Wednesday, April 16, 2014

ሰማሀኝ? መቀሌም የትውልድ መንደሬ ናት!

“ኣንት ቆሻሻ እንደሆንክ ቢያይም፣ ዝናብ መዝነቡን ኣያቆምም

ያነባሁም ለታ፣
የፈገግሁም ለታ፣
የተበትሁም ለታ፣
ትህትና’ንደጉንጉን የበተንሁም ለታ፣
ጥላቻ ቋጥሬ የታመምኩም ለታ፣
በፍቅር ሰክሬ የዘመርኩም ለታ፣
ይህች ፅጌረዳ፣ መፍካቷን መሽተቷን፣ ኣታቆምም ይሀው። 
እኔም ተፈጥሮዬን፣ ለመኖር ስጀምር፣ ህቅ ይለኛል ምነው?


ጉልቻ እኔ ከመወለዴ በፊትም ጉልቻ ነበር። ስለዚያ እኔ ምንም ማድረግ ኣልችልም። ማድረግ እምችለው ነገር ግን ኣለ። … ይህችን ጥበብ የሰጠችኝ፣ በህይወቴ ውስጥ እንደታላቅ ምሰሶ የቆመች፣ ኣንዲት ሳምንት ነች። ያው፣ እንደሌሎች ሳምንታት ሁሉ ሰባት ቀናት ናቸው ያሏት። ያኝ ቀናት ግን ሰባት የመቅደሴ ኣውታሮች ናቸው። ይህች የህማማት ትዝታዬ፣ ይህች የትንሳኤ ስጦታዬ ነች። እነሆ፦


ሰማሀኝ? መቀሌም የትውልድ መንደሬ ናት!

ህማማት። 1987 ዓመተ-ም.ህ.ረ.ት። ኣዋሳ። ሰባት ወር የዘለቀ ጉዳይ ነበረኝ። የቅጥር ጉዳይ። ያለስራ ዓመት ከጠበቅሁ በሁዋላ ወቅቱ ያቀረበልኝ ኣማራጭ የወረዳ የተፈጥሮ ሃብት ፅ/ቤት ሃላፊ ተብዬ መሎ ወረዳ መውረድ ነበር። እምፈልገው ስራ ነበርና ሹመት ለመቀበል ኣላቅማማሁም። ዓመት ሰራሁ። የዘመኑ ገምጋሚዎች ዓመቴን ኣብጠለጠሉብኝ። እነሱ መናገር የፈለጉትን ተናገሩ። እኔም መናገር ያለብኝን ተናገርሁ። ከዚያ በሁዋላ ኣብረን መቀጠል እንደማንችል ግልፅ ሆነ። በፍቅሩ የጣለኝ ቦታ ነበር። ግን ምንም ማድረግ ኣልቻልኩም። በቃ፣ ሥራ ለቀቅሁ። እነሆ ሰባት ወር። ስንት ከንፈር መምጠጥ ተቋቁሜ፣ ቅጠሩኝ ብዬ ስመላለስ። ህማማት። 1987 ዓመተ-ምህረት፣ ኣዋሳ።

በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኣንድ ክፍል ውስጥ። ከክፍሉ ሃላፊ ፊት ቆሜኣለሁ። እሱ ወንበሩ ላይ ዘና ብሎ ተቀምጧል። ሽቅብ ያየኛል። ቁልቁል ኣየዋለሁ። እኔ እማየው እሱን ብቻ ኣልነበረም። እማየው የተረጋገጠ ተስፋዬንም ነበር። ይህ ሁሉ ምልልስ ዛሬ መቋጫ ያገኛል። ኣቤት፣ ስንቴ ተመላለስኩ! ለቤርጎና ለምግብ ስንት ገንዘብ ኣፈሰስኩ!

ከኔ ጋር ኣንድ ጉዳይ የነበራቸው ብዙ ብጤዎቼ ቅጥር ጨርሰው ስራ ይጀምራሉ። እንዴት እንዳሳኩ እጠይቃቸዋለሁ። ይነግሩኛል።

"እንዲህ’ኮ ማድረግ ነበረብህ! ቀላል ነበር’ኮ ጉዳዩ!"

በእያንዳንዱ መምጣቴ እርግጠኛነት ይዤ ነበር ኣዋሳ እምገኝ። ሳምንት ኣስራ ኣምስት ቀን ቤርጎ ተቀምጬ፣ ቢሮ ተመላልሼ፣ እንኳን ጉዳዬን ማስፈፀም ቀርቶ፣ ኣግኘው የተባልኩትን ሰው ሳላገኘው እመለሳለሁ። ባለስልጣናቱ ላለመገኘት ሁልጊዜም ምክንያት ኣላቸው። ኣንዳንዴ፣ ተሳክቶልኝ ተፈላጊውን ሰው ኣግኝቼና እንደማይሆን ሰምቼ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ማንንም ሳላገኝ ገንዘቤን ጨርሼ እመለሳለሁ። ያኔ ታዲያ፣ መልካም ዜና እሚጠብቁ ቤቶቼን ማየት ሲያስፈራ!

ከኔ በሁዋላ ሌላ ሰው ተቀጥሮ ሲመጣ ኣይና እንደገና እጠይቃለሁ። እንደገናም ይነግሩናል። እንደገናም እሄዳለሁ። እንደገናም ያለፍሬ እመለሳለሁ። ጓደኞቼ ያልነገሩኝ መንገድ እንዳለ ማሰብ የጀመርኩት ቆይቶ ነው።

ተስፋ ኣልቆረጥኩም። ያለው ኣማራጭ ተስፋ ማድረግ ብቻ በሆነበት ሰዓት ተስፋ በዘፈቀደ ኣይቆረጥም። ደግሞም፣ ተስፋ መቁረጥ ብርታት ይጠይቃል ኣንዳንዴ። ልቤ ብርቱ ኣልነበረችም መሰል ያኔ።

እንደገና፣ ወይ በሬዲዮ፣ ወይ በጋዜጣ፣ ወይ በወሬ ኣንድ ተስፋ ያዘለ ነገር እሰማና እሄዳለሁ ወዳዋሳ፤ ወደ ተስፋዋ ምድር። የተዘጋ በር ይገጥመኛል። የተዘጋ ኣንደበት፣ የተዘጋም ልብ ይገጥመኛል። ኣፎች የሚከፈቱት ከንፈር ለመምጠጥ ብቻ ይሆንብኛል። እመለሳለሁ።

ሰባት ወር። ኣሁን ታዲያ እማያጠራጥር ነገር ይዤ ነው የመጣሁት። የዞኑን ሃላፊን እራሱን ኣግኝቼው ነበር ከመምጣቴ በፊት። በስንት ደጅ ፅናት!

"ጥፋቱኮ ያንተ ነው።" ብሎኛል እሱም፤ "የት መሄድ እንዳለብህ እንኳ ኣታውቅም። ዝም ብለህ ጊዜህን ታባክናለህ? ኣትጠይቅም?" ብሎኛል።  

ግልፅ ነው። ይህ ሁሉ ጊዜ የባከነው በራሴ ጥፋት ነው። ደግነቱ፣ በመጨረሻ የት መሄድ እንዳለብኝ፣ ማንን ማናገር እንዳለብኝ ኣውቄኣለሁ። የተባልኩትን ሰው ታላገኘሁ ብዬ ሶስት ቀን ጠብቄኣለሁ። እነሆ፣ ኣሁን እፊቱ ቆሜኣለሁ። ተስፋዬ ግዘፍ ነስቶ፣ ሰው ሆኖ እየታየኝ። "ተስፋ ኣለመቁረጥ እንዴት መልካም ነው!" እያስባለኝ።  

ጉዳዬን ኣብራራሁኝ። የተባልኩትን ተናገርኩኝ። የላከኝንም ኣሳወቅሁኝ። እውነት ነው፣ ይህ ሁሉ ባላስፈለገ። እምጠይቀው ግልፅ ነው። እምጠብቀውም ግልፅ። ዘመኑ ያ መብቴ መሆን ኣለመሆኑን እንድጠራጠር ቢያረገኝም፣ ኣዎ፣ ማብራሪያ እማይሻ ጉዳይ ነው ጉዳዬ።

"ልክ ነህ፤" ብሎ ጀመረ ሰውዬው። "ትክክለኛው ቦታ ነው የመጣሀው። ኣሁን ግን፣ በጀቱ ገና ስላልፀደቀ ኣንድ ሶስት ወር ያህል …"  

ከዚያ በሁዋላ የተናገረውን ኣላስታውስም። የሆነ ታላቅ መበጠስ በውስጤ ተበጠሰ። ተስፋዬ ነበር። ያኔ ልቤ ብርታት እንዳላት ኣወቀች መሰል፤ ተስፋዋን ጧ! ኣድርጋ በጠሰች።  

ለካስ ተስፋ ድንገት ሲቆረጥ ደም ኣይደለም እሚወጣው። ዕምባ ነው ለካስ! የዕምባ መዓት። ኩራትም የለም በዚያ ሰዓት። ተደብቄ ኣነባበት ጓዳ ልፈልግ፣ ብሎ ቅንጦትም የለም በዚያ ሰዓት። "ወንድ ብቻውን ነው እሚያነባ፤" ብሎ ምክር ኣይታወስም በዚያ ሰዓት። ተስፋ ድንገት ሲቆረጥ እንዲያ ነው ለካስ። ጥልቅ በሆነ ዝምታ ውስጥ ዕምባ ግድቡን ይጥሳል ፀጥ ካለ ነፍስ እየተንሿሿ ይወርዳል። የት እንደተቆመም ተረስቶ!   

"በማልቀስ’ኮ እሚሆን ነገር የለም፣" ሲለኝ ይሰማኛል የክፍሉ ሃላፊ።
ስራ እንዲሰጠኝ እማነባ መስሎታል።
"በዕምባ እሚሆን የለም፣ ወዳጄ።"
ዕምባዬ ልመና መስሎታል።
"ዕምባ ምንም መፍትሄ ኣያመጣልህም።"  
ለራሴ እማነባ መስሎታል።

ምናልባት፣ ያነባሁት ለርሱ ነበር። ያነባሁት ለዘመኑ ነበር፣ ምናልባት። ዕምባዬ ምህረት ነበር፣ ምናልባት። በዚያች ሰዓት እያንዳንዱ ሰው ቅድስና እንዳለው ተገልፆልኝ ነበር፣ ምናልባት። እያንዳንዱ ሰው ለቅፅበት ታህልም ራሱን ለዓለም ሃጢዓት እንደሚሰዋ ታይቶኝ ነበር፣ ምናልባት። ዓለም መንፃቷን እምትጎናፀፈው እያንዳንዱ ሰው በሚያዋጣት የዕምባ ጠብታ እንደሆን ተሰምቶኝ ነበር፣ ምናልባት። ዕምባዬ የወረደው የሆነ ያልታወቀ ትንቢት ለማሟላት ነበር፣ ምናልባት። ለዚህ ሁሉ ምንም ማረጋገጫ የለኝም። ይህንን ግን ኣውቃለሁ - ያነባሁት ለራሴ ኣልነበረም።

ይህንንም ኣውቃለሁ - ዕምባዬ ቃል ነበረ። ያ ባለስልጣን የገባውን ያህል ኣነበበ። እኔ የራሴን ኣንደምታ መደረት ኣላሻኝም። ፊቴን ኣዙሬ ከቢሮው ወጣሁ። …       

ሰዎች፣ "ሚስጢር ለሚስጥረኛ ነው እሚነገር፤" ሲሉ እሰማለሁ። እኔ ምስጢረኛዬ ማን እንደሆን እስተዛሬ ሳላውቅ ኣለሁ። ያን ቀን ግን ኣንዲት ሚስጥረኛ ኣግኝቼ ነበር። ኣረፋፈዴን እያሰብሁ ያማረ ሆቴል ውስጥ ሻይ እጠጣለሁ። ምኔ እንደሳባት እንጃ። በምን ወሬ እንደጀመረንም እንጃ። ያስተናገደችኝ ልጅ፣

"ዛሬ ከሰዓት እረፍት ነኝ። ለምን ኣብረን ቤት ኣንሄድም? ቡና ኣፈላልሃለሁ። ከፈለግህም ጫት እንቅማለን።" ኣለችኝ።  

ከዚያች ሰዓት በፊት ተገናኝተን እምናውቅ ኣይመስለኝም። እማላውቀው ሰው ጋር ለመቀራረብ ድፍረት ያለኝ ኣልነበርኩም። ግን፣ ከሰዓት ራሴን እመደቧ ላይ ኣገኘሁት። ያኔ ነው እሷ ምስጢረኛዬ እንደሆነች ያወቅሁት። እና፣ ላደርግ ያሰብኩትን ነገርኳት፦

"ልሄድ ነው። ደቡብን ጥዬ ልሄድ ነው።"
"ወዴት?"
"እንጃ፣ ምናልባት ወደ ኣፋር። ምናልባት ወደ ጋምቤላ። ምናልባትም ወደ ትግራይ።"  

በእውነቱ፣ ለኔ የትኛውም ምንም ልዩነት ኣልነበረውም። እርግጠኛ የሆንኩት ወደ ቤት እንደማልመለስ ብቻ ነው። እዚህ እምጠብቀው ምንድነው? ከዚህ ኣካባቢስ እምለምነው ምንድነው? ብሄድ እሚቀርብኝስ ምንድነው? ያዶላ ወርቅ የኔ ነው?   

ያችን ሚስጥረኛዬን ስሟን እንኳ የጠየቅሁዋት ኣይመስለኝም። ከሳምንት በሁዋላ ደግሜ ባያት ኣላስታውሳት ይሆናል። በሆነ የቅፅበታት መጠላለፍ ልብ ለልብ ተገናኘን። ልብ ለልብ ኣወጋን። እና፣ ተለያየን። ኣሁንም ግን ልቤ ውስጥ ነች። ይሁን፣ … ያ ይበቃል።

በዚያን ቀኑ ተነገወዲያ ታዲስ ኣበባ ወደ መቀሌ የሚሄድ ኣውቶብስ ላይ ተቀምጬ ተገኘሁ። ኤላን ፍለጋ ውስጥ ይህ ቃል ኣለ፦  

"ወደ ኣባያ ነበር መሄድ የነበረበት። እግሮቹ ግን ወደ ጫሞ ይመሩታል። ኣልታገላቸውም። ዝም ብሎ ተከተላቸው። እግር ኣለምክንያት በመንገድ ኣትወስንም። …" (ገፅ 232)

ሁለት ሰው በሚያስቀምጥ ወንበር ላይ ነኝ። በመስተዋቱ በኩል። እጎኔ ኣንድ ተጋዳላይ ተቀምጧል። ኣውቶብሱ ውስጥ ጫጫታ ይጨፍራል። በኔ ውስጥ ግን ዝምታ ነግሷል። ለምን የመቀሌን ትኬት እንደቆረጥኩ ኣስባለሁ። …

ያ የለውጥ ዘመን ነበር። ለምደን የቆየናቸው ነገሮች ሁሉ እንዳልነበሩ ሆነው ነበር። እናያለን ብለን ያላለምናቸውንም ነገሮች ኣየን። የረጋው ጊዜ ድንገት ነው የተናጠው። ከዚያ ውስጥ የወጣው ግን ቅቤ ብቻ ኣልነበረም።

ጓደኞቻችን ተለወጡብን። ጓደኛ ነበሩ። ያም ብዙ ነገር ማለት ነበር። ተለወጡ። ብሔር ሆኑ። ፓሪቲ ሆኑ። ያ መለወጥ ከልባችን ኣንዳች ነገር ቦጭቆ ወሰደ። ኣዲስ የህመም ዓይነት ኣወቅን።

መታወቂያችን ላይ ኣዲስ ቃል እንድንፅፍ ተገደድን። ብሄር። ብሄራችን የቱ እንደሁ ለማወቅ ኣታካች ፍለጋ ያደረግንም ነበርን። የኛ ምርጫ ብቻ በቂ ኣልነበረም። ባካባቢ መወለድ፣ ባካባቢ ማደግ፣ ያካባቢን ቋንቋና ባህል ማወቅ ብቻ በቂ ኣልነበረም። ኣካባቢውን ፍፁም መውደድና ራስን ለዚያ ለመስጠት ማዘጋጀት በቂ ኣልነበረም። ባንድ ክፍል ውስጥ ይማሩ፣ ባንድ ዶርምና ፍራሽ ይተኙ፣ ባንድ መደብ ላይ ይቅሙ፣ ባንድ ኣፍም ይናገሩ፣ … የነበሩ ወዳጆች ብሄር ሆነው፣ ፓሪቲ ሆነው፣ ጩቤ ሲማዘዙ መስክረን ነበር። "እንዴት ራሳቸውን ይህን ያህል ያዋርዳሉ?" ብለንም ፈርደን ነበር። እነሆ ዛሬ፣ ያው የብሄር ጥያቄ በየመታወቂያችን መጣ። እነሆ ዛሬ፣ ያው የብሄር ጥያቄ፣ የሌለ በር ከፋች፣ የተከፈተ በር ዘጊ፣ ሆኖ መጣ። ሌላም ብዙ ቀድሞ እማናውቀው ነገር ሆነ። እና፣ ዘር መርጠን ተቀየምን። ዘር መርጠን ቂም ቋጠርን። …

የለ፣ ያ የተናጠ ጊዜ ቅቤ ብቻ ኣልነበረም ያፈለቀው። 

ልብ ሳልለው፣ በልቤ ዙፋን ላይ ጥላቻ ነግሶ ኣገኘሁት። ድፍን ጥላቻ ነበር። ያ ህመሙን ኣብሶታል። "ለማፍቀር ምክንያት ማግኘት ከባድ ነው፤" እሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ። ለኔ ግን የከበደኝ ለመጥላት ምክንያት ማግኘት ነበር። እምደረድረው ምክንያት ሁሉ በቂ ሆኖ ኣይገኝም። በተለይ ለዚያ ጥላቻዬ ምክንያት ማግኘት ኣቃተኝ። ልቤ ውስጥ ያለውን ኣዝማሚያ ኣውቀዋለሁ። ህዝብን ወደመጥላት እያጋደለ ነው። ወዴት እየወረድኩ ነው? የሰው ዘር ሁሉ ኣፍቃሪ ነበርኩ። በ’ርግጥ፣ ቀድሞ ያን ለራሴ ነግሬ ኣላውቅም። ጎዳና ላይ ወጥቼም፣ "የሰው ዘር ሆይ፣ እወድሃለሁ!" ብዬ ለፍፌም ኣላውቅም። ኣሁን ልቤ ውስጥ ያለው ህመም እሚነግረኝ ኣንድ እውነት ኣለ። ያ ተፈጥሮዬ ኣይደለም። ጥላቻ ከቶም ተፈጥሮዬ ኣይደለም። በተለይ ህዝብን መጥላት። ግለሰቦች መጥፎ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዴት ኣንድ ህዝብ መጥፎ ሊሆን ይችላል? እንዴት በህዝብ ላይ ቂም ይያዛል? …

እና፣ በዚያች ጥዋት፣ በዚያ ኣውቶብስ ውስጥ ሆኜ፣ በጫጫታ በታጀበው ዝምታዬ ውስጥ ኣድፍጬ፣ ይህንን ኣስባለሁ።

ሌሎች ነገሮችንም ኣስባለሁ። ከኮሌጅ እንደወጣሁ ለራሴ የመቶ ሃያ ዓመት ዕቅድ ነድፌ ነበር። እዚያ ውስጥ ለኣራት ለኣምስት ዓመታት ገዳም ገብቶም የገዳምን ህይወት ማየት፣ ትምህርቱንም መቅሰምም ኣለበት። ያ ዕቅዴ ኣሁን ባሰብኩት መንገድ እየሄደ ኣይደለም። ትግራይ የገዳማት ምድር ነው። ቋንቋውም ለግዕዝ ቅርብ ነው። ምናልባት የመቀሌን ትኬት ባስቆረጠኝ ምክንያት ውስጥ ያም ምክንያት ይኖራል። 

ህይወት የራሷ ፈለግ ኣላት። የኤላን ፍለጋው ኩሴ፣ "ያለምክንያት እግር በመንገድ ኣትሰለጥንም፤" ያለው ያንን እያሰበ ይሆናል። ህይወት ለምን ባንድ ኣቅጣጫ እንደመራችን ሺ ምክንያቶች መደርደር እንችል ይሆናል። ነገር ግን፣ ሁል ጊዜም እኛ እማናውቃቸው ሌሎች ሺ ምክንያቶች ይኖራሉ። በዚያ ጉዞዬ ውስጥ፣ "ይህን የትግራይ ህዝብ ቀርቤ ማወቅ፣ ቀርቤ መረዳት ኣለብኝ፤" የሚል ዓይነት ምክንያት ደምቆ ይሰማኝ እንደነበር ኣስታውሳለሁ። በልቤ ጥልቀት ድምፃቸውን ኣጥፍተው የተደበቁ ምክንያቶች የቶቹ ይሆኑ? …   

ልቤ ውስጥ ታላቅ ደስታ ነበር። ድፍን ፍርዴን ለመስበር ኣንድ እርምጃ ወስጃለሁ። ያ ከወዲሁ የነፃነት ስሜት ኣጎናፅፎኛል። እጎኔ ያለው ተጋዳላይ ደግሞ ብዙ ነገር ያወራኛል። ልብ ለልብ ለመነጋገር ረጅም ጊዜ ኣልወሰደብንም። ከተራመድኩት የከረምኩትን ኣንድ መንገድ ዳግም እየተራመድኩ ነበር። ሰዎችን እንደግለሰብ የመቅረብ መንገድ። እንደግለሰብም ስሜቴን ገልጬ ስሜታቸውን የማድመጥ መንገድ። እዚያ ውስጥ የሆነ ተፈጥሮኣዊ፣ የሆነ ትክክል ነገር ኣለ። በዛፎች በተሰመረ የእግር መንገድ ላይ በእርካታ የመራመድ ያህል ነው። ስሜት ውሃልኩን ሲያገኝ ይታወቃል። 

የመቀሌ መንገድ ሁለትና ሶስት ቀን ነበር የሚፈጀው ያኔ። ለመተዋወቅ ሰፊ ዕድል ኣለ። ዙሪያዬ ብዙ ሰዎችን ኣወቅሁ። ኣባቶች እንደ ኣባት፣ እናቶች እንደ እናት፣ ወጣቶችም እንደ እህትና ወንድም ይቀርቡኛል። እዚያ ውስጥ ምንም ማስመሰል የለበትም። ተጋዳላዩ እሚያወራኝ ታሪኩ ውስጥም ምንም ማስመሰል የለበትም። በእምነት ኣንድ ኣይደለንም። በታመምንለት፣ በደማንለትም ምክንያት ኣንድ ኣይደለንም። በየተቀበልነው ህማም ጥልቀትም ኣንድ ኣይደለንም። ሁለታችንም ግን ኣንድ የሆኑትን ያኝን ሰብዓዊ ስሜቶች እናውቃቸዋለን። ቢያንስ በዚያ ኣንድ ነን። ያ በመሃከላችን የሚፈጥረው ድልድይ ሰፊ ነው። ጎን ለጎን በነፃነትና በወንድማማችነት ስሜት ልንራመደው እንችላለን።

ያ ተጋዳላይ ለኔ ግለሰብ ነበር። የለም፣ ፓሪቲ ኣይደለም። የለም፣ ብሄር ኣይደለም። እሱ፣ ከሆነ ከማያውቀው ሰው ጋር፣ ኣንድ ተራ ጉዞ ተጓዘ። ለኔ ግን፣ ታላቅ መንቃትን ሰጠኝ። ካውቶቡሱ ስንወርድ ተለያየን። ስሙንም፣ መልኩንም ኣላስታውስም። ትዝታው ግን ከነፍሴ ተሸምኖ ይኖራል።      

ረፋድ ከሰዓት ላይ ነው መቀሌ የደረስነው። ከቤት ወደ ኣዋሳ የወጣሁት ላጭር ቀን ነበር። ኣንድም የተረጋገጠውን የስራ ዕድል ወዲያው እንደምጨርስ ስለገመትኩ። በተጨማሪም፣ የበዓል ወቅት ስለሆነ በዓሉን ቤት ተመልሼ እንደማከብር ስለታሰበ። የያዝኩት ገንዘብም ብዙ ኣልነበረም። ኣዋሳ ላይ ሶስት ቀን፣ ኣዲስ ኣበባ ኣንድ ቀን ኣድሬኣለሁ። ትኬት ለመቁረጥ ስሄድ ዘጠና ብር ነበር በእጄ። ለትኬት ስልሳ ብር ከፈልኩ። ሰላሳ ብር ቀረኝ። እመንገድ ላይ ምን በልቼ፣ እንዴት እንዳደርኩት ኣሁን ኣላስታውስም። ወይ ከሹፌሮች ጋር፤ ወይ ባምስትና በስድስት ብር ማደሪያና ምግብ ኣግኝቼ ነበር። መቀሌ ስገባ ሃያ ኣራት ብር እጄ ውስጥ ነበር። ይህ ግን፣ ምንም ስጋት ኣላሳደረብኝም።

መቀሌን ስረግጥ በሁለቱ የጉዞ ቀናቴ ይሰማኝ የነበረው ሃሴት ጉልላቱ ላይ ደርሶ ነበር። ይህች ወደ ነፃነት የወሰድኳት ትንሽዬ እርምጃ ናት። ለልቤ ያመጣችው ሃሴት ግን ከስፍር በላይ ነበር። ከረጅም መለየት በሁዋላ ኣገሬ የተመለስኩ ነበር የመሰለኝ። እንዲያውም በሰፈሬና በመንደሬ ያለሁ። ኣንድ እማቀውን ሰው ድንገት ባገኝ፣ በሩቁ ብቻ እጄን ኣውለብልቤ እማልፍ። በቃ፣ እዚያው፣ በቦታዬ የተገኘሁ። ሰዎችም ሁሉ እማውቃቸው፣ ነበር የመሰለኝ። ያን ስሜት መቼም ድጋሚ እማገኘው ኣይመስለኝም። ምናልባት ስሞት እንደገና እኖረው ይሆናል። ነፍሳችን እምትመኘውን ደጋግማ መኖር ትችላለች ኣሉ ስንሞት።

እኔ ከመወለዴ በፊትም ጉልቻ ጉልቻ ነበር። ከሞትኩ በሁዋላም ጉልቻ መሆኑን ይቀጥል ይሆናል። እኔ በዚያ ምርጫ የለኝም። ይህንን ግን መምረጥ እችላለሁ፦ መቀሌም ምድሬ፣ መቀሌም መንደሬ ናት። 

ቤርጎ ሳይሆን በመኖሪያ ቤት ውስጥ ለተደረደሩ ኣልጋዎች ስድስት ብር ከፍዬ ኣደርኩ። ያ ቅንጦት ነው በ’ርግጥ። ግን፣ ከተማዋን ተዟዙሬ እስከማያት እንዳደረግሁት መስዋዕትነት ነው የቆጠርኩት። ማምሻውን በቀጣዮቹ ቀናት ማደሪያ የሚሆነኝን ቦታም ኣገኘሁ። እራት ኣንድ ሁለት ብር ሳያነሳብኝ ኣልቀረም። ምን ይደረግ!

በበነጋው በጠዋት ተነስቼ የሄድኩት መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ነበር። ያን እማላውቀውን መንገድ ስጓዝ በልቤ ኣንድ ሰው ነበሩ፦ ዶክተር ምትኩ። የዓለማያ ኣስተማሪዬ ነበሩ። ያኔ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት። ተራ የተማሪና ያስተማሪ ግንኙነት ነበረን። ቢያዩኝ እሚያስታውሱኝም ኣልመሰለኝም። ቢሆንም፣ እማውቀው ኣንድም ነፍስ በሌለበት ምድር ያች ትንሽ መተዋወቅ ወደ’ሳቸው ልትስበኝ ብርታት ነበራት።

እዩኒቨርሲቲው በር ደርሼ ዘበኛውን ኣናገርሁት፦  
"ኣዎ፣ እዚህ ናቸው።" ኣለኝ። "ዛሬ ያው ስራ ስለማይገቡ፣ ነገ መጥተህ ልታገኛቸው ትችላለህ።"
"ዛሬ ለምንድነው ሥራ እማይገቡት?"
"ዛሬ ሰንበት ኣይደል?"

ገረመኝ። ቀኑን እንኳ ረስቼዋለሁ። በጉዞ ብዛት ቀኑ እንደጠፋብኝ ነግሬው፣ ኣመስግኜው መንገድ ስጀምር፣ "በጭራሽ!" ኣለኝ ዘበኛው። "ይህን ያህል ተጉዘህ መጥተህማ ሳታገኛቸው ኣትሄድም። መኖሪያ ቤታቸው እዚሁ ግቢ ውስጥ ነው። እቤታቸው እወስድህና ኣግኝተሃቸው ሂድ።"

ላብራራለት ሞከርኩ፦ የመጣሁት በራሴ ምክንያት ነው። እሳቸው ጭራሹኑ ላያውቁኝም ይችላሉ።እንዲሁ ላገኛቸው ፈለግሁ እንጂ ጉዳዬም ከሳቸው ጋር ኣይገናኝም። …

እምቢ ኣለ ግን እሱ። ሁኔታው ትህትና ውስጥ ኣስገባኝ። እየከበደኝ ለሱ ብዬ በጅ ኣልሁ። ይዞኝ ሄደ ቤታቸው። እዚያም ተመሳሳይ ነገር ገጠመኝ። በሩን የከፈተችልን ሴት ዶ/ር ምትኩ እቤት እናዳሉ፣ ግን እንደተኙ ነገረችን። ልመለስ ስል፣ በጭራሽ! ኣለች እሷም በተራዋ። ለሷም ሁኔታውን ማብራራት ኣላዳነኝም። እንደገና እየከበደኝ እሽ ኣልኩኝ። ገባሁና ተቀሰቀሱ።

"ዓለማያ ነበርክ ኣይደል?" ኣሉኝ እንዳዩኝ። ስላስታወሱኝ ደስ ኣለኝ። ጉዳዬን ሰምተው ሲያበቁ፣
"ቃል እምገባልህ የተዘጋጀ ነገር የለም። ነገ መመለስ ከቻልክ ግን የተወሰኑ ቦታዎች ደዋውዬ ልጠይቅልህ እችላለሁ። ትግራይ ሁሉም ሰው በሰላም ሰርቶ እሚኖርበት ቦታ ነው። ጠንካራ ሰራተኛ እስከሆንክ ድረስ እሚያገኝህ ክፉ ነገር ኣይኖርም።"

ቃላቸው ብቻ ኣይደለም ተስፋ የሰጠኝ። በተለይ፣ ተጀምሮ እስቲጨረስ የተስተናገድሁበት የወዳኝነትና የፍቅር ስሜት ነው። በሳቸው ብቻ ሳይሆን በገጠሙኝ ሰዎች ሁሉ። ስመለስ፣ "በእውነቱ፣ ምድሬ ይህች ነች።" እያልኩ ነበር።

መሸና ወዳዲሱ ማደሪያዬ ሄድኩ። ሚካኤል ቤተክርስቲያን በረንዳ ላይ ነበር። ሽርጤን ተከናንቤ ተጠቅልዬ ተኝቻለሁ። ሌሊት ላይ፣ ሁለት ሰዎች ቀሰቀሱኝ - ኣንድ ኣዛውንትና ኣንድ ልጅ።

"ማነህ? … እዚህ ምን ኣመጣህ?" ኣሉኝ።

ነገርኳቸው። ግን፣ ስለማንነቴ ምንም ማስረጃ ኣልነበረኝም። መታወቂያ ኣልነበረኝም። ጊዜያዊ ዲፕሎማ ብቻ። ያ ደሞ ፎቶ የለው፣ ምን የለው። መጠየቄ ኣናደደኝ፣ እኔ። ግንፍል ብዬ፣

"ለምንድነው እምትመረምሩኝ? ይህ የእግዚኣብሔር ቤት ኣይደል’ንዴ? ማንኛውም መንገደኛ ሊያድርበት ኣይችልም?"

ረጋ ብለው ሁኔታውን ሊያብራሩልኝ ሞከሩ። ይህ እንደ መሃል ሃገር ኣይደለም። ብዙ ነገሮች ኣልፈዋል በዚህ ክልል ውስጥ። ያልታሰቡ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ለክፋት ኣይደለም የጠየቁኝ። … ቀስ በቀስ ተረጋጋሁ። ቀስ በቀስ ተግባባን። በመጨረሻም፣ እደወል ቤት ውስጥ ገብቼ ከልጁ ጋር እንዳድርም ፈቀዱልኝ። ካርባምንጭ ለመጣ ሰው መቀሌ ብርዳም ነው። ልጁ የራሱን ኣንሶላ ደረበልኝ። ሰላማዊ ምሽት ኣሳለፍኩ። ያ ልጅ እማላውቀው ወንድሜ ነበር። ኣወቅሁት ያኔ።

ሰኞ ዕለት እንደታሰበው ዶ/ር ምትኩን ኣገኘሁዋቸውና የተወሰኑ ቦታዎች ደዋውለው የት የት መሄድ እንዳለብኝ ነገሩኝ። የዚያኑ ዕለት ኣምስት የቢሮ ሃላፊዎችን ኣገኘሁ። ያ ኣዋሳ ሰባት ወር ተመላልሼ ካገኘሁት የሃላፊ ቁጥር ይበልጥ ነበር። ምን ዓይነት ልዩነት ነው? እሚያስገርመው ቁጥሩ ብቻ ኣይደለም። ግንኙነቱ ሌጣ ግንኙነት ኣልነበረም። በቀና ስሜት የተሞላ ነበር። ኣንድ ምሳሌ ይህንን ያሳይልኛል፦

ሳርት ወደተባለ ኣዲስ መስሪያ ቤት ሄድኩኝ። (ያ ሁዋላ ለሶስት ዓመታት የሰራሁበት መስሪያ ቤት ነው።) ያገኘኝ ልጅ (ገብረመድህን) እንዲህ ኣለኝ፦

"ሃላፊው ኣሁን የለም። ለጥቂት ሳምንታት ኣይመለስ ይሆናል። ኣዲስ የጥናት ቡድን እያዋቀርን ባንተ ሞያ ብቻ ሰው ጎድሎን ነበር። ጥሩ ጊዜ ነው የመጣሀው። የሚወስነው ግን እሱ ስለሆነ የማስረጃህን ፎቶኮፒ ኣስገባና ካንድ ከሁለት ሳምንት በሁዋላ ተመለስ።"

ኣንድ ሁለት ሳምንት ለመቆየት ምንም ነገር የለኝም። እየጠየቅሁት ያለሁት በሙያዬ ለመስራት ኣይደለም። ማንኛውንም የቀን ስራ ነው። እነሱ የግድብ ስራ ስለሚሰሩ ለኔ የሚሆን የቀን ስራ እንደማያጣ እርግጠኛ ነበርኩ። ያን ስነግረው ፊቱ ሲለዋወጥ ታየኝ፣ ገብረመድህን። ዓይኖቹ ደመና ሲለብሱ፣ ዕምባ ሲያፈልቁም ታየኝ። የሱ ዕምባዎች ከኔም ዓይኖች የዕምባ ጨሌዎችን ፈነቀሉ።

ይህ ኣስገራሚ ነገር ነው። ከዚህ ቀደምም የቀን ስራ ጠይቄ ኣልተሳካልኝም። እኔና ጓደኛዬ፣ ተሾመ፣ ያለስራ መቀመጥ ቢያሰለቸን ወደ ኣዋሽ ጥጥ ለቀማ ለመሄድ ወሰንን። ያኔ፣ ኣርባምንጭ ላይ ምዝገባ ነበር። እኛ ግን ሲሌ-ወራ-ጋሞ በተባለው ጣቢያ ላይ ለመመዝገብ መከርን። ኣርባምንጭ የሚያውቀን ሰው ብዙ ስለሚሆን። ስሌ ላይም እኔን እሚያቁኝ ሰዎች ብዙ ሊሆኑ ስለሚችሉ ተሾመ ሄዶ ሁለታችንንም እንዲያስመዘግብ ተስማማንና ሄደ። ማታ ሳይመዘገብ ተመለሰ። "ለምን?" ብለው፣

"እምቢ ኣሉኝ ባክህ። እያሾፍክብን ነው፤ ኣሉኝ። ኣንተን የመሰለ ሰው እንዴት ቀን ስራ ይሰራል? ኣሉኝ። ብለምናቸው ጭራሹኑ ተናድደው ኣስወጡኝ።"

እግዚኣብሔር ይመስገን ብርቱ ኣካል ኣለኝ። እግዚኣብሔር ይመስገን እማይሞት ተስፋ ኣለኝ። እግዚኣብሔር ይመስከን ሆዴ በንፍሮም በዶሮም እኩል ይሞላል። እና፣ ኑሮዬን ከሸለቆ ውስጥም፣ ከተራራ ላይም ከመጀመር እሚያግደኝ ምን ነገር ኣለ? ያን ግን ያኝ ሰዎች ኣልተረዱም። ትክክሉ እነሱ እሚያስቡት ብቻ እንደሆነ ኣመኑና ያችንም ዕድል ከለከሉን። ወደ መቀሌ ስመጣ ማንኛውንም ስራ ሰርቼ ህይወቴን እንደማቀና ኣምኜ ነበር። እነሆ፣ ያው ጥያቄዬ ሌላ ዓይነት የስሜት ክር ነካ።  

(ያ ኣንብቶ ያስነባኝ ልጅ፣ ያኔ ኮሞሮስ ደሴት ውስጥ በወደቀው ኣውሮፕላናችን ህይወቱ ኣልፏል። ያን ኣደጋ ባሰብኩት ቁጥር ኣስበውና፣ "በዚያ ውስጥ ቢያንስ ኣንድ ደግ ሰው ነበር፤" እላለሁ።) 

በዚያኑ ቀን የግብርና ቢሮ የሁለት መቶ ኣርባ ብር ጊዜያዊ ስራ ሰጠኝ። የቢሮ ሃላፊው ኣቶ ብርሃነ በዚያው በትህትና በተሞላ የደግነትና የወዳጅነት ስሜት ነበር ያስተናገዱኝ። ያም ሆነ ግዜያዊ ቅጥሬ ከጠየቅሁት በላይ ነበር። ከዚያ በሁዋላ የሆነው ሁሉ ታሪክ ብቻ ነው።  

እንግዲህ ይህ ሁሉ የሆነው በኣንድ ሳምንት ውስጥ ነበር። ሰኞ ኣዋሳ ገባሁ። በሚቀጥለው ሰኞ መቀሌ ላይ ስራ ኣገኘሁ። ያገኘሁት ስራ ብቻም ኣልነበረም። በነዚያ ሰባት ቀናት ብዙ ነገሮች ሆኑ። ብዙ ዓይነት ሰዎችም ገጠሙኝ። በመንገዴ ያገኘሁዋቸው ያኝ ሰዎች ሁሉ ግለሰቦች ነበሩ። ፓሪቲ ኣይደሉም። ዘር ኣይደሉም። ግለሰቦች። ግንኙነታችንም በግል ደረጃ ነበር። በዚያ ደረጃ ፍቅር ሰጥተን ፍቅር መቀበል እንደምንችል ኣስታወሱኝ። ያ ወደዘነጋሁት ተረት ኣነቃኝ። ያ ወደ ተፈጥሮዬ መለሰኝ። ያ በሰው ልጅ ላይ የነበረኝን እምነት ኣፀናልኝ። ሰባት የህማማትና የትንሳኤ ቀናት። ኣዳኝ!    

ደቡብ ላይ የገጠሙኝን ባለስልጣናትም የተገናኘሁት በግል ደረጃ ነበር። እነሱም ያንኑ ደግነት፣ ያንኑ የወዳጅነትና የፍቅር ስሜት ሊያሳዩኝ ምርጫ ነበራቸው። በሆነ ምክንያት ያንን ሊያደርጉ ኣልቻሉም። ያ ግን ሰብዓዊነቱ እውስጣቸው የለም ማለት ኣይደለም። እንዲህ ያለው ስሜት ኣንድ ቦታ ተፈብርኮ በፓርቲ የሚታደል እንዳይደለ ኣውቃለሁ። ያሳደገኝ ተረት እንደሰው ምን ያህል የተሳሰርን እንደሆንን ነው ሲነግረኝ የኖረው። ያ የተናጠ ጊዜ ያንን ተረታችንን ኣስረሳን መሰል፣ በግዜያዊ ስሜት ያን ልንቁስ የድር ህብር በጣጠስነው መሰል፣ በምትኩ የፈጠርነው ኣዲስ ተረታችን ሊያስተሳስረን ጉልበት ኣጣ መሰል፣ በልባችንም በቃላችንም መቃቃር ደምቆ ተሰማ። ሃይማኖታችን ኣንድ ሊያደርገን ጉልበት ኣጣ። ሃገርም ኣንድ ልታደርገን ጉልበት ኣጣች። ሰው መሆንም ኣንድ ሊያደርገን ጉልበት ኣጣ።  

ያ የህማማት ገጠመኜ፣ ይህ የዝንጋዔ ዘመን ሊነጥቀኝ ከነበር ከዚያ ጥንታዊ የተረት ማህፀን፣ እንደገና ኣዋለደኝ። ቦታው ደግሞ መቀሌ ነበር። እና፣ ባልተፈጠረና ባልተፈጠርኩለት ኣጥርና ድንበር ደልድሎኝ፣ ያለተፈጥሮዬ እንድኖር የሚሰብከኝን የዘመኔን ጎበዝ እንዲህ እለዋለሁ፦ "ሰማሀኝ? መቀሌምኮ የትውልድ መንደሬ ነች!"

በቅርቡ ኣውስትራሊያ ደርሶ የተመለሰ ወዳጄ የገጠመውን ነገረኝ። የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ነው ልጁ። ቤተ-ክርስቲያን መሄድ ፈለገና ጠየቀ። ጓደኞቹ፣ ጥያቄውን በጥያቄ መለሱለት፦   

"ወደየትኛው ነው መሄድ እምትፈልግ? ወዳማራ ኦርቶዶክስ? ወደትግሬ ኦርቶዶክስ? ወይስ ወደኦሮሞ ኦርቶዶክስ?"  

"በዚህ ዘመን እንዲህ ባለ የክፍፍል ኣረንቋ ውስጥ መዘፈቅ ኣያሳዝንም?" ኣለኝ ወዳጄ።

እኔ ታዲያ፣ ይህ ወገኔ፣ ይህ ዘመኔ፣ የገባበትን እንዲህ ያለውን ነገር ሳስብ ሁሌ እምጠይቀው፣ "ሰውን በግል ደረጃ፣ በሰውነቱ ብቻ፣ እሚቀርቡበትን ኣጋጣሚ ሳያገኙ ቀርተው ይሆን?" እያልኩ ነው።

እርግጥ ነው፣ ያ ኣይሆንም። ይህ የቡራኬ ዘመን ነው። የፈጣሪ ችሮታ ከየትኛውም ዘመን ኣብልጦ የዘነበበት ዘመን ነው ይህ። እንኳን የራስን ወገን፣ እንኳን የራስ ሃይማኖትን ምዕመን ለመቅረብና ለማወቅ ቀርቶ፣ ከሺ ኣድማስና ከሺ ምዕራፍ ርቆ ያለን ነፍስ ልብ ለልብ ለማውጋት የነበረውን ገደብ በሙሉ ማለት ይቻላል ኣንስቶልናል ዘመኑ። እና፣ … በዚህ በተቀደሰው ዘመኔ ውስጥ፣ ይህ ወገኔ ምን ነካው? ያውም ኣውስትራሊያን፣ ያውም ኣውሮጳን፣ ያውም ኣሜሪካን በመሰለ ቦታ እሚኖረው ይህ ወገኔ ምን ነካው?

ኣንዲት ኣፍሪካዊት ኣባባልም ትታወሰኛለች ደሞ፦
"ኣንት ቆሻሻ እንደሆንክ ቢያይም፣ ዝናብ መዝነቡን ኣያቆምም።"
ይህ የፈጣሪ ቸርነት ነው። እኔ ምን ፅልመትን ብመርጥ ፀሃይ መውጣቷን ኣታቆምም። እኔ ምን ጥላቻን ባራግብ፣ ኣእዋፍት መዘመራቸውን ኣያቆሙም። እኔ ምን ኣፍንጫዬን ብይዝ፣ ፅገሬዳ መዓዛዋን መናኘት ኣታቆምም። ይህ የፈጣሪ፣ ይህ የተፈጥሮ ደግነት ነው።

ደግሞ ይህንን ኣውቃለሁ፦ ከፀሃይም፣ ከኣእዋፍትም፣ ከፅገሬዳም የከበርኩ የእግዜር ስራ ነኝ፣ እኔ። የፍጥረት ሁሉ ቁጨት ነኝ እኔ።   

ትርጉሙ፣
የፍጥረት ቁጨቱ
በኔ ላይ ካረፈ።
እንዳይተረተር፣
ከርሬ ልቋጠር።         ኣርባ ጠብታዎች፣ ቁጨት፣ ገፅ 24

የፍጥረተ-ዓለም ትርጉምና ቁጨት የሆንኩት እኔ፣ ይህንን ብኩርናዬን የሁዋሊት ጥዬ፣ በርክሰት ውስጥ ለመኖር እንደምን እመርጣለሁ? ያውም በዚህ የፈጣሪ በረከት ያለከልካይ በሚወርድልኝ፣ ያለ ዳኛ፣ ያለእረኛ በሚታደለኝ ዘመን! … ድሮ፣ ድሮ፣ ለጥፋት ዘንቦ ነበር ኣሉ ዝናቡ። ኣሁን ግን ያ ዝናብ (እውነት እንበለው እውቀት፣ ሳይንስ እንበለው ቴክኖሎጂ) እሚዘንበው ሊያጠፋኝ ሳይሆን ሊያነፃኝ እንደሆን ኣውቃለሁ። መንፃት ምርጫ ነውና እኔ እምቢኝ እል ይሆናል። ዝናቡ ግን መዝነቡን ኣያቆምም። ፈጣሪ፣ በኔ እምቢታ፣ ፍጥረትን ሁሉ ኣይቀጣምና። እኔ፣ ምን በሃጥዓት፣ ምን በኣመፃ ብኖር፣ በውስጤ ያለውን መልካምነትም ኣያጠፋም እርሱ። እውስጤ ያኖረውን የራሱን እስትንፋስ ይወዳልና እርሱ። ያን የእርሱን ብርሃን ከኔ ብቻ ውስጥ እንኳ ቢያጠፋ የፍጥረቱ ቁጨት ይበተን፣ የነበረውም እንዳልነበር ይሆናልና። እሱ እያንዳንዱን ፍጡሩን በሃያል ጥበቡ ከሌላ ከየትኛውም የፍጥረቱ ቤተሰብ ጋር በስውር ህብር ኣስተሳስሮ መስርቷልና። ኣዎ፣ በከበበኝ ጥቀርሻ ብርሃኔ ምን ቢደበዝዝ፣ እኔ በእርሱ በኩል ሁሌም እምንጨለጨል ጧፍ ነኝ። ኣያጠፋኝም!

ኣበቦች ኣብበው ሳይ፣ ኣዕዋፍት ሲዘምሩ ሳደምጥ፣ ፋፋቴ ሲንሿሿ ስሰማ፣ የጥቁር ኣፈር ሽታ ባፍንጫዬ ሲገባ፣ ፈገግ እላለሁ። ይህችን ታህል መልካምነት ሁልጊዜም እውስጤ ኣለች። ለፍጥረት እማልነፍገውን ፈገግታ ለወንድሜ ከቶም ኣልነፍግም። የትኛውም ሰው፣ በየትኛውም ቦታና ጊዜ፣ ያችን ታህል ብጣቂ መልካምነት ሊያደርግ እንደሚችልም ኣውቃለሁ። እኔ፣ እማልከስም ብርሃን ነኝ። እሱም እማይከስም ብርሃን ነው። እኔ፣ የህይወት ኣጋጣሚዎች ኣሸንፈውኝ፣ ዛሬ ክፉ መስዬ እታይ ይሆናል። ነገም ስቆጣ፣ ሳማና ሳደማ እገኝ ይሆናል። በውስጤ ግን፣ በነፍሴና በልቤ ግን፣ ጥሩ ሰው፣ ብሩክ ሰው ነኝ እኔ።

ፊቶች ይረሳሉ። ቆይቶ፣ ያኔ፣ በዚያ የመቀሌ ምካኤል የደወል ቤት ውስጥ፣ ኣንሶላውን ያዋሰኝን ልጅ መቀሌ ኣየር-ማረፊያ ኣገኘሁት። ኣድጎ ነበርና ኣላወቅሁትም። እሱ ግን ኣወቀኝ። መናገር የተሳነው ነው ልጁ። በምልክት ቋንቋ ማንነቱን ኣብራራልኝ። ማንነቴንም ነበር የነገረኝ። ኣስታወስኩት። ኣዎ፣ ዛሬ በመንገዴ እሚገጥሙኝን ነገ እንደዚያ ልጅ፣ እንደዚያች ምስጢረኛዬ፣ እንደዚያ ተጋዳላይ፣ … እረሳቸው ይሆናል። በእውነቱ፣ ያችን ደግነት የሰራልኝ ቀጥሎ መንገዴን እሚያቋርጥ ማንኛውም ሰው ሊሆን ይችላል። እና፣ ፊት ማስታወስ፣ ስም መጥራት፣ ምን ይበጀኛል? እና፣ ሃይማኖት መለየት፣ ዘር መቁጠር ምን ይበጀኛል? እና፣ ፓርቲ መሸንሸን ሃብት ማስመዘን ምን ይበጃል? … ሳገኘው፣ ያገኘሁት ሰውነቱንም ሰውነቴንም እንደሁ ማሰብ ኣይበቃኝም? ከየትኛውም ዓይነት ኣንድነት ያ ኣይጠነክርም? ከየትኛም ዓይነት የመለያየት ምክንያት ያ ኣይጠነክርም?   


እውነት ተብለው በምድር የተነዙ ብዙ እውቀቶች ኣሉ። የእኛን ምርጫ ሳይጠይቁ፣ ተሰርተውና ተወስነው የቆዩንና የሚቆዩን ብዙ ነገሮች ኣሉ። ጉልቻ እኔ ከመፈጠሬ በፊትም ጉልቻ ነበር። ስለዚያ እኔ ምንም ማድረግ ኣልችልም። ይህንን ግን እችላለሁ፦ እኔ ከእምነትም መርጬ ኣምናለሁ። ከእውቀትም መርጬ ኣውቃለሁ። ከቃልም መርጬ እናገራለሁ። በመንገዴ በሚገጥመኝ ብጤዬ ሁሉ ውስጥም ራሴው ውስጥ ያለውን እማይከስም መልካምነት ለማየት እተጋለሁ። ኣዎ፣ እማይከስም። ይህ ተስፋ ብቻ ኣይደለም። ይህ እውቀት ነው። ይህ እውነት ነው። በልቤ መዳፍ ውስጥ ጨብጬ የያዝኳትን ይህችን ብጣቂ እውነት ሊነጥቀኝ የሚችል ማንም የለም። መ.ቼ.ም!  

Friday, April 4, 2014

እማይገባኝ የሰውነትና የኢትዮጵያዊነት ዕዳ

የግለሰብ እንጂ፣ የባህልና የሃገር ፈሪም ኣለ’ንዴ?

“ኣንዳንድ ጥያቄዎች ኣሉ፤ ሺ ጊዜ ተጠይቀውም፣ ሺ ጊዜ ተመልሰውም፣ እንደገና ሺ ጊዜ እሚጠየቁ፤” ብሎ ነበር ኣሉ ከብልህ ደብተራዎቻችን ኣንዱ የሆነው ሰለሞን ደሬሳ። እኔ ግን ይበልጥ እሚያስጨንቁኝ፣ ጠይቀን ምላሽ ያጣንባቸው ጥያቄዎች ሳይሆኑ፣ እማንጠይቃቸው ጥያቄዎች ናቸው። ሂሊናችንን እየሞገቱም፣ ምናልባትም በየጓዳችን እያማንባቸውም፣ በገሃድ ግን፣ እንደ ህዝብ ግን፣ እንደ ሃገር ግን፣ እንደ ሰው ግን፣ … እማንጠይቅባቸው፣ እማንወያይባቸው፣ ኣቋማችንን በነፃነት እማንገልፅባቸው፣ ጥያቄዎች። በነዚህ ጥያቄዎች ላይ እማየውን ዝምታ ሳስብ፣ “የግለሰብ እንጂ የባልህና የሃገር፣ የህዝብም ፈሪ ኣለ’ንዴ?” እላለሁ። ታዲያ፣ እንደ ሃገር፣ ቢያንስ እማይጠየቁ ጥያቄዎች እሚጠየቁበትን ነፃ ሸንጎ ማቋቋም እንዴት ይሳነናል? እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች እንዲጠየቁ እምናበረታታበትን፣ ደፍረው ለሚጠይቁም ህጋዊ ከለላ እምንሰጥበትን፣ ስርዓት ማበጀት እንዴት ይሳነናል? ማንነታችንን እሚያቆስሉ፣ ወደፊታችንንም እሚያጨልሙ፣ እሚመስሉንን ጉዳዮች እያየን፣ ኣብረን ዝም እምንለው ለምንድነው? እኚህ እማይጠየቁ ጥያቄዎች ናቸው ይበልጥ እሚያስጨንቁኝ እኔን። ኣንድ ሺ ኣንድ ናቸው በቁጥር። ጥቂቶቹን ኣነሳቸዋለሁ ዛሬ። እነሆ፦-    

እማይገባኝ የሰውነትና የኢትዮጵያዊነት ዕዳ


ነገ ያላት መስሏት፣ ነገ ያላት መስሎኝ፣  
… ነገዋን ስታየው፣ ነገዋን ሳይላት፣
የኔኣጎጠጎጤ፣ የኔ ድንግል ውበት፣
ኑሮ’ሚያክል ገንቦ፣ ተጀርባዋ ጭና፣
… ዋሻ’ሚያክል ሃሳብ ተልቧ ኣንጥፋ፣
ለምኞቷ ልትደርስ፣ ለምኞቴ ልትደርስ፣  
በዘመን ኣቀበት ስትል ቆም ጎተት፣ ስትል ቀና ደፋ፣
እግሯ …
ተጠለፈ፤ ... በኣንዳች እንቅፋት፣ በኣንዳች ልጥ ነገር፣ በኣንዳች ቀረፋ።
ታ’ይን በሚያመልጥ ፍጥነት፣ …
ገንቦው … ተሰበረ። … ልጅቱም … ተደፋች።
… ዓለም… ዓለም ይህን ኣይታም፣ …
ዓለም ይህን ኣይታም … ዙረቷን፣ ዙረቷን፣ ዙረቷን፣ … ቀጠለች።

የፀጋዬን ቁዘማ ከእኔ ኣዳቅዬ ምርኩዜን ላበጅ ነው፦

እና አንዳንዴ፣ አንዳንዴ ብቻ፣ እኔው ከኔው ስመካከር
ከልቤ ጋር ስከራከር
ያው መቸም እኔም እንደሰው
የሐቅ ራብ ነፍሴን ሲያመው       (የፀጋዬ፣ እሳት ወይ አበባ፣ ማነው ምንትስ?)
ራሴን መልሼ እምጠይቀው፣
የህ ዜግነት ብሎ ነገር፣ የህ ሰብዓዊነት እምለው፣
የግዴታው ልኬት እስኬት፣ ያገባኛሉስ ምን ያህል ነው? 
እያልኩ ነው።                   (የኔ)
ከኣስርና ኣስራ ኣምስት ዓመታት በፊት፣ ኣራት ኪሎ ኮርዲያል ካፌ ውስጥ ኣንድ ስዕል ነበረች። ዓናት ላናት የተገናኙ ሁለት ደብተሮች በምታክል ሸራ ላይ ትልቅ ገንቦ ተሸክማ እምትታይ ሴት ልጅ ያለችባት ስዕል። መንገድ ዳር እንደሚሸጡ፣ ባህላዊ ሰዓሊያን እንደሳሏቸው፣ ዓይነት ያለች ስዕል። ግትር ያለው የስዕሉ ቅብና መዋቅር፣ ግትር ስላለ ነገር ያሳስባል። የቸኮለን፣ ይህ የሰዓሊው ኣለመቻል ነው፤ ያስብላል። ረጋ ያለን፣ በዚያ ኣለመቻል ውስጥ ስለተገለጠ እውነትም ያመራምራል። 

ለማይገባኝ ምክንያት ኣንድን ቦታ እለምድና እደጋግማለሁ። ያኔ ኮርዲያልን እደጋግመው ነበር። በሻይ ቤቱ ውስጥ፣ በየቅፅበቱ ከሚለዋወጡ ፊቶች ባሻገር፣ ያችን የማትለወጥ ስዕል፣ ያችን የማትለወጥ ፊት፣ ኣያለሁ። ዘመን ቆሟል። በዚያች ሸራ ላይ ዘመን ቆሟል። በሸራው ላይ በምትታየው ባለገንቦ ልጅ ህይወት ውስጥም ዘመን ቆሟል። እሷ ያንን ግዙፍ ገንቦ ተሸክማ ያንን የረጋ ጊዜ ሰንጥቃ ለማለፍ እምትታገል ይመስል። ያኔ ይሁን ኣሁን ኣላውቅም፣ "ይህ የኢትዮጵያ ህይወት ነው፤" ኣልኩ ለራሴ። ያኔ ይሁን ኣሁን ኣላውቅም፣ "ይህ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው፤" ኣልኩ ለራሴ።  

በረጋ ጊዜ ውስጥ ኣቋርጦ ለማለፍ ስለሚደረግ ትግል ማሰብ የጀመርኩት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሁን ከዚያ ቀድሞም ኣላውቅም። ይህ ቁዘማ በሌሎች ቦታዎችና ስራዎቼም ተደጋግሞ መጥቷል። ልጥቀስ?

ጊዜም በታማኝ ክርስቲያን ጦር ጭንቅላቱን ተወግቶ ከምድር እንደተላከከ እባብ፣ ራሱን ኣፈር ውስጥ ቀብሮ ተጋድሟል። እንዲያውም በድኑ ሳይሆን ይቀራል እሚታየው? ኣዎን፣ ጊዜም ሞቷል። በቀደምት ሙት ዘመናት ደንደስ የሰለጠኑ ወደል ምስጦች እሬሳው ላይ እንደአሸን ይርመሰመሳሉ። ያልደረቀ ቆዳውን ጠርስቀው ያልረጋ ደሙን ሊመጡ ይጣደፋሉ። በቅቷቸው በተውት የቆዳው ሽንቁር ውስጥ የታሪክና የትንቢት ቅይጥ፣ መግልም፣ እዣትም፣ ደምም፣ ብርሃንም፣ መስሎ መውረድ ጀመረ። እንደ ባዶ ኣንኮላ የሚንኳኳውን የፍጡራን ልቦና ስንጥቃት እየተከተለ ቢሽሎከለክም ልብ ያለው ግን ኣልነበረም። …
[ማሜ] የትኛው ኣምላክ ኣይዞሽ እንዳላት’ንጃ። የትኛው መልኣክ የማሪያም መንገድ እንደሰጣትም እንጃ! የኣለትን ስንጥቅ እያነፈነፈ እንደሚሰርግ ጥንታዊ ጠብታ፣ ምድሪቱን የሸፈኑትን የጨረር ጦሮችና የፍጡራን ደንደሶች እያቆራረጠች፣ የረጋውን ጊዜ፣ የረጋውን ነፋስ፣ የረጋውን የድምፅና የህልም ደለል እንደ ቡሄ ዳቦ እየገመሰች እዳሷ ተቃረበች። ለካስ፣ …
የሲሳዬ ልጆች/ኬክሮስና ኬንትሮስ ገፅ፦ 294-295

ይህ በህዝብና በባህል ውስጥ ብቻ ሳይሆን በግል ህይወትም ውስጥ ይሆናል፦

ንጋት፣
የረጋ ነበር። ኩሴ ሳይሆን ንጋቱ። የሚያልፍ ኣይመስልም ነበር ጊዜው። ደቂቆቹ ረግተው፣ ደለል ሰርተው፤ ከድንጋይም እንደከፋ በረዶ ደድረው። ኩሴ ነው ቆርጧቸው ያለፈ። ጊዜ እንዲያ ሲቆም ስለት ያበጃል፦ የእያንዳንዱ ሰከንድ በራድ ባልጩት እያረደው፣ የእያንዳንዱ ደቂቃ ስል ፍላፃ እየሸቀሸቀው። …
ኤላን ፍለጋ/የኣዞ ኮሌጅ፣ ገፅ፦ 117

እርግጥ ነው፣ የታሪካችን ስንክሳር፣ የመሆናችን ድርሳን፣ ስለዝህች ልጅ እምብዛም ኣያትትም። ምስሎቻችንም የቅዱሳንን ህይወት እንጂ የእሷን ኑሮ ኣያሳይዩም። ግን፣ የቆመ ጊዜ እማያብል መዝገብ ነው። በረዶን በማያውቀው በዚህ ፀሃያማ ሰማይ ስርም፣ እንደበረዶ በረጋው ሶስት ሺ ዘመናችን ላይ የሁዋሊት ብንንሸራተት፣ ያች ልጅ ያንኑ ገንቦ ተሸክማ እናገኛታለን፤ በየትኛውም ዘመን፣ በየትናውም ኣድባር። እና፣ በዚያች ስዕል ላይ እማያት ባለገንቦ፣ ልክ እንደ ኩሴና እንደ ማሜ፣ ያን የረጋ፣ ያን ባልጩታም፣ የጊዜ ደለል እየሰነጠቀች ለማለፍ እምትታገል ይመስላል። የጊዜው ብርቱ መቆም ኣቁሟታል። እሷ ግን የተሸነፈች ኣትመስልም። ኣዎ፣ ቢያንስ በዚህ የቆመው ጊዜ ምስጋን ይግባውና፣ ታሪክ ቆፋሪ ሳይሻ፣ ታሪክ ይናገራል። … ይህ የዚህች ምድሬ ድርሳን፣ ይህ የዚህች እህቴ መዋዕል ነው፤ ኣልሁ።

ኣያድርስም ኣይደል? ያ ለዘመናት የተሸከመችው ገንቦ ሳያንሳት፣ ይህ ዘመኔ ደግሞ፣ ከወደሌላ ኣድማስ የጊዜ ደራሽ፣ የጊዜ ፈረሰኛ ኣምጥቶ፣ በዚያ ጠጣር ዘመን ላይ እምትዳክረውን ልጅ … ጠለፋት። … እና፣ ወደቀች! … እና፣ ገንቦዋ ተሰበረ። … እና፣ ልጅቱም ተደፋች! … እና፣ ዋይ! ኣለች እህቴ! … እና፣ ምን ይጠበስ? … ምን ደንታ’ላት ዓለም ለዚህ? "ዋይታሽ ለገንቦው ነው ለራስሽ?" ብላ’ንኳ ኣትጠይቃትም ዓለም። ብትጨነቅ እሷ፣ ያው ለገንቦው ነው። … ነገ ሌላ ገንቦ ኣብቅላ ከጀርባዋ ትጭን የለ? ምን ደንታ’ላት ዓለም ለዚህ! …

ይህንንም ያንንም ኣስብና እኔም እንዳለም ወደኑሮዬ እጣደፋለሁ። ነገ ስመለስ ያችን ልጅ ኣለችበት ኣገኛት ይሆናል። …
ግን ግን፣ ምን ስላረግሁ፣ ወይም ምን ስላላረግሁ፣ ይሆን ይህ እንዲህ ሆኖ እሚቀጥል?

መግቢያዬ ያደረግሁዋት ግጥም የተወለደችው ከዚያ ስሜት ነው። ያኔ ሳይሆን ኣሁን። የተንደረደርኩበት ሃሳብ የተቀፈቀፈው ከዚያ ስሜት ነው። ያኔም ኣሁንም። ያኔም ኣሁንም፣ ያችን ስዕል ባየሁዋት ቁጥር ትዝ ትለኝ የነበር፣ ትዝ እምትለኝ፣ ሌላ ልጅ ኣለች።

ትግራይ ውስጥ ነው። በማይ-ነብሪ የገጠር ቀበሌዎች፣ በቀበሌዎቹም ውስጥ ከሰው ገሸሽ ብለው በሚቆዝሙ ኣቀበቶችና ሸለቆዎች ላይና ታች፣ ለመስኖ እርሻ የሚሆን ቦታ ኣሰሳ እወጣለሁ፤ እወርዳለሁ። ብቻዬን ነበርኩ። ባንድ፣ ጎርፍም እግርም ጊዜም በፈጠረው ቦረቦር ውስጥ ባለ የእግር መንገድ ሳልፍ፣ በቅርብ ርቀት፣ ኩፍስ ያለ ኣዳፋ ኩታ ነገር ታየኝ። መጀመሪያ ቀልቤን ኣልሰጠሁትም። ቀርቤ፣ ኣልፌው ልሄድ ስል፣ የደከመ ዓይኔን ጣል ኣረግሁ በዚያ የጨርቅ ክምር ላይ። እና፣ ደነገጥሁ! ጨርቁ ይንቀሳቀሳል። ልቤ ኣካሌን ቀድሞ ሮጠ። … ከጨርቁ ስር ልጅ ኣለች! እንዲያውም በደንብ ትታያለች። እንዴት ጨርቁን ብቻ እንዳየሁ! … ባካሌም ሮጬ ቀረብሁዋት።

ልጅቱ ለማብራራት በሚከብድ ኣወዳደቅ ወድቃለች። የቦረቦሩን ሰያፍ ተከትላ ሽቅብ ልትወጣ የዘረጋችው እግሯ ወዲያና ወዲህ ተንፈራኳል። እሷ ወደታች እንደመንጋለል ብላለች። ከጀርባዋ ተንሸራትቶ መሬት የነካ፣ መውደቁን ግን ያልጨረሰ፣ ከረጢት ኣለ። ከልብሷ የሚመሳሰል ከረጢት። ጥሬ ነገር የተሞላ። በራሱ ክብደት እየተገፋ ቁልቁል ለመሄድ የሚፈልግ። መውደቁን ያልጨረሰ ከረጢት። ልጅቱ፣ ከረጢቱን ኣልለቀቀችውም። ልትለቅቀውም ኣትችልም። ሁለቱም እጆቿ፣ ኣጥብቄ እይዝ ብላ፣ ጯፉን በጠመጠመችበት የከረጢቱ ኣፍ ታስረዋል። ቁልቁል መውረድ እሚፈልገው ከረጢት ሁለቱንም እጆቿን የሁዋልት ስቦ፣ ጨምድዶ ይዟል። ኣንዱ ክንዷ ኣንገቷን ኣንቆ ለመጮህም ለመተንፈስም እንዳትችል ኣድርጓታል። የኣስራ ኣንድ የኣስራሁለት ዓመት ልጅ። ምናልባትም ያስራሶስት። ቀጭን እንደወፍቾ። ተጥመልምላ። ጉልበቷ በስቃይዋ ተሟጦ። ህይወት በቋፍ ውስጥ ሆና። በዕምባ በተጋረዱ፣ በፈጠጡ ዓይኖቿ ሰማዩን እያየች። ሰማዩን እየተማፀነች። ወይ ውሰደኝ፣ ወይ ልቀቀኝ፤ እያለችው፣ ሰማዩን። …

ልጅቷን ከሞት ኣፋፍ ካላቀቅሁዋት በሁዋላ፤ ቁጭ ብዬ ማሰብ ያዝሁ። ምነው ቤቶቿ ይህንን ፈረዱባት? ሸክሙን ትችለዋለች ቢባል እንኳ በምን ሆዳቸው ሰው የማያዘወትረውን ሸለቆ ብቻዋን እንድታቋርጥ ለቀቋት? እንዲህ ሆና እስከ ወዲያኛው ብትለያቸው ምን ይሉ፣ ማንን ይከስሱ፣ ነበር? …

ያኔ ማድረግ የቻልኩት፣ ወይም የታየኝ፣ ልጅቷን ሰዎች ኣሉበት ኣድርሼ እስከምትሄድበት ወፍጮ ቤት እንዲሸኟት መለመን ብቻ ነበር። ሁዋላ ግን፣ "ያን ብቻ ነበር እምችለው?" ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። "ለምን ቤተሰቦቿ ጋ ኣልሄድኩም? ለምን ድጋሚ እንዲያ እንዳያደርጉ ኣልነገርኩም? ለምን ቢያንስ ስለዚያች ልጅ የወደፊት ደህንነት ኣልተሟገትኩም? …" ደግሞ እንዲህ ብዬ ኣስባለሁ፣ "… እኔ በሰው ልጅ የሚያገባኝ ምን ያህል ነው? በወላጅነት ማዕረግ ውስጥ፣ በቤተሰብ ጓዳና ማህፀን ውስጥ፣ ገብቼ ይህን እል ዘንድ የማሪያም መንገድ የሚሰጠኝ የቱ ህግ፣ የቱ ወግ ነው? …" መልሼም እንዲህ እላለሁ፦ "እያሳበብኩ ነው? እያሳበብኩ ነው? … እያሳበብኩ ነው? …"
እና፣
ያኔም ዛሬም ይህንን እጠይቃለሁ፦
በኢትዮጵያዊነቴ፣ በሰብዓዊነቴ፣ የሚያገባኝ ምን ያህል ነው?

"ህግ እኮ ኣለ፤" ትሉኝ ይሆናል። ኣውቃለሁ። "ዕድሜ ለዘመናዊ ሰብዓዊ እሴቶች!" እንበል? ልጆች ዕድሜኣቸውና ኣቅማቸው በማይፈቅድ ስራዎች ላይ እንዳይሰማሩ የሚከለክል ህግ ኣለ። እማይገባኝ ግን፣ ይህ ወደ ሃገሬ፣ ይህ ወደ ኣድባሬ፣ ይህ ወደ ቤቴና ወደ እምነቴ ሲመጣ፣ እንዲህ ያሉ ህጎች የሚሰጡኝ የመጠየቅም የመናገርም መብት እስከዬት እንደሁ ነው።

ሌላ ምሳሌ ልጨምርና ጉዳዬን ከሌላ ኣንፃር ለማሳየት ልሞክር፦

በቅርቡ ኣንድ ጓደኛዬ፣ ከኣንዲት ዘመናዊት ወጣት ጋር ያደረገው ጭውውት ኣስገርሞት፣ ጉዳዩን በፌስቡክ ላይ እንድንወያይበት ኣቅርቦ ነበር። ጭውውታቸው በጋብቻና በልጅ ጥያቄ ዙሪያ ነበር። የልጅቱ ምርጫ፣ ከኣንድ ከሆነ ወንድ፣ እምታውቀውም ይሁን እማታውቀው፣ እምታፈቅረውም ይሁን እማታፈቅረው፣ ብቻ፣ በመልክም በኣዕምሮም ጥሩ ከሚመስላት ወንድ፣ መፀነስ። ለሰውዬው ሳትነግረው፣ መውለድና ማሳደግ። በቃ! የምን ጋብቻ ብሎ ጣጣ፣ የምን ቤተሰብ ብሎ መጓተት ነው!

ይህ፣ በኣገራችን እንግዳ ይሁን እንጂ፣ በሌሎች ዓለማት የብዙ ወጣት ሴቶች ምርጫ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው። ለዚህ ዓይነት ህይወት ኣራማጆች፣ ይህ ዘመናዊነት እሚሰጠው ነፃነት፣ ይህ የግል ስሜትና ምርጫ ጉዳይ ነው። ምዕራቡ ዓለም ለዜጎቹ ይህንን ነፃነት በመስጠቱ ይኮራል። ስልጣኔ!

ጥያቄው ታዲያ፣ "ይህ ምን ያህል መልካም ነው?" የሚል ነበር። ከወንዶችም ከሴቶችም የልጂቱን (የዘመኑን) ኣካሄድ እሚደግፉም፣ እሚቃወሙም፣ ሃሳቦች ተሰነዘሩ፦ ከሃይማኖት ኣንፃር፣ ከባህልና ከባህል ወረራ ኣንፃር፣ ከግል መብትና ነፃነት ኣንፃር፣ ከዘመኑ ሩጫና ቁንጥጫ ኣንፃር፣ …። በፍቅር ተፀንሶ በፍቅር ያልተወለደ ልጅ፣ ምን በኣካል ቢደላው፣ በመንፈስ በልቦናው ላይ የሆነ ጠባሳ ኣያጣውም፤ በሚሉ የኔብጤዎች ምናብ ውስጥ ምክንያትንና ሎዢክን ለማሳየት ቢከብድ እንኳ፣ እስቲ ጉዳዩን፣ የሰለጠነው ዓለም፣ የኛ የስልጣኔ ትሩፋት ነው፤ ከሚለው የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ኣንፃር እንመልከተው፦  

የትኛውም ሰው፣ በራሱ የነፃነትም ሆነ የፍትህ፣ የምቾትም ሆነ የመሰልጠን፣ እይታና እሾት ተመርቶ፣ በሌሎች ህይወት ላይ ለመወሰን ምን መብት ኣለው? ኣንዲት ሴት፣ የኣንድን ኣባት ፈቃድ ሳትጠይቅ፣ የኣባትነት መብቱን የመንፈግ ምን መብት ኣላት? የትኛውም ወላጅ፣ ያልተወለደ ልጁን ፈቃድ ሳይጠይቅ እናት-ኣልባ ወይም ኣባት-ኣልባ ኣድርጎ ወደዚህ ዓለም ሊያመጣው ምን መብት ኣለው? … ወደዚህ ምርጫ የሚያስገቡ ባህላዊም ሆነ ስነ-ህይወታዊ ምክንያቶች ካሉ፣ ይህንን ምርጫ ግድ ለማድረግ፣ የነዚህ ሁኔታዎች ኣስገዳጅነት እስከምን ሲሆን ነው ጉዳዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እማይባለው? ስለ ሰብዓዊ መብት ኣብዝቶ የሚጨነቀው፣ ኣብዝቶ የሚለፍፈው፣ ኣብዝቶም የሚሟገተውና የሚከስሰው ዓለም፣ ይህንን የህይወት መላ እንደ ስልጣኔ ለማራመድ ሲነሳ፣ በዚህ ጉዞው የብዙ ልጆችን ሰብዓዊ መብት እየጣሰ እንደሁ እንዴት ኣልታየውም? የግለሰብ መብት በማህበራዊ ደህንነት መብት ላይ እንዲረማመድ የሚፈቀድለትስ እስከምን ድረስ ነው?

እኚህ ጥያቄዎቼ ሁዋላቀርነቴን ባያሳዩ እንኳ ኣፍሪካዊነቴን እሚያሳዩ ይመስለኛል። ኣዎ፣ ኣፍሪካዊ ነኝ። ኣዎ፣ ባህላዊ ነኝ። ሁዋላ-ቀር ግን ኣይደለሁም። የኣመለካከቴ ድርና ማግ የተቃኘው በኣፍርካዊነቴ ነው። በኣፍሪካ ምድር የተበጀችው ነፍሴ የምትነግረኝ ኣንድ እውነት ኣለ፦ የግል ደህንነት ከፍጥረተ-ዓለም ደህንነት ተነጥሎ ኣይታይም። ለኔ ይህ ጨቋኝነት፣ ይህ ሁዋላ-ቀርነት ኣይደለም። የግለሰብን ነፃነትና ደህንነት የሚነጥቅም እኩይ ስርዓት ኣይደለም። በፍጥረተ-ዓለም ውስጥ ያለውን የማይበጠስ ትስስርና ህብር ከመረዳት ብስለት የመነጨ እውነት እንጂ ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ፣ የዚህ ህብር ወሳኝ ቀለበት እንደሁ የመረዳት ውጤት እንጂ ነው። ሰምታችሁት ከሆነ፣ ኣፍሪካዊው እረኛ ይህንን ኣዚሞ ነበር፦

እንዲያ ተፈታትለን፣
ትንፋሽሽን ስምገው፣ ገላሽን ስሞቀው፤
እውስጥሽ ሰጥሜ፣ ውስጤን ስወስጠው፤
ሆኖ ኣገኘሁት፣
የሃር ዳንቴል ፍጥረት፣ ህላዌ ሰንሰለት፤
መነሻ የሌለው፣ መድረሻ የሌለው፣ ልል በልል ቁርኝት።
መሆናችን ኣይደል፣ ኣንች ኣንዷ ዘለበት፣ እኔም ዘለላ ክር?
ሁለት ሁለንተናን፣ ባንድነት ምናስር!
ከዚህ ልንቁስ ህብር፣
ቢሰበር ቀለበት፣ ቢመዘዝ ኣንድ ክር፣
በሞቴ ንገሪኝ፣ ነበር ይኖር ነበር?            (ኣርባ ጠብታዎች፣ ኣንቺና-’ኔ)

ይህ እረኛ እንደሚለን፣ በ’ንደኔ ዓይነት ኣፍሪካዊ ህይወት ውስጥ፣ የትኛውም ግለሰብ፣ ሁለንተና ነው። የትኛውም ግለሰብ፣ ሌሎች ብጤ ሁለንተናዎችን የሚያስተሳስር ክር ነው። የትኛውም ግለሰብ እንደ ህይወት ድንገቴ (accident) ኣይታይም። ሲወለድ በፉጨትና በሆታ በሚቀበሉት ሰዎች መሃል ይመጣል፤ በምርቃትና በቡራኬ፣ በሆታና በዕልልታ፣ በኣምልኮ ስርዓቶችም ታጅቦ የዕድሜውን የተለያዩ እርከኖች ይሸጋገራል። ሲዳር በታላቅ ክብር፣ ሲወልድና ሲከብድም በታላቅ ክብር፣ ሲሞትና ሲሸኝም በታላቅ ኣጀብና ክብር፣ ነው። ኣፍሪካዊው ግለሰብ፣ ሞቶም እንኳን የማህበራዊ ስርዓቱ ኣካል እንደሆነ ይቀጥላል።

እንደገና ላስረግጠው፦ በኔ ብጤው ኣፍሪካዊ ህይወት ውስጥ፣ ግለሰቡ የህይወት ሂደት ተራ ድንገቴ ኣይደለም። ግለሰብ ህዝብ ነው። ግለሰብ ሁለንታ ነው። ክብሩም የሚገለፀው በዚህ ህብር ውስጥ በሚኖረው ድርሻ ነው። ምጉቴ፣ ይህ በሁሉም ኣፍሪካዊ ባህሎች ውስጥ፣ ለሁሉም የማህበረሰቡ ኣባላት፣ ፍፁም ፍትህ ሊኖረው ይችላል፤ የሚል ኣይደለም። ይልቅ፣ በየትኛውም ባህላዊ ስርዓት ውስጥ እንከን ቢኖር፣ ያንን እንከን ለመንቀስ የሚመጣው መላ፣ ይህንን የደረጀ ህብር እሚያፈርስ መሆን የለበትም፤ እሚል ነው።

ኣንድ ግለሰብ ወደ ምንምነት ቢለወጥ፣ ምልዓተ-ፍጥረትን እሚያስተሳስረው ኣንድ ክር የተበጠሰ ያህል ነው እሚሆነው። በኣንድ ግለሰብ ምክንያት የፍጥረተ-ዓለሙ መዋቅር ሊናጋ፣ "ነበር" እምንለው ነገር ሁሉም እንዳልነበር ሊሆን፣ ይችላል። በኣፍሪካዊው መላ-ህይወት ውስጥ ግለሰቡ ይህን ያህል ሃያል፣ ይህን ያህል ክቡር ነው። ግለሰብን ኣከበርኩ ብሎ ያዋረደው ዓለም ሊያሳምነን እንደሚጥረው፣ ግለሰብ ድንገቴና ኣጋጣሚ ኣይደለም። ግለሰብ፣ ማንም ባለመብት ነኝ ባይ፣ የበኩርነት መብቱን በዘፈቀደ እንዲሸረሽርበት የሚፈቀድበት ምስጥ ያበጀው ኩይሳ ኣይደለም። ግለሰብ፣ በሌሎች መንገድና ምርጫ ውስጥ ሳይጋበዝ የመጣና የሚመጣ ደንቃራ ኣይደለም። በዓላማና ለዓላማ የሚፈጠር ክቡር የህይወት ፀጋ ነው፣ ግለሰብ። እና፣ …

በዚህ በምኮራበት ኣፍሪካዊ እውነቴ፣ በዚህ የሰብዓዊነት ጉልላት በምለው እምነቴ፣ ውስጥ፣ "ልጄ ነው ምን ኣገባህ? ገላዬ ነው ኣንተ ተዚህ ምን ዶለህ?" እሚለኝን እንዴት ልቀበል እችላለሁ? ይህ ልጆችን እንደጫጩት በማሽን ከማስፈልፈል ምን ያህል ይርቃል? ይህ፣ ልጆችን በፋብሪካ እያባዙ ከማከፋፈል ምን ያህል ይርቃል? … እና፣ ይህ የሚያሳስበኝ እኔ፣ ኣንዲት ልጅ ልጇን ያለኣባት ልትወልደው፣ ያለማህፀን ልትሰራው፣ … ስትመርጥ ባይ፣ "የለ፤ ኣትችዪም!" ብዬ ለመሟገት ምን ያህል መብት ኣለኝ? እንደ ኣፍሪካዊ፣ እንደ ኢትዮጵያዊ፣ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር፣ ይህንን ልጠይቅ፣ ይህንን ልሞግት እምችለው እስከዬት ድረስ ነው?     

ያች ባለገንቦ ልጅ፣ ዛሬ ደግሞ ዘመናዊ ገንቦ ከነትኩስ ኣተላው በጀርባዋ ሳይሆን በደረቷ የታቀፈች ልጅ፣ ሰርክ በመንገዴ ከሚገጥሙኝ፣ የዘመንና የባህል ሸለቆ ሲበላቸው እያየሁ፣ እያመመኝም ምንም ሳልል ከማልፋቸው፣ ዓዕላፍ ወገኖቼ ኣንዷ ብቻ ነች። ምንም ሳልል እማልፈው ጨካኝ ስለሆንኩ ኣይደለም። ለመናገር፣ ለመጠየቅ፣ ለመሟገት፣ … ምን መብት እንዳለኝም ስለማላውቅ፣ ወይም የመብቴ ጣሪያ እስከምን እንደሁ ስለማይገባኝ ነው። እንዲህ ካሉ ግራ ኣጋቢ ጉዳዮች ኣንድ ሁለቱን እንደ ምሳሌ ልጨምር፦

ካገር ቤት ለኣምስትና ለስድስት ዓመታት ራቅ ብዬ ስመለስ በጣም ካስደነቁኝ ነገሮች ኣንዱ የሙዚቃና የፊልም ሲዲዎችን፣ መፅሃፍትን፣ … የመሳሰሉ የባህላዊ ምርቶች እንደኣሸን መፍላት ነው። በተለይ ከመንፈሳዊ ህይወት ጋር የተያያዙ ባህላዊ ምርቶች። ብዛታቸውን ሳይ፣ "ምናልባት በባለፉት ሃምሳ ዓመታት ከተመረቱቱ በነዚያ ኣምስት ዓመታት የተመረቱቱ ሳይበልጡ ይቀራል?" ብዬ ኣሰብኩ። ያመለጠኝ ብዙ፣ እጅግ ብዙ፣ እንደሁ ግልፅ ነው። እና፣ የቻልኩትን ያህል ቅኝት ብጤ ለማድረግ ሞከርኩ። በተለይ የሚስቡኝ፣ በመንፈሳዊ ህይወት ዙሪያ ያሉ ስራዎች ናቸው። በባህል ላይ፤ በተለይ የኛን ኣገር በመሰሉ፣ ለመንፈሳዊነት ስስ ልቦና ባላቸው ኣገሮች ባህል ላይ፣ ከፍተኛውን ተፅዕኖ የሚያኖረው ሃይማኖት እንደሁ ይሰማኛልና። ኣንድ ምርት (መፅሃፍ፣ ሲዲ፣ …) ብዙ ሰዎችን እየነካ እንደሁ እስከታየኝ ድረስ፣ ምንጩ ከየትኛውም ሃይማኖት ቢሆን ሳይገድበኝ፣ ምንነቱንና ይዘቱን ለማወቅ እሞክራለሁ።

ቤተሰቦቼም፣ ጓደኞቼም፣ ኣየሩም፣ "… እኚህንስ ማየት ኣለብህ፤ ኣንተ እምትወዳቸው ዓይነት ናቸው፤" ያሉኝን የሃይማኖት ቪዲዮዎች ማየት ጀመርኩ ኣንደዜ። "የእሬትን መራርነት ለማወቅ ሽክና ሙሉ መጠጣት የለብህም፤" ይባላል። ጠብታ ቅምሻ ብቻ ይበቃል። ኣንዱንም ሲዲ ኣልጨረስኩም። የጀመርኩትም ሆነ የሌሎቹ ተከታታ ሲዲዎች ይዘት ምን እንደሆነ በዚያች ቅምሻ ግልፅ ሆነልኝ። "በቃኝ፤" ኣልኩኝ። ጓደኞቼም ቤቶቼም ማየት ኣለመፈለጌ ኣስደነቃቸው። "ህፃን ሽማግሌው ኣይቶ ያደነቀውን ኣንተ እማትወደው ምን ብትሆን ነው?" ተባልኩ። ከቶም ልቀበለው ያልቻልኩት ነገር የመጣው ከዚያ በሁዋላ ነው። ያኝን መዓት ሲዲዎች በቤተሰቡ ውስጥ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያለ ሰው ኣይቷቸዋል። ምናልባትም በሌሎች ቤተሰቦችም ውስጥ። ምናልባትም በሃገሪቱ ሁሉ ውስጥ። ህፃናትን ጨምሮ። ታዳጊዎችን ጨምሮ። ወጣቶችን ጨምሮ! …    

"ይህ ከቶም መሆን የለበትም፤" ኣልኩ። ኣዋቂዎች፣ በመረጡት እምነት ውስጥ ኖረው ያረጁ ኣዋቂዎች፣ ልቦናቸው በመረጡት መንገድ ኣድጎ የደረጀላቸው ኣዋቂዎች፣ … ያሻቸውን ቢያዩና ቢያደምጡ፣ እሚያሳስብ ነገር ኣይኖር ይሆናል። ግን፣ ህፃናትና ልጆች?
ግልፅ ልሁን፣ እኔ፣ በነዚያ ሲዲዎች ላይ ያለኝ ጥያቄ የይዘታቸው እውነትነት ወይም ሃሰትነት ኣይደለም። በልጆች ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉት ተፅዕኖ ጉዳይ ነው ጥያቄዬ። እውነት እንደሆኑ እሚያምኗቸውም ቢሆኑ ይዘታቸው በልጆች የዓዕምሮ ዕድገት ላይ፣ በነፃ የማሰብ ክህሎታቸው ላይ፣ ነገሮችን በራስ ዓይን ኣይቶ በመበየን ኣቅማቸው ላይ፣ ተፈጥሮን በልበሙሉነት መርምረው ሚስጢሯን በማወቅ ፍላጎታቸው ላይ፣ ከየትኛውም ብሄርና ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ህብራዊ ትስስር ፈጥረው በመኖር ዝንባሌኣቸው ላይ፣ … ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያኖሩ እንደሚችሉ እሚከራከሩ ኣይመስለኝም። ይህ መሆኑን ካወቁ ታዲያ ልጆች እንደምን ያለከልካይ እንዲያዩኣቸው ፈቀዱ? ጉዳዩን የከፋ እሚያደርገው፣ እነዚህ ነገሮች በሃይማኖት ስም ስለሚሰሩ ነው። ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ስራዎች፣ ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ክልከላ ስለሚደረግባቸው፣ ተፅዕኖኣቸው ቀለል ሊል ይችላል። እኚህ፣ ሁሉም ሰው እንዲያያቸው፣ ኣይቷቸውም እንዲያምናቸው፣ እሚሰሩ ስራዎች ናቸው። ቤተሰቦች መፍቀድ ብቻ ሳይሆን ማበረታታትን ይጨምሩበታል። ልጆች፣ በኣካልም በስነልቦናም ምንም ማምለጫ፣ ምንም መከላከያ ኣይኖራቸውም።     

ከቤቶቼም ከጓደኞቼም ጋር መከራከሩ ዋጋ ኣልነበረውም። "ወደ ምንጩ መሄድ ኣለብኝ፤" ኣልኩ። "የትኛውንም ቤተ-ሃይማኖት ወክለው፣ እነዚህን ምርቶች ወደሚያወጡና ወደሚያከፋፍሉ ድርጅቶች እየሄድኩ፣ ቢያንስ፣ የሚያወጧቸው ምርቶች ለልጆች እማይገቡ ከሆነ፣ የዕድሜ ገደብ እንዲፅፉባቸው መናገር ኣለብኝ፤" ኣልኩ። ይህ ስሜት ኣልለቀኝ ብሎ ሰነበተ ያን ሰሞን። ክፍለሃገር ነበርኩ። ኣዲስ ኣበባ መጥቼ ያሰብኩትን ማድረግ እስከምጀምር ቸኮልኩ። … ትንሽ ቆየሁ። በመሃል፣ ስሜቴ እየበረደ፣ ምክንያት ተብዬ ሃሳቦች በልቦናዬ እየገቡ፣ መጡ። " … ኣሁን የቱን ከየቱ ላዳርስ ነው? ከኣንዱ እንኳ ሄጄ ለመናገር ብሞክር፣ ከፀብና ከምጉት በቀር በዚህ መንገድ ለውጥ ማምጣት እችል ይሆን? በሌላ ሃይማኖት ውስጥ ገብቼስ፣ ይህንን ኣድርጉ፣ ይህንን ኣታድርጉ፤ ለማለትስ መብት እሚሰጠኝ ህግና ደንብ የቱ ነው? …"    

ኣንድ ሰው ራሱን ለማጥፋት ሲጥር ባይና ከጥፋቱ ላድነው ጥረት ባላደርግ፣ ህግ እንደሚጠይቀኝ ኣውቃለሁ። በማንኛውም "ህጋዊ" ኣካል የሚፈፀም "ህጋዊ" ድርጊት፣ ትውልድ ሊያጠፋ እንደሚችል እየተሰማኝ ዝም ብል እሚጠይቀኝ ህግ እንዴት ይጠፋል? ባይጠይቀኝ እንኳ ይህን ኣደርግ ዘንድ እሚያነሳሳኝም፣ ከለላ እሚሰጠኝም ህግ እንዴት ይጠፋል? … ቢያንስ በዜግነታችን ኣንድ በሆንንባት በዚህች ምድር፣ እንደ ኣንድ ህዝብ፣ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ኣንስተን በግልፅ እማንነጋገረው ለምንድነው? እንዴት ኣብረን እየሞትን ኣብረን ዝም እንላለን? …   

በኢትዮጵያዊነቴ፣ በሰው ልጅነቴ፣ ይህን ልጠይቅ መብቴ ምን ያህል ነው?

በቅርቡ በኣንድ የቀበሌ መዝናኛ ውስጥ ከኣንድ ኣሜሪካዊ ጓደኛዬ ጋር ተቀምጠን እንጨዋወታለን። ጓደኛዬ በግድግዳ ላይ የተለጠፈ ግዙፍ የቢራ ማስታወቂያ ዓይኑንም ቀልቡንም ይስበውና እንዲህ ይለኛል፦   

"ያንን የቢራ ማስታወቂያ ታየዋለህ? ፅሁፉን ተመልከት፣ ‘One People, One Beer’ (ኣንድ ህዝብ፣ ኣንድ ቢራ) ይላል። ኣይገርምም? ‘ምን በብሄር፣ ምን በሃይማኖት፣ ምን በኑሮ ደረጃ የተለያያችሁ ብትሆኑም ቢራ ኣንድ ያደርጋችሁዋል!’ ማለቱ‘ኮ ነው፤" ኣለኝ። ቀጠለ ወዳጄ፣  

"ይህ ሃገር ኣሜሪካን እየሆነ ነው። በኣሜሪካዊያን ልቦና ላይ በንግድ ማስታወቂያዎች ኣማካኝነት እጅግ ኣሳዛኝ ጥፋት ደርሷል። የኣሜሪካ ሸቀጥ ሻጮችና ኣሻሻጮች፣ ለዘመናት፣ ‘ይህንን ሸቀጥ መጠቀም ዘመናዊነት ነው፤ ይህንን ቅባት መጠቀም ውብ ያደርግሻል፣ ይህንን ኣገልግሎት መጠቀም ከምርጥ ዜጎች ተርታ ያሰልፍሃል፤ …’ ሲሉ ቆይተዋል። ዛሬ ታዲያ፣ ኣብዛኛው ኣሜሪካዊ ያን ምርት ወይም ኣገልግሎት በመጠቀሙ፣ በዚያ ክበብ ውስጥ በመታቀፉ ብቻ፣ ብልህ፣ ደስተኛ፣ ውብ፣ ጨዋ፣ … የሆነ ይመስለዋል። ሰው በሰብዓዊ እሴቶች ኣይለካም። እንደ ሸቀጥ በሸቀጥ ይመዘናል፤ በሸቀጥ ይሰፈራል። ኣብዛኛው ኣሜሪካዊ፣ ሳያውቀው ራሱን ከሸቀጥ ኣስተካክሏል። … እንደ ኢትዮጵያ ባለ፣ በማንነቱ፣ በባህሉና በዜግነቱ እኮራለሁ በሚል ህዝብ መሃል እንዲህ ያለ ነገር ሲደረግ ዝም ብሎ ማየት የሚያሳዝን ተቃርኖ ኣይፈጥርም?"

እምመልስለት ኣልነበረም። ያ ጥያቄው ለኔ ብቻ እንዳይደለ ማሰብ ያዝሁ። ይህንን ጥያቄ ዜጋ ነኝ ለሚል ሁሉ እንዴት ማድረስ እንዳለብኝ ማሰብ ያዝሁ። ጓደኛዬ ቀተለ፦

"የእንዲህ ዓይነት ማስታወቂያዎች ስውር ተፅዕኖ ቀላል ኣይምሰልህ። ተፅዕኖኣቸው በቢራ ኣፍቃሪዎች ላይ ብቻም ኣይደለም። ዛሬ፣ በኣዲስ ኣበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች ውስጥ በሚገነቡ ትልልቅ ህንፃዎች ላይ እጅግ ገዝፈው የሚታዩት የቢራ ማስታወቂያዎች ናቸው። (በልቤ፣ "በሬድዮንም በቲቪም በጋዜጣም በመፅሄትም፣ እጅግ ገዝፈው፣ የክብር ተብለው፣ ተወድሰውና ተደንቀው፣ በቅኔና በሙዚቃ ታጅበው፣ በምናከብራቸውና በምንወዳቸው ከያኒዎቻችንና ጋዜጠኞቻችን ድምፅ ተሞካሽተው፣ … የሚታዩት የቢራ ማስታወቂያዎች ናቸው፤" ብዬ ኣከልኩበት።) በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያለ ልጅ እኚህን ማስታወቂያዎች ሰርክ ያያቸዋል (ያደምጣቸውማል)። ማስታወቂያዎቹ እሚሰሩት መሰሪ በሆነ ስሌትና ብልጠት ነው። ደንታ የለኝም፤ ኣላያቸውም፤ ኣላደምጣቸውም፤ የሚለው ሰው እንኳ ከተፅዕኖኣቸው ኣያመልጥም። በፍዝ ልቦናው የፍላጎት ሃውልት እየገነባ ያድጋል። እና፣ ወደደም ጠላም፣ ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ፣ ለነዚህ ማስታወቂያዎች ይገብራል። ተመልከተው የዚህን ማስታወቂያ ይዘት፦ ስዕሉ የተለያዩ መያዣዎችን ያሳያል። የተለያዩ ሰዎች በላቸው። በሁሉም መያዣ ውስጥ ያለው ግን ቢራ ነው። ምስሉ፣ ፅሁፉን ለማያነብም እንኳ፣ ያንኑ መልዕክት ያስተላልፋል ምን በኣካል፣ ምን በባህልና በሃይማኖት ብትለያዩም፣ ቢራ ኣንድ ያደርጋችሁዋል፤ ይላል። ይህ ክብረ-ነክ ኣይመስልህም?"   

ወዲያው ማሰብ የጀመርኩት፣ ኢትዮጵያዊያንን በኣስተሳሰብ ኣንድ እያደረገ ያለ ስለሚመስለኝ ሌላ ተፅዕኖ ነው። ዛሬ እግር ጥሎት የፓርላማ ኣባላት በሚሰባሰቡበትም፣ የነጋዴዎች ህብረት በሚዝናናበትም፣ የምሁራን ዕድሮች በሚሰየሙበትም፣ … የሚገኝ፤ በየመንገዱ ኣብረውን ያሉ ባተሌዎች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ወደ ገጠር ወጣ ስንልም እምናገኛቸው ኣራሾችና ኣርቢዎች፣ … ሲገናኙ ለሚጨዋወቱበት ጉዳይ ጆሮውን የሚሰጥ፣ ሁሉም እሚያወሩት ስለኣንድ ጉዳይ ሆኖ ያገኘዋል፦ ስለ ኣውሮጳ የዓይንና የጆሮ ኳስ። በእይታውም በንግግሩም፣ በጥያቄውም በመልሱም፣ ውስጥ ያለው ጥበብ ኣንድነት ደግሞ ይበልጥ ያስገርማል፦ ፑዞ የሚባል ተጫዋች በስንት እንደተሸጠ፣ በልደቱ ላይ ብርጭቆ እንደሰበረ፣ ካልሲውን ኣይጥ እንደበላበት (ውሸት ነው፣ ኣውሮጳ ኣይጥ የለም፤ እንዳትሉኝ።)፣ ከሚስቱ እንደተቀያየመ፣ ከጓደኛው ጓደኛ ጋር ሲማግጥ እንደተገኘ፣ … ። የባሰባቸው ደግሞ በኣውሮጳዊያኑ ቡድን ተቦድነው፣ የነሱን መለያ ለብሰው፣ ኣርማቸውን ከማተባቸው እኩል ኣንገታቸው ላይ ኣስረው፣ … እርስ በርስ ይፎካከራሉ፤ ይከራከራሉ፤ ይኮራረፋሉ፤ ይፋለማሉ። (እኔ ኣንዳንዴ፣ "በብሄርና በመንደር ተከፋፍሎ፣ በፖለትካም በሃይማኖትም ተሸንሽኖ መከራከርና ፀብ መፍጠር፣ ምንም ያህል ሁዋላ-ቀርነት እንደሆን ቢሰማኝም፣ ከዚህ ምን ያህል ክቡር ነው!" እላለሁ። ቢያንስ በዚያ ውስት፣ ከሌጣ ስሜት የሚልቅ፣ የኛ የሆነ ነገር ኣለ።)  

እና፣ ቢራና ኳስ በጥቅምም በውጤትም ተደጋግፈው ሲሄዱ ታየኝ፦ ምን በትምህርት ደረጃ፣ ምን በኑሮ ደረጃ፣ ምን በመልክና በባህል ብንለያይ፣ እምንዝናናው ያው በእግርኳስና በድራፍት፣ እምናስበውና እምናወራው ያው ስለኳስና ስለድራፍት፣ እምንኮራውም ይህን የድራፍት ዓይነትና ያንን የኳስ ቡድን በመምረጣችን፣ … ነው። ምስጋን ላውሮጳ ኳስ፣ ምስጋን ለቢራ፣ ኣንድ እየሆንን ነው! … እና፣ ጓደኛዬ የጠየቀኝን ጥያቄ ራሴኑ መልሼ ጠየቅሁ፦ ይህ ክብረ-ነክ ኣይደለም? …

ምናልባት ይህንን እሚያነብ፣ ኣጉል የተለጠጠ በመሰለው ንፅፅሬ ይቆጣ ይሆናል። እሱንም እንዲያስብበት እጠይቀዋለሁ፦ ይበልጥ ክብረ-ነክ መስሎ እሚሰማህ የቱ ነው - ንፅፅሩ? ወይስ በንፅፅሩ ውስጥ ያለው እውነት? … ዛሬን ሳይሆን፣ ነገ ሊመጣ ያለውን ኣስበው። ኣንተ ዛሬ፣ "መጠጥ ክልክል ነው፤" ነገ ደግሞ፣ "ትንሽ መጠጥ ይፈቀዳል፤" እያልህ ቀኖናህን ታጠብቅ ታላላ ይሆናል። ግን፣ የ’ንዲህ ዓይነቱ ማስታወቂያና የ’ንዲህ ዓይነቱ ልቅ ኣካሄድ ተፅዕኖ፣ ካንተ የሰንበትና የበዓላት ተለዋዋጭ ቀኖና ይልቅ፣ እጅግ የበረታ፣ እጅግም ሁለ-ነክ ነው። ነገ፣ ማጣፊያው ኣጥሮህ፣ "በእውነቱ እኔ ማነኝ? ይህን ልጄን፣ ይህንን ትውልድስ እንዲህ ኣርጎ የቀረፀብኝ ማነው?" ብለህ ከመጠየቅህ በፊት፣ ዛሬ ይህንን ጠይቅ፦ እውን ክብረ-ነኩ የቱ ነው - መጠየቁ ወይስ ኣለመጠየቁ? ቀድሞ ማሰላሰሉ ወይስ በስሜትና በጥቅም ወጀብ ተመትቶ ማዕበሉን መከተሉ?    

እና ታዲያ እኔ፣ እንደ ሰውነቴና እንደ ዜግነቴ፣ "ይህ ጉዳይ ኣቤት እሚባለው ለማን ነው?" እላለሁ። እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ እኔው ከኔው ስመካከር፣ ደግሜ ደጋግሜ ይህንን እጠይቃለሁ፦ በዜግነቴ፣ በሰው ልጅነቴ፣ ይህንን መጠየቅ እምችለው እስከዬት ድረስ ነው? በዚህ፣ በትውልድ ላይ የሚፈፀም ጥፋት፣ በባህልና በግላዊም ሆነ በማህበራዊ ፈቃድ (will) ላይ የሚፈፀም ጄኖሳይድ በሚመስለኝ ጉዳይ፣ ይግባኝ! ማለት እምችለው ለማን ነው? በዚህ ሂደት ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ ኣከላት ሁሉ መልስ እንዲሰጡኝ ልሞግታቸውና ላስገድዳቸው እሚያስችለኝን መብትና የህግ ጥበቃ እማገኘው ተወዴት ነው?

መቼም ኣቤቱታዬ በዝቷል፤ ፅሁፌም ረዝሞብኛል። መቼም፣ እንዲህ ያሉ ግራ ኣጋቢ ነገሮች የትየለሌ ናቸው። የሚያነበኝን ትንሽ ትዕግስት ልለምንና፣ እጅግ ኣብከንካኝ ከሚሆኑብኝ ጉዳዬች ኣንዱን ጨምሬ፣ ከተቻለ ምላሻችሁን፣ ካልሆነም ኣብረን ይግባኝ እንድንል ፈቃዳችሁን፣ ልጠብቅ፦

ከኣስራ ኣምስት ዓመታት በፊት ነው። ኢስራኤል ውስጥ ነበርኩ። የቁምም የእንቅልፍም ህልሜ መማር ብቻ ነበር። መማር እምመኘውን ያለከልካይ ተምሬ ማድረግ እምመኘውን በብቃት ማድረግ። ግን፣ ይህ ምኞቴን እውን ለማድረግ ኣቅሙም፣ መስመሩም ኣልነበረኝም። ማድረግ እምችለው ኣንድ ነገር እንደብቸኛ ኣማራጭ በልቦናዬ ተደቀነ፦ የኣካሌን ክፍል ሽጬ ለትምህርት የሚያስፈልገኝን ገንዘብ ማግኘት። እና፣ በኣሜሪካና በኣውሮጳ ለሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ይህንኑ ሃሳቤን ኣካፈልኩ፦
"መማር እፈልጋለሁ። እምከፍላችሁ ገንዘብ ግን የለኝም። ከተቀበላችሁኝ፣ ኩላልቴን ሽጬ ልከፍላችሁ ዝግጁ ነኝ።"

ከፃፍኩላቸው ዩኒቨርሲትዎች ከኣንዱ ምላሽ መጣ፦
"በኣሜርካም ሆነ በምትኖርበት በኢስራኤል ህግ፣ የኣካልን ክፍል መሸጥ ህገ-ወጥ ነው። በዚህ ልንረዳህ ኣንችልም። ይቅርታ!"

ይህንን ኣላውቅም ነበር። ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ህግ ይኑራት ኣይኑራት ኣላውቅም ነበር። ግን ያንን ምላሽ እንዳነበብሁ ንደቴ ነበር የገነፈለብኝ። ዓለም ኣብሮ ህልሜን እውን እንዳላደርግ መሰናክሉን ያበዛብኝ መሰለኝ። የህጉ ምክንያትም ኣልገባኝ ኣለ። ባለ ሁለት ኩላሊት መሃይም ሆኜ ከምኖር፣ የተማረ ባለ ኣንድ ኩላሊት ብሆን ምንድነው ጥፋቱ? ደህንነቴን ለከፋ ኣደጋ እስካላጋለጠ ድረስ፣ ኣካሌን ሽጬ ኣዕምሮዬንም ልቦናዬንም ባበለፅግ ምንድነው ጥፋቱ? ባለ ሁለት እጅ ሆኜ የመቅደስ ዲንጋይ ከምጠርብ፣ ባለ ኣንድ እጅ ሆኜ የራሴን መቅደስ ለመቀየስ ብበቃ ምንድነው ጥፋቱ? … ደግሞ፣ ህጋችን ኣይፈቅድም! … በዓለም እየዞሩ ኩላሊት እሚሸምቱት እነማን ሆኑና? የኩላሊት ሽያጭ የደራው በማን ገበያ ሆነና? … ህግ ኣለን ብሎ መመፃደቅ! የሰብዓዊ መብት ኣክባሪዎች፣ ስልጡኖች ነን፤ ለማለት ነው? … ከህግ ውጭ በመሸጥ ኩላሊቴን እንዳረክስላቸው ነው? …    

ጉዳዩ ቢያስቆጣኝም፣ መንገዴ የተዘጋብኝ ቢመስለኝም፣ ከህግ ውጭ ሆኜ መኖር እንደሌለብኝ ስለማምን ተውኩት። የህጉ ሎዢክ ባይረዳኝም፣ ምናልባት ያ ህግ የወጣው፣ በኔ ድርጊት ምክንያት፣ በሌሎች ሰዎችም ሆነ በማህበራዊ ደህንነት ላይ፣ ሊመጣ የሚችለውን ጥፋት ለመከላከል ሊሆን ይችላል፤ ብዬ በህጉ መኖርን መረጥኩ። ዛሬም ይህንኑ ነው እማስበው፦ እምኖርበት የትኛውም ማህበረሰብ ላወጣው ድንጉግ ህግ ተገዢ ሆኜ መኖር። ያልገባኝ ነገር ካለ፣ እጠይቃለሁ። በዚያም ለውጥ ለማምጣት እጥራለሁ። ግን፣ እምጠይቀው ተፅፎ የፀደቀውን ህግ ብቻ ኣይደለም። ያልተፃፈውንም ህግ ጭምር ነው። እንዲያውም፣ የከፋ ተፅዕኖ ያለው እሚመስለኝ ይህ ያልተፃፈ ህግ ነውና በተለይ እሱን እጠይቃለሁ።

ላነሳው የፈለግሁት ጉዳይ እላይ ከጠቀስኩት ገጠመኜ ጋር ይመሳሰላል። ከሌላ ኣንድ ጉዳይ ጋርም ይገናኛል። ያገራችን ህግ፣ በህመም ምክንያት በሚመጣ ተፅዕኖ፣ የመዳን ተስፋ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ፣ ከመድሃኒት በመታቀብም ሆነ በሌላ ዘዴ ህይወትን ማብቃት ወይም ሌሎች ህይወታቸውን እንዲያቆሙ መርዳትን (Marcy Killing/Euthanasia) የሚፈቅድ ኣይመስለኝም። ሰውዬው፣ መድሃኒቱንም ሆነ ምግቡን ያለመውሰድ መብት ኣለው፤ ሊባል ቢችልም፣ ይህ ራስን እንደማጥፋት ስለሚቆጠር፣ ህገወጥ እንደሆነ እሚታሰብ ይመስለኛል። ግን ግን፣ በእምነት ስም፣ ከዚህ የከፋ ነገር ሰርክ በዙሪያዬ ሲሆን ኣያለው።

ኣንድ፣ በኣገሪቱ ህግ፣ ህገወጥ የተደረገ ነገር እንኳ በሃይማኖት ስም ሲደረግ ህገ-ወጥነቱ እማይጠየቀው ለምንድነው? የኣገራችን የዘመናዊ ህክምና ጉዳይ እጅግም እሚያስመካ እንዳይደለ ማስረጃ ኣያሻውም። በማወቅም ባለማወቅም በሚፈጠሩ የሃኪሞች ስህተቶች መድሃኒት መውሰድም ካለመውሰድ እኩል ለሞት ሲዳርግ ኣብዝተን እናያለን ዛሬ ዛሬ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ህዝቡ እሚመካበትን ሌላ ኣማራጭ ቢፈልግ ኣያስወቅሰውም፤ እንል ይሆናል። ግን፣ ኣንዳንድ በግልፅ በህክምና መዳን የሚችሉ ነገሮች፣ በሃይማኖቶች ክልከላ ወይም ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ግፊት ምክንያት፣ ሰዎችን ለህልፈትና ለኣካላዊም ሆነ ለልቦናዊ ጉዳት ሲዳርጉ ስናይስ?

በግሌ፣ በእንዲህ ባሉ ክልከላዎች ምክንያት፣ ወዳጆቼም እማላቃቸውም ሰዎች ተነጥቀውብኝ፣ ቁስለትና ህማም ተቀብያለሁ። ተሟግቼም ሳልሸነፍ ተሸንፌኣለሁ። ምንም ማድረግ ስላልቻልኩ ምንም ማድረግ ያልቻለውን እነኔቴን ወቅሼኣለሁ። ይህ ወግና ባህል እሚሉትን ሸክም፣ ይህ እምነት እሚሉትን ዕዳ፣ ተቀይሜኣለሁ። … ግን፣ ቅያሜ ይዤ መኖር ኣልሻም። ልቤ ለባህሌ በሚሰጠው ክብር ላይ ጥቀርሻ የሚያበጀውን ይህን ቅሬታ ተሸክሜ መዝለቅ ኣልሻም። ጥያቄዬ ፈውሴ ነው። እጠይቃለሁ። መልስ ባገኝም ባላገኝም እጠይቃለሁ። እንደ ዜግነቴ፣ እንደ ሰው ልጅነቴ፣ ይህንን ያገርና የህዝብ ጉዳይ በጋራ እማንጠይቀው፣ በጋራ እማንሞግተው፣ በጋራ ምላሽ እማናፈላልግለት ለምንድነው? እላለሁ።  

ጥያቄዬን ግልፅ ለማድረግ፣ ኣንድ የገጠመኝን ነገር፣ ወደ ምናባዊ ተረክ ለውጬ ላስነብባችሁና ልሰናበት። ይህ ግን፣ በየትኛውም እምነት ውስጥ ከማየው፣ በጉዳዩ ላይ እንደዜጋና እንደሰብዓዊ ፍጡር ኣቋሜ ምን መሆን እንዳለበት ግራ ከሚያጋቡኝ፣ ድርጊቶች ኣንድ ምሳሌ ብቻ ነው። ጥያቄዬም በሃይማኖቱ ላይ ኣይደለም። እንዲህ ባሉ፣ ያለጥያቄ መቀበል እንዳለብን በምንገደድባቸው፣ ሃይማኖታዊ ወይም ባህላዊ ድርጊቶች ብቻ ላይ ነው፦     

ቅልል፣ ቅልቅል ያለች ልጅ ናት። ያያት ሁሉ ቅልል ይለዋል። መንቀልቀል የተፈጥሮው ባይሆንም እንዳያት እንደሷ መንቀልቀልም ያሰኘዋል። ትስቃለች። ለሷ፣ ፍጥረት ሁሉ የሳቋ ቆስቋስሽ ነው መሰል፣ ቅፅበታት ሁሉ ብብቻዋን እየኮረኮሩ ያልፋሉ መሰል፣ በየደረሰችበት ትስቃለች። በየቅፅበቱ ትስቃለች። ከሳቋ የሚወጣው ደስታ ብቻ ነው። እና፣ ያያት ሁሉ ይስቃል። ያያት ደስታዋ ይጋባበታል። ያያት ሁሉ ለመሳቅ፣ ለመደሰት፣ ምክንያት እንደማያስፈልግ ይገለጥለታልመ መሰል፣ እሚስቀው ያለምክንያት መሆን ኣለመኑንም ሳያስብ ኣብሯት ይንተከተካል። እሷ በደረሰችበት ዕምነበረድም ኣበባ ሆኖ እሚፈካ ይመስል ነበር። ሰው ወደዚህች ዓለም የሚመጣው በተለይ ኣንድ ነገር ለማድረግ ከሆነ፣ በተለይ ያቺን ነገር ለመፈፀም ከሆነ፣ እሷ ለኛ ሳቅ ልትሰጥ ነው የመጣችው።

ታመመች። ምክንያቱ ምን እንደሁ ኣይታወቅም፤ ድንገት ታመመች። መድሃኒት ተሰጣት። መድሃኒቱ ህመሟን እንዲያብስባት የተሰጣት ዓይነት፣ ኣብሶባት፣ ኣዳክሟት ተገኘ። ማሰብ በሚከብድ ፍጥነት ህይወቷ እቋፍ ላይ ሆነ። ባይኔ ስር ያደገች የጎረቤቴ ልጅ ነች። የታላቋ ጓደኛ ነኝ። ሳቋ በኔ ላይ የተለየ ሃይል ነበረው መሰል፣ ከእቶቼም ኣብልጬ እወዳታለሁ። ከወንድሟ ኣብልጣ ትቀርበኛለች። ችግሯ እስኪታወቅ፣ ህይወቷን ለማቆየት የነበረንን ብቸኛ ኣማራጭ ሃኪሞች ነገሩን። ደም ያስፈልጋታል። ደግነቱ፣ የሚስማማትን ደም ለማግኘት ኣልከበደንም። ወንድሟ ዝግጁ ሆነ። እኔም ተመረመርኩ። ለሁሉም ሰው የሚሆን የደም ዓይነት ነበረኝና ዝግጁ ሆንኩ።

ይህ በቀላሉ በመሆኑ ደስታችን ልክ ኣልነበረውም። እና፣ ደም ልንሰጣት መሆኑን ለወላጆቿ ስንነግር ኣስደንጋጭ ነገር መጣ። ሃይማኖታችን ኣይፈቅድም፤ ተባልን። ያን በሰማሁ ቅፅበት የተሰማኝን መናገር ኣልችልም። ከዚያ ቦታ ድንገት ኣንዳች የነጠቀኝ ያህል ነበር። ቀልቤን እንደገዛሁ፣ ቃል በቃል ነው ብላችሁ ኣላጋነንሁም፣ የሰማዩን ኣጎበር ቁልቁል ጨምድጄ ስለሰማዩ ብዬ ተማጠንኩ። "ኣይሆንም!" ተባልኩ። ወላጆቿ፣ "ኣይሆንም!" ኣሉኝ።

"እመኑኝ፣ እመኑኝ፣ እግዚኣብሄር ይሰማኛል። በዚህ እምቢ ኣይለኝም፤ እመኑኝ። እኔ ስለሷ ገሃነም ልግባና፣ እሽ ብላችሁኝ እሷ ብቻ ትዳንልኝ፤" ኣልኩኝ።  

እምለውን ኣላውቅም ነበር። እምለው ግን ኣንድም ማስመሰል ኣልነበረውም። እኔ ብቻ ኣይደለሁም፣ ወንድሟም ተማጠነ። "ኣይሆንም!" ተባልን። በመስለምለም ላይ ያሉትን ዓይኖቿን ኣየሁዋቸው። ኣሁንም ሳቅ ኣለባቸው። እሷም ጭንቅላቷን ወዘወዘች። ኣይሆንም! …  

ያኔም ኣሁንም፣ ያ የእምነት ጉዳይ፣ ያ የግል ጉዳይ፣ እንደሆነ ለማሰብ ልቤ ኣልፈቀደም። ዓይኔ እያየ ዓይኖቿን ብርሃን ራቃቸው። ዓይኔ እያየ፣ ዓይኖቿን የእንቢታ እጆች ከደኑላት። ዓይኔ እያየ ሳቆቿ ከተከደኑ ዓይኖቿ ጀርባ በሚያስፈሩ ጥፍሮች ተለቅመው ተወሰዱ። ሁሉም ነገር ቀዘቀዘ። በቃ፣ … ሳቋን ይዛው ሄደች። ልትሰጠን የመጣችውን ሳቅ ይዛው ሄደች።

ካለፈ በሁዋላ፣ "መጮህ ነበረብኝ፤" ኣልሁ። የሆነው ሁሉ የሆነው በኔ ጥፋት ሆኖ ተሰማኝ። ከውስጤ ይሁን ከሆነ ከማይታወቅ ቦታ የሚመጣ ድምፅ፣ ነግቶ በመሸ ቁጥር፣ "ኣንተ ብትጮህ ኖሮ ኣትሞትም ነበር!" ይለኛል። በዚያው፣ በክፍሏ ውስጥ፣ በሆስፒታሉ እያንዳንዱ ክፍል እየሮጥኩ፣ በመንገድ ላይም እየበረርሁ፣ መጮህ ነበረብኝ። እንደ ዕብድ ብጮህ ኖሮ፣ ሰዎች ይሰበሰቡ ነበር። ብዙ ሰዎች ክፍሏን ከበው፣ "ምን ተፈጠረ?" ይሉ ነበር። ብዙ ዓይኖች የወላጆቿን ዓይኖች እያዩ፣ "እባካችሁ እዘኑላት፣" ይሉ ነበር። ብዙ ልቦች በዕምባ ተውጠው፣ ከፈጣሪም ይልቅ ወላጆቿን ይማፀኗቸው ነበር። እሷንም ይማፀኗት ነበር። … እና፣ ይራሩላት፣ ትራራልን፣ ነበር። ቢያንስ የሰው ዓይንን ፈርተው፣ ቢያንስ የሰው ቃል ከብዷቸው፣ "ይሁን፣ ይህችን ሃጢኣት ብቻ ትስራ፤" ይሉ ነበር። ይራሩላት፣ ይራሩልኝ፣ እሷም ለራሷ ትራራ ነበር፣ … ብጮህ ኖሮ፣ ኣልሁ።

እነሆ፣ ሳቅ ልትሰጠን የመጣች፣ ስቃ ያልጠገበች፣ ኩንስንስ የሳቅ እመቤት፣ የኔንም ሳቅ ጨምራ ይዛ ሄደች።

ምን ነበረበት ብጮህ ኖሮ፣ … ብጮህ ኖሮ፣ … ብጮህ ኖሮ፣ … ብጮህ ኖሮ፣ … ብጮህ ኖሮ!!!! …