል፤ ኣልሁ።

ህንዶች እባብ ቢያስቸግራቸው፣ ገድለው ጨረሷቸው ኣሉ ኣንዴ። ያ እፎይታ የሚያመጣላቸው መስሏቸው ነበር። ኣይጦች ምድሪቱን ወረሯት። ኣይጥ እንደ እባብ ውብም፣ ገራምም፣ ጨዋም ኣይደለችም። እማትገባበት ጓዳና ጉድጓድ፣ እማትቀድደው፣ እማትበጥሰውም ነገር የለም። የባሰ ጥፋት፣ የባሰ መከራ መጣ በህንዶች ላይ። ኣይጥን እንደ እባብ ኣድኖ ማጥፋቱም ቀላል ኣልሆነም። ኣይጥ ብልጧ ከብልሆቹ ህንዶችም በልጣ ተገኘች። ሴይጣን በእባብ በኩል መጣ፤ እሚባለውን ትተው፣ በኣይጥ በኩል መጣ ኣሉ የህንድ ጉሩዎች ። የምድሪቱ ሳይንቲስት ቢቸግራቸው፣ ኣንድ መላ መቱ፦ እባቦችን በምርምር ጣቢያ ውስጥ ኣራብተው በምድሪቱ ላይ ይለቅቁ ጀመር።

ከመፃፍ ቅዱስ ኣጉል የይለፍ ቃል ኣገኘሁ ብለህ ያገሬን እባብ ኣናት ኣናቱን እየቀጠቀጥህ መድረሻ ያሳጣሀው፣ ስማኝ ወገን! ስማኝ ይበጅሃል ጃል! መልካሙ መጣፍ፣ ኣትግደል፤ እንጂ ነው እሚል፣ ሰውን (ብቻ) ኣትግደል፤ ኣይደል። ፈጣሪ በጥበቡ ለጥበቡ የፈጠረውን ሁሉ ኣትግደል! ነው እሚል። ያን ጥበብ ፈልግ ካሻህ፤ ያን እውነት ቆፍር ከጀገንህ፣ ያን ሚስጢር ፈልፍል ከተጠበብህ! ነው እሚል ኣንደምታውም። ማነህ፣ ጎበዝ! ቃል ይገድላልና በቃል እያመካኘህ ኣትግደል!

(የለ የለ፣ ኣሁንም ስለትንኞቻችን ነው እማወራ። ያይጦቻችን ጉዳይ እልፍ ስትሉ ብቅ ይላል።)

ይህንን ስላወቅሁ ከትንኝ በፍቅር ኣልወደቅሁም። ኣሁንም ጩሀቷ ያሳብደኛል። ኣሁንም የምታመጣብኝ ህመም ያስፈራኛል። ኣሁንም ንክሻዋ ያነጫንጨኛል። "ኣምላክ ስላፈቀረን ልጁን ሰጠን፤ ከጥፋት እንዲታደገን፤" ይላሉ ሃይማኖተኞች። "ለሌላ መታደግም ሌላ ልጁን፣ ሳይንስን፣ ሰጠን ፈጣሪ፤" ይላሉ ይበልጥ የገባቸው እንደ ደብተራ ዘነብ ያሉ ሊቆች። እነሆ በዚህ በዘመነ-ቡራኬ፣ ለኣልጋዬ ኣጎበር፣ ለገላዬ ትንኝ ማራቂያ ቅባት (በሃይማኖተኛ ቋንቋ፣ ሴይጣን ማራቂያ ጠበል ወይም ድግምት፣ ልትሉት ትችላላችሁ።)፣ ለሆዴ የጤና መሰረት፣ አመጣልኝ ሳይንስ። ዛሬ ትንኛችን ደሜን ልትመጥ ቋምጣ፣ ልትቀርበኝ ግን መላ ኣጥታ፣ ከርቀት ስታንጎራጉር እሰማታሁ። "በለጥኩሽ፣ በለጥኩሽ፣ በለጥኩሽ፣ …" እያልሁ በሆዴ፣ ፈጣሪ በሷ በኩል ሊሰጠኝ ስለፈቀደው ጥበብ ኣስባለሁ።

ያ ኣካሉን ለጥበብ ያሟሟ መምህር ምስጋን ይግባውና ቢያንስ የጥበቡ መጀመሪያው ይህ እንደሁ ኣወቅሁ፦ ኢትዮጵያዊ ትንኞች ደም ቢመጡ፣ ሳይጋበዙ ህመም ቢያመጡ፣ ተጆሮ እያፏጩ እንቅልፍ እረፍት ቢያሳጡ፣ … በዚያ ውስጥ የኔና ያንቺም እጅ ይኖራል! እነሱ እኖር ብለው ያን ያረጋሉ። የኑሮን ግዴታ፣ በደም የመኖርን ውለታ፣ የሰጣቸው ደግሞ እግዜሩ ራሱ ነው። እግዜር ስህተት ኣልፈጠረም ኣይደል? "ምን ላርግ፣ ምን ልወቅ፣ ምን ልዘይድ?" በይ። ያልፈጠርሽውን ነፍስ ኣትግደይ።

ኢትዮጵያዊ የሌሊት ወፎች

እንደ ኢትዮጵያዊቷ ትንኝ ሁሉ፣ ኢትዮጵያዊቷ የሌሊት ወፍም ኣብራኝ ነው ያደገች። ግዛቷ ግን የጨለማ ነው። ጎሬዋም ድብቅ። መልኳ ከሩቅ እሚያርቅ። ቀርቤ ላያት ኣላጓጓችኝም። ኣልዋሽሽም፣ ከብርሃን ጨለማን በመምረጧ ሳማት፣ በምላስ ሳደማት ነው የኖርኩት። እውን ወፍ ትመስለኝ ነበር ድሮ። ኮሌጅ እንደበጠስኩ፣ የተማረ ገበሬ ሆኜ፣ መሎ ወደሚባል ያገራችን ድብቅ ኣድባር ተላክሁ። ስደርስ፣ ለዘመናት ሰው ያልከፈተው፣ ሰው ያልጎበኘው ቢሮ ተሰጠኝ። በዚያ፣ በመጀመሪያው ቢሮዬ ውስት፣ የሌሊት ወፎችን በግላጭ ኣየሁዋቸው። ያኔ፣ ከወፍ ይልቅ በራሪ ኣይጦች እንደሆኑም ኣወቅሁ።

ይህች የጨለማ ፍጡር እነሆ በቀልጣጣው ብርሃን ቢሮዬን ተጋርታለች። ግን፣ ጥግ ይዛ ነው። ግን፣ በቀንም ጨለማ ለብሳ ነው። ይህ የጨለማ ፍጡራን ምልክት መሆን ኣለበት፤ ኣልሁ ለራሴ። ከብርሃን ጨለማን ይመርጣሉ። በላያቸው ላይ ከሚዘንበው ወገግታ መሸሽ ሲያቅታቸውም፣ እንደ ቀንዳውጣ በገዛ ራሳቸው ቅርፊት ውስጥ ጠልቀው ለመጥፋት ሽምቅቅቅቅ፣ ሲሉ ይታያሉ። "ድመት፣ የሰረቀች ስለሚመስላት፣ የተጋበዘችውንም ወተት ስትጠጣም ዓይኖቿን ጨፍና ነው፤" ይሉ ነበር ኣንድ መምህሬ። በፀጋ የተቸራትን በስርቆት ካገኘቸው መለየት የተሳናት ተላላፊ! ለዚያ መሆን ኣለበት፣ እንዲያ በብርሃን መሸማቀቋ፤ እንዲያ በመገላለጥ፣ በመታየቷ ማፈሯ፤ ኣልሁ።

ኢትዮጵያዊቷ የሌሊት ወፍ ከነቤተሰቧ ከላዬ ተደርድራ ልቤን ኣርግቼ ኣልቀመጥም፤ መቼም፣ ኣልሁና፤ ደግሞ ሽንቷ! መጥፎ ነው ኣሉ ሽንቷ፤ ወይ ይመልጠኝ ወይ ያሮጠኝ ይሆናል፤ ኣልሁና፣ እንዳገሬ ሰው፣ "መሽናት ክልክል ነው፤" ብዬ ብለጥፍም ከመሽናት ኣትመለስም መቼም፤ ኣልሁና፤ መላ ቤተሰቧን ልነቅል ማስላትና ማድባት ያዝሁ። "እሷም የፈጣሪ ጥበብ ነች፤" እሚል ሃሳብ ከልቦናዬ ሌማት እንጎቻ ታህል’ንኳ ኣልተዘረጋም። ሌላ ምክንያት ፍለጋ መቆየት ሳይኖርብኝ፣ እሷው ‘ራሷ ሌላ የመግደያ ምክንያት ጨመረችልኝ። ፉርር፣ እያለች ወዳንድ ጥግ። ፉርር! እያለች ወደሌላ ጥግ። ኣስጨነቃት ማለት ነው ብርሃኑ፤ እረፍት ነሳት ወጋገኑ! ድሮም የጨለማ ፍጡር! ኣልሁና፤ እንግዲህ፣ መጥፊያሽን በቅብጠትሽ ጠራሽው፤ ሞትሽን በገዛ‘ጅሽ ኣመጣሽው፤ ከደሙ ንፁህ ነኝ እኔ፤ ኣልኩና፤ ኣናቷን ብዬ ልገላግላት የቁም መጥረጊያ ኣነሳሁ። ተንጠራርቼ ኣይምሬ ምቴን ላሳርፍባት ስንደረደር፤ የሆነ ነገር የተቃጣ እጄን እመሃል ሰማይ ኣቆመው። የሌሊት ወፏ በተቀመጠችበት ሆና ስትራወጥ፣ ከሆነ ነገር ነፃ ለመሆን ስትጥመለመል፣ ስትጥር ስታጣጥር፣ ኣየሁዋት። …  

በሆነ በታላቅ ስቃይ ውስጥ ነች። እላይዋ ላይ የሆነ ነገር ኣለ። ወንበሬ ላይ ተሰቅዬ ቀረብ ብዬ ኣየሁ። ኣዎ፣ በሰራ ኣካሏ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ደሟን የሚመጡ፣ ነፍሷን እረፍት ያሳጡ፣ መጥማጭ ጠላቶች ወርረዋታል። እሷ፣ ጀርባዋን ደርሶ በማያክክ ጥፍሯ፣ መሳሪያ ሊሆናት ተስኖት መላ በጠፋው ኣፏና ጥርሷ፣ የተተከለባትን ሰንኮፍ ነቅላ ለመጣል ኣይከፍሌ ጣዕር ውስጥ ነች። ለካስ እሷም የራሷ ጠላት፣ ለካስ እሷም የራሷ ጭንቀት፣ ለካስ እሷም የራሷ ስቃይና የትግል ህይወት፣ ኣላት! … ኣሳዘነችኝ። እነሆ፣ እኔ በሰንካላ ምክንያቴ ህይወቷን ልነጥቃት ገላጋይ በትሬን ኣንስቻለሁ። እነሆ፣ ይህች ምስኪን ፍጡር፣ ማምለጥ ባልቻለችው ጠላት ተይዛ፣ በራሷው ዓለም የኑሮ ፈተና ውስጥ ህማም ትቀበላለች። ኣምላኳ ይታደጋት ዘንድ በራሷው ቋንቋ ትማፀናለች። እንደምን ትንሽ ፍርሃትን መቋቋም፣ እንደምን ትንሽ ኣለመመቸትን መታገስ ተሳነኝ? ኣልሁ። እንደምን የዚያ የመልካም መምህሬን ቃል ረሳሁ? ኣልኩ። … ምን ያለሁ ነኝ፣ ጃል!  

እነሆ፣ ከኢትዮጵያዊቷ የሌሊት ወፍ ቢያንስ ይህችን ጥበብ ኣነሳሁ፦ ፈጣሪ በፍጡራኑ ውስጥ የደበቀው የህላዌ ምስጢር፣ የኑባሬ ምክንያት፣ ኣንች ከሚመስልሽ እጅግ የራቀ፣ እጅግም የረቀቀ ነው። ልታውቂው ብትጥሪ መዳኛሽን ተዚያ ታልተገለጠ ምክንያት ታገኚያለሽ። ውስን ልብሽ በሸመነው ምክንያት ተሸንፈሽ፣ በየኩርባው እጅሽን ለመግደል መዘርጋትን ከመረጥሽ ግን፣ ያ ምክንያትሽ ለዚያ ድርግትሽ ከቶም በቂ እንዳይደለ እወቂ። ያንች የምክንያት ዓለም ጠባብ ነው። ከፈቀድሽ፣ ከታገስሽና ከተጋሽ፣ የምክንያት ግዛትሽ፣ ሰርክ እየሰፋ፣ ሰርክ ፍጡራንን ሁሉ እያቀፈ፣ ሰርክ በብርሃን እርከን ላይ ሽቅብ፣ በፍቅርም እርከን ላይ ወደላይ፣ እያወጣሽ ይሄዳል። ስለበለጠች ህብር፣ ስለበለጠች ደግነት፣ ስለበለጠች ትእግስት፣ ስለበለጠች ጥበብም ይነግርሻል። ኣርነትሽ ያለው በዚያ ውስጥ ነው። በምክንያትሽ ተሸንፈሽ መግደልን ማምለጫሽ፣ ማጥፋትን ምሽግሽ፣ ማማትን መሳሪያሽ፣ ፍርሃትን መለያሽ፣ ሽሽትን ምግባርሽ፣ … ካደረግሽ ግን፣ ያ ምሽግሽ፣ እያደር ከኣለት ዋሻም ብሶ ከቶም ብርሃን እማያስገባ ጨለማ፣ ከቶም እማታመልጭበት መታሰሪያ፣ ከቶም ምህረት እማያውቅ መቀበሪያ፣ ይሆንብሻል።

ቢያንስ፣ "የሚያስጨንቁኝ የሌሊት ወፎች፣ የሚያስፈራሩኝ የጨለማ ፍጡሮች፣ እንዲያ እረፍት የሚነሱኝ፣ ማጅራታቸውን ምን ነገር ቢነክስ ነው?" ብለሽ ጠይቂ።  

(ኣሁንም በመንደርደር ላይ ነኝ። ኣይጦቻችን እየመጡ ነው፤ ትንሽ ጠብቁ።)

ኢትዮጵያዊ ትሁዋች

ስለ ኢትዮጵያዊ ትሁዋኖች በተደምሞ ማሰብ የጀመርኩት ትግራይ ውስጥ ነው። ትግራይ፣ ለግድብ ስራ እሚሆን መሬት ኣሰሳ በየገጠሩ ይዘምቱ ከነበሩ የጥናት ቡድኖች ያንዱ ኣባል ነበርኩ። ገጠር እንገባና ጥናቱን እስከምንጨርስ ወይ እድንኳን፣ ወይ እኪራይ ቤት ውስጥ እንገጥራለን (እንከትማለን፣ ከማለት ይህ ይገልፀዋል)። ኣንዴ፣ ወዳንዲት የገጠር መንደር ደረስን። የነበርኩበት መኪና በሆነ ምክንያት ዘግይቶ ነበር። እቦታው ስደርስ የቀደሙኝ ጓደኞቼ ጥሩ ያሉትን ቤት ቀድመው ተከራይተ ኣብቅተዋል።

ይህ ገጠር ነው። እሚከራዩ ቤቶች ቀርተው የኣጠቃላይ ቤቶች ቁጥርም ከጣቶቻችን ቁጥር ኣይዘልልም። ብቻዬን መሆን ነበርና እሚመቸኝ በየሄድኩበት የብቻዬን ክፍል ነው እምከራይ። በፍለጋ ብዙም ሳልጓዝ፣ ባልደረቦቼ ቀድመው ከተከራዩኣቸው ቤቶች የተሻለ እሚመስል ያልተከራየ ቤት ኣገኘሁ። "ሰዉ እንዴት ይህንን የመሰለ ቤት ዘለለው?" ብል፣ "ትሁዋን ብቻ ስለሆነ ነው ሁሉም የፈራው፤" ተባልኩ። "ትሁዋኖችስ ያለኛ ማን ኣላቸው!" ብዬ፣ "ተው፤" እያሉኝ ተከራየሁት። መቼም ትሁዋኖችን በብልጠት ማሸነፍ ኣያቅተኝም። እንዴ! ሰው ኣደለሁ? እሚያስብ እንሰሳ ኣይደለሁ? እያልኩ በሆዴ። "ይቅርብህ፤ ከኛ ተዳበል፤" ቢሉኝም ጓደኞቼ በጅ ኣላልኩም። ብቸኝነቴ መቅደሴም፤ ድንግልናዬም ነችና ላስገስሳት ኣልወደድሁም።   

ኣሁን ያስተማሪዬን ቃል ኣልረሳሁም። ወዲያው ትሁዋኖችን ሳልገድላቸው ልበልጣቸው መላ ማስላት ጀመርሁ። የመንገድ ኣልጋዬን ከግድግዳና ለትሁዋኖች ድልድይ ሊሆን ከሚችል ነገር ሁሉ ኣርቄ እቤቱ መሃል ወጠርኩ። ችግሩ፣ ከመሬት ሽቅብ እንዳይደርሱብኝ ማድረግ ነው። መቼም ኣልጋን ኣየር ላይ መዘርጋት ኣይቻልም። ወዲያው፣ ኣንድ ጥሩ ዘዴ መጣልኝና በኣሳቢ እንሰሳነቴ ደስ ኣለኝ። ይህ ነበር ዘዴዬ፦

የኣልጋዬን እግሮች በኩባያ ወይም በጎድጓዳ ሳህን ውስጥ ማቆም፤ ከዚያም ኩባያዎቹን በውሃ መሙላት። መቼም፣ ትሁዋኖች ምን ኢትዮጵያዊ ቢሆኑ፣ ምን ባህር ኣይተው ባያውቁ፣ ውሃ እንደሚያሰጥማቸው መገመት ኣይሳናቸውም፤ ኣልሁ። እንግዲህ፣ መለኛ መጥቶባቸዋልና ራሳቸውን ይጠብቁ። ከደሙ ንፁህ ነኝ እኔ፤ ኣልሁ፣ ለራሴ።

ሳይመሽ ወይ ኩባያ፣ ወይ ጎድጓዳ ሳህን፣ ፍለጋ ወጣሁ። እንዴት ገጠር መሆኑን እንደረሳሁ! ከየት ሊገኝ ስድስት ኩባያ? ወይ ስድስት ድስት፣ ወይ ስድስት ገንቦ፣ ወይ ስድስት እንክርት! … ይዘን የመጣነው የሻይ ኩባያ ብቻ ነው። ያን ለትሁዋን ማስጠሚያ ወይ ማስፈራሪያ ስጡኝ ብል በጅ እሚለኝ ይኖራል? ቀን ቀን ሻይ እንጠጣበት፤ ማታ ማታ ትሁዋን ላስጥምበት፤ ብል እንኳ እማያዋጣ ጥያቄ ይሆናል። ስለ ኤፊሼንሲ ማሰብ ኣልተጀመረም መሰል ያኔ። ሌላ ዘዴ ፍለጋ ያዝሁ። 

ቀጥሎ ያገኘሁት ዘዴ ከቀደመው እማይተናነስና ተግባራዊ ነው። ጠንከር ያሉ ክርታሶችን በሳሁና በስድስቱ የኣልጋዎቼ እግሮች እስተመሃል ኣስገብቼ ዲሽ ወይም ዣንጥላ እሚመስል መሰናክል ኣበጀሁ። ኢትዮጵያዊ ትሁዋኖች፣ ምንም ያህል ፈጣን፣ ምንም ያህል ብርቱ ሯጮች ቢሆኑም፣ ያን ኣዳላጭ የብረት እግር ወጥተው፣ ያኚን ሰፋፊ የካርቶን ዣንጥላዎች ዞረው፣ እኔ ዘንድ እስኪደርሱ፣ እኔ ያባቢላዋ ልጅ፣ ሌሊቴን ጨርሼ፣ እንቅልፌን ኣድርሼ፣ እነሳለሁ፤ ኣልሁና፤ ሰው መሆን እንዴት ጥሩ ነው! ኣልሁና፣ ትሁዋኖችን በመብለጤ በራሴ ረክቼ፣ እግሬንም ሃሳቤንም ሰቅዬ፣ ተኛሁልሽ፤ የታባቱ!   

ሌሊት ላይ ግን፣ መጀመሪያ በህልም እሚታይ እሳት፣ ቀጥሎም ቀስቅሶኝም ማቃጠሉን ያልተወ ነበልባል፣ ተለቀቀብኝ። የእጅ ባትርዬን ኣብርቼ ኣልጋዬን ባይ፣ መዓት ያገሬ ከሲታ ትሁዋኖች ሰፍረውበታል። እንዴት ሊሆን ይችላል? ኣልሁ። በዬት በኩል ኣልፈው እዚህ ደረሱ? ኣልሁ። መቼም ክንፍ የላቸው ኣይበርሩ፣ ወይ እንደዝናብ ኣይዘንቡ፣ ኣልሁ። (ከኢትዮጵያ ሰማይ፣ ዓሳ ዘነበ እንጂ ትሁዋን ዘነበ እሚል ነገር ሰምተን ኣናውቅ!)

ለማንኛውም ብዬ ወደ ጣሪያው ኣበራሁ። ኣንዲት ኣመዳም ትሁዋን፣ እንዳበራሁባት የተንጠላጠለችበትን የጣሪያ እንጨት ለቅቃ፣ ቁልቁል ወደ ኣልጋዬ ስትወረወር ኣየሁ። "በጉድህ ወጣህ ጋሊሊዮ ጋሊሌ! ኣንተ የነፃ ወደቃን (Free Fall) ጥበብ ከሁሉ ቀድሜ ኣገኘሁ ስትል እነሆ ኢትዮጵያዊቷ ትሁዋን ቀድማህ ተገኝታለች! … ዘይገርም ነገር!"

ጉዳዩን ላጠና ኣከባቢውን ሁሉ ብቃኝ፣ የኣገር ትሁዋኖች ከያሉበት ለቅቀው፣ ቀጥታ ኣልጋዬ ላይ ለመውደቅ ወደሚያስችላቸው ወደጣሪያው ማዕከል እየዘመቱ ነው። እውነት፣ ዘይገርም ነገር! እንግዲህ ከዣንጥላ ወይ ከትንኝ ኣጎበር በቀር እሚያዋጣኝ የለም። ያኝን ደግሞ ከዬት ላገኝ?

ኣደን ኣልገባሁም። የተጨፈለቀ ትሁዋንን ሽታ እሚያቅ ለገደላ ኣይቸኩልም። ኣልጋዬ ጠርዝ ላይ ቁጭ ብዬ፣ እሚዘንቡብኝን ትሁዋኖች፣ ጀግኖች ኣባቶቼ ወራሪዎችን እንዳረጉት፣ ቢያንስ ገፍትሬ፣ ኣስወጥቼ ከድንበሬ፣ ልጣለቸው እየተጠባበቅሁ፣ ማሰብ ጀመርሁ።

እኔ እዚህ እንዳለሁ እንዴት ሊያውቁ ቻሉ? ዓይናቸው ይህን ያህል የሰላ ነው? ሸተትኳቸው ይሆን? ሽታ ኣቅጣጫ ኣለው? ሞቅሁዋቸው ይሆን? ሙቀት ኣቅጣጫ ኣለው? እና፣ እኔን ከጣሪያው፣ እኔን ከሰማዩ የሚያገናኘኝን መስመር በምን ኮምፓሳቸው፣ በምን ካርታቸው፣ ፈልገው ኣገኙ? …  

የደሜ ፍላት፣ ያካሌን ሙቀት ሽቅብ እየለቀቀ ይሆን? ከኔ የሚወጣ፣ ከዚያም ሽቅብ ወደ ሰማይ የሚሰመር፣ የሆነ የብርሃን መስመር፣ የሆነ የብርሃን ቦይ፣ የሆነ የብርሃን ገመድ፣ … ይኖር ይሆን? ከሰው የተሰወረ፣ ለትሁዋኖች ግን የሚታይ፣ የሆነ የመላዕክት ጎዳና፣ የሆና የማሪያም መንገድ፣ … ይኖር ይሆን? ይህንንም ኣሰብኩ፤ ያንንም ኣሰብኩ።

መላምቶቼን እማረጋግጥበት መንገድ ኣልነበረም። ግን፣ እንቅልፍ በራቃት ሌሊቴ፣ ያልተረጋገጡ መላምቶች ሌሎች መላምቶችን እያዋለዱ፣ ኣንዲት እውነት፣ ኣንዲት ጥበብ ተልቤ ኣወረዱ።

ትሁዋኖችን የሳባቸው የደሜ መዓዛ ይሆናል፤ ሙቀቴም ይሆናል፤ ከሰማይ የተሳሰረው የነብሴም እትብት ይሆናል፤ ወይም የመናፍስት የትል-ቀዳዳ (wormhole)፤ ኣላውቅም። ቢያንስ በዚህ ግን እርግጠኛ ነኝ፦ ትሁዋኖች በህይወት ስላለሁ ነው ያወቁኝ፣ በጊዜታ (space-time) ውስጥ ትክክለኛ ቦታዬን ስላወቁ ነው ያገኙኝ፣ ራሳቸውን ከኔ ኣስምረው በነፃ ወደቃ የዘነቡብኝ። ደሜ ሙቅ፣ እስትንፋሴም ህያው፣ ኣካሌም በብርሃን የተሞላ ቢሆን ነው። ህልውናዬን ተህልዉ ዓለም እሚያስተሳስረው ህያው ወደሮ ቢኖር ነው። የሞትኩ ብሆን፣ ደሜ የቀዘቀሰ፣ ስሜተም የነበዘ ቢሆን፣ በጊዜታ ውስጠ ቦታ ባይኖረኝ፣ ሌጣ ምንምነት (absolute nothingness) ብሆን፣ ይህ ኣይሆንም።

ደስ ኣለኝ። በዚህ ደስ ኣለኝ። ኢትዮጵያዊ ትሁዋኖች በዚያ ያሉት መኖሬን ሊነግሩኝ ነው። ሰምተሻቸው እንደሁ፣ ውሮጳዊያን፣ "በማሰቤ መኖሬን ኣወቅሁ!" ስላለ ጠቢባቸው ሲሰብኩን ዘመናት ኣልፈዋል። ኣንቺ’ና’ኔ ግን ኣፍሪካዊ ፈላሶች ነን። ሃሳብ ኣለኣካልም እንደሚኖር ኣሳምረን እናውቃለን። ማሰባችን በኣካለስጋ መኖራችንን እንዳይነግረን እናውቃለን።

እንግዲህ ይህንን ልብ በይ፦ ኢትዮጵያዊ ትሁዋኖች፣ ጢንዚዛም፣ ቁንቡርስም፣ ገንቦም፣ … እንደሆንሽ ሊነግርሽ በሚችል የራስ-ለራስ ሃሳብ መባዘን ሳይኖርብሽ፣ ስለመኖርሽ ይነግሩሻል። በሌላው ህላዌ ሰው ራሱን ያገኛል፤ እናዳለው ዘማሪው (ኣርባ ጠብታዎች፣ ሙላት 3)፣ በብቸኝነትና በግላዊነት ውስጥ ሳይሆን በህብረትና በህብር ውስጥ ራስሽን ፈልገሽ እምታገኚበት መስተዋት ይሆኑሻል። ካንቺ ጋር የሆነ ጥምረት እንዳላቸው ያስረዱሻል። ያንቺ ህይወት ህይወታቸው፣ ያንች ኑሮ ኑሮኣቸው፣ እንደሆነ ይሰብኩሻል። ኣትግደያቸው።

እግዚኣብሄር በፍጥረት ውስጥ ስህተት፣ በፍጥረት ውስጥ ጉድለት ኣላኖረም። ሁሉንም በምክንያት፣ ሁሉንም ለምክንያት ፈጠረ። በዚያም ደስ ኣለው። ኣንችም በዚህ ደስ ይበልሽ። ፍፅምናን ለራሱ ያረገው ስለሰሰተ ኣይምስለሽ። ፍፅምናሽን በስራሽ ትቀዳጂው ዘንድ ስለወደደ እንጂ ነው። ፍፁም ፍቅሩም የተገለፀው በዚህ የነፃነት ፈቃዱ ነው። ለየግል ፍፅምናችን እንበቃ ዘንድም በፀጋው ሞላን። ኣትጠራጠሪ፤ ሙሉ ነሽ። ትሁዋኖችም እንዲሁ። እነሱ፣ ደምሽን ሊመጡ እንዲያ እሚተጉት፣ እንዲያ በግራሽም በቀኝሽም፣ በጣሪያሽም በወለልሽም ያሰፈሰፉት፣ ያንቺን ጉድለት ስለሻቱ ኣይደለም። የራሳቸውን ሙላት ስለፈለጉ እንጂ ነው። ሙላታቸውም ባንች በኩል እንደሆነ ስላወቁ እንጂ ነው።

ኣዎ፣ ኢትዮጵያዊ ትሁዋኖች፣ ከምልዓተ-ፍጥረት ጋር ያለሽን ስሙር ህብር ያስታውሱሻል። ይህ ውስብስብ ከሆነብሽ፣ ህብር በደም ግብር መጠበቅ ያለበት ካልመሰለሽ፣ ጥበብ ከነፍስሽ ባድማ እንደ ጣዝማ ትደማ ዘንድ፣ "ውበት ምንድነች?" ብለሽ ጠይቂ። በቱማታ (በውጥንቅጥ) ውስጥ ስርዓትን ማየት ኣይደለችምን? "ህብር ምን ትሆን?" ብለሽም ጠይቂ። እኔ በላጭ፣ እኔ ተመራጭ፣ የኔ ህይወት ብቻ ባለዋጋ፣ የኔ ነፍስ ብቻ ባለፀጋ፣ ማለትን ትቶ የጋሪዮሻዊ ስርዓትን መመስረት ኣይደለችምን? "ብቃትስ ምን፣ ቅድስናስ፣ ምንድነች?" ብለሽ ጠይቂ። ፈጣሪ በፀጋው ፍፁም ያደረጋት ሙላት፣ በሌላ ሙላት ኣትፈርስ፣ ኣትደመሰስ እንደሁ ኣውቆ፣ ኣለፍርሃት፣ ኣለስጋት፣ ኣለጥርጣሬ መኖርም ኣይደለች?

ኣድምጪ፣ ያገርሽ እረኛ ባርባ መልካዎችና ጋራዎች፣ ባርባ መስኮችና ሸለቆዎች፣ … ይህንኑ ያዜምልሻል፦

ቱማታን፣ በስርዓት መርታት ውበት ነውና ትርጉሙ፣
መባለጥን በህብር መጥለፍ የኣብሮኛነት ጣዕሙ፣
ሙላት በሙላት እንዳይፈርስ መረዳት ነውና ብቃት፣
ይህን ኣድምጠኝ፤ ሙላት።
(አርባ ጠብታዎች፣ ሙላት 3)
       
ኢትዮጵያዊ ኣይጦች

እነሆ በመጨረሻም ስለ ኢትዮጵያዊ ኣይጦች እምናወራበት ኣምባ ላይ ደረስን።

ከገበሬነት ወደ ወዛደርነት ተሸጋገርሁና (በደረጃ ዕድገት ኣይደለም።) ማተሚያ ቤት ማደር ጀመርሁ። ኣንዳንድ ቀን፣ ከነዚያ፣ የኢትዮጵያን የህትመት ስራ በእግሩ ቆሞ እንዲሄድ ካደረጉ ብርቱ የማተሚያ ሴቶች፣ ጋር። እነሱ ቆመው፣ እኔ ተጋድሜ። ስንፍናዬ! ተኝቼ፣ ተኝቼ፣ ተኝቼ፣ … ስነቃ እማየው ያኝን ሴቶች ነው። እየሰሩ። ኣሁንም ተኝቼ፣ ተኝቼ፣ ተኝቼ፣ ስነቃ፣ እማየው እነሱኑ ነው። እየሰሩ! እንዲያ ቆመው ኣድረው፣ ለሌላ የቁም ውሎ ኣዲስ ቀንን ይቀበላሉ፤ ኑሮ ያጀገናቸው ብርቱ ያበሻ ልጆች።

እነሱ ኣብረውኝ በሌሉ ምሽት ማተሚያ ቤቱን ኣይጦች ይወርሱታል። ተኝቼ ተኝቼ ብድግ ስል፣ ኣፍንጫዬ ጋ ኣንድ ኣይጥ ኣገኛለሁ። ተኝቼ ተኝቼ ብንን ስል፣ ብርድልብሴ ውስጥ ኣይጥ፣ ኣይጦችና ኣይጣት ኣገኛለሁ። ሲሻቸው ህልሜም ውስጥ ገብተው፣ በነፍሴ ውድማ ላይ ሲዳሩ ያድራሉ። በሰላም ኣብረን እንኑር ባልሁ፣ ህልሜን ተዕውኔ፣ ንቃቴን ከቅዠቴ ቀላቀሉብኝ፣ ኢትዮጵያዊ ኣይጦች። እኔን ያጡ ለታ ደሞ፣ ልብሴን ተልትለው፣ መፃፌን ቀርጥፈው፣ ይጠብቁኛል። … በቃ፣ ላጠፋቸው ወሰንኩ።

ለኣይጦች እንጂ ለኛ በማይሰማ ድምፅ ኣስፈራርቶ እሚያባርራቸው፣ በመብራት እሚሰራ መሳሪያ ኣለ፤ መባሉን ሰምቼ ደስ ኣለኝ። ድሮ መርዝና ወጥመድ ነበር እማውቅ። የወጥመዱ ጭካኔ ሲያሳቅቀኝ ነው የኖረ። እነሆ ዛሬ፣ ሳንገድል ድንበራችንን እናስከብር ዘንድ ዘመን መጣ። እውን በሰብዓዊነት እየጀገንን፣ እውን እንደሰው እየሰለጠንን ነው፤ ኣልሁ። ያንን መሳሪያ ግን ፈልጌ ኣጣሁ። ኣማራጭ ጠፋ። መርዝ ተገዛ።

ኣትግደል፤ ይላል መልካሙ መጣፍ፤ ኣውቃለሁ። ኣይጦች እኔን ሊገድሉኝ ሆነ፣ ምን ላድርግ? ቢያንስ ግን ማሳወቅ ኣለብኝ። ትልቁ ሃጥኣት፣ ትልቁ ፍትህ ማጓደል፣ ባላሳወቁት ህግ መቅጣት እነደሆነ ይገባኛልና። ኣውቀው ምርጫቸውን ይውሰዱ ካሻቸው።

መርዙን እነሱ ተሚወዱት ምግብ ለውሼ ሳበቃ፣ እመመገባቸውም እመንገዳቸውም ላይ ኣስቀመጥኩና፣

"ይህ የኣይጥ መርዝ ነው። ይገድላል። ኣይጦች ሆይ፣ ይህን እወቁ!" ብዬ ፃፍኩ፣ ከየመርዙ ኣጠገብ።

በበነጋው፣ መርዙ ተበልቶ ኣገኘሁ። ለጥቂት ወራትም፣ ኣይጦች እዙሪያዬ ኣልታዩም።

ሳያነብቡ ቀርተው ይሆን? ኣልሁ።

ኣይጦች ማንበብ ኣይችሉም፤ እሚል ድምዳሜ ላይ ግን ኣልደረስኩም። ያ ግልብ ማጠቃለያ ይሆንብኛል። ደጋግሜ በቂ ሙከራ ማድረግ ኣለብኝ። ከወራት በሁዋላ የኣይጥ ሰራዊት መመለስ ያዘ። በነሱ ዓለምም ትንሳኤ ታለ፣ ከቀድሞዎቹ ኣይጦች ፃዲቅ ፃዲቆቹም ይኖሩበታል።

በመጀመሪያ ሙከራዬ የፃፍኩት ባማርኛ ነበር። ኣይጦቹ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ቋንቋውም ኣማርኛ። ሰፈሩ ግን ቦሌ ነው። የቦሌ ኣይጦች እንደቦሌ ልጆች ከእንግሊዘኛ በቀር ኣያነብቡ ይሆናል፤ ብዬ ኣሰብሁ። English for New Ethiopia ይል ለነበር መፃፌ ምስጋን ይግባውና፣ ቅልብጭ ባለች የእንግሊዝ ቃል፣ ግልፅ ማስጠንቀቂያ ፃፍኩ፦  

This is Rat Poison. It Kills. Beware, oh Rats!  

ማስጠንቀቂያዬን ከመርዜ ጋር ሰጠሁዋቸው።
ኣሁንም ኣይጦች መርዙን በሉ።
ኣሁንም ለወራት ጠፉ። 

ኣይጦች ማንበብ ኣይችሉም፤ ብዬ ደመደምሁ። ወዲያው ግን ሌላ ሃሳብ መጥቶ ድምዳሜዬን ተፈታተነው፦

"ሙከራህ በኢትዮጵያ ኣይጦች ላይ ነው። ማንበብ ቢችሉም እንደማያነብቡት ያገርህ ሰዎች፣ ኣበሻዊ ኣይጦችም እየቻሉ ኣያነብቡ ይሆናል። ማጠቃለያህ፣ ለዓለም ኣይጦች ሁሉ እንደሚሰራ እንዴት እርግጠኛ ሆንህ? …" እሚል ሃሳብ።

እንግዲህ፣ የሌላ ኣገር ኣይጥ ኢንፖርት ኣድርጌ እንዳልሞክር፤ ያስመጪና ላኪ ፈቃድ የለኝ። ውጭ ሃገር ሄጄ ተመሳሳይ ሙከራ እንዳላደርግ፣ ፈንድ የለም። (ያፈንዳውና ይህ ፈንድ፣ የኢትዮጵያን ሳይንስና ሳይንቲስት ሊያፈነዳ!)

እጄን ኣጣጥፌ ግን ኣልተቀመጥኩም። የሃሳብ ምርምር ማድረግ ጀመርሁ።

ኢትዮጵያ የስብከት ኣገር፣ የተረትም ምድር ናት። እነሆ፣ የተሰበከልንን ደግመን ስንሰብክ፣ የተተረተልንን ደግመን ስንፅፍ፣ የተዘመረልንን ደግመን ስንዘምር፣ … ሺ ዘመናት እንደዋዛ ኣለፉብን፣  የኣይጦቻችንን ያህል’ንኳ ሳያስደነግጡን። እነሆ፣ ኣብዛኞቻችን ልማድ ሆኖብን፣ የውርስ የውርዴ ነገር ሆኖብን፣ በኣበው ትጋት እናቅራራለን፤ በኣበው እውቀት እናውቃለን፤ በኣበው ሚዛን እንፈርዳለን፤ እንጂ በራሳችን መሮና መዶሻ ሰርስረንና ጠርበን ማነፅ፣ በራሳችን እውቀትና ጥበብ ኣንብበና መርምረን መጠበብ፣ በራሳችን ስሜትና ልቦናም መዝነን መፍረድና መቀበል፣ ባህል ማፍረስ፣ ታሪክ መክዳት ሆኖ ይታየናል። እነሆ፣ ብዙዎቻችን፣ በቅኔዎቻችንም፣ በሙዘቃዎቻችንም፣ በትወናዎቻችንም፣ … በቁስላችን ውስጥ እንጨት ከሚሰዱ ፌዞችና ቀልዶች በስተቀር ማድመጥም ማንበብም ዳገት ይሆንብናል። እነሆ፣ "ኢትዮጵያ ውስጥ ብር መደበቅ ከፈለግህ፣ መፅሃፍ ውስጥ ደብቀው፤ ማንም ገልጦት ኣያየውምና።" እያልን ከምርቅዛችን ውስጥ ፅሉም ቀልድ እናመግላለን፤ በውድቀት በውርደታችን እያስካካን እንስቃለን። ያለኣንዳች ሃፍረት! ያለኣንዳች ፀፀት!

ባይገርምሽ፣ ይህ የጠቀስኩልሽ ቀልድ ነው ወደ ሃሳብ ምርምር ያስገባኝ። በሃሳቤ፣ ብዙ የተገለጠ መፅሃፍትን፣ ለብዙ ዘመናት፣ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ሰዎችና ኣይጦች መንገድ ላይ ኣኖርሁ። መፃፍቱን ዞርም ብሎ ያየ ኣላገኘሁም። እያደር ገፆቹ በኣቧራ ተሸፈኑ። እያደርም ቃላቶቹን ትብያም ጥቀርሻም ዋጣቸው። እያደር መፅሃፍቶቹ ተቀበሩ። በቀን ብዛትም በላያቸው ንብርብር ዓለት ተፈጠረ። ኢትዮጵያዊያኑም የተቀበረ ቃላቸውን፣ የተቀበረ ክታባቸውን፣ የተቀበረ ታሪካቸውን፣ የተቀበረ ማንነታቸውን፣ … ተረማምደው ማለፍ ያዙ። … ይህንንም ኣየሁ፦ የነገ ኣርኪዮሎጂስቶች፤ ያኝን ሳይነበቡ የተቀበሩ መፅሃፍት በቁፋሮ ያወጡኣቸዋል። የነገ ኢትዮጵያዊያምንም፤ ደረታቸውን ነፍተው፣ የሰለጠንን ነበርን፤ የሰለጠንንም እንሆናለን፤ እያሉ በጋዜጦቻቸውም በሬዲዮኖቻቸውም ይናገራሉ። …     

"የተቀሰመ ትምህርት በዘር ይተላለፋልን?" የሚል ጥያቄ የተነሳው ተዚህ በሁዋላ ነበር። "እማያነብ ኣባት፣ እማያነብ ልጅ ይወልዳልን?" የሚል። ያኔ ነው፣ ስለነዳርዊን ያሰብኩት። እውን እነሱ እንደሚሉት የተቀሰመ ትምህርት በዘር ኣይተላለፍምን? … ምርምሬ ስለኢትዮጵያዊ ኣይጦች ነበርና፣ ይህንን ከነሱ እሚያገናኝ ጥያቄም ተወለደ፦ የሰው ባህል በኣይጦች ባህል ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላልን? …      

ዳርዊናዊያን ስለኣካላዊ የልውጠት ሂደት ነው እሚያወሩት። ያ እንደምን ውስን ነው! ኣንቺና እኔ ግን ኣፍሪካዊ ፈላሶች ነን። ሰው ስጋና ደም ብቻ እንዳይደለ እናውቃለን። የልቦና ሃይል ከድርጊት ሃይል ይልቅ ብርቱ እንደሆነችም እናውቃለን። ኣፍሪካዊ ፈላሶች ነን፤ ስለ ድግምት እናውቃለን፦ ሰው በቃሉ፣ ሰው በፈቃዱ፣ መጫኛ ያቆማል። ኣፍሪካዊ ፈላሶች ነን፤ ስለ እርግማንም ስለቡራኬም እናውቃለን፦ ሰው በቃሉ ቁጣ፣ በፈቃዱም ፀጋ ያዘንባል። ኣፍሪካዊ ፈላሶች ነን፤ ስለ ቆሌም ስለ ከራማም እናውቃለን፦ ያበው መተላለፍ በልጆች ይወረሳል። ኣፍሪካዊ ፈላሶች ነን፤ ስለታቦትም ስለጠበልም እናውቃለን፦ ቃል ተግዑዝ ውሃም፣ ተግዑዙ ኣለትና እንጨትም ሰርፆ ቅድስና ያኖራል፤ የማድረግ ሃይልን ይከትባል። ኣፍሪካዊ ፈላሶች ነን፤ ስለዝናብ ጌታዎችም፣ ስለፈዋሽ ቃልቻዎችም እናውቃለን፦ ሰው በቃሉ፣ ሰው በፈቃዱ፣ ኣዳኝ ዝናብንም ፈዋሽ መናፍስትንም ይጠራል። …

ዛሬ ታዲያ፣ ይህ ኣዲሳቸው የሆነ የባህር ማዶ ሳይንቲስቶች፣ "የሰው ልቦና፣ የሰው ቃል፣ የውሃ ሞለኪዩሎችን መዋቅር ሊያፈርስም ሊያቀናም እንዲችል ደረስንበት፤" ይሉናል። ምስክርነታቸው፣ ጥንታዊ እውነትሽን፣ ዛሬም እምትኖሪበት ፍልስፍናሽን፣ ይበልጥ እውነት ባያደርገውም፣ ይህ ቃላቸው እውነት ነውና ኣድምጫቸው።

እንግዲህ ለኔና ላንቺ ይህ ግልፅ ነው፦ ፈቃድ ንኪኪም ሳይኖር ይወረሳል። ቃል፣ ቋንቋ ሳይገድበውም ይደመጣል። ምኞት ኣጥር ሳያቆመውም ይጋባል፤ ይተላለፋል። … ታዲያ እነዳርዊን፣ "የሰው ልቦናዊ ቅርስ፣ ካንዱ ወዳንዱ ኣይወረስ፤" እሚሉን እንዴት ነው? ታዲያ፣ "የሰው ባህል፣ የሰው ባህሪይ በኣይጦች ባህልና ባህሪይ ላይ ተፅዕኖ ኣያኖርም፤" እሚሉን እንዴት ነው? ያውም፣ "ሰው ከኣይጥ መጣ፣ ሰው ከዝንጀሮ መጣ፤ …" እያሉን። ያ ቃላቸው እውነት በሆነና፤ ልጅ ያባቱን ጥመት እንዳይወርስ ባሳየሽኝና፣ መላምቴ ፍፁም ስህተት፣ ምርምሬም ድምዳሜዬም ፍፁም ዕብለት፣ እንዳለው በተግባር ባረጋገጥሽልኝና፣ ኣንች የባህልሽና የምድርሽ ፀጋ ተቋዳሽ እንጂ፣ የውስንነቷና የደዌዋ ወራሽ እንዳይደለሽ፣ በሰብዓዊነትሽና በልብ-ኣወቅ ምርጫሽ ከዚያ ፍፁም የላቅሽ፣ ፍፁምም ከፍ ያልሽ እንደሆንሽ፣ በነፍስሽም በስጋሽም ባስመሰከርሽና፣ … እንደምን ደስ ባለኝ! (እዚህጋ፣ ከላይ "ትግሬ፣" ስል፣ "ወላይታ፣" ስል፣ "ኢትዮጵያዊ፣" ስል፣ ምን ማለቴ እንደሁ ግልፅ ይሁን፦ በዚያ ባህል ሙሉዕ ቁሳዊና ኢቁሳዊ ተፅዕኖ ውስጥ ያደገ ሰው፤ ማለቴ ነው። በስጋ ትግሬው ፍፁም በሆነ የወላይታ ባህል ተፅዕኖ ውስጥ ተወልዶ ካደገ፣ ወላይታ ነው። ወላይታው፣ ፍፁም በሆነ የትግሬ ባህል ተፅዕኖ ውስጥ ካደገ፣ ትግሬ ነው። "ፍፁም ንፁህ፣ እሚባል ባህል በሌለበት፣ ፍፁም የሆነ ተፅዕኖ ብሎ ነገር ኣለ ደሞ?" ብለሽ ትጠይቂ ይሆናል። ግሩም ጥይቄ። ያ ግን ማለት የፈለግሁትን ግልፅ ከመሆን እሚያስቀረው ኣይመልለኝም።)

እንግዲህ ይህችን ጥበብ ተልብሽ ኣኑሪና ኑሪባት፦ የፈቃድ ሃይል ከድርጊትም ሃይል እጅግ የበረታች ነችና፣ ፍጥረትሽ ከምልዓተ-ፍጥረቱ ሁሉ ጋር ከምታስቢው በላይ የተሳሰረች ነችና፣ "ኢትዮጵያዊው ዝናብ ወቅቱን ባለመጠበቁ ውስጥ የኔ ድርሻ ምን ይሆን?" ብለሽ ጠይቂ። "ኢትዮጵያዊ ችግኞች፣ መፅደቅ እምቢ በማለታቸው ውስጥ የኔ ድርሻ ምን ይሆን?" ብለሽ ጠይቂ። "ኢትዮጵያዊ ኣለቆች፣ ቃል ነጣቂ፣ ዕምባ ኣፍላቂ፣ ቆሽት ኣድባኝ፣ ራዕይ ኣፋኝ፣ … በመሆናቸው ውስጥ የኔ ድርሻ ምን ይሆን?" ብለሽ ጠይቂ። "በኢትዮጵያዊው ልብ ጥመት፣ በቅናቱም በምቀኝነቱም፣ በልግምተኛነቱም በዳተኛነቱም፣ በዕብሪቱም በንቀቱም፣ … ውስጥ የኔ ድርሻ ምንድን ይሆን?" ብለሽ ጠይቂ።

ተረት መልካም ነች፤ እምነትም ፀጋ ነች። ይሁን፣ ኢትዮጵያ ታላቅ ነበረች፤ ቅድስት ምድርም ነበረች፤ ብለሽ እመኚ። ይሁን፣ ሃይማኖተኛ ነኝ ብለሽም ወደ መስጊድሽም፣ ወደ ቤተክርስቲያንሽም መሄድሽን ቀጥዪ ግን፣ … ፈቃድሽ በመቅደሱም፣ በማህሌቱም፣ በኣጥቢያውም፣ በሰበካውም ኣንድ ይሆን ዘንድ የልቦናሽን ካዝማና ዋልታ በፀዳች ቃል፣ በፀዳች ፈቃድም ኣፅኚ። … ይህንን ያደረግሽ ለታ፣ ኢትዮጵያዊው ምድርና ሰማይ በተውሳክ ሳይሆን በፀጋ ይሞላል። ኢትዮጵያዊቷ ትንኝ የዲያብሎስ ዝየራ ሳይሆን የመላእክትን ዝማሬ ታሰማለች። ኢትዮጵያዊው ንጋትም ሆነ ምሽት፣ በጥፋትና በፍርሃት ኣማጭ ፍጡራን ሳይሆን፣ ተስፋንና ትፍስህትን በሚዘምሩ ኣእዋት ይሞላል። ኢትዮጵያዊ ትሁዋኖች ብሩክ ሽቱ ረጪ፣ ቅብዓ-ቅዱስም ኣምጪ ይሆናሉ። ኢትዮጵያዊ ኣይጦች ህብስትሽንም፣ ብራናሽንም፣ ህልምሽንም፣ ትልምሽንም፣ መቀርጠፉን፤ የማንነትሽን መሰረትም፣ የመሆንሽን ጣሪያም፣ መሰርሰሩን ትተው፤ ቅዱስ ቃሉንና ቃልሽን ማንበብ፣ እንደ ፈቃዱና እንደ ፈቃድሽም መኖር፣ ይጀምራሉ።


ፈቃድ እልብሽ ካለ፣ የመንፃት ኣምባ ሩቅ ኣይደለችምና፣ እምነትሽን ኣፅኚ፤ እግርሽንም ኣንሺ። … እነሆ መንገዱ፣ …